እንጨት ወደተፈለገው አቅጣጫ በመለወጥ ሊገራና ሊታረቅ ይችላል።ደረቅ እንጨት ከሆነ ግን እጣ ፈንታው መሠበር ነው።እናርቅህ ቢሉት አይታረቅም።እንደተወላገደ ተሰባብሮ ለማገዶነት በመዋል መንደድ ነው…የደረቅ ሰው ተግባርም ከደረቅ እንጨት የተለየ አይደለም።እንደ ደረቀ፣ እንደ ገረረ፣ እንደተወላገደ የሰዎችን ምክርና ሐሳብ ሳይቀበል ይሠበራል።ይህ አይነቱ ክስረት ሰዋዊ ባህሪን ተለብሶ በየአካባቢያችን በስፋት ይስተዋላል፡፡
የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች እጣ፣ እንደ ህብረተሰብና እንደ አገር የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ ደረቅ እንጨትነትን የሚያመላክት ነው።አብዛኛዎቹ አገዛዞችና መሪዎቻቸው የአገርና የህዝቦቻቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው አይመስልም። ይህ እንዳለ ሆኖ ለህዝብ ጥቅም በህዝብ ሊከናወኑ የሚችሉ አያሌ ተግባራት ሳይከናወኑ ይቀሩና መንግስት ዝንተ ዓለም ሲወቀስ እንዲኖር ያደርጉታል።
አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን መጠቆም ‹‹እኛም እነርሱን፣ እነርሱም እኛን ይሉናል›› የሚለው ተረክ፤ በሁሉም የሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የሚስተዋል ክስተት ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ይህ ክስተት በሀገራችን የለውጥ ሂደት ውስጥ በተለይም በፖለቲካው ውስጥ እየገነገነ መጥቷል። ህዝብ በራሱ መወጣት የሚችለውን ኃላፊነት ዘንግቶ ወደ መንግስት ጣቱን ሲጠቁም አይተናል፤ ሰምተናል፤ ታዝበናል።
የልማዳችን ጥጉ በየግላችን ለምናጣቸው እድሎች ሁሉ ተጠያቂ የምናደርገው ሌላውን ሰው መሆኑ ነው።ይህንን ዓረፍተ ነገር ሊያዳብርልኝ የሚችል አንድ ጉዳይ ላንሳ።ሰፈራችን ውስጥ ቱቦ ፈንድቶ የጋራ የሆነው መጸዳጃ ቤት ፍሳሽ አስፓልት ላይ በመፍሰስ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል።በዚህ መጸዳጃ ቤት ቢያንስ 18 የሚደርሱ አባወራዎች ይጠቀሙበታል።ታዲያ ፍሳሹ በጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ ከቁብ ሳይቆጥሩት አፍንጫቸውን በማፈን ያልፉታል።ለምን አታሰሩትም ሲባሉ ‹‹ይሄ የመንግስት ሥራ ነው፤ እርሱ ነው ይሄን ሁሉ ጣጣ የሚያመጣብን…›› የሚሉ መሰል የማላከኪያ ቃላትን ሰካክተው ይናገራሉ።
እንግዲህ ቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ገመድ ሲበላሽ ‹‹መንግስት ይወረድ››፣ በሙያ እጥረት ምንያት እንጀራ እየተጋገረ ካረረ ‹‹ድሮም እኮ ይሄ መንግስት››፤ ሲያስነጥሱ ‹‹የመንግስት ሴራ ነው››፤ አየሩ ከቀዘቀዘ ‹‹መንግስት ተነስቶብናል››… እያሉ በሆነውም ባልሆነውም መንግስት ላይ አፍ ማሾል መብት ነውን? በቱቦ ብልሽት ምክንያት ውሃ ሲያቁር እንደ ዜጋ ተረባርቦ መስራት ሲገባ አገር ገዢው ከቤተ መንግስት ትዕዛዝ እስኪያስተላልፉ የሚጠብቁ ሰዎች እኮ በርካታ ናቸው ።ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ የሚኖርበት አገር ከመፈለግ አልፎ የአገሪቷ መሪ ፍጹማዊ እንዲሆኑ የሚመኙም አልጠፉም፡፡
ጎበዝ ምን ነካን ጠቅላዩ እኮ ከአማልክት ወገን ሆኖ የተፈጠረ አይደለም።አሊያም ፈጣሪ ከሰማይ መና እንዲያወርድ የፈጠረው አይደለም። ውሀን ወደ ወይንጠጅ የሚቀይር፣ ሙታንን የሚያስነሳ፣ ድንቅ ታአምራትን የሚያደርግም አይደለም።ይልቁንም እንደኛ የሚፈርስ ስጋ የተሸከመ ሰው ነው።አንዳንድ ጊዜ ራሳችን በፈጠርነውና እኛው በቀላሉ መፍታት የምንችለውን ነገር አግዝፈን ከመንደር ውስጥ አውጥተን ተራራ አሳክለን ባለ ሥልጣናትን እንጎሽምበታለን፡፡
