ወደ አንድ ጎን ያዘመመው ታድፖሊን ሸራ ከአናቱ መጠናቸው አነስተኛ ድንጋዮች ተበትነውበታል። ላስቲኩን ለመወጠር ያረፉት ቋሚ እንጨቶች ከላይ ያረፈባቸው የድንጋይ ሸክም የከበዳቸው ይመስላሉ። እናቶች የ“ስጥ” ላስቲካቸው ንፋስ እንዳይረብሸው ዳር ዳሩን በድንጋይ እንደሚያስይዙት ሁሉ በቤት ቅርጽ ተሠርተው የተወጠሩትን ሸራዎች የተመለከተ ታዛቢ የነዋሪዎቹን ችግር በቀላሉ ለመረዳት ይቻለዋል። አለፍ አለፍ ብለው የሚታዩት በተወጠሩ ሸራዎች መሀል በሚገኘው ክፍት ቦታ የሚጫወቱት ልጆች ድሎት የማይታይበት ገጽታቸው ከቤቶቹ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ወደ ውስጥ ሳይዘልቁ የኑሯቸውን ደረጃ ያሳያል። አንዳንዳንዶቹ ሸራዎች ደግሞ ለተሽከርካሪ በተዘጋጀው ጠባብ መተላለፊያ አስፓልት ዳር መገኘታቸው ሌቱን እንዴት ያሳልፉት ይሆን? የሚል ጥያቄን ያጭራል።
ቦታው ከቤተመንግሥት እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት ብዙም ሳይርቅ ነው። ከአራት ኪሎ ወደ አምባሳደር አካባቢ በሚወስደው መጋቢ መንገድ ግራና ቀኙን የላስቲክ ሸራ (ታድፖሊን) ወጥረው ሕይወትን የሚገፉት የሕብረተሰብ ክፍሎች ቀደም ባለው ወቅት ቦታው በመልሶ ማልማት ሳይፈርስ ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ። ታዲያ አብረዋቸው የነበሩ ባልንጀሮቻቸው ለዓመታት ሙሉ ሕይወታቸውን በሚባል ደረጃ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ መውጣት፣ አብሮ አደጋቸውን መሰናበት የሞት ያክል ቢከብዳቸውም እንኳ አድርገውታል። መንግሥት የልማት ተነሺዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት እንዳልታየ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ አራት ለሚጠጉ ዓመታት ኑሯቸውን በስቃይ እንዳሳለፉ ዓይኖቻቸው ካዘሉት ዕንባ ጋ ተናንቀው ይገልፃሉ። ዕርምጃችንን ዝግ አድርገን ወደ አንዱ መኖሪያ ጠጋ አልን። ይሄኔ ታዲያ ሁሉም ችግራቸውን ሊያወጉን የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው የናፈቁት ነዋሪዎች ብቅ ይሉ ጀመር። እኛም ለዛሬ ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ ከሚመለከተው አካል ምላሽ ጋር አቀናብረን ያዘጋጀነውን ዘገባ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ከአንደበታቸው
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የቀድሞ ቀበሌ 17 ውስጥ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በዚያው ያደረጉት አቶ ንጋቱ ታደሰ በቅድሚያ ያነጋገርናቸው አቤቱታ አቅራቢ ናቸው። መጀመሪያ በስፍራው በጥገኝነት ይኖሩ እንደነበር በማስታወስ፤ በኋላም አካባቢው ለልማት ተፈልጎ ሲፈርስ ላስቲክ ጠልለው ለመኖር እንደተገደዱ ነው የሚናገሩት። በወቅቱ አንገታቸውን ማስገቢያ የነበረው መኖሪያቸው ሲፈርስ ሸራ ወጥረው መኖር ይጀምራሉ። በዚህ መልኩ ለአንድ ዓመት ያክል ሸራው ሳይፈርስባቸው አስተዳደሩ ምትክ እንደሚሰጣቸው በተነገራቸው ተስፋ ይቀመጣሉ። በቆይታም መረጃቸው እንደተጣራና ቤት እንደሚሰጣቸው ቢገለጽላቸውም ዛሬ ነገን እየወለደ ተስፋው ጉም ሆኖ እንደቀረ ይገልፃሉ።
የሦስት ልጆች አባት እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ንጋቱ፤ አምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ለማስተዳደር በቀን ሥራ ተሠማርተው እንደሚገኙ ነው የሚያስረዱት። በአሁኑ ወቅት ከግለሰብ መኖሪያ ቤት ተከራይተው ሕይወትን እንደ አዲስ ‹‹ሀ›› ብለው እንዳይጀምሩ የኢኮኖሚ አቅማቸው እንደማይፈቅድላቸው በመግለጽ፤ የችግራቸውን መጠን ያብራራሉ። አስተዳደሩ ደግሞ ተጠልለው የሚገኙበት ላስቲክ ቤት ሳይፈርስ እንደማይሰጣቸው ገልፆላቸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኀዘን ድባብ የወረሰው ፊታቸውን ደገፍ አድርገው በአንድ ወቅት ያጋጣማቸውን ችግር በተሰበረ ልብ ያስታውሳሉ።
