አዲስ አበባ፡- በ6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሊጠናቀቁ የታቀዱት የዛሬማ ሜይዴይ እና የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክቶች 20 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መፍጀታቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ግኝት አመለከተ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲትር መስሪያ ቤት ሪፖርትን መሰረት በማድረግ ትናንት ከውሃ፣መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረገው ውይይት ግድቦቹ የጥናት፣ የዲዛይንና የክትትል ጉድለት እንደነበረባቸው አመላክቷል፡፡ ከጊዜና ከወጪ አንጻርም ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተሉ ጠቁሟል፡፡
የዛሬማ ሜይዴይ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል የሚገኝ ሲሆን መጀመሪያ ግድቡን ለመገንባት ኃላፊነት ወስዶ የተረከበውም የስኳር ኮርፖሬሽን ነበር፡፡ ኮርፕሬሽኑ ባሉበት የአቅም ውስንነቶች ምክንያት ሥራውን በተፈለገው መንገድ ማስቀጠል ባለመቻሉ 40 ከመቶ የሚሆነውን የፕሮጀክት ሥራ ከሠራ በኋላ ቀሪውን ሥራ ለማከናወን የውሃ ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መረከቡን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡
ለፕሮጀክቱ የአዋጭነትና የቅድመ አዋጭነት ጥናት ሳይደረግ የግንባታው ሥራ መጀመሩ በፕሮጀክቱ ላይ ለተስተዋሉት ችግሮች ምክንያት መሆኑን በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡ ፕሮጀክቱ የተሟላ ዲዛይንና የአካባቢ ጥበቃ ግምገማም እንዳልተካሄደበት ታውቋል፡፡ የመንግሥት የግዥ መመሪያን በጣሰ መንገድ ያለምንም ግልጽ ጨረታ በቃለ ጉባኤ ብቻ ስቱዲዮ ጋሊ ኢንጂነሪንግ ለተባለ ድርጅት የማማከሩ ሥራ መሰጠቱና ለሱር ኮንስትራክሽንም እንዲሁ ያለ ጨረታ ግንባታው መሰጠቱን የኦዲት ግኝቱ አረጋግጧል፡፡
ግንባታው ሲጀመር ጠቅላላ ወጪው አራት ቢሊዮን አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃምሳ አምስት ሺ አምስት መቶ አራት ከስልሳ ሰባት ሳንቲም ብቻ ሲሆን፤ አሁን 347.7 በመቶ ጨምሮ አስራ አራት ቢሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና አራት ሺህ አንድ መቶ ሶስት ከስልሳ ስምንት ሳንቲም ከፍ ብሏል፡፡ የገንዘቡ ልዩነትም አስር ቢሊዮን ሶስት መቶ ሀምሳ ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር መሆኑን የኦዲት ግኝቱ አስረድቷል፡፡
የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሽ በሰጠበት ወቅት አብዛኛዎቹ የተጠቀሱት የአሠራር ጉድለቶች ትክክል እንደሆኑና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን ወስዶ ማስፈጸም ከጀመረ ወዲህ ለታዩ ችግሮች ተጠያቂ መሆኑን ተቀብሏል፡፡ ከመሰረቱ ግን የስኳር ኮርፖሬሽን ለችግሩ ምክንያት እንደነበርም ጠቅሷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘው የመገጭ መስኖ ግድብ አፈጻጸምን በተመለከተም የኦዲት ግኝቱ የተለያዩ ችግሮችን አቅርቧል፡፡ ፕሮጀክቱ በገለልተኛ ባለሙያዎች ያልተገመገመ የጸደቀ ዲዛይን ያለው ቢሆንም የአዋጭነት ጥናት ያልተሠራለት ነው፡፡
የመገጭ መስኖ ግድብ ግንባታ በመጀመሪያው እቅድ መሰረት ሊገነባ የታቀደው በሁለት ቢሊዮን አራት መቶ ሃምሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ከስልሳ ስድስት ሳንቲም ሲሆን፤ አሁን አምስት ቢሊዮን ስድስት መቶ ስልሳ ሰባት ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ከሃምሳ ሶስት ሳንቲም ከፍ ማለቱን የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል፡፡
የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከውሃ መስመር ዝርጋታና ከመስኖ እርሻ ዝግጅት ጋር የተቀናጀ የጋራ ዕቅድ እንደሌለው፣ ክትትል እንደማይደረግለት እና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሳይሟላ የካሳ ክፍያ እንደተፈጸመበት የሚያመላክቱ የኦዲት ግኝቶች ቀርበውበታል፡፡
በአጠቃላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የፈሰሰባቸው እነዚህ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ህገ ወጥ አሠራር ስለተፈጸመባቸው ለሌብነት የተጋለጡ ሆነው ዋጋቸው ሊገነቡ ከታቀዱበት ከፍ ማለቱ ትልቅ ሀገራዊ ኪሳራ እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡ ይህን ያህል ሀገራዊ ክስረት እንዲመጣ ያደረጉ አካላትም በህግ አግባብ መጠየቅ እንዳለባቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያት ሰጥተዋል፡፡ በቀጣይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እራሱን በመፈተሽ ያሉበትን ድክመቶች ማረም እንደሚገባው በውይይቱ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
ኢያሱ መሰለ