የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት እንደ ተቋም በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችና ሥያሜዎችም የነበሩት ነው፤ በ1973 ዓ.ም ራሱን ችሎ በአዋጅ ከመቋቋሙ በፊት፣ በሲቪል አቬዬሽን ስር ነበር:: በአሁኑ ሰዓትም የኢትዮጵያን የአየር ጸባይ ሁኔታና አዝማሚዎችን በመተንበይ፤ በመረጃ የተደገፈ የአየር ሁኔታን ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት እያደረሰ ይገኛል::
በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን በዚሁ ተቋም ላይ በማተኮር፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ጠባይ ትንበያን መረጃን የማቅረብ ደረጃውን፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ የአየር ጠባይ ትንበያን ተደራሽ የማድረግ ተግባሩን፤ የተደራጀና ተከታታይ መረጃዎችን በመሰነድና በመተንተን ውጤታማ የትንበያ አሰራር ሥርዓት እውን ከማድረግና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፤ ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ዋና ትኩረቱ አድርጎ የሚሰራው ምንድን ነው?
አቶ ተሾመ፡- ኢንስቲትዩቱ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራቸው ተግባራት አንዱ የኢትዮጵያ መልካምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ የሜትሮሎጂ መረጃ መሰበሰቢያ ጣቢያዎችን ማቋቋም ነው:: ሁለተኛው፣ ከተቋቋሙት ጣቢያዎች መረጃዎችን መሰብሰብ ነው:: ሥስተኛው፣ የተሰበሰቡ መረጃዎች የጥራት ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ በብሔራዊ መረጃ ቋት ውስጥ በመደረጃት፣ ለምርምር ተቋማት፤ ለውሳኔ ሰጭ አካላት፤ መረጃዎችን ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ነው::
እራሱም እንደ ተቋም እነዚህን መረጃዎች መሰረት በማድረግም የአጭር፤ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የአየር ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ይሰጣል:: የተሰጡ ትንበያዎችን መሰረት በማድረግም ለግብርና፤ ለውሃ፤ ለጤና፣ ለአቬሽንና መሰል ዘርፎች ምክረ ሀሳቦችን ይሰጣል::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ ያለው የትንበያ እና የመረጃ ተደራሽነት አቅሙ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ፈጠነ፡– የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን እያሳደገ፤ የመረጃ አቅርቦቱንም እያሰፋ መጥቷል:: ቀደም ሲል የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎቻችን የገጸ ምድር (መሬት ላይ ያሉ) ጣቢያዎች ብቻ ነበሩ:: ይህም የኢትዮጵያን መልካዓምድራዊ አቀማመጥን መሰረት በማድረግ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ:: አሁን ላይ ይህን ሁኔታ በመቀየር በሁሉም አካባቢዎች የሜትሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን የማስፋት ስራ ሰርቷል::
ከጊዜ ወደ ጊዜ የሜትሮሎጂ መረጃ ጣቢያዎች ቁጥራቸው እያደገ በመምጣቱ በአሁኑ ጊዜ በገጸ ምድር በሰው መረጃ የሚሰበሰብባቸው ጣቢያዎች አንድ ሺህ 372 ደርሰዋል:: አውቶማቲክ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ደግሞ 300 ደርሰዋል:: ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ አቅም እየተገነባ መሆኑን የሚያሳይ ነው::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያላትን የመልካዓምድር አቀማመጥ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዝቅተኛ፤ በደጋማ፤ በወይና ደጋማ አከባቢዎች ጣቢያውን የመገንባት ስራ ተከናውኗል:: በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው የምክረ ሀሳብ፤ የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የክልል ሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተቋቁመዋል::
በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሶስት ሶስት ቅርንጫፍ ማዕከላት፤ በኦሮሚያ ጅማ፣ አዳማ እና ባሌ-ሮቤ፤ በአማራ በኮምቦልቻ፣ ባሕርዳር፣ ምዕራብ አማራና ምስራቅ አማራ፤ በሌሎች ክልሎች ደግሞ በእያንዳንዳቸው አንዳንድ ጣቢያዎች ተቋቁመው እየሰሩ ነው:: እነዚህ ጣቢያዎች ጂኦግራፊያዊም ይሁን የፖለቲካዊ ድንበር ሳይገድባቸው መረጃዎችን በመሰብሰብ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት ይሰጣሉ:: ስለዚህ በእኛ ግምገማ ተደራሽነቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከቁጥር ባለፈ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ውጤት ስለመኖሩ መለኪያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ፈጠነ፡- ሁለቱም ጽንፍ የረገጡ የአየር ጠባይ (climate extremes) ብለን የምንጠራቸው የአየር ጸባዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጥማሉ:: የዓለም አቀፍ ኢሊኖ ወይም ላሊና ተጽዕኖ በሀገራች ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል:: በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሕንድና በሜድትራንያን፤ በፓሲፊክ እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚስተዋሉ የባህር መሞቅና መቀዝቀዝ በኢትዮጵያ የሚኖረው የአየር ሁኔታን ከመወሰን አንጻር አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ::
