የተወለዱት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባቲ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአፋር ክልል ገዋኔ በሚባል አካባቢ የሚገኝ መታካ በተባለ ትምህርት ቤት ነው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አሰብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም አዲስ አበባ በሚገኘው ንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ አገኙ። በመቀጠልም በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ ዲፕሎማና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ። በዚህም ሳያበቁ በህግና ማኔጅመንት ተጨማሪ ሁለት ዲፕሎማዎችን አገኙ። በዚያው የትምህርት መስክ ማስተርስ ዲግሪያቸው በሕንድ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በቱርክ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በማመር ማግኘት ችለዋል። ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑት እኚሁ ግለሰብ ታዲያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመንግሥት፣ በግልና መንግሥታዊ ባልሆኑ መስሪያቤቶች ሰርተዋል። በሙያቸው ካገለገሉባቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል በአፋር ክልላዊ መንግሥት ምክርቤት፣ በአፋር ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩትና ትምህርት ቢሮ ተጠቃሽ ናቸው። በግል ኮሌጆችም አስተምረዋል። በእናቶችና ሕፃናት፥ በትምህርትና በልማት ላይ በሚሰሩ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራትም ገብተው ለአገራቸው ሕዝብ የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ ቆይተዋል።
በልማት ድርጅቶችና በክልሎች ተዘውረው በሚሰሩበት ወቅትም በተለይም የገጠሩ ማህበረሰብን የዕለት ተዕለት ኑሮ ይመለከቱ ስለነበርም ይህንን ሕዝብ ከከፋ ድህነት ማውጣት የሚቻልበትን ሁኔታ በአዕምሯቸው ያሰላስሉ ገቡ። በተለይ ደግሞ ምቹ የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የሰው ኃይል ባለበት ሁኔታ የሕዝቡ ኑሮ እያሽቆለቆለ የመምጣቱ ጉዳይ ያሳዝናቸው ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ ብቃት ያለውና ለመረጠው ሕዝብ ታማኝ የሆነ አመራር ያለመኖሩ መሆኑን አመኑ። በመሆኑም ይህ ሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ችግር በመቃወም ፓርቲ ማቋቋም እንዳለባቸው ተገነዘቡና ዶክትሬት ዲግሪያቸው ከቱርክ አግኝተው እንደተመለሱ ፓርቲው የሚመሰረትበትን ሁኔታ ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ጠነሰሱ። ከጥንስስም አልፎ እውን ማድረግ ቻሉ። የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ መስራችና ሊቀመንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም የዛሬ የዘመን እንግዳችን ናቸው። ስለፓርቲያቸው አመሰራረትና ስለአጠቃላይ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚሉትን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካው ለመግባት የተለየ ምክንያት አልዎት?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- በተለያዩ ቦታዎችና ኃላፊነቶች ላይ ስሰራ ያጋጠሙኝና ያየኋቸው ችግሮች ሁልጊዜ ራሴን እንድጠይቅ ያደርጉኝ ነበር። በተለይም አፋር ውስጥ እሰራ በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ ላይ የነበረው ከፍተኛ ድህነት፣ ሴቶች ላይ ያለው የኑሮ ጫና፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ሕፃናት የመማር ዕድል ያላገኙ ወገኖችን ስታዪ እንደዜጋ የሚሰማሽ ነገር አለ። በተለያዩ የበጎአድራጎት ተቋማት በምሰራበት ጊዜም የተዘዋወርኩባቸው የኦሮሚያ፣ የሱማሌና ደቡብ ክልሎች ምቹ የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የሰው ኃይል ቢኖራቸውም ሕዝቡ በጣም በሚያሳቅቅ የኑሮ ደረጃ የመኖሩ ጉዳይ ሁሌም ምስጢር ይሆንብኝ ነበር። በተለይም ኢኮኖሚክስ ተማሪ እንደመሆኔ ለእድገት የሚያስፈልጉ የሚባሉት መሬት የሰው ሀብት እያለ በከፋ ድህነት ውስጥ ለምን ለመኖር ተገደድን