የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ ስያሜው የዓለም ሕዝቦች ድምጻቸው የሚሰማበት፤ ጥቅምና ፍላጎታቸው የሚከበርበት፤ ተሳትፎና ውክልናቸው ያለ አድሎ በፍትሃዊነት የሚገለጥበት መድረክ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስምና ግብሩ እየተነጣጠሉ፤ የዓለም መንግሥታት መድረክ መሆኑ ቀርቶ የጥቂት ኃያላን ፈላጭ ቆራጭነት ጎልቶ የሚታይበት ሆኗል፡፡
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ የኃያላኑ ጉዳይ አስፈጸሚ የሆኑ አንጃዎች በፈለጉት ሰዓት የፈለጉትን ነገር ሲፈጽሙም፤ ሲፈጸምላቸውም የሚታየው፡፡ በአንጻሩ ለእነዚህ ኃያላን ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን ለሀገራቸውና ሕዝቦቻቸው ታምነው የሚንቀሳቀሱ ሀገራት መንግሥታትን በእጅጉ ሲወገዙ፤ አለፍ ሲልም በማዕቀብ ሲናጡ፤ ከፍ ሲልም ይፋዊ የቀጥታና የእጅ አዙር የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዲናውዙ ሲደረግ የሚስተዋለው፡፡
አፍሪካም፣ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ ከስም የዘለለ ይሄ ነው የሚባል ተሳትፎም፤ ተደማጭነትንም ተነፍጋ የምትገኝ አህጉር ናት፡፡ አፍሪካውያን (ሕዝቦችም፣ መንግሥታትም) ከመድረኩ ሊኖራቸው የሚገባ ተሳትፎና ውክልና የማይገባቸው ተደርገው የተቆጠሩበት፤ ከዚህ የተነሳም ከፍ ላለ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎችም የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ጫና ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ቆይተዋል፡፡
ምክንያቱም፣ ምንም እንኳን አፍሪካ የሃምሳ አራት የአፍሪካ መንግሥታት አህጉር፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ተመድን የመሠረቱ ሀገራት ምድር፤ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ (ያውም አምራች እና ትኩስ ኃይል የሆነው ወጣት የበዛባት) ሕዝብ፤ ከፍ ያለ የተፈጥሮ ሀብት እና የመልማት እምቅ አቅም ያላት ብትሆንም፤ ይሄን ሁሉ ከፍ ያለ አቅም ባለቤትነቷን የሚመጥን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተሳትፎም፣ ተደማጭነት የሚያስገኝላትን ሥፍራም ማግኘት የማይጨበጥ ሕልም ሆኖባት ዘልቋል፡፡
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ አፍሪካውያን ሃምሳ አራት ሆነው እንደ አንድ በመቆጠር የአንድ ለብዙ መድረኮችን በመጠቀም ድምጻቸውን ለማሰማትና የልማት አቅማቸውን አውጥቶ ለመጠቀም ሲጥሩ የሚታየው፡፡ ለዚህም ነው አፍሪካውያን ኃያል ነን በሚሉ፣ ነገር ግን ኢፍትሃዊነትን ባነገቡ ሀገራትና ተቋሞቻቸው አማካኝነት የሚመጣን ፖለቲካዊም፣ ኢኮኖሚያዊም ሸክም በጫናቃቸው ላይ ለማኖር የተገደዱት፡፡
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ አፍሪካውያን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መታየት የሌለባቸው የልማት ጉዳዮቻቸው ጭምር አጀንዳ ሆነው እየቀረቡ የመልማት ጉዟቸው እንዲደናቀፍ ሲሠራ የሚታየው፡፡ ለዚህም ነው አፋሪካውያን በፈጸሙት ተጋድሎ የተጎናጸፉትን የነጻነት ብርሃን፤ በሌላ ቅኝ ገዥነት እሳቤ አፍሪካን ድጋሚ ለመቀራመት የሚደረገው እሽቅድምድም ጎልቶ የሚስተዋለው፡፡
እነዚህ አይነት ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን፣ ዲፕሎማሲን፣ ሰላምና ፀጥታን፣… ማዕከል አድርገው የሚደረጉ የእጅ አዙር አፍሪካን የማተራመስ፤ የማዳከም እና አቅም ነስቶ ዳግም በሌላ የቅኝ ግዛት ማዕበል ለመናጥ የሚደረግ እሽቅድምድም ግን፤ ዛሬ ላይ አፍሪካውያን የሚቀበሉትም፤ የሚሸከሙትም አይደለም፡፡
አፍሪካውያን ከትናንቱ ተምረዋል፤ በመሪዎቻቸውም፣ በአርቆ አሳቢ ልጀቻቸውም ታግዘው ስለ ነጋቸው ተልመው ዛሬን ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ከዚህም በላይ ለልማታቸው፣ ለሰላምና ፀጥታቸው፣ ለዲፕሎማሲ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸው የሌሎችን ውሳኔና ይሁንታ ከመጠበቅ መውጣት እንዳለባቸው ስለሚያምኑም፤ አፍሪካውያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ባሉ አደረጃጀቶች ሁሉ ተገቢውን ውክልና ለማግኘት የሚያስችላቸውን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ይሄ ጥያቄ ደግሞ ለመጠየቅ ያህል የቀረበ አይደለም፡፡ ይልቁንም አፍሪካውያን የሳራቸውን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ሁሉ ጉዳይ ግድ ይላቸዋል እና በዚህ ላይ መምከርም መወሰንም የሚያስችላቸውን የቬቶ ፓወር ውክልናም ጭምር ማግኘት እንዳለባቸው አበክረው ያምናሉ፡፡ ይሄንኑም እንዲፈጸም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አሳስበዋል፡፡
ይሄ ጥያቄያቸው ታዲያ ሊደመጥ ብቻ ሳይሆን ተመዝኖ በልኩ መልስ ሊያገኝ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም አፍሪካ በሁሉም መስክ ይሄን ጥያቄዋን መልስ እንድታገኝ የሚያስገድድ አያሌ ጉዳዮች አሏትና ነው፡፡ ከሰሞኑም የአዲስ አበባ ለይፋዊ ጉብኝት የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስም ይሄንኑ እውነት የተገነዘቡ ይመስላል፡፡
ዋና ፀሐፊው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትም ሆነ ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት በዚሁ ጉዳይ ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል፡፡ መጠቆም ብቻም ሳይሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአፍሪካውያን ተሳትፎም ሆነ ተጠቃሚነት እውን መሆን፤ ለሕብረቱም ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት፤ አፍሪካ ላይ ለሚፈጸም ማናቸውም ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ በተለይም ጊዜውን በማይመጥን የፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ደባ ከመከላከል አኳያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በቅርበትም፣ በጋራም እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
ይሄ የዋና ፀሐፊው ገለጻ ተገቢም፤ ለተመድ እንዲወጣ የሚጠበቅ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እነዚህን ጉዳዮች ማዕከል ባደረገ መልኩ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በቅርበት መሥራት፤ የአፍሪካውያን ጥያቄ በልኩ ተገንዝቦም ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ አበክሮ መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም