በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ የኮሙዩኒኬን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሰሞኑን በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው ጹሑፍ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ያጸደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም ድምፅ ሲሰጥ የጎዛምንን ህዝብ ወክለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተሾመ እሸቱ ድምፀ ተዓቅቦ ማድረጋቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ተወካዩ ያንጸባረቁት አቋም የጎዛምንን ህዝብና አስተዳደር የማይወክል መሆኑንና የጎዛምን ህዝብና አስተዳደርም የፓርላማውን ውሳኔ የሚደግፍና የሚፈፅም መሆኑን ገልጾ ቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎችንም ህግና መመርያን ተከትሎ እንደሚያከናውን አሳውቋል፡፡
በሰፈረው ጽሑፍ ላይ በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ተወካዩ ያንጸባረቁት አቋም የወረዳውን ህዝብ ፍላጎት የማይወክል በመሆኑ ከእንደራሴነታቸው መውረድ እንዳለባቸው የሚገልጹ ናቸው፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ውዱ ድረስ በሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀም ግለሰብ ‹‹…ያንጸባረቁት አቋም የጎዛምንን ህዝብ የማይወክል በመሆኑ በአስቸኳይ ከምርጫ ወንበራቸው እንዲነሱ ወረዳው ማከናወን የሚገባውን ተግባር ፈጥኖ ቢጀምር እኔ በበኩሌ የድርሻዬን እወጣለሁ…›› በማለት ወረዳው ግለሰቡን ከእንደራሴነት ለማንሳት እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡
‹‹ህዝብ በመረጠው የምክር ቤት አባላት ላይ አመኔታ ሲያጣ ተመራጩን ከምክር ቤት አባልነት በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲታገድ ማድረግ ይችላል። ስለዚህ የወረዳው ህዝብ ግለሰቡ ከምክር ቤት አባልነት እንዲነሳ አዴፓን መጠየቅ አለበት›› በማለት አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ደግሞ ጌታሁን ዋሌ በሚል ስም ፌስቡክ የሚጠቀሙ ግለሰብ ናቸው፡፡ ብርሃኑ ይትባረክ በሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀም ዜጋ በበኩሉ ‹‹በፍጥነት ውክልናውን አንሱት፡፡ ያለዚያ እናንተም የሱ ተባባሪ እንደሆናችሁ እንድናስብ እንገደዳለን›› በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
የጎዛምን ወረዳ አፈ ጉበኤ አቶ ይበልጣል ዘበናይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤አቶ ተሾመ የአካባቢው የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ለሦስተኛ ጊዜ በ2007 የተመረጡ ሲሆን፤ አሁንም ህዝቡን በመወከል በምክር ቤት በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
የአካባቢውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ ሥራዎችን ባለማከናወናቸው ከአባልነታቸው ለማስነሳት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በቅርቡም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሲቋቋም ድምፀ ተዓቅቦ ማድረጋቸውን ከተለያዩ ሚዲያዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ታማኝ ምንጮችም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ተወካዩ በዕለቱ በድምፀ ታቅቦ ያንጸባረቁት አቋም የጎዛምንን ህዝብ ስሜት ሳይሆን የራሳቸውን አስተያየት ነው፡፡ የወረዳው ህዝብና መንግሥት ኮሚሽኑ ተቋቁሞ በድንበርና በማንነት ጉዳዮች የሚታዩ ችግሮች የሚቀረፉበት ጥናት እንዲያከናውን ይፈልጋሉ፡፡ የወረዳው የፌስ ቡክ ገጽ ላይም ፓርላማው ያጸደቀውን ኮሚሽን መቋቋም የወረዳው ህዝብና መንግሥት የሚደግፈው መሆኑን አሳውቀናል ብለዋል፡፡