እያልኩ አሰላስል ነበር። ከእኛ በጣም ያነሰ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው አገራት ከእኛ በላይ ብዙ ርቀውን ሄደዋል። ይሄን ጉዳይ በሚመለከት ለረጅም ጊዜ ከራሴም ሆነ ከጓደኞቼ ጋር አወራለሁ። በመጨረሻ ችግሩ ብለን የተረዳነው በዚህች አገር ከፍተኛ የሆነ የአመራር ክፍተት መኖሩን ነው። ያለንን ውስን የተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚወስኑት ፖለቲከኞች ናቸው። ከፈለጉ መንገድ ይሰሩበታል፤ ከፈለጉ ደግሞ ውጭ አገር ሄደው ይዝናኑበታል። ይህንን ነገር ከባድ ቢሆንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለን ድምዳሜ ላይ ደረሰን።ለዚህ ደግሞ ብቸኛው አማራጭ ፖለቲካውን መቀላቀል እንደሆነ አመንን።
እንደነገርኩሽ ወደ ፖለቲካ መስመር የመግባቱ ሃሳብ ለትምህርት ውጭ ከመሄዴም በፊት በውስጤ ሲመላለስ የነበረ ነው። ነገር ግን በአገሪቱ የነበረው ሥርዓት ፖለቲካውን ለመቀላቀል ቀርቶ የምንሰራባቸው ሲቪክ ማህበራት ራሳቸው በግድ ነበር የሚንገታገቱት። ከለውጡ ወዲህ ግን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅም ሆነ የመደራጀት መብት በተግባር በመታየቱ ያንን ለረጅም ጊዜ ስንጠነስሰው የነበረውን ሃሳብ እውን ወደ ማድረጉ ገባን። ሃሳቤን ከተጋሩ ጥቂት ሰዎች ጋር በመሆን ብዙ መከርን ሁኔታው እንዳሰብነው አልጋ ባልጋ ባይሆንም ግን የፖለቲካውን መስመር መጀመሩ ተገቢ መሆኑን አመንን። በዚህ መሠረት በ2011 ዓ.ም ጥቅምት ወር ውስጥ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲን ለማቋቋም የመጀመሪያውን የአደራጅ ኮሚቴ ስብሰባ አደረግን። በመቀጠልም ፓርቲ ለመሆን የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አሟልተን ዛሬ ላይ ፓርቲያችን አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት ከተሰጣቸው ፓርቲዎች መካከል አንዱ መሆን ቻለ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካው የገፋዎት የሕዝቡ ኋላቀር ኑሮ እንደሆነ ገልፀዋል፤ ግን የሕዝቡን ኑሮ ለመለወጥ የግድ ፖለቲከኛ መሆን ያስፈልጋል?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- አንቺ እንዳነሳሽው ወደ ፖለቲካ ለመግባቴ ገፊ ምክንያት ብዬ የማምነው የሕዝቡ የከፋ ድህነት አንዱ ምክንያት ቢሆንም እውነተኛ ዴሞክራሲ ያለመኖሩም ጭምር ነው። በተለይም የመናገር የመፃፍና ሃሳብን በፈለጉት መንገድ የማራመድ መብቶች ያለመከበራቸው ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ እንድታገል ምክንያት ሆኖኛል። አርብቶ አደሩ ጋር ስትሄጂ የምታዪው ድህነት በጣም ያሳቅቃል፤ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያለመወጣታቸው ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የሲቪል መብቶች ከማይከበሩባቸው አገራት አንዷ ነበረች። ሚዲያዎች ከሚገባው በላይ ቁጥጥር የሚደረግባቸው፤ የግሉ ዘርፍ በሞት አፋፍ ላይ እስኪደርስ ድረስ ጫና ይደርስበት የነበረበት ሀገር ውስጥ መሆናችን በራሱ ሥርዓቱን ገፍተን እንድንቃወም ያደርገናል። በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊም ማህበራዊ ፖለቲካዊም ጥያቄዎች ነበሩን።
በነገራችን ላይ ሁልጊዜ በሌሎች አካላትም ለምን አዲስ ፓርቲ ትመሰርታላችሁ ተብለን እንጠየቃለን። እንደተባለው እኛ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ስናስብ ከነበሩት አመራጭ ፓርቲዎችን መቀላቀል አንዱ ሲሆን ሌላው ከዜሮ መጀመር ነው። የመጀመሪያው አመራጭ አይተን ነበር፤ ነገር ግን መቀላቀል ቀላል መስሎ አልታየንም። ምክንያታችን ደግሞ በነበረው ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ድርጅቶች ተዳክመው ነበር። በቁጥር በጣም ብዙ ቢሆኑም በተጨባጭ ውጤታማ ሆነው የሚሰሩትና
መሬት ላይ ጽሕፈት ቤታቸውን ፈልገሽ ፓርቲ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በተጨማሪም በፓርቲዎቹ ውስጥ ራሱ ችግሮች ነበሩ። የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ ታሪክ በአብዛኛው የውስጥ ሹኩቻ የበዛበት ነው። ብዙ ፓርቲዎች ከሌላ ፓርቲ ተገንጥለው የራሳቸውን የመሰረቱበት፤ እንኳን አዲስ ሃሳብ ይዘሽ ልትቀላቀያቸው ይቅርና ውስጣቸው ያለውን ሃሳብ ማመቻመች ያልቻሉበት ሁኔታ እያለ ነባሮቹ ጋር መቀላቀል በጣም ከባድ ሆኖ ነው ያገኘነው። እነዚህ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ፓርቲዎቹን አግኝተሽ ቁጭ ብለሽ መወያየት አስቸጋሪ ነው። ስንቱ ፓርቲስ የተፃፈ ፕሮግራም እንዳለው አላውቅም።
