አዲስ አበባ፡- የሶማሌዎች መብት በሕገ መንግሥቱ መሰረት ከተከበረ መነጠል አስፈላጊ መሆኑን እንደማያምን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ ግንባር አስታወቀ፡፡
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ዋና ጸሐፊና መስራች የሆኑት አቶ አብዱልራህማን መሀዲ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳስታወቁት፤ የሶማሌዎች መብት የሚገኘው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ መብቶች ከተከበሩ መነጠል አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኦብነግ በፕሮግራሙ የሶማሌ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለማስቻል የተቋቋመና እስከ መገንጠል የሚለውን ሃሳብ የሚያቀነቅን ድርጅት ነበር በአቋም ደረጃ የተለወጠ ነገር አለ ተብለው የተጠየቁት አቶ አብዱልራህማን ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በጣም ሰፊ ነው፡፡ መብትህን እንደ ብሄር መጠቀም፣ የራስህን ባህል መጠበቅ፣ የራስህን ተቋማት መገንባት፣ የራስህን ጉዳይ በራስህ ማስተዳደር፤ በሰላም መኖር፤ በሌሎች ብሄሮች አለመጨቆንን ያቅፋል›› በማለት፤ እነዚህ መብቶች ከተጣሱ መገንጠል ከተከበሩ ደግሞ አብሮ መኖር እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ ይህ መብት በህገ መንግሥቱም መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ አብዱልራህማን ማብራሪያ፤ አንዳንድ አካላት የኦብነግ ዓላማ መገንጠል ነው እያሉ ይፈርጃሉ፡፡ ይሄን ፍረጃ የሚያቀርቡት ሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ ነው የሚፈጥሩት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ መብታቸው ከተከበረ አብረው ይኖራሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ የብሄሮችና ብሄረሰቦች መብት መከበርና መብቶቹን ማስጠበቅ ከሌሎችም ጋር ተቻችሎና አብሮ መኖር ነው፡፡
‹‹ብሄሮችና ብሄረሰቦች በመንግሥት ማእቀፍ ተሳስረው ይኖራሉ፡፡ መንግሥት አይደለም፤ ሕዝብ ነው መንግሥትን የሚመርጠው›› ያሉት የኦብነግ ዋና ፀሐፊ፤ ለሕዝብ ተጠያቂ የሆነ ዴሞክራሲዊ መንግሥት ካለ መገንጠል አማራጭ አይደለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን የገለጹት አቶ አብዱልራህማን፤ኦብነግ ለተወሰዱት ተግባራዊ ዕርምጃዎች አድናቆት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል፡፡
ኦብነግ እኤአ በ1984 የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን፤ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በተያዘው ዓመት ህዳር ወር ወደ አገር ውስጥ ገብቷል፡፡
ጥር 2/2011
ወንድወሰን መኮንን