ተወካዩ የወረዳውን ህዝብ ጥቅም የሚጸረር ተግባር ሲፈጽሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም የሚሉት አቶ ይበልጣል፤ ከዚህ በፊትም የወረዳውን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር እየሠሩ አልነበረም ብለዋል፡፡ ተወካዩ ወደ ተመረጡበት አካባቢ መጥተው ከህዝቡ ጋር ሲወያዩ ህዝቡ የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ካለማግኘታቸውም ባሻገር ተገቢ ግብረ መልስ እንኳ ተሰጥቶባቸው አያውቅም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ይበልጣል ማብራሪያ፤ የህዝቡን አቋም ወደ ጎን ትተው የራሳቸውን አቋም በማራመዳቸውና የህዝቡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አለማድረጋቸው ከወንበራቸው ለማውረድ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከወንበር የማውረድ ተግባርም ህገ መንግሥቱን በመንተራስ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የህዝብ ድጋፍ በአስቸኳይ ተሰባስቦ እንደራሴው ውክልናቸው ሊነሳ ይገባል የሚል ጫና እየፈጠሩ ነው፡፡ ከዞኑ ከክልሉ የድርጅትና የአስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር በምን መልኩ መከወን እንዳለበት ውይይት ተጀምሯል፡፡
አቶ ተሾመ እሸቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን አዋጅ ሲጸድቅ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳይ ላይ ጥናት የሚያካሂድ ኮሚሽን መቋቋም የለበትም የሚል አቋም ስላላቸው አይደለም፡፡ ጥናት አይጠና ወይም ጥናቱ ሀገርን ይጎዳል የሚል አቋምም የላቸውም፡፡ እንዲያውም ጥናቱ ዘግይቷል የሚል አቋም አላቸው፡፡ እስከአሁን ድረስ ኮሚሽን ባይቋቋም እንኳ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸው ጥናት አድርገው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያቀርቡ ይገባ ነበር፡፡ ይህን የሚከለክል የህገ መንግሥት አንቀጽም ሆነ አዋጅ የለም፡፡ አሁንም ኮሚሽን መቋቋሙ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለማን ይሁን በሚለው ላይ የተለየ አቋም አላቸው፡፡ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚሆን ይልቅ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ቢሆን የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ፡፡
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ‘ስህተት’ ነው ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩት አቶ ተሾመ ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ቢሆን ግን ጠቀሜታው የጎላ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ያነሳሉ፡፡ ኮሚሽን ሲመሰረት ባለሙያዎች መሰብሰቡ ስለማይቀር ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲጠናከር እገዛ ይኖረው ነበር ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በፓርላማ ድምፅ በተሰጠበት ወቅት ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም በዚሁ አቋማቸው እንደሚገፉበት አሳውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ፤ ምክር ቤቱ ሲገለብጡት ይገለበጣል፤ ሲያቃኑት ይቃናል ሲባል ኖሯል፡፡ አይቃወምም፤እጅ አውጣ ሲባል እጁን ማውጣት ብቻ ነው፤የሃሳብ ልዩነት አይታይበትም የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ከርሟል፡፡ የሃሳብ ልዩነት በድምፀ ተአቅቦ፣ በተቃውሞ ወይም በድጋፍ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የሃሳብ ልዩነት መኖር እንዳለበት እሙን ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው እንቅስቃሴ የሃሳብ ልዩነት በፓርላማ ውስጥ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አይጠቅምም፡፡ የሃሳብ ብዝሃነትንም የሚገድል ነው፡፡
የምክር ቤት አባል በነፃነት መሥራት አለበት የሚሉት አቶ ተሾመ፤ በምክር ቤቱ ያንጸባረቁት አቋም ስህተት ነው ብለው እንደማያስቡ በመግለጽ፤ስህተት ሆኖ ቢገኝ እንኳ ሊወገዙ እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ በምክር ቤቱ ያንጸባረቁትን አቋም ተከትሎ የሚታየው እንቅስቃሴ የእርሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዜጎችም የትም ሆነው የመሰላቸውን ሃሳብ የማንጸባረቅ መብታቸውን የሚገድብ ነው፡፡ አሁን የተጀመረው ዘመቻ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ በተለይም የሃሳብ ብዝሃነት የሚከበርባት ሀገር እንገነባለን እየተባለ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተለየ ሃሳብ የያዘ አካል ላይ ውግዘት መፈጸም ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