ሌላው በጣም አስፈላጊና ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን የተነሳንበት የፖለቲካ መስመር አሁን ካለው በብዙ መልኩ ይለያል። አሁን ያሉትን ስናይ ሁለት ዓይነት ጎራ ነው ያለው። አንዱ ብሔር ተኮር፤ ሌላው የዜግነት፤ ሁለቱም ፅንፍ የረገጡ ናቸው። በነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እይታ የማንነት ጥያቄዎች ከዚህ በፊት ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይቀጥላሉ። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያለ ፖለቲካ አንዱ መገለጫ ነው። ብዙ ሰዎች በተለያየ ምክንያት የምንነት ጥያቄ አንስተው ይታገላሉ። ምክንያቱም ከኢኮኖሚ እድገት በፊት ሰው ማንነቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል። በብሔሩ፥ በፆታና በሃይማኖቱ ማንነቱ እንዲረጋገጥለት ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ተፈጥራዊ ነው፤ ነገር ግን ገደብ ሊኖረው ይገባል። አንድ ሰው መብቱን መጠየቁ ተገቢም ነው፤ ያንን አለማድረጉ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ነገር ግን ይሄ ጥያቄ በጣም ተለጥጦ ክልል ሀገር እስከመሆን ደርሷል። ዓለም ወደአንድ መንደር በመጣበት በዚህ ዘመን «እኛ እና እነሱ» እየተባባልን፤ አለፍ ሲልም «በሰፈሬ ማለፍ አትችልም» እየተባባል እርስ በእርሳችን እንሻኮታለን። በመሆኑም የብሔር ፖለቲካን መከተል ራሱን የቻለ ችግር እንዳለው ተገነዘብን።
በተቃራኒው ደግሞ ያለው የአንድነት ጎራ ተብሎ የሚታወቀው ከውጭ ስታዪው ምንምዓይነት ልዩነት እንዲኖር የማይፈልግና አስፈሪ ገፅታ ያለው ነው። ምንአልባት በውስጣቸው ከውጭ እንደምናየው ላይሆን ይችላል። እንዲያውም አሁን ላይ ውስጥ ገብቼ ሳየውና ከኃላፊዎች ጋር ቁጭ ብዬ ስንነጋገር አለመቀራረብ የፈጠረው ስጋት እንጂ የአንድነት ካምፕ የሚባለው ልዩነትን የማይቀበል፤ ኢትዮጵያን አንዲት ብቻ ነች ብሎ የሚያምን አለመሆኑን ተገንዝቤያለሁ። እኛ ፓርቲያችንን ባቋቋምንበት ጊዜ ግን አህዳዊ ሥርዓትን አራማጁ የሚመስል ገፅታ ነበራቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ልዩነት የሚከበርባት ግን ደግሞ አንድ ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖለቲካ ማህበረሰብ ያስፈልጋታል ብለን እናምን ስለነበር ሁለቱንም አማራጮች ለመቀበል አልወደድንም። እስካሁን ድረስ ከመጣንበት የግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪክ እንኳ ብናይ በማንነት ዙሪያ ብዙ ዋጋ የከፈልን ብዙ ወጣቶች ከእኛ ታላላቅ የነበሩ በዚህ ምክንያት ገብቷቸውም ሆነ ሳይገባቸው አልፈዋል። ከውጭ በተቀዳ ሃሳብ ቁጭ ብለን ሳንነጋገር ብዙ ዘመን ባክኗል።
ስለዚህ የሚሻለውና አሸናፊ የሚሆነው ጉዳይ ቁጭ ብለን እነዚህ ዋልታ ረገጥ የሚባሉ ሃሳቦችን የምናመቻችበት ደህንነታችን ተከብሮ በጋራ የምንኖርባት አገር መፍጠር መሆኑን እምነት ያዝን። በወቅቱ ይህንን ሃሳብ በሌሎች ፓርቲዎች ላይ አላየንም። በነበሩት ቴክኒካል ችግሮች እያሉ ተነጋግሮ ተደራድሮ ነባር ፓርቲ ውስጥ መግባት እንደዚህ ቀላል አይሆንም። ለአፈፃፀም ምቹ ሆኖ ያገኘነው አዲስ ራዕይና አዲስ ተስፋ ያለው አዲስ ፓርቲ መፍጠር ነው። እዚህ ጋር ሳልጠቅስልሽ ማለፍ የማልፈልገው አንዳንዶቹ የኋላ ታሪካቸው አይተሽ የዚያ አካል መሆን የማትፈልጊባቸው ፓርቲዎች አሉ። በውስጥ ሽኩቻና ጥቃቅን በሚባሉና ኢትዮጵያን በማይመጥኑ ጉዳዮች የተጠመዱበትን ሁኔታ ታያለሽ። በቅርቡ ሰምተሽ እንደሆነ አላውቅም አንድ ፓርቲ በሀብት ክፍፍል ላይ ግጭት ፈጥሮ ነበር። እናም እንዲህ ያለው ሁኔታን እየሰማሽ እዚያ ፓርቲ ውስጥ ልተገቢ ቀርቶ መራቅ ነው የምትፈልጊው። የተሻለ ሆኖ ያገኘነው አዲስ ፓርቲ መመስረት ነው። በእርግጥ ሁሉንም ነገር ከዜሮ የምትጀምሪ በመሆኑ ከባድ ነው፤ ብዙ ፋይናንስ ማውጣት ይጠይቅሻል፤ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ነገን ካሰብሽ ተስፋ ያለው ፓርቲ መመስረት የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው።
አዲስ ዘመን፡- ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ እንደማይታደር ሁሉ ችግር አለ ተብሎ ከሁሉም ፓርቲ ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት ከአዋጭነቱ ይልቅ ጎጂነቱ አያመዝንም?
