የአንጀት ተስቦ በሽታ (Typhoid Fever ) ሕይወትን ሊያሳጣ የሚችል በሽታ ነው፤ በሽታውን የሚያስከትለው የሳልሞኔላ ባክቴሪያ (Salmonella bacteria) ሲሆን እንደአገራችንን ባሉ ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ባለባቸው ደሃ አገሮች በብዛት የሚታይ ነው። በሽታውን መከላከል የሚቻል ሲሆን መኖሩ እንደታወቀ በፀረ-ተዋሲያን መድኃኒት ማከም ይቻላል፤ በሽታው በስፋት ወደሚታይባቸው አካባቢዎች የምንጓዝ ከሆነ ወይም ደግሞ በሽታው በስፋት ያለባቸው አካቢዎች የምንኖር ከሆነ ደግሞ ክትባቱን በመውሰድ መከላከል ይቻላል።
የበሽታው ስሜቶችና ምልክቶች ምንድናቸው?
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከሚያሳዩት ምልክቶች ውስጥ ከፍተኛ ትኩሳት ማለትም በ39 እና 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ አካባቢ በአብዛኛው ይኖራል፤ የሰውነት መድከም፣ የሆድ ሕመም፣ ራስ ምታት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሌሎች የሚታዩ ምልክቶች ናቸው። አልፎ አልፎ ደግሞ ቀላ ያሉ ሽፍታዎች በሰውነት ላይ ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው መኖሩ የሚታወቅበት ዋነኛ ምርመራ የደም ወይም የሰገራ ናሙና በመውሰድ ሲሆን በሽታውን የሚያስከትለው የሳለሞኔላ ባክቴሪያ (Salmonella bacteria) ሲገኝ ነው።
ከላይ የተገለፁት ምልክቶች የሚታዩ ከሆነ በፍጥነት ወደ ሕክምና በመሄድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ በሽታው የሚታከመው በፀረ-ተዋሲያን መድኃኒቶች ነው፤ መድኃኒቱ የተሰጣቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በሁለትና ሦስት ቀን ውስጥ የመሻል ስሜት ይኖራቸዋል። በሽታው እያለባቸው ሕክምናውን ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች ለሳምንታት የሚቀጥል ትኩሳት ይኖራቸዋል እየጠነከረ ሲሄድም ከፍተኛ ጉዳት በሰውነት ላይ በማስከተል እስከሞት ያደርሳል።
በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶች
በሽታውን የሚያስከትለው ባክቴሪያ በሰዎች ብቻ ላይ የሚኖር ነው፤ በእንስሳት ላይ አይታይም። ባክቴሪያው በበሽታው በተለከፉ ሰዎች ደም እና አንጀት ውስጥ ይገኛል፤ በተጨማሪም ጥቂት ሰዎች ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ካገገሙ በኋላ ባክቴሪያውን በሰውነታቸው ውስጥ እንደተሸከሙ ይቀራሉ። እነኝህ የሕመም ምልክት የሌለባቸው ነገር ግን ባክቴሪያው በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ጤነኛ ተሸካሚዎች ወይም በሽታውን አስተላላፊዎች ይባላሉ። ችግሩ ጤነኛ ተሸካሚዎችም ሆኑ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ባክቴሪያው ከዐይነምድር ጋር አብሮ ስለሚወጣ የመበከል ሁኔታ ሁልጊዜ ይኖራል። ባክቴሪያው በተበከለ ምግብና መጠጥ አማካኝነት ወደ ሰውነት ከገባ ራሱን በማራባት ወደ ደምና ደም ዝውውር በሚዘልቅበት ጊዜ ሰውነት ትኩሳትና ሌሎች ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል።
ራሳችንን ከበሽታው እንዴት እንከላከል?
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከሕክምና በኋላ በሐኪም የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት ሙሉ በሙሉ መጨረስ ይኖርባቸዋል። ከመፀዳዳት በኋላም በሳሙናና በውኃ እጅን ሙልጭ አድርጎ ማጠብ ያስፈልጋል፤ ለሌሎች ሰዎችም ምግብ ማዘጋጀትም ሆነ ማቅረብ የለባቸውም፤ ምክንያቱም ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድልን ለመቀነስ ነው። በተጨማሪም መድኃኒት ወስደው የመሻል ስሜት ቢኖርም ባክቴሪያው ከሰውነት ጠርቶ ላይወገድ ይችላል፤ ስለዚህ በሽታው ተመልሶ ሊመጣ ከመቻሉም በላይ በሽታውን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ ሁኔታ ይኖራል። ሰዎች ከባክቴሪያው ነፃ ለመሆናቸው ሐኪም ዘንድ ቀርበው በድጋሚ ማረጋገጥ አለባቸው።
በሽታውን ለመከላከል ዋናው መፍትሔ ምግብና መጠጥ በባክቴሪያው ሊበከሉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መከላከል ነው፤ ወይም ከተበከሉ አካባቢዎች ሊመጡ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ የምግብና መጠጥ ምንጮችን አለመጠቀም ነው። ሌላው መከላከያ ደግሞ ክትባት መውሰድ ነው።
የአንጀት ተስቦ ክትባት
የታይፎይድ በሽታ ይኖርባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች የምንጓዝ ከሆነ ወይም ሥራችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና ሆቴል መመገብ የሚበዛው ከሆነ ክትባቱን መውሰድ መልካም ነው። ስለክትባት ሁኔታ ሐኪሞች ጋር ጎራ ብሎ ማናገር የተሻለ ነው።
ተጨማሪ ጠቃሚ ምክሮች
• የታሸገ ውኃ መጠቀም፣ የታሸገ ማግኘት ካልቻሉ ደግሞ ከመጠጣትዎ በፊት ውኃውን በሚገባ ማፍላት።
• በረዶን እንደንፁህ በመቁጠር የሚጠጡት ውኃ ወይም ሌላ መጠጥ ላይ በመጨመር መጠቀም ማቆም፤ ምክንያቱም በረዶው የተሰራበት ውኃ ሁልጊዜ ንፁህ ላይሆን ይችላል።
• ምግብ በደንብ የተቀቀለ ወይም የተጠበሰ መሆን አለበት፤ በትኩስነቱም መመገብ አለብን።
• መላጥ የማይችሉ ፍራፍሬዎችን ወይም በደንብ ያልበሰሉ ቅጠላቅጠሎችን አለመመገብ፤ በተለይ ጥሬ የሚበሉ ቅጠላቅጠሎች በቀላሉ ሊበከሉ ስለሚችሉ ተገቢውን የማፅዳት ሥራ ካከናወኑ በኋላ መመገብ።
• ተልጠው የሚበሉ ፍራፍሬዎች ራሳችን ልጠን መብላት፤ ነገር ግን ከመላጥ በፊት እጅን በሳሙና በደንብ መታጠብ።
• በጎዳና ላይ የሚሸጡ ምግብና መጠጦች ጤንነት አስተማማኝ ስላልሆነ ከመመገብ መቆጠብ።
References: ሐኪም በሌለበት (በጠና አበረ), www.goshhealth.org,
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012