አስተዳደሩ የሰጣቸውን ተስፋ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ መላ ቤተሰባቸው ከቤት ወጥተው ሲመለሱ አንድ ፍጹም ያልጠበቁት ነገር ያጋጥማቸዋል። እንዲሁ በድንገት ለጊዜው ብለው የወጠሩት ሸራ ፈርሶ ይጠብቃቸዋል። አቶ ንጋቱ ለአምስት ቀናት የፈረሰውን ላስቲክ አንጥፈው ውርጭና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው እንደነበር በማስታወስ፤ ሁኔታው በተለይ ለወላጅ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የሚታየው ነው ይላሉ። በተለይም የመጀመሪያ የአብራካቸው ክፋይ የሆነችው ሴት ልጃቸው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ዘወትር ወደ ትምህርት ገበታዋ ስትሄድም ሆነ ስትመለስም የሚያሳስባት መጠለያቸው በቦታው እንደነበረ ባይገኝስ? የሚል ስጋት መሆኑን ይናገራሉ። በአካባቢው ተወልዳ ያደገችው ይህች ልጃቸው ታዲያ ከቃል ባለፈ በተግባር በማይታየው የአስተዳደሩ ተስፋ በተፈጠረባት ስጋት ትምህርቷን ከመከታተል ይልቅ ስለመኖሪያቸው መጨነቅ የእርሷ ዕለት ተዕለት ኑሮዋ ሆኗል።
ለመጠለያ ብለው የወጠሩት ሸራ ለንፋሱ መከላከያ ድንጋይ ለማስቀመጥ ቢያስችላቸውም የበጋውን እርግብግቢት ዘልቆ የሚሰማ ሙቀት ግን ሊያድናቸው አይችልም። መፀውና በጋ አለፍ ሲሉ ደግሞ የተፈጥሮ ግዴታ ነውና የበልግና የክረምቱ ወቅቶች ይተካሉ። ሌቱን ውሃ ማጠራቀሚያ ሲደቅኑና የታቆረውን ሲደፉ ለማደርም ይገደዳሉ። አንዱ ቀዳዳ ሲያፈስ ሲደቅኑ ነፋሱን ተከትሎ የሚያዘነብለው የወጠሩት ሸራ ደግሞ በሌላኛው ማዕዘን በኩል ዝናቡን ወደ ውስጥ ሲያሳልፍ ያያሉ። ሌላ ማጠራቀሚያ ሲደቅኑ እንዲሁ ሌቱን ሲጠባበቁ ያነጋሉ። ቀን ሲለፋ የዋለ ጎናቸውን ማሳረፍ ሳያሻቸው እንዲሁ የማለዳው ውጋገን ሲፈነጥቅ በላስቲኩ ቀዳዳዎች የሚገቡት የብርሃን ጮራዎችና የንጋት አብሳሪ የወፎች ጫጫታ ይሰማል። ይህንን ሁኔታ ተቋቁሞ ቀጣዮቹን ወቅቶች ለመመልከት ታዲያ የሁሉም ቤተሰብ አባላት ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነ በመናገር፤ በዚህ መልኩ ያሳለፉት ሌት በንጋት ሲተካ ተማሪው ወደ አስኳላው ሠራተኛውም ወደ ሥራው ያቀናል።
በአጠቃላይ በአካባቢው የሚኖሩት በአባወራ 30 የሚጠጉ ቤተሰቦች እንደሆኑ የሚጠቁሙት አቶ ንጋቱ፤ መብራትና ውሃ አገልግሎቶች እንዳሌሏቸውና የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸውን አለማወቃቸውንም ይገልፃሉ። ከዚህ ኑሮ የማይሻል የለምና የጋራ መጠለያ ቢሰጣቸው እንኳ ደስተኛ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ። ነገር ግን በየጊዜው የወረዳ አስተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች (አመራሮች) ዝውውር ችግራቸውን ወይም ጉዳያቸውን ሰርክ አዲስ አድርጎታል። በዚህም ችግራቸው ሳይፈታ እንዲሁ ሠዎች ብቻ እየተቀያየሩ ጉዳያቸውን እንደ አዲስ ሲያስረዱ፤ የተረዱትም ሲነሱ፤ ያለ ለውጥ ዓመታትን እያሳለፉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጆሮ ሰጥቶ ለችግራቸው በአግባቡ ምላሽ የሚሰጣቸው አካልም ውስን መሆኑን ነው የሚናገሩት። በቀን ከሌባ፤ በምሽት ደግሞ ከጅብ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ሕይወታቸውን እንደሚመሩ በመግለጽ መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው አቶ ንጋቱ ይጠይቃሉ።