ኢንስቲትዩቱ እነዚህ የአየር ጸባይ ዓለማቀፋዊ የሜትሮሎጂ ክስተቶችን በመተንተን፤ በሀገር ውስጥ በተተከሉት የአየር ትንበያ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች የሚገኙ የረጅም ጊዜ መረጃዎችን ወደ ኋላ ሂዶ በመተንተን፣ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ወቅቶች መሰረት በማድረግ እንደ ሀገር ሊከሰት የሚችለውን የአየር ሁኔታና ጸባይ ቀድሞ መረጃው ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ተደራሽ ያደርጋል::
ለምሳሌ ኢትዮጵያ በጋ፤ ክረምት፤ በልግ ተብለው እያንዳንዳቸው አራት አራት ወራትን የያዙ ወቅቶችን ታስተናግዳች:: ስለዚህ የበጋ ወቅት ከመግባቱ በፊት ለባለድርሻ አካላት ባሉበት መረጃው ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል:: በጋ ብለን ስጠራ ከጥቅምት ጀምሮ እስከ ጥር ያሉትን አራት ወራት የሚያጠቃልል ነው:: በልግ ደግሞ ከየካቲት ጀምሮ እስከ ግንቦት ያሉትን ወራት ያካትታል:: ክረምት ተብሎ የሚጠራው ከሰኔ ጀምሮ እስከ መስከረም ያሉትን አራት ወራቶች የሚያጠቃልል ነው::
እነዚህ ወራቶች ከመግባታቸው በፊት ከሕብረተሰቡ ጀምሮ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በአካል ጭምር በመገናኘት መረጃው እንዲያገኝ ይደረጋል:: የተሰበሰበው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖን በማሳየት የትንበያ መረጃ ይሰጣል:: በግብርና፤ በውሃ፤ በጤና ዘርፎች ላይ ሊያመጣ የሚችለውን በጎም ሆነ አሉታዊ ጫና የሚቀርብት ሁኔታ አለ::
በተጨማሪ የውሳኔ ሰጭ አካላት በብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ውስጥ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ምክር ቤት አለ:: በምክር ቤቱ ውስጥ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት አባል ሆኖ መረጃዎችን ለውሳኔ ሰጭ አካላት፤ ለክልል ፕሬዚዳንቶች፤ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌደራል ሚኒስቴር ተቋማት ባሉበት ምን አይነት የአየር ሁኔታ ጸባይ እንዳለና አሉታዊና አዎንታዊ ጫና እንዳለው ገለጻዎች ይሰጣሉ:: ይህን መረጃ ፖሊሲ አውጪው ወስዶ ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ በግብርና፤ በውሃ፤ እና በጤና፤ ላይ ምን አይነት እርምጃ መወሰድ አለበት የሚለውን አቅጣጫ ይሰጣል::
የመረጃ ተደራሽነቱ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እናረጋግጣለን፤ በመገናኛ ብዙሃን በኩልም መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ እንሰራለን:: በታችኛው አስተዳደር እርከን የሚገኙ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ከግብርና ሚኒስቴር፤ ከውሃ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት መረጃ ሕብረተሰቡ እንዲያገኝ ይደረጋል:: በዚህ መልክ ተደራሽነቱን እለካለን:: በዚህም የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስ ተችሏል:: ለባለድርሻ አካላት ቃለመጠይቅ በማድረግና ሰርቬይ በመተንተን ጭምር ውጤታማነቱን እናረጋግጣለን::
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እንደ ድርቅ፣ ጎርፍና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ተከስተው ጉዳት ተስተናግዷል:: ተቋማዊ የትንበያ አቅማችሁ ውጤታማ ከሆነ እነዚህን ለምን ቀድሞ መገንዘብ አልተቻለም? ሙከራው ከነበረስ አደጋን በመቀነስ ረገድ የነበራችሁ አስተዋጾስ ምን ነበር?
አቶ ፈጠነ፡– ከአየር ጠባይና ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አደጋዎች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እየፈተነ ነው:: አደጋው ማስቀረት በተአምር አይቻልም:: ለምሳሌ፣ በቅርቡ በአሜሪካ ፍሎሪዳ የተከሰተው አውሎ ንፋስ ሀሪኬን መሰረት ያደረገ ከፍተኛ የሆነ ውድመት አድርሷል:: ስለዚህ እንደዚህ አይነት አደጋዎች መከሰታቸው አይቀርም:: ሆኖም የአየር ጠባይ ለውጥን ተጽዕኖን መቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ::
ለዚህ ግን የሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተሰጠው ስልጣንና ተግባር እንዲሁም የሀገሪቷን የመልክዓምድርና የወቅቶች ስብጥር ማየት ጠቃሚ ነው:: ምክንያቱም፣ አንዳንድ ጊዜ ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ ይከሰታል:: በሌላ ጊዜ ድርቅ ወይም የዝናብ እጥረት የሚያጋጥምበት ሁኔታዎች አሉ:: ይህ ይለያያል::
