ጤፍ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለው ባህላዊም ሆነ ታሪካዊ ግንኙነት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምርቱ እጅግ ተወዳጅና ተመራጭ ከመሆኑ የተነሳ በየዘመኑና በየባህሉ የማይተው ብቻ ሳይሆን የማይቀየር ምግብ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአምስት ዓመት በፊት የሚታረሰው የጤፍ መሬት ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ሲሆን፤ አሁን ወደ ሦስት ነጥብ አንድ አምስት ሚሊዮን ከፍ ብሏል፡፡
በመቶኛ ሲሰላም በአራት ነጥብ አምስት አድጓል ማለት ነው፡፡ በምርት ደረጃም የዛሬ አምስት ዓመት የነበረው አጠቃላይ የጤፍ ምርት 44 ነጥብ ሰባት ሚሊየን ኩንታል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ 58 ነጥብ አንድ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል፡፡ ምርታማነቱም በሄክታር ይገኝ ከነበረው ከ16 ወደ 18 ኩንታል ማደግ ችሏል፡፡
የጤፍ ምርት ከማሳው ጀምሮ ጉሮሯችን እስኪደርስ ድረስ የሚያልፋቸው ሰንሰለቶች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ምርቱን አንዱ ለሌላው ሲያሻግረው ምክንያታዊም ይሁን አይሁን ማትረፍ መፈለጉ አይቀሬ በመሆኑ ዋጋው ሲወደድ ይስተዋላል፡፡
በዚህ ሂደት በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች የሚስተዋለውን አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት መነሻ በማድረግ በከተሞች ያሉ ነጋዴዎች አርሶአደሩ ዘንድ በመድረስ የጤፍ ምርቱን ለመግዛት ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በወኪሎቻቸው /ደላሎች እና ነጋዴዎች/ እጅ ለመውደቅ ተገዷል፡፡ ይህ ደግሞ ምርቱን ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያጋልጠዋል፡፡
የጤፍ ዋጋ ከአርሶአደሩ ጀምሮ የሚያመርትበት ዋጋ እያሻቀበ ከመምጣት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ አርሶአደሩ ጤፍ ሲያመርት ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ገዝቶ ነው፡፡ ለመሸጥ ሲሞክርም እንደ እስከ ዛሬ 20 እና 30 ዓመቱ የገበያ ዋጋ መጠበቅ አይገባም፡፡
የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ ይሸጣል፡፡ ደላላውም ሆነ ነጋዴው ደግሞ ጤፉን የገዛበትን ዋጋ እንዲሁም ሌሎች ምክንያታዊም ሆነ ምክንያታዊ ያልሆኑ
ወጪዎችን ደምሮ ለሸማች ያቀርባል፡፡ በዚህ የምርት ሰንሰለት ውስጥ የህገ ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎችን ሚና ስናክልበት ምን ያህል እንደሚሆን ለሸማች ጫንቃ የሚተው ነው፡፡
ከምርት እስከ ሸማች የሚደርስበትን ሂደት ስንመረምር በተለይ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ የጤፍ ዋጋ መናር ምክንያታዊ ናቸው የሚባሉትን ጉዳዮች ስንመረምር በዋናነት ከህዝቡ ቁጥር ማሻቀብ እኩል የጤፍ ፍላጎታችንን የሚሸከም አቅርቦት አለን ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በሁለተኛነት ሊነሳ የሚገባው ጤፉ የሚመረትበት የማምረቻው ዋጋ ግብዓትን ጨምሮ ወጪው እያደገ ለመምጣቱ ደግሞ አርሶ አደሩ ግብዓት የሚገዛበት ዋጋ ምን ያህል ነው? የሚለው ሌላው አስረጅ ነው፡፡
ከእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ተነስተን መንግሥት ምን ማከናወን ይገባዋል የሚለውን ማንሳት ወሳኝ ነው፡፡ አንደኛው መፍትሔ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚስማሙበት እና የዓለም ተሞክሮ አርሶ አደሩን መደጎም ነው፡፡ መንግሥት አርሶአደሩን ሲደጉም በተዘዋዋሪ የከተማውን ሰው እየደጎመ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡
በነጋዴው በኩል ዋጋ ለመጨመር ምክንያቶች ተብለው የሚነሱ የንግድ ሱቅ ኪራይ፣ የውሃና መብራት ታሪፍ ፣ የትራንስፖርት ወጪዎች ተመጣጣኝ መሆን እንዲችል ጉዳዩ ወደ መንግሥት ይመጣል፡፡ ሌላው ቁልፉ ጉዳይ የገበያ ሰንሰለቱን ጤነኛ ማድረግ ነው፡፡ በንግድ ሰንሰለቱ ያሉትን ተዋናዮች በሚገባ የመለየቱ ሥራ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ወቅት የጤፍ ዋጋ ንሮ መገኘት ቁልፉ ምክንያት አርሶ አደሩ ላይ፣ ነጋዴው አሊያም መንግሥት ላይ የሚወረወር አለመሆኑ በተግባር የሚታይ በመሆኑ የችግሩ ውስብስብነት መፍትሔውና የችግሩ ባለቤት አንዱ አካል ብቻ አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ በመሆኑም የጤፍ ዋጋን በተለይ ምርት ተሰብስቦ ጎተራም ሆነ ገበያ በሚቀርብበት ወቅት ዋጋው እንዲቀንስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122