‹‹የጎጃም ህዝብ የመረጠኝ አዴፓ ባቀረበው ፖሊሲ ነው እንጂ በራያና በወልቃይት ጉዳይ አይደለም›› ያሉት አቶ ተሾመ በራያና በወልቃይት ጉዳይ ላይ በያዙት አቋም ምክንያት ህዝቡ ከምክር ቤት መቀመጫቸው ሊያስነሳቸው የሚፈልግ ከሆነ ግን ከምክር ቤት ለመነሳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት እንደሚሉት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12(3) መሠረት ሕዝብ በመረጠው እንደራሴው ላይ አመኔታ ካጣ ማውረድ እንደሚችል ለመራጩ መብት ሰጥቷል፡፡ የክልሎች ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ መልኩ ለመራጮች መብት ይሰጣል፡፡ ስለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራረጥ የሚናገረው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በአንቀጽም 54 (7) ላይ መራጩ ሕዝብ አመኔታ ያጣበትን ተመራጭ ማውረድ እንደሚችል ደንግጓል፤ በክልሎችም እንዲሁ፡፡
በህገ መንግሥቱ መሰረት የጎዛምን ህዝብ የወከላቸው አካል ካላመነባቸው የማንሳት መብት አለው የሚሉት አቶ ውብሸት ህዝቡ አመኔታ ባጣበት ወቅት ጥሪ ማቅረብ እንደሚችል አንስተዋል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና አጠቃላይ የፓርቲው አባላት በደገፉት የኮሚሽን መቋቋም ሃሳብ ላይ ድምፀ ተአቅቦ አድርገው ቀርቶ አዴፓ የኮሚሽኑን መቋቋም የሚቃወም ቢሆንና ህዝቡ የኮሚሽኑን መቋቋም የሚፈልግ ቢሆን ተወካዩ የህዝቡን ፍላጎት ከማንጸባረቅ ይልቅ የፓርቲውን ፍላጎት በማንጸባረቁ ህዝቡ ከወንበሩ ሊያስነሳቸው እንደሚችል ነው ያብራሩት፡፡ መራጮቻቸው አመኔታ ያጡባቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዴት እንደሚያወርድ ሥርዓት ለማበጀት ሲባል በወጣው አዋጅ ቁጥር 88/1989 መሰረት 100 ሰው አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡
እንደ አቶ ውብሸት ማብራሪያ የምርጫ ቦርድ፣ የቀረበለትን አቤቱታ ካመነበት በወረዳው የምርጫ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ደጋፊዎች ከመቼ እስከ መቼ መመዝገብ እንዳለባቸው ያሳውቃል፡፡ በምርጫ ወረዳው ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች 15 ሺ ወይንም የወረዳው ምክር ቤትም ወስኖ ከሆነ 10 ሺ ሰው ከተመዘገበ ተወካዩ ይወርዳል፡፡ ይህ የምዝገባ ሒደት እንደ ማንኛውም የምርጫ ምዝገባ በየቀበሌው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ሰው ታዛቢ የሚሆኑትን ወኪሎቹን በየምርጫ ጣቢያዎቹ የማስቀመጥ መብት አለው፡፡
እንድ አቶ ውብሸት ገለጻ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዴት እንደሚወርዱ ሥርዓት ለማበጀት ሲባል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 88/1989 ላይም መራጩ ሕዝብ ወኪሉን ለማውረድ ምክንያት ማቅረብ እንዳለበት አላስቀመጠም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ደንብ ላይ፣ ወኪላቸው እንዲወርድ መራጮች ያቀረቡትን አቤቱታ ለይውረድልኝ ጥያቄው መነሻ አይሆንም ብሎ ካመነ ምርጫ ቦርድ አቤቱታውን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ምን እንደሆኑም በደንቡ ላይ አልተገለጹም፡፡ በደፈናው፣ ለሕዝቡ አቤቱታ መነሻ የሆነው ነገር በቂ ካልመሰለው ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል ብቻ አስቀምጧል፡፡
በአመኔታ እጦት የይውረድልኝ አቤቱታ አማካይነት ሊወርዱ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አሠራር የለም የሚሉት አቶ ውብሸት፤ የምርጫ ሥርዓታቸው የተመጣጣኝ ውክልና ከሆነ በእምነት ማጣት አማካይነት የሚወርደው ሙሉ ምክር ቤቱ ነው ይላሉ፡፡ ጥሪ ማድረግ(Recall) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በአንዳንድ አገራት፣ዜጎች አይበጀንም የሚሉት ሕግ እንዲሻርላቸው ወይንም በአዲስ እንዲተካላቸው የሚከተሉትን ሒደትም ያካትታል፡፡ ጥቂት አገራት ደግሞ ተመራጮች ብቻ ሳይሆኑ ተሿሚዎችንም በጥሪ ያወርዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
መላኩ ኤሮሴ