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሃ የሆነ የአግሮ ኢኮሎጂካል ዞን አለ:: ለምሳሌ ከመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ጀምሮ ከፍ ያሉት አከባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ክረምት ነው:: የምዕራብ የሀገሪቱ ከተሞች ደግሞ ‹‹ሞኖሞዳል›› የአንድ ወቅት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች ናቸው:: ሰሜን-ምስራቅ የሀገሪቱን ክፍል ብንወስድ ደግሞ አፋር፤ ምስራቅ አማራ፤ ምስራቅ ኦሮሚያ፤ ምስራቅ ትግራይ ብወስድ ደግሞ በልግ ሁለተኛ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው::
የደቡብ የሀገሪቱን ክፍል አጋማሽ ስንወስድ ደግሞ በክረምት ወቅት ምንም ዝናብ የማያገኝ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነ ሲሆን በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው:: ስለዚህ ብዝሃ የሆነ የአየር ጠባይ እና ሁኔታ የሚስተዋልበት አካባቢ ነው:: ከነዚህ አካባቢዎች ጋር የተጣጣመ አገልግሎት እየሰጠን ነው:: ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቀውም ከእነዚህ የሚገኘውን መረጃ መስጠት እና ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ ማድረግ ነው:: እያንዳንዱ ተቋም ካላቸው ነባራዊ በሁኔታ አንጻር ዝግጅት ያደርጋሉ::
ለምሳሌ፣ የጤናው ዘርፍ የአየር ሁኔታው ለዋባ ስርጭት ምቹ ነው? አይደለም? የሚለውን ተንትኖ ወረርሽኙን መግታት የሚችልበት መረጃ እንዲያገኝ እናደርጋለን:: ግብርናም በተመሳሳይ ዝናብ ቶሎ ገብቶ ዘግይቶ የሚወጣ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ሰብሎችን መዝራት ብቻ ሳይሆን፤ ምን አይነት ሰብልም መዝራት እንዳለበት ይወስናል::
ቦረና ላይ ባለፈው ድርቅ እንደነበር ይታወቃል:: ለተከታታይ ዓመት ዝናብ አልነበረም:: የድርቁን ጉዳት ለመቀነስ እንዲቻል የትንበያ መረጃዎቹን ለማድረስ ስራዎች ተሰርቷል:: ባለፈው የነበረው ድርቅ በዚህ ዓመት ለሌሎች አካባቢዎች ትምህርት የሚሰጥ ነው:: በድርቅ በሚታወቀው አካባቢ የስንዴ ምርት ማምረት እንዲቻል ተደርጓል:: ለዚህ ደግሞ የትንበያ መረጃ ወሳኝ ሚና አለው:: በዚህ በኩል በተሰራው ስራም ድርቁን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችም ተወስደዋል::
አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ የቦረናን ድርቅ ጨምሮ የመሬት መንሸራተት፤ ጎርፍ የመሳሰሉ አደጋዎች በሰው ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንዲያስችል የተንበያ መረጃ ተሰጥቶ ነበር?
አቶ ፈጠነ፡– አዎ፤ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት በነበረው መስከረም ወር ላይ ሁሉም ባለድርሻ ተቋም አስፈላጊውን ጥንቃቄና እርምጃ መውሰድ እንዲችል ምክረ ሀሳብና የትንበያ መረጃዎችን ሰጥተናል:: የትንበያ መረጃ እጥረት አልነበረም፤ ሆኖም በምክረ ሀሳቡ ልክ እርምጃ አልተወሰደም:: ለምን የሚለውን፣ የሚመለከትን ተቋም መጠየቅ ይገባል:: ከአየር ጠባይ ትንበያ አኳያ ግን መረጃ ቀድሞ ተሰጥቷል::
ይህ ብቻ ሳይሆን የትንበያ መረጃዎች ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች በኢትዮጵያ አቆጣጠር ለሁለት ዓመት ስድስት ወር የሚሆን የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃ ቀድሞ ይሰጣል:: ይሄን መነሻ ያደረገ ስራ እንዲከናወን ያስችላል:: ለምሳሌ፣ በቦረና ድርቅ ከሌሎች አካባቢዎች የሚገኝ የግጦሽ ሳርና መኖ ወደ ቦታው እንዲወሰድ በማድረግ እንስሳትን መታደግ ተችሏል:: ከዚህ ውጭ ከትንበያ መረጃ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ምንም ክፍተት አልነበረም::
አዲስ ዘመን፡- ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ባህላችሁስ?
አቶ ፈጠነ፡- ችግሮችን ለመቅረፍ ዓላማ ያደረገ የተጠናና የታተመ ሰነድ እንዲኖር አድርገናል:: የኢትዮጵያ የሜትሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል? የሚል (baseline assessment survey) የሚል ጥናት በገለልተኛ ወገን ተሰርቶ እንዲቀርብ ተደርጓል:: የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ምን እንደሚመስል ከተተነተነ በኋላ፤ ሌሎች ተቋማት የአጠቃቀምና የግንዛቤ እጥረታቸው ምንድ ነው የሚመስለው? የሚለው ተንትነናል:: ችግሮችን እንዴት እንፍታ? የሚል የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተሰርቷል:: ይህም የተቋሙ ሳይሆን ከግብርና፤ ውሃ እና ጤና ተቋማቱ ጋር በመሆን ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት (national framework) የሚል ስራ ተሰርቶ፤ ክፍተቶች፤ እድሎችና ስጋቶች እንዲለዩ ተደርጓል::
የተነደፈውን እቅድ በብሔራዊ፤ በክልል ደረጃ፤ በዞን ደረጃ እንዴት እንተግብር የሚል የቅንጅት መመሪያ (cordination guideline) ተዘጋጅቷል:: ይህ እንዲተገበር ባለድርሻ አካላት ፈርመው አጽድቀዋል:: ስለዚህ የቅንጅት፤ የትብብርና የመተጋገዝ ጉዳይ ምላሽ ያገኘ ነው:: ሁሉንም በንቃት በመከታተል ባለሙያዎቻቸው መድበው እኛ ጋር ሰርተው እንዲቀርቡ ይደረጋል:: የተጠና የተሰነደ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስራ እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ዘመናዊ የሜትሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን ከመጠቀም አንጻር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ፈጠነ፡– የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅት የወሰነው የመረጃ መሰብሰቢያ ስታንዳርድ አለ:: በዚህ ሁኔታ የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የሜትሮሎጂ ጣቢያዎች አሉ:: ሳይኖቲክ ተብለው የሚጠሩ አሉ:: እነዚህ በዓለም አቀፉ ስታንዳርድ መሰረት በየሶስት ሰዓት ልዩነት መረጃዎች ይሰበሰቡና ወደ መረጃ ቋት ይልካሉ:: ሁለተኛ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ የሚባሉም አሉ:: ሶስተኛ ደረጃ ዝናብና ሙቀት ብቻ የሚለካ፤ አራተኛ ደረጃ ዝናብ ብቻ ሚለኩ የ‹ሜትሮሎጂ ጣቢያዎች አሉ:: እነዚህ መረጃዎች ከየጣቢያዎቹ ተሰብስበው ለውሳኔ ሰጭ አካላት ይተነተናሉ፤ ይሰነዳሉ:: ለምርምርም አጋዥ ናቸው::