ዶክተር አብዱል ቃድር፡- መጀመሪያ ከቁጥሩ ጋር በተያያዘ በደንብ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ያህል የፓርቲ ቁጥር ለምን አስፈለገ ብለሽ ካሰብሽ በእኔ እይታ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የተፈጠሩት በገዢው ፓርቲ ሆን ተብሎ ነው። ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የመጣ አይደለም። ደግሞም በነበረው ሥርዓት ፓርቲዎቹ ውስጥ ለሁለትና ለሦስት ያልተከፈለ የለም። አንድ ጠንካራ ፓርቲ የገዢው ፓርቲ ስጋት መስሎ ከታየ ከሱ ጎን ሌላ ፓርቲ ይፈጠርለታል። ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ይህንን ያህል ፓርቲ አይፈጠርም። አሁን ባለው የለውጥ ሂደትም የፓርቲዎቹ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀንሳል ብዬ እገምታለሁ። ሜዳው ነፃ ሲሆን ፓርቲዎቹ እንደምናየው በተለያየ መልኩ እየተወያዩ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተቻለ ራሳቸውን አክስመው ውህደት ይፈጥራሉ፤ ካልሆነ ግን ጥምረት እየፈጠሩ በጋራ የሚደራጁበት አግባብ ይኖራል።
በሌላ በኩል አዲሱ አዋጅም የፓርቲ መብዛት ላይ የራሱ ገደብ ጥሏል። ይህ አዋጅ ፓርቲዎች ወይም ግለሰቦች ወደ ምስረታ ከመሄዳቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው ብዬ አምናለሁ። በእኔ እይታ የቁጥሩ ነገር አንዳንዴ በጣም ይጋነናል። ሌሎች አገሮችን በንፅፅር ለማየት ስትሞክሪ እንደኛ በርካታ ብሔር ብሔረሰብ ሳይኖራቸውና ከእኛ በታች የሕዝብ ብዛት ያላቸው ከእኛ በላይ የፓርቲ ቁጥር ያላቸው አሉ። ስለዚህ ያን ያህል የተጋነነ አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን ቁጥሩ ቢቀንስ ደስ ይለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርዕዮተ ዓለም ብትከፋፍዪ የትም አገር ላይ ከአምስት በላይ ፓርቲ ሊኖር አይችልም። በጣም ተለጥጦ ግራና ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ካሉ ከአምስት አይበልጡም። ከ100 በላይ ፓርቲ የሚያስፈልግበት ምንም አግባብ አይኖርም። ግን ጉዳዩ የርዕዮተ ዓለም ወይም የፕሮግራም ብቻ አይደለም። ሰዎችን ፓርቲ እንዲያቋቁሙ የሚገፋቸው በጣም ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ። እኛ አገር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ናቸው። ሁሉም ብሔረሰብ መብቴ አልተከበረም ብሎ ሲያስብ ፓርቲ ያቋቁማል። ስለዚህ የብሔር ፓርቲ እንዲያቋቁሙ የሚያስገድዳቸው ስጋቶች ከተቀረፉላቸው አንድ ላይ መጥተው የማይሰሩበት ምንም ምክንያት ይኖራል ብዬ አላምንም። እንደኛ ዓይነቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎችም ከሌሎች ጋር ጥምረት ለመፍጠርና ምርጫው ከመምጣቱ በፊት አንድ ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት የጀመርነው ሂደት አለ።
አዲስ ዘመን፡- ከእነማን ጋር ጥምረት ለመፍጠር እንዳሰባችሁ ለአንባቢዎቻችን ግልፅ ሊያደርጉልን ይችላሉ?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- አሁን ስማቸውን መጥቀስ ትክክል ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ገና ድርድር ላይ ነን። ከእነዚህ ውስጥ አገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲዎች አሉ። ተስማምተን በምን አግባብ ነው ጥምረቱ የሚፈጠረው? ጊዜው እስከመቼ ነው? የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች አሉበት። ወደ እዚያ ውስጥ ከተገባ በኋላ በጥምረቱ ለመቀጠል የሚያስቡ ፓርቲዎች ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ስማቸውን መጥቀስ ትክክል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ሌላው ፖለቲከኞች ፓርቲ የምትመሰርቱት ሕዝብን ለመጥቀም ሳይሆን የራሳችሁን ጥቅም ለማጋበስ እንደሆነ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ አንዳንዶቹ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን መዝግበው ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የእናንተ ፓርቲ ይህ ጉዳይ አይመለከተውም ብለው ያስባሉ?