በአካባቢው መኖር ከጀመሩ ከ10 ዓመት በላይ እንደደፈኑ የሚናገሩት ወይዘሮ ፈቲያ ኑርበዲን ስምንት ቤተሰብ የሚኖርበት ቤታቸው ከሌሎቹ ቤቶች ተነጥሎ በጠባቡ የተሽከርካሪዎች መተላለፊያ መንገድ አንዱን ጠርዝ ይዞ የሚገኝ በመሆኑ ሌቱን በሰቀቀን እንደሚያነጉም ይናገራሉ። በተለይም ከቤተሰባቸው መካከል ገና ቦርቀው ያልጠገቡ ሁለት ሕፃናት ልጆች መገኘታቸው ስጋታቸውን ከፍ በማድረጉ ቢመጣ እንኳ ሊያድኗቸው ከማይችሉት አደጋ ሌቱን ቁጭ ብለው የልጆቻቸውን ዓይን ሲመለከቱ እንዲያነጉ አድርጓቸዋል። አካባቢው ከመፍረሱ በፊት ወንድማቸው የንግድ ፈቃድ አግኝተው በንግድ ሥራ ቤተሰቡን ያስተዳድሩ እንደነበርም ነው የሚናገሩት።
አካባቢው ለመልሶ ማልማት ሥራ እንደሚፈርስ ሲገለጽ ንግዱም እንደቆመ በመናገር፤ በወቅቱ አስከፊ ችግር ማሳለፋቸውን ወይዘሮ ፈቲያ ያስታውሳሉ። ሌት በእንቅልፍ እጦት የዛለ ሠውነታቸውን ለማሳረፍ ቀን ጋደም ሲሉ ደግሞ ካለቻቸው ላይ ቀማኛ እንደበረታባቸው ይገልጻሉ። ወደሚመለከተው አካል
ጥያቄያቸውን ለማድረስ እንግልቱ ቢያስቸግራውም እስከአሁን ግን ምንም ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም። ይልቁንም የተጠለሉባት ላስቲክ እንደምትፈርስ ስለተነገራቸው ይህንንም እንዳያጡ ስጋታቸውን ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት በአካባቢው የሚገኝ አንድ የኤሌክትሪክ ማስተላፊያ ምሰሶ ወድቆ ስለነበር ስጋት ገብቷቸው ለሚመለከተው አካል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አፋጣኝ ምላሽ ሳያገኙ እንደቆዩ በመግለጽ፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የተዘነጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው የመጣ እንደሆነ በኀዘን ይናገራሉ። መንግሥትም ችግራቸውን ተረድቶ የገባላቸውን ቃል እንዲፈጽም ይጠይቃሉ።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው ነዋሪ አቶ አዳነ ተካ ናቸው። ነዋሪነታቸውን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀበሌ 17 በጥገኝነት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። በወቅቱ በጥገኛነት ማመልከቻ አስገብተው እንደነበር በማስታወስ፤ ቤት ይሰጣቸዋል እየተባሉ በአጉል ተስፋ ኑሯቸውን ገፍተዋል። መሰል ተመሳሳይ ጉዳይ የነበራቸው ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ምትክ ቤት ተሰጥቷቸው ሲሄዱ እነርሱ ግን ይኸው ብርድና ሙቀቱን ችለው ተቀምጠዋል። በዚህም በተራ በሒደት እንደሚሰጣቸው ከአስተዳደሩ ምላሽ አግኝተው የነበረ ቢሆንም በተመሳሳይ ሁኔታ ኑሮን ለመግፋት ተገድደዋል።
በሚኖሩበት አካባቢ በጥገኝነት በሚኖሩበት ቤት ቁጥር የነዋሪነት መታወቂያ እንደተሰጣቸው በመግለጽ፤ የቤቱ ባለቤቶች የጋራ መኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው ስለሄዱ እነርሱ ግን በቦታው ላይ በላስቲክ ተጠልለው ይኖሩ ጀምረዋል። ችግራቸው የመጠለያ በመሆኑ ከቀማኞች ጋር ለመኖር እንደተገደዱ የሚናገሩት አቶ አዳነ፤ እርሳቸውና ባለቤታቸውን ጨምሮ አንድ የቤተሰብ አባላቸው አብሮ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። ይህንን ከተስፋ ያልዘለለ ምላሽ የሚሰጣቸው አስተዳደሩም የምርጫ ወቅት ሲደርስ ለቅስቀሳ ይነሳል። ምንም እንኳ መንግሥት መጠለያ ቤት አልሰጠኝምና ለምን ምርጫ ቅስቀሳ ይደረግብኛል? ማለቱ ተገቢና አሳማኝ ባይሆንም መጠለያ ቤት የሌላቸውን፣ ̀አናውቃችሁም̀̀̀ የተባሉና የተዘነጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በምርጫ ወቅት ማስታወስ ግን ትክክል አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።