አሁን ላይ ጊዜው የዲጂታል ዘመን እየሆነ ስለመጣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ አውቶማቲክ የአየር ጻባይ ጣቢያ እየተቀየሩ ነው:: ሰው አልባ የሆነ አውቶማቲክ የአየር ጻባይ ሁኔታ መከታተያ ጣቢያዎች 300 ደርሰዋል:: ከየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ በ15 ደቂቃ ልዩነት ውስጥ መረጃዎችን በሞባይል ሲም ካርድ ወደ ማዕከል ማስገባት የሚያስችል ስርዓት ተፈጥሯል:: ይህም ዋና ጠቀሜታው በጦርነት በተጎዳ አካባቢ፤ ሰዎች በአካል ሂደው መረጃ መሰብሰብ ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ከማዕከሉ ሰርቨር ላይ ማግኘት ይችላሉ::
አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለውን መረጃ ለመሰብሰብ ያግዛል:: በተለይ ለጎርፍ፤ ለድርቅ አስፈላጊ መረጃዎችን የሚይዝ ነው:: ይህ ራዳር ሻውራ ላይ አለ:: በቅርቡም ሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ ላይ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ከፍታን መሰረት ያደረገ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር የመትከል ስራ ተሰርቷል:: በሀዲያ ዞንና በቡኖ በደሌ ላይ በተመሳሳይ ተከላ ላይ ነው::
ይህ ራዳር በጣም ውድ ነው ነገር ግን የሜትሪዮሎጂ መረጃ ከማዘመን አንጻር ከፍተኛ ሚና አለው:: ሌላው የሳተላይት መረጃ ሲሆን ጣቢያዎቹ በሌሉባቸው አካባቢዎች ከሳተላይት የተቀዳ መረጃን በመጠቀም መረጃን መተንተን የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል:: ኢትዮጵያ የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አባል ናት:: ኢትዮጵያ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉርን በፕሬዚዳንትነት እየመራች ነው::
አዲስ ዘመን፡- መረጃዎችን ከመሰነድ እና ከማስቀመጥ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር ግብአት እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ በተቋሙ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ፈጠነ፡– እዚህ ሀገር ውስጥ የተደራጀ መረጃ ሊኖር የሚችለው የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ ነው:: ጥሩ እና በተደራጀ መልኩ ‹‹በሃርድ ኮፒ›› እና ‹‹በሶፍት ኮፒ›› መረጃዎችን አደራጅተን እናስቀምጣለን:: <<የሃርድ ኮፒው>> መረጃው ላይ ድንገት እሳት ቢነሳ ወይም ጦርነት ተነስቶ ቢወድም ‹‹ዳታ ሪስኪዩ›› ወይም ዳታን ከአደጋ መከላከል በሚል በዲጂታል መንገድ መረጃዎችን እናስቀምጣለን::
የተጠቃሚዎች የመረጃ አጠቃቀም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ነው:: ይሄ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የሜትሮሎጂ መረጃ ሳያመጣ የዲግሪ ማሟያ ጽሁፉን ሊያስገባ አይችልም:: በማስተርስ እና በዶክትሬት ደረጃ ለጽሁፍ ማሟያቸው የሚጽፉት የኛን መረጃ ይዘው ነው:: በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ እና ዓመታዊ የዝናብ መጠን በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ ምንድ ነው የሚመስለው? የሚለውን ለማወቅ የሜትሮሎጂ መረጃን ሳይጠቀም ማስቀመጥ አይቻልም:: ተቋማት መረጃዎቻችንን ለምርምር ይጠቀሙበታል:: መረጃው በጣም ወሳኝነት ያለው ስለሆነ ተጠቃሚውም በዛው ልክ እያደገ ነው::
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ሰራተኞችም እድገት የሚያገኙት ምርምር በሰሩ ቁጥር ነው:: ተቋሙ የምርምር ተቋምም እየሆነ ነው:: ኢንስቲትዩት የሚለው የምርምር ተቋም እና የአቅም ግንባታ ተቋም መሆኑን የሚሳይ ነው:: ስለዚህ አንድ ሰራተኛ ከአንድ የስራ እርከን ወደ ሌላኛው መሸጋገር የሚችለው በሚያቀርበው የጥናት እና የምርምር ውጤት መሰረት ነው:: አንድ ሰራተኛ አንድ ግዜ ያደገበት የምርምር ስራ ውጤቱ ለሌላ ግዜ እድገት ለማግኘት ስለማይሆን ሰራተኞች ‹‹ሰርቫይቭ›› ለማድረግ ሲሉ ምርምሮችን ያደርጋሉ:: እነዚህ የምርምር ስራዎች በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ፤ በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ሶሳይቲ (ማህበር) እና በኢንተርናሽናል ጆርናሎች ላይ ይታተማሉ:: ይሄም መነሳሳትን ይፈጥራል::
አዲስ ዘመን፡- ጥናቶቹ በተጨባጭ መፍትሄ ከማምጣት እና አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ትንበያዎችን ከመስጠትስ አኳያ ያላቸው ጠቀሜታ ምን ይመስላል?