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- ለእኔ እንደዜጋ ሲጀምር አገሬን ይመራሉ፤ ሕዝብ ያስተዳድራሉ ተብለው የሚታሰቡ የአገራችን ፓርቲዎች በዚህ ደረጃ መፈረጃቸው ያሳዝናል። ፓርቲዎች በዚህ መልኩ የሚታዩባት አገር መፍጠራችን በጣም የሚያሳዝንነው። እኔ ለፓርቲዎች ሊኖር ይገባል ብዬ የማምነው እይታ ራሳቸውን መስዋትነት ከፍለው አገርና ሕዝብን ማስቀደም የሚፈልጉ መሪዎች ያሉባቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ነው። አሁን ሕዝብ ዘንድ ያለው እይታ አንቺ እንዳልሽው ነው። ደግሞም ይሄ አስተሳሰብ የለም ብዬ ለመናገር አልደፍርም። አንዱም ለዘርፉ መውደቅ አገራችን አሁን ላለችበት ደረጃ መድረስ ምክንያትም ራዕይ የሌላቸው፥ አጭር የሚያስቡ፥ በትናንሽ ነገር ጊዜ ማጥፋት የሚፈልጉ ፓርቲዎች መኖራቸው ነው። ይህንን እንግዲህ የሚያስተካክለው አንዱ ሕግ ነው። የሚገራ ሕግና ሥርዓት መኖር አለበት። መንግሥት በተለይ ደግሞ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸው ግልፅ የሆነ ለአገርና ለሕዝብ መስራት የሚችሉ መሪዎችን ማፍሪያ ቦታ እንዲሆን ለማድረግ ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ ብዙዎቹ ፓርቲዎች አሁን እንደሚባለው የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶችና ሕግና ደንብ ሳያሟሉ የተቋቋሙ ናቸው። አሁን እንግዲህ ምርጫ ቦርድ ቀን ገደብ ጥሏል። ፓርቲዎች ሁሉንም ነገር አሟልተው እንደአዲስ ራሳቸውን ከጊዜው ጋር እንዲያሳድጉ ካልሆነ ግን መቀጠል እንደማይችሉ አስቀምጧል። እንደእኛ ያሉ አገር አቀፍ ፓርቲዎች አስር ሺ ሰው ማስፈረም አለባቸው። የክልል ፓርቲዎች አራት ሺ ፊርማ ማምጣት አለባቸው። ለረጅም ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል፤ በመሆኑም እነዚህ ፓርቲዎች በአፋጣኝ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ይጠበቅባቸዋል።
የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንከር ሲል እንዲህ ዓይነት የሕዝብንና የአገርን ጥቅም አሳልፎ የመስጠቱ፣ ፖለቲካን ለግል መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌ በተወሰነ ደረጃ ይቀንሰዋል ብዬ አስባለሁ። እኛ እንግዲህ አዲስ ፓርቲ ነን፤ አንዱን ፓርቲ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ያደረገን ወይም የገፋን ምክንያት አሁን አንቺ ያልሽው ፓርቲዎች አካባቢ የሚነሳ አሉታዊ ምልከታ ነው። በመሆኑም እኛም ዋና ዓላማችን በሌሎች ከሚታየው ግድፈት ራሳችንን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት የበለፀገችና ሰላም የሰፈነባት፥ ዜጎች የማይፈናቀሉባት አገር መመስረት ነው። ምን ያክል በቃላችን እንኖራለን የሚለውን አብረን የምናየው ነው የሚሆነው። ደግሞም ዛሬ ላይ ከሁሉም ነገር ንፁህ ነን ብለን ምለን ብንዘገት ጠቃሚ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ፓርቲያችሁ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልቶ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል ማለት ይቻላል?