ከፊት ለፊታቸው በቅርብ ርቀት ላይ ቤተመንግሥት፤ ከጀርባቸው ደግሞ ያማሩ ሕንፃዎች ብርሃን እንጂ የላስቲክ ቤቶቻቸው መብራትና ውሃ እንዳሌላቸውም ይገልጻሉ። ‹‹ካገኘን ብንበላ ካጣንም ባዶ ሆድ ብናድር ችግር የለብንም›› የሚሉት አቶ አዳነ መንግሥት ይህንን ችግራቸውን ተረድቶ መጠለያ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
የወረዳ አስተዳደሩ
የነዋሪዎቹን አቤቱታ ካደመጥን በኋላ ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ መንገዳችንን አቀናን። የወረዳውን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መንበረ አግዘው በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በተደጋጋሚ በጽሕፈት ቤታቸው ብንገኝም ልናገኛቸው አልቻልንም። በተመሳሳይ በስልክ መረጃውን እንዲሰጡን ጥረት ብናደርግም ፈቃደኛ ሊሆኑ ግን አልቻሉም።
ክፍለ ከተማው
ነዋሪዎቹ መስተንግዶ ያላገኙበት ምክንያት ምን ይሆን? አስተዳደሩ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የሄደበት ርቀት፣ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት አሉ ወይ? ቀጣይ መፍትሔውስ ስንል የአራዳ ክፍል ከተማን አነጋግረናል፡፡ የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የፐብሊክ ሠርቪስና ሠው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሕይወት ጉግሳ ችግሩን እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡
በክፍለ ከተማው ወረዳ አንድን ጨምሮ ወረዳ ስምንትና ዘጠኝ ላይ መሰል ችግሮች እንዳሉ አምነው፤ በመልሶ ማልማት የተነሱ ሕጋዊ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያልተስተናገዱ እንደሌሉ ነው የሚገልጹት፡፡ ነገር ግን ክፍለ ከተማው ችግሩን ለማቃለልና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወይንም የደሃ ደሃ በሚል የተለዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም ባለው ቁርጠኝነት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በዚህም ከ258 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በመስፈርቱ መሠረት እንደየችግር መጠናቸው በደሃ ደሃ ተለይተዋል።
ለተለዩት የሕብረተሰብ ክፍሎች በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የጋራ መኖሪያ ገንብቶ ማጠናቀቁንና የተወሰኑ ዜጎች እንዲገቡ መደረጉንም ወይዘሮ ሕይወት ይናገራሉ፡፡ በቤቶቹ የሚገቡ በእነዚህ ወረዳዎችና በመሰል ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሕብረተሰቡ ያመነባቸውና የለያቸው በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች እንደ ችግራቸው መጠን ተለይተው አስተዳደሩ ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቢቆይም ለደሃ ደሃ በሚል በተገነቡት በእነዚህ ቤቶች ላይ ግን ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች እንደገቡ ተናግረዋል፡፡
ክፍለ ከተማው ችግሩን እንዳወቀ መፍትሔ የሚላቸውን እንቅስቃሴዎች ጀምሯል የሚሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ቤቶቹ ከሚገኙበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር የተነጋገረ ሲሆን፤ እስከአሁን ግን ግለሰቦቹ የያዟቸውን ቤቶች እንዳለቀቁ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሚነሱትን ችግሮች በፍጥነት ለማቃለል አልተቻለም ሲሉ ያጋጠማቸውን ችግር አብራርተዋል፡፡ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
ፍዮሪ ተወልደ