አቶ ፈጠነ፡- የተቋማት ተግባርና ኃላፊነት አለ:: ምርምሮቹ ውጤት እያመጡ ናቸው:: ከተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የሚሰሩ ጥናቶች አሉ:: ጥናቶቹም ችግር ፈች መሆን አለባቸው:: የተለያዩ ዲፓርትመንቶች አሉን:: ለምሳሌ የትንበያ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚባል አለ:: ይሄ ክፍል ሳይንሱን መሰረት አድርጎ፤ የ‹‹ኢሊኒኖ›› ተጽኖ፤ የ‹‹ላኒናን›› ተጽእኖ፤ የ‹‹አረቢያን ሲ›› በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ በመውሰድ በራሱ ደረቁ ሳይንስ ላይ ጥናት ያደርጋል::
ሁለተኛ የሚመጣው ተጽእኖው በዘርፎች ይለያል:: በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊ፤ በውሃ፤ በግብርና እና በጤና ላይ ምን ተጽእኖ አለው? ግብርናም እንዲሁ ለብቻው በበቆሎ፤ በማሽላ፤ በአተር፤ በቅባት እህሎች እና በጥራጥሬዎች ላይ ያለው ተጽእኖ ለማወቅ ከተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ማዕከላት እና ዋና መስሪያ ቤት ላይ ያሉ መረጃዎችን በመጠቀም ጥናትና ምርምሮች ይካሄዳል:: እነዚህ የምርምር ውጤቶች ለባለድርሻ አካላት እየቀረቡ ይተነተናሉ:: ስለዚህ በሚቀርበው ምክረ ሃሳብ መሰረት የበለጠ ዋናው ግቡ የትንበያውን እና የተጽእኖ ተጋላጭነት መጠኑን የሚቀንስ ጥናትና ምርምር ይደረጋል::
አዲስ ዘመን፡- የመሬት መንሸራተት ጉዳይ ላይ ምን ያህል ጥናቶችን ትሰራላችሁ? ቅድመ ትንበያስ ትሰጣላችሁ?
አቶ ፈጠነ፡- ‹‹የላንድ ስላይድ›› ጉዳዩን በተመለከተ በተቋም ደረጃ ኃላፊነቱ የኛ አይደለም:: ተቋማት የተቋቋሙለት ዓላማ አለ:: የሜትሮሎጂ መረጃ ሲባል ከገጸ ምድር በታች አንድ ሜትር ጀምሮ እስከ ከፍታ ውስጥ 30 ኪሎ ሜትር ያሉትን መረጃ የሚያጠቃልል ነው:: ከአንድ ሜትር በታች የሆነ ጉዳይ ከሆነ የኛ ጉዳይ ሳይሆን የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጉዳይ ነው:: እኛ ከመሬት አንድ ሜትር ወደ ውስጥ የምንሰራው የአፈሩን ‹‹ቴምፕሬቸር›› እና የእርጥበት መጠኑን መረጃ እንሰበስባለን:: ይሄ ለአስፓልት ስራዎችም ጠቃሚ ነው::
ከዛ ያለፈ ደግሞ ‹‹ከቮልካኒክ ኢራብሽን››ጋር፤ ‹‹ላንድ ስላይድ›› እና ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮች ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በዋናነት ይሰራል:: ምክንያቱም ለዚህ ተቋም ያስፈልጋል:: ጃፓንም ውስጥ የሲስሞሎጂ እና ጂኦሎጂ ተብሎ አንድ ላይ ነው:: ኮሪያ እና ቻይና አደረጃጀታቸው ተመሳሳይ ነው:: ከኛ ሀገር አንጻር ሁሉን መረጃ አይደለም የምንከታተለው እኛ የምንከታተለው ከአየር ሁኔታ ጸባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነው::
የሰው ሰራሽ አደጋዎች ማለትም በግጭት እና በጦርነቶች የሚነሱትን መተንበይ አንችልም:: እንደ ዜጋ ይመለከተናል ግን ዋና ስራችን አይደለም:: ዋና ስራው የሆነ ሌላ ተቋም አለ:: ስለዚህ የነዚህን ጥልቅ መረጃ የምናገኘው ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ነው:: ተቋሙ ካለ የምመክረው (ሪኮመንድ የማደርገው) በአዋጅ እና በስልጣን ሲሰጥ ለዛ የሚያስፈልገውን ባለሙያ ጭምር ማደራጀት ያስፈልጋል:: አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተለያዩ ባለሙያዎች አሉት:: የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሙያዎችንም አካቶ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል:: እኛ ግን የምናተኩረው ከአየር ጸባይ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጉዳዮችን ነው::
አዲስ ዘመን፡- መረጃ ከሰጣችሁ በኋላ ሰዎች መረጃውን እየተጠቀሙበት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ትገመግማላችሁ? ከሆነስ ውጤቱን በምን መንገድ ትከታተላላችሁ?