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- እስካሁን ድረስ ምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት የሚሰጣቸው ፓርቲዎች ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ነበረ። ግን አዲስ መመሪያ ዳግመኛ ወጥቷል። መመሪያው ላይ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች በአዲሱ አዋጅ መሰረት በዝርዝር ተቀምጧል። በዚያ መሰረት የመጀመሪያው ከእኛ የሚጠበቀው ነገር አባላቶቻችን 10 ሺ ማድረስ ነው። እኛ ስንመዘገብ በነበረው አዋጅ ያስፈልግ የነበረው 1ሺ500 ያህል ብቻ ነበር። አሁን ባለው አዋጅ መሰረት ከሰባት ክልል ወደ 2ሺ500 ፊርማ ሰብስበናል። አሁን የቀረንን ወደ 7ሺ500 አካባቢ ምርጫ ቦርድ ማሟላት እንዳለብን ደብዳቤ ፅፎልናል። እኛ አሁን ያንን የሚያስፈልገንን ፊርም በማገባደድ ላይ ነን። በዚህ መሰረት ቦርዱ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀደም ብለን ዝግጅት ጨርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈትና አባሎችን በመመልመል ሂደት ወደ ተለያዩ ክልሎች በሚሄዱበት ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞና ክልከላ እያጋጣመቸው መሆኑን እንስማለን፤ ከዚህ አኳያ የእናንተ ፓርቲ ያጋጠመው ችግር አለ?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- እስካሁን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከፈትንባቸው ክልሎች አማራ፣ ሱማሌ፣ ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ ናቸው። እነዚህ ክልሎች ላይ አንዳንዶቹ ሁለትና ከዚያ በላይ የከፈትንበት ሁኔታ አለ። ጽሕፈት ቤቶችን የመክፈት ሂደት እስከ ምርጫው ድረስ አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን ቢያንስ ቢያንስ በእያንዳንዱ ክልል አንዳንድ ለመክፈት አቅደናል። እንግዲህ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ሂደት ትልቁ ችግር የፋይናንስ እጥረት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ሂደት ውስጥ እኛም ያን ያክል በጣም የተጋነነ ችግር አጋጥሞናል አንልም። ይሁንና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትንሽ የማዋከብ ነገር በተለያዩ ክልሎች አይተናል። ለምሳሌ ጉባኤ ለማካሄድ አንድ ሆቴል ውስጥ ቦታ አስይዘን፤ገንዘብ ከፍለን፤ ተስማምተን እያለ ፕሮግራሙ ሊጀመር አንድ ቀን ወይም ሰዓታት ሲቀረው ማታ ላይ ባለ ሆቴሎቹ ደውለው ፕሮግራማችንን ማካሄድ እንደማንችል ይነግሩናል። አንዳንዶቹ የሌላ ኃይል ጫና እንዳለባቸው በግልፅ ያስረዱናል። እንደዚህ ዓይነት መሰል ችግሮች አሉ። ግን ያለንም ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለማለፍ እንሞክራለን። አንዳንዴም ፕሮግራማችንን እንሰርዛለን፤ አልያም ተግባብተን ለማካሄድ እንሞክራለን። በአጠቃላይ ሁኔታውን ስናየው ሌሎች ፓርቲዎች የሚያጋጥማቸው ተመሳሳይ ችግር እኛም ላይ ደርሷል ማለት እንችላለን። በገዢው ፓርቲ ጫና የሚደርስበት ሁኔታ አለ፤ በሌላ በኩል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚፈጥሩት ጫና ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል። ይህም ሁኔታ ሄዶ ሄዶ ማንም ያድርገው ማንም ምርጫው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ጋር ተያይዞ የእርሶ ፓርቲ ምርጫው መካሄድ አለበት ብሎ ያምናል?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- እንዳልሽው ቀላል አይደለም፤ በመጀመሪያ ምርጫ መካሄድ አለበት? ወይስ የለበትም የሚለው ጉዳይ አንድ ጥያቄ ነው። ከዚያ በኋላ መቼ መካሄድ አለበት የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። እንደነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ምርጫው በጊዜው ቢካሄድ ይሻላል የሚል እምነት አለን። ላሰምርበት የምፈልገው ነገር ግን ምርጫ መካሄድ አለበት ስንል ምንም ምን ችግር የሌለበት፥ በተለይም መካሄድ የለበትም የሚሉ ወገኖች የሚያነሷቸውን ስጋቶች አሳንሰን በማየት አይደለም። እንደተረቱ ሁለት መጥፎ ነገር ሲያጋጥምሽ አነስተኛውንና በጣም የማይጎዳሽን መጥፎ ነገር ትመርጫለሽ። አሁን ያለው ሁኔታ የተሻለውን መጥፎ ነገር ለመምረጥም በጣም አዳጋች የሆነበት ነው። ሆኖም አገር ያለምርጫ ትቀጥላለች፤ ዴሞክራሲውም ይኖራል ተብሎ አይታሰብምና ምርጫው መካሄድ አለበት።