የአገሪቷን መሪ በትንሽ በትልቁ በመርገም ተጠያቂ ማድረግ አግባብ አይመ ስለኝም።ከሚስት፣ ከጎረቤቴና ከተለያዩ ሰዎች ጋር አምባጓሮ እየፈጠሩ ጠቅላዩን ማማረር፤ ዳቦ ሲወደድ በእርሱ ጊዜ ነው ይህ የሆነው፤ ስለማይቆጣጠር ህግ የታለ ወዘተ… በማለት የእርግማን ናዳ ማውረድ ልማድ ሆኗል። በመጀመሪያ እኛ ጎረቤታችን ያለውን ባለሱቅ ሸቀጥ ለምን አስወደድክ? ብለን ምንም እቃ ባለመግዛት ተፅእኖ አናደርግበትም።እርሱ ያመጣው እቃ ካልተሸጠ እላይ ያለው ነጋዴ እቃውን ማን ይወስድለታል? የኛን ድርሻ ተወጥተን ቢሆን ኖሮ በትልልቅ ጉዳዮች ደግሞ መንግስትን ብንወቅስ የተሻለ ነበር።ነገር ግን ሁሉንም ድርሻ ለመንግስት ብቻ መስጠት ለምዶብን በየት በኩል የኛን ድርሻ እንወጣ፤
ከአንዳንድ ወገኖች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በግል ስናወጋ ልክ እንደ ተረቱ በትክክልም ‹‹እኛም እነርሱን፣ እነርሱም እኛን ይሉናል›› የሚል ነገር እያደመጥን ነው። እቅጭ እቅጯን እናውራ ከተባለ ህዝብ ራሱ ማስከበር የሚችለውን የቤተሰቡን ሠላም ጭምር መንግስት ላይ ማላከክ የለበትም። ሁሉም በየፊናው ለወገኖቻችን ሰላምና ደህንነት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። ህዝቡ በሰላም ዙሪያ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን ከመፈጠራቸው በፊት ተገቢውን ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል።ይህን ማድረግ ከቻሉ እነማን በህዝብ ሰቆቃና ስቃይ እንደሚቆምሩ ለማወቅና አውቆም አስቀድሞ ለመከላከል የሚቻል ይመስለኛል።
እርግጥ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ መሆኑን አላጣሁትም። ነገሮች እንደ ሸማኔ ድር ከወዲያ ወዲህ እየተወረወሩ ነው። ይሁንና የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን ጉዳይ አሊያም ማህበረሰብ ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ላይ መንግስታዊ ጥረት ለብቻው የሚያመጣው ለውጥ ያለ አይመስለኝም። በተለይም የችግሩ እምብርት የሆነው ህዝብ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ችግሮችን ለማስቀረት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። ይህ የተቀናጀ ጥረት ከተደረገ የችግሩ መፍትሔ ስለሚታወቅ ሌላ ተግባር በመከወን የተሳሳተን በር እንዳናንኳኳ ያደርገናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ መመገብ የምንችላቸውን ምግቦች በማስወደድ ህዝባችንን በማስራብ የውጪ ዜጋን በመመገብ ስራ ላይ የተሰማሩ ልማታዊ ባለሃብቶች ለህዝባችን በማንኪያ ህዝባችን ላልሆኑት ደግሞ በጭልፋ በማቀበል ዶላር ቆጠራ ሲያደርጉ መንግስት እስከሚቆነጥጣቸው ድረስ ህዝብ መጠበቅ የለበትም።እነዚህን ጉደኞች ለመንግስት አካላት አሳልፎ መስጠትን የመሰል ነገር ምን አለ?
እስቲ መንግስትን ለማገዝ የድርሻችንን እንወጣ፤ እርስ በእርስ በመፋቀር አንድነታችንን እናጠንክር።እስቲ እራሳችን ለሰፈራችን ዘብ እንቁም።ከዚያ አገራችንም ትጠበቃለች።ይህን ስል ግን መንግስት መወቀስ የለበትም ለማለት አይደለም። መንግስትም ለአመፀኞች ህግ ያውጣ።ህግ ያስከብር።ዜጎች የሰላም አየር መተንፈስ የሚችሉት ኮስተር ያለ ህግ ሲኖር ነው።ልፍስፍስ ህግና አተገባበሩ ለአንድ አገር የአሸባሪ መፈልፈያ ጉድጓድ መቆፈሪያ ዶማ ነው።ልፍስፍስ ህግና አተገባበሩ የአገሪቱን ወታደሮች የወንበዴዎች አሽከር ያደርጋቸዋል።መንግስት እራሱን፣ አገሩንና ህዝቡን ከጥፋተኞች ጨከን ብሎ መጠበቅ አለበት፡፡
ዜጎች የአገር ሉአላዊነትን ከማስከበር ጀምሮ የአገር ኩራትና ክብር በመሆን ለገጽታ ግንባታ የሚኖራቸው ትሩፋት በመንግስትና በተቋማቱ ወይም በሹመኞችና አስፈጻሚዎቹ ሊተካ የማይችል ሚና እንደሆነም ጠንቅቀን እንገነዘባለን፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 3/2012
አዲሱ ገረመው