አቶ ፈጠነ፡- ባልተሰጠኝ ስልጣንና ኃላፊነት ውስጥ ይሄ ነው ማለት አልችልም:: ጦርነት እና የሰዎች መፈናቀልም አደጋ ነው:: በዋናነት የሜትሮሎጂ ስራ ሊሆን ግን አይችልም:: አደጋ መከላከል የሰብአዊ ድጋፍን ከማቅረብ አንጻር ተጎጂዎችን ለይቶ ከማገዝ ጋር ስራውን ሊሰራ ይችላል:: ሜትሮሎጂ ደግሞ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀለ ሰው ቢኖር መጠለያ ከሌለው ዝናብ እየመጣ ነው ወይም ድርቅ አለ የሚለውን በመንገር መንግስት ዝግጅት እንዲያደርግ ምክረ ሃሳብ ይሰጣል::
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚባለው የምርምር እና አገልግሎት ሰጭ ተቋም ነው:: ባለስልጣን የተባሉት ደግሞ ተቆጣጣሪ ናቸው:: ለምሳሌ የሲቪል አቬሽን ባለስልጣን የአየር መንገዱ እና የኢትዮጵያ የሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት፤ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት አሰራርን እና የዓለማቀፍ የሲቪል አቬሽን አሰራርን ተከትለው መስራታቸውን ያረጋግጣል:: ከዛ ያነሰ ስታንዳርድ እየሰጡ ከሆነ የመቅጣት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት::
እኛ ግን የምንሰጠው አዋጁ ላይም የተቀመጠው አገልግሎት ነው:: አገልግሎት መስጠት ሲባል ለጤና፤ ለውሃ እና ለግብርና ሴክተሮች እንዲጠቀሙ ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን:: ሴክተሮቹም የኛን መረጃ እና ትንበያ መጠቀም ይፈልጋሉ:: ስለዚህ ስለተቆጣጠርናቸው፤ ለምን አልተጠቀማችሁም ስላልናቸው ወይም ስላሰርናቸው ሳይሆን ‹‹ሰርቫይቭ›› ለማድረግና የተሻለ ምርት እንዲኖራቸው ሲሉ የሜትሮሎጂ መረጃን መጠቀም ግዴታ ነው::
ግብርና ላይ ያሉት የአግሮ ሜትሮሎጂ ምክረ ሃሳብን ማግኘት አለባቸው:: መቼ ልዝራ? መቼ ልጨድ? መቼ መኸር ይሰብሰብ? የሚለውን ለመለየት መረጃ ይወስዳል:: ማዳበሪያ የሚወስደው ስላስገደድነው አይደለም:: ሕብረተሰቡም ስለሚያስፈልገው ነው:: ይሄም መረጃ እንደ አንድ ግብአት ስለሆነ መረጃውን ይጠቀማል:: እኛም ይሄንን አልፈን አስገዳጅ አላደረግነውም:: በየግዜው የምናካሂደው ግምገማዎችም የባለፈው የሰጠነው ትንበያ ምን ይመስላል? ምን ያህል ጠቅሞናል? ምንስ የጎደለ ነገር አለው? ምን መሟላት አለበት? የሚለውን በስፋት አንስተን እንገመግማለን:: ባለድርሻ አካላት ላይ የሚነሳ ክፍተት ካለ በዛው መድረክ ላይ ምክረ ሀሳቦችን እንሰጣለን::
አዲስ ዘመን፡- ምክረ ሃሳብ የምታቀርቡበት የግዜ ገደብ አለ? ወይስ አደጋዎች ሲከሰቱ ነው ምክረ ሃሰብ የምታቀርቡት?