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ግን ዋናው ስጋታቸው ምርጫ እንዳይካሄድ የሚፈልጉ አካላት አንደኛው የሰላም ጉዳይ ነው። ከዚህ ተነስተው አንዳንድ ፓርቲዎች ምርጫ ብናካሂድ የሚፈለገው ውጤት ሳይሆን በተቃራኒው ሊሆን ይችላል ብለው ስጋታቸውን ይገልፃሉ። በእርግጥ ከምንም በላይ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት። ሕግ አንዴ መጣስ ከጀመረ በስተመጨረሻ ማጣፊያው ሊቸግረን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት ሕጋዊነቱ የተረጋገጠ አይደለም። ያም ሆኖ አሁንም በጊዜ ውስጥ ነው ያለው። ምርጫው ሳይካሄድ ጊዜው ካለፈ ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ከባድ አይደለም። የሆነ ክልል የሆነ ቡድን ተነስቶ «ማንም ሊገዛኝ አይችልም፤ መንግሥት የለም» ብሎ ቢያውጅ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ይታወቃል። ስለዚህ የሚፈጠረው አደጋ ምርጫ አካሂደን ከሚፈጠረው አደጋ ያነሰ ስለሆነ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል ቁርጥ አቋም አለን። ምርጫውን ሳናካሄድ ግን አሁን ያለውና ሕጋዊነቱ ያልተረጋገጠው መንግሥት ዕድሜውን ማራዘም ትክክል አይሆንም።
ምንአልባት ምርጫው ፍፁም ላይሆን ይችላል፤ ግን ዴሞክራሲ ሂደት በመሆኑ የዛሬ አምስት ዓመት የተሻለ ምርጫ ማካሄድ እንችል ይሆናል። ደግሞም ምርጫውን ማድረግ ሕገ መንግሥታዊም ግዴታ ነው። በእኔ እምነት አሁን ካለው ምክር ቤት የተሻለ ወካይ የሆነ ምክር ቤት ይፈጠራል። ይብዛም ይነስም ተቃዋሚዎች ይገባሉ። ምክንያቱም በጣም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ የተሻለው አመራጭ ምርጫውን ማካሄድና ዴሞክራሲውን በሂደት መገንባት ነው። ግን ምርጫው ይካሄድ ሲባል ዝም ብሎ ያለበቂ ዝግጅትና ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን ሳይወጣ የሚሆን ነገር አይደለም። እንደዜጋም ሚዲያ ተቋማት፥ ሲቪክ ማህበራትም ሁሉም ኃላፊነት አለባቸው ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን። መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ወይም ምርጫ ቦርድ ብቻውን የሚሰራው ሥራ አይደለም። ሁላችንም ግን ከተባበርንና ከሰራን ምርጫው ይብዛም ይነስም ዓለምአቀፍ ደረጃውን ያሟላ ለመራጩም፤ ለፓርቲዎችም ለታዛቢዎች ተቀባይነት ያለው ማድረግ አለብን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም የራሳችንን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳሉት አሁን ያለው መንግሥት ከሚታማባቸው ችግሮች የሕግ የማስከበርና ሰላም የማስፈን ሁኔታ ነው፤ በእርሶ እይታ ቀጣዩ ምርጫ በሰላም እንዲከናወን መንግሥት ምን መሰራት አለበት?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- በመጀመሪያ ለውጡ እንደአንድ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ በምንም መለኪያ ቀላል ነው ሊባል አይችልም። ታሪካዊ ነው። አንዳንዴ ሰዎች የተደረገልንን ቶሎ እንረሳለን። ይህ አግባብ አይደለም። ከእስር የተፈቱ ቤተሰቦች፤ ለዓመታት አገራቸው እንዳይገቡ የታገቱ ፖለቲከኞች ሥርዓቱን በመቃወማቸው ምክንያት ብዙ መከራና እንግልት ያሳለፉ ሰዎችን ስናስብ ለውጡ በጣም ትልቅና ሊመሰገን የሚገባ ነው። ሁለተኛ ለውጡ እንደማንኛው አገር ሊያጋጥም የሚችል ውጣ ውረዶች ይኖሩታል። እንደዚሁ አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም። ባለፈው አንድ ዓመት ተኩልም አገራችን በጣም ብዙ ዋጋ ከፍላለች፤ ብዙ ዜጎች ሞተዋል፤ ተፈናቅለዋል። ይሄ ባይሆን እንመርጥ ነበር፤ ግን ያም ሆኖ በግሌ ተስፋ አደርጋለሁ።በብዙ ዜጎች መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ በግለሰብ ወይም በቡድን ፍላጎት በቀላሉ አይቀለበስም። በዘር፣ በሃይማኖት፣ትንኮሳዎች አሉ። ብዙ ችግሮችንም እያየን ነው። ጥሩው ነገር ግን ሕዝቡን ይህንን የመሸከም አቅም ያለው በመሆኑ ነው። ጠንካራው አብሮ የመኖር ታሪካችን በትናንሽ ችግሮች የሚናድ ቢሆን ኖሮ እስካሁን መቆየታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር። ስለዚህ አሁንም መፍትሄው ያለው በእጃችን ነው። አብረን መቆየት ሰላማችንን መጠበቅ የምንፈልግ ከሆነ ማድረግ እንችላለን። አንዳንድ በግል ወይም በቡድን ጥቅም ሰላም የሚጎዳ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን ማስቆም እንችላለን።
በእርግጥ ከለውጡ ኃይል ጋር በአንዳንድ አስተሳሰቦች ላይ ልዩነት አለን። ግን በአገር ጉዳይ ላይ መተባበር መቻል እንዳለብን እናምናለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሁኑ ከእሳቸው ጋር ለውጡን የሚመሩ አካላት የሚፈጥሯቸው ስህተቶች ይኖራሉ። ምንም ጥያቄ የለውም። ሰብአዊ ስህተቶች ያጋጥማሉ፤ ይህም ከልምድም ማነስ ሊመጣ ይችላል። በመሆኑም እነዚህ ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆኖ ሰላማችንን እና ለውጡን የማስጠበቅ ሥራ ላይ መተባበር አለብን ብዬ አስባለሁ። ምንም ዓይነት የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ላይ መተባበር ከቻልን ምርጫው በተሻለ ሰላም ሊከናወን ይችላል። ከምርጫም በኋላ ድህረ ምርጫ ቅቡልነት ያለው ይሆናል ብዬ አምናለሁ። የተረጋጋ ፖለቲካ ካለ ደግሞ ኢኮኖሚያችንም ይቀየራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሳጠቃልለው ከስጋቶቼ ተስፋዎቼ ይልቁብኛል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳሉት አሁን ላይ ግጭቱ ከብሔር ወደ ሃይማኖትም ከፍ እያለ ነው፤ በዚህ ረገድ ይህ ችግር ማብቂያ ላይኖረው ይችላል ብለው የሚሰጉ አሉ፤ ይህንን ስጋት ይጋራሉ?
ዶክተር አብዱልቃድር፡- እውነት ነው ግጭቶች በተለያየ መንገድ ዛሬ ላይ ተበራክተዋል። ከዚያ ውስጥ አንዱ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ናቸው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ ብዙ ትናንሽ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ግን በጣም አደገኛ ነው ብዬ የማስበው የቤተእምነቶች መቃጠሉ ነገር ነው። ይህ ድርጊት ኢ-ሰብዓዊም የሆነ፤ ሕገወጥ የሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ተግባር ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ሞጣ ላይ የደረሰው የመስኪድ መቃጠል ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ቤተክርስቲያናት ተቃጥለዋል። ይህም በፍፁም ልትሸከሚው፤ ልትችይው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። በነገራችን ላይ አንድ ቤተእምነት ሲቃጠል የተቃጠለው አንድነታችን ነው ብዬ ነው የማስበው። ይህንን በሕጋዊ መንገድ ማስቆም ተገቢ ነው። አስተውለሽ ከሆነ መስኪዶች ሲቃጠሉ መጀመሪያ ከፊት ቆሞ የሚከራከረው ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ነበር፤ ቤተክርስቲያኑም ሲቃጠል በተመሳሳይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ነበር ሲቃወም የነበረው። ሰሞኑን ለሞጣ መስኪዶች ብዙ የማውቃቸው ክርስቲያኖች ሲያዋጡ ነበር። ይሄ የአብሮነት ባህላችን አንዱ መገለጫው ነው፤ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ከዚህም ባለፈ ግን የሚመለከታቸው አካላት እንደዚህ ዓይነት አጥፊ ሙከራቸውን ማስቆም የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር አለባቸው። ምክንያቱም አንዳንዴ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ። ወደ ፀጥታ መደፍረስም ሊወስዱ ስለሚችሉ እነዚህ ነገሮች ከመደረጋቸው በፊት የደህንነት፤ የፖሊስ እና የሰላም ኃይሎች እነዚህን ነገሮች ከምንጫቸው ማስቆም ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር አብዱል ቃድር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ማኅሌት አብዱል