አቶ ፈጠነ፡- በየሳምንቱ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ጀምሮ እስከ ሚዲያ አካላት ድረስ በየቀኑ መረጃ ያገኛል:: ለፕሬዚዳንቱ በየእለቱ ተፈርሞ መረጃው በ‹‹ሃርድ ኮፒ›› ይገባል:: ለግብርና ሚኒስቴር እና ለመከላከያ መረጃው ይሰጣል:: ይሄም የሚደረገው አደጋ ካለ ሰዎችን ለማውጣት እንዲቻል ነው::
የአጭር ግዜ፤ የመካከለኛ እና የረጅም ግዜ በመባል የምንሰጠው ትንበያ በሶስት ይከፈላል:: የአጭር ግዜው ቅጽበታዊ ጎርፍ በሚከሰትበት ወቅት የሚያገለግል ነው:: መካከለኛ ግዜ የሚባለው እስከ 10 ቀን ያሉትን ለውሳኔ ሰጭ አካላት ምን እንደሚመስል መረጃ የምንሰጥበት ነው:: ከሶስት እስከ አራት ገጽ የሆነ ምክረ ሃሳብም እንሰጥበታለን::
በየሴክተሩ ደግሞ ፕላትፎርም አለ:: የአግሮ ሜትሮሎጂ ግብረኃይል አለ፤ የውሃ ሜትሮሎጂ (ሀይድሮ ሜትሮሎጂ) እና ከጤና ጋርም ራሱን የቻለ ግብረ ኃይል አለ:: እነዚህ ዘርፎች ራሳቸውን የቻሉ ፕላትፎርም አላቸው:: በዛም መረጃ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ:: ክልሎችም እንዲሁ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሚኛ ለሁሉም ለሚመለከታቸው ተቋማት መረጃ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ:: ውሳኔ ሰጭው ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የአየር ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን በየ10 ቀናት ውስጥ መረጃው በቢሯቸው ይገባል:: ስለዚህ ወቅት ጠብቀን አይደለም መረጃ የምንለዋወጠው::
በግብርና ስራ ውስጥ የሚዘራ ነገር ስላለ የአጭር ግዜ ትንበያ አይደለም የሚስፈልገው የረጅም ግዜው ነው:: የዝናቡ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን ቅድመ ጥቆማ እንሰጣለን:: አምስት ወር ቀድመን የበልግ ትንበያ እንሰጣለን:: ውሃ የሚያዝ ከሆነ ለመያዝ እንዲያመች በአጠቃላይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነ ሁኔታ ካለ ቀድመን እርምጃ ለመውሰድ የሚስችለን መረጃ የምንሰጥበት ነው::
አቬሽንን ብንወስድ ቀን ተጠብቆ ሳይሆን በየሰዓቱ መረጃ ይሰጣል:: አውሮፕላን ሲነሳ፤ ሲጓዝ እና ሲያርፍ መረጃ እንሰጣለን:: ይሄንን መረጃ በመጠቀምም አውሮፕላኑ ለመነሳት ይዘገያል? ወይም አይዘገይም? የሚለውን እና ለማረፍም የአየሩን ሁኔታ እናሳውቃለን:: አየሩ የማያሳርፍ ከሆነ እስኪከፍት ድረስ ካለበት አይነሳም ወይም ሰማይ ላይ የሚሽከረከርበት እና ወደ አቅራቢያው ባለው ኤርፖርት የሚያርፍበት ሁኔታ ካለ እናሳውቃለን:: ስለዚህ ይሄን አይነቱ የመረጃ ልውውጥ በሰዓታት ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- በስራችሁ ሂደት እንቅፋት ወይም ተግዳሮት የሆኑባችሁ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ችግሮች ወደ እድል ከመቀየር አኳያስ ምን ሰራችሁ?
አቶ ፈጠነ፡– እንደማንኛም ስራ ከየትኛውም ዩንቨርሲቲ የተመረቀ የሰው ኃይል አይደለም የምንወስደው:: ሙያው ልዩ ትኩረትን ይፈልጋል:: ተቋሙ በአብዛኛው በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ከማቆየት አንጻር ውስንነት ነበረው:: ብዙዎቹ ወደ ሌሎች ግብርና እና ሌሎች ተቋማት ላይ የመስራት እድል አላቸው::
ከአቬሽን ጋር አብረን እንሰራለን:: የአየር በረራ ስኬታማ የሚያደርጉት የአቬሽን ሜትሮሎጂ የሚባል ዲፓርትመንት አለ:: ካሉን ሰራተኞች እና በጀት አንጻር ወደ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ለዚህ ዲፓርትመንት ነው የምናውለው::
አየር መንገዱ የተሳካ በረራ እንዲያደርግ የእኛም ድርሻ አለበት ብለን እናምናለን:: ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ስኬታማነት በርካታ ተቋማት ሚና አላቸው:: ሜትሮሎጂ አንዱ እና ዋናው ነው:: የትኛውም አውሮፕላን የሜትሮሎጂ መረጃ ሳያገኝ መነሳት፤ መብረር እና ማረፍ አይችልም:: ዓለማቀፍ ሕጉም ያስገድደዋል:: መረጃ ሳያገኝ ምናልባት ተነስቶ አደጋ ቢመጣ የኢንሹራንስ ተቋማቱ ካሳውን ለመከፈልም ይቸገራሉ::
የእኛ ተቋም ከዛሬ አምስት ስድስት ዓመት በፊት የሰው ኃይል ችግር ነበር:: ከጥቅማ ጥቅም እና ከክፍያ አኳያ ቅሬታም ነበራቸው:: በዛም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራተኛም ይለቃል:: ይሄንን በመያዝም የሰው ኃይል ሃብታችን ላይ በቁርጠኝነት መስራት ነበረብን:: በዚህም በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ 121 የሚሆኑ ተመራማሪዎችን በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ማስመረቅ ተችሏል::
ከአርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ጋር በመስማማት በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች፤ ‹‹የክላይሜት ሪሌትድ ሰርቪስ›› ከሚሰጡ ተቋማት ጋር እና ከዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ጋር እንዲሁ በሕብረት በመስራት የሚሰጡንን እድሎች በመጠቀም በቻይና እና በአሜሪካ ከሚገኘው ተቋም ጋር በመነጋገር ጅግጅጋ፤ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላሉ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ አድርገናል:: ችግሮችም የተቀረፉበት ሁኔታ አለ:: የሜትሮሎጂ ተጨባጭነትም ጨምሯል::
መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት የሰጠበት እና የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ጋር በመነጋገር የአፍሪካ የሜትሮሎጂ ጽህፈት ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ማድረግ ችለናል:: ይሄንን ለማድረግም ከብዙ ሀገራት ጥያቄውን አቅርበው ስለነበር እኛ በቀኝ ገዥዎች ያልተገዛን መሆናችንን፤ ተቋሙ በየግዜው እያደገ ያለ መሆኑን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድም በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ላይ በረራ ያለው መሆኑን በማስረዳት ጽህፈት ቤቱ እዚሁ እንዲሆን ማድረግ ችለናል:: ስለዚህ ያጋጠሙንን ችግሮች ወደ እድል መቀየር ችለናል::
አዲስ አበባ፡- ተቋሙ በቀጣይ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ጭምር ለመስራት ምን አቅጣጫ አስቀምጧል?
አቶ ፈጠነ፡– ዋናው መዘመን ነው:: በሆነ ግዜ አንድም ራዳር አልነበረንም በቅርብ ወደ አራት ተክለናል:: ዋጋው ውድ ስለሆነ እንጂ ለኢትዮጵያ አራት ራደር ብቻ በቂ አይደለም:: በስቴሽን ማስተር ፕላናችን መሰረት 12 ራዳር ያስፈልገናል:: ስለዚህ ገና ስምንት ያስፈልገናል:: ለዚህ ደግሞ ሃብት የማፈላለግ ስራ ይጠበቅብናል:: ዓለም አቀፍ የመረጃ ልውውጥንም የማጠናከር ስራ መስራት አለብን:: ይሄንንም ታሳቢ በማድረግ የሃብት ማፈላለግ ስራ እየተሰራ ነው:: በአብዛኛው ሀገራችን የተሳካላት ሀገር ናት:: በጣም ውስን የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በቅርቡ ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ሪሶርስ ያገኘንበት ሁኔታ አለ::
ለአውሮፕላን በረራ የሚደረገው የሜትሮሎጂ ትንበያ መሳሪያውን ራሱ አውሮፕላኑ ላይ መግጠም እና አውሮፕላኑ በሚበርበት ከፍታ ልክ መረጃ እየሰበሰበ እንዲልክልን በማድረግ እና በመተንተን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ መረጃ ሰብስቦ የሚመጣልንን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራን ነው:: በአጠቃላይ በአስቀመጥነው ራዕይ መሰረት የሜትሮሎጂ መረጃዎችን የሚያዘምን ስራ ይሰራል::
ሌላኛው፣ የዓለም ሜትሮሎጂ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት መቀመጫው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ማድረግ ችለናል:: ለዚህም ቦሌ ላይ እየገነባን ያለነው ሕንጻ ‹‹የካፓሲቲ ቢዩልዲንግና›› የምርምር ተቋም ነው:: ይህ ማለት በአብዛኛው የአፍሪካ ተቋማት ‹‹የሪጂናል ትሬዲንግ ሴንተርን›› በማጠናከር ለሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችን አገልግሎት በመስጠት ከዓለም ሜትሮሎጂ የሚገኘውን አቅም በመውሰድና በራሳችን ያለንን አቅም በማጠናከር ታዋቂ የሜትሮሎጂ ሴንተር እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው::
አንዱ የሜትሮሎጂ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ለማድረግ ከዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅት ጋር እና ከአፍሪካ ጽህፈት ቤት ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል:: አንዱ የሜትሮሎጂ መረጃ በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን የማረጋገጥ፤ ከአደጋ ተጋላጭነት ስጋት ነጻ የሆነ ማህበረሰብን የማየት ሕልም ይዘን እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ቀረ የሚሉት እና የሚያስተላልፉት ሀሳብ ካለ እድሉን ልስጥዎ!
አቶ ፈጠነ፡– ሚዛኑን የጠበቀ የአየር ንብረት እንዲኖረን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብራችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል:: በሀገራችን የዝናብ መጠናችንን ለመጨመርና የውሃ ምንጮቻችንን ለማጎልበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብራችንን ማጠናከር ያስፈልጋል:: በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ስራዎችን መንከባከብና በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ጠቃሚ ይሆናል:: ሕብረተሰቡም ይሄንን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል:: በተቋም የሚሰጡ ትንበያዎችን በመጠቀም የመኸር እና የመስኖ ስራዎችን በማጠናከር የሕብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ያስፈልጋል::
የኮሊደር ልማቶቹም የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል ሚና ይኖራቸዋል:: ለምሳሌ በአዲስ አበባ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ችግር ነበረባቸው:: አሁን የተጀመረው ኮሊደር ስራ በከተሞች ላይ የሚፈጠረውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ሚና አለው:: በገጠር አካባቢዎች እና በረባዳማ ቦታዎች ላይ እንዲሁ ለሚከሰቱ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተቶች ጥንቃቄ ለማድረግ ሲባል ከወዲሁ የአሰፋፈር ሁኔታዎችን ማስተካከል ተገቢ ስለሆነ ዝግጅት ቢደርግበት መልካም ነው::
አርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ የሚሰጡ ትንበያዎችን በመመልከት በመኸር ግዜ የሚፈጠረውን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብን በሚመለከት የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን በመስማት እርምጃ መውሰድ እንዲችል መልእክቴን አስተላልፋለሁ:: እነዚህን አጠናክረን ከቀጠልን ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ጉዞ ማስቀጠል እንችላለን::
አዲስ ዘመን፡- ለጊዜዎትም ለሀሳቦትም አመሰግናለሁ!
አቶ ፈጠነ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ሞገስ ተስፋ እና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም