
እኛ ኢትዮጵያውያን ለጊዜ ያለን አመለካከት እና ከልባችን ምት እኩል የሚጓዘው የጊዜ ቀመር ፍሰቱ ለየቅል በመሆኑ ይህው በየዕለቱ “…የሀበሻ ቀጠሮ…” እያልን እንተርታለን። ከተረት ያለፈ መሻሻል ብናሳይም ባናሳይም፤ ለውድ ጊዜ ዋጋ ብንሰጥም ባንሰጥም፤ ጊዜ የለኝም በሚል የውሸት ብንጨናነቅም ባንጨናነቅም፤ ብንተርትም ባንተርትም ጊዜ እንደሁ ያው ጊዜ ነውና ላፍታ እንኳ ሳይዘናጋ ይነጉዳል።
እኛም ከጊዜው እኩል ያለምንም እረፍት አንዳንዴም በብዙ እረፍት ውስጥ ሆነን “ቢዚ ነኝ” በሚል ፈሊጥ ተሸብበን አለን። በእርግጥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለምናባክናቸው ሽርፍራፊ ሰኮንዶች፣ ደቂቃዎች፣ ሰዓታት፣ ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት ለምን ብለን አንጠይቅም። ብንጠይቅም ብዙ ሺህ ውጫዊና በጣም ጥቂት ደግሞ ውስጣዊ ምክንያቶችን መደርደር እንችላለን። ይሁንና ምክንያቶቹ ያለፈውን ውድ ጊዜ አይመልሱልንም። እኛም ባለፈው ጊዜ ስንቆጭ አንታይም።
ሌላው ቀርቶ የቀጠሮ ሰዓታችንን ባለማክበር ላጠፋነው የሌሎች ሰዎችን ጊዜ እንኳን ይቅርታ አንጠይቅም። ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ያው እንደተለመደው የትራንስፖርት እጥረቱን፣ የመንገድ መዘጋጋቱን፣ የአስፓልቱን መቆፋፈርና መሰል የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ምክንያቶችን በማከታተል የተለመደ አይደል “የሀበሻ ቀጠሮ እኮ ነው…” እያልን እንተርታለን።
እኔ እምለው ተረት ባይኖር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን እንዴት እንሆን እንደነበር አስባችሁታል?… ነገራችን ሁሉ እኮ የሚደምቀው በተረትና ምሳሌያዊ አነጋገራችን ነው። እስኪ አስቡት ሲቸግረንም፣ ሲከፋንም፣ ሲደላንም፣ መንግስት ቢቀያየርም፣ ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም፣ ለውጡ ቢቀጥልም ቢደናቀፍም የምንተርተው ተረት አናጣም። ባስ ካለም በግልፅ ማስተላለፍ ያልፈለግነውን ጉዳይ በሙዚቀኞቻችን አማካኝነት በዜማ እንለዋለን።
ትንሽ ግር እና ግርም የሚለኝ ግን ተረቶቻችን ሁሉ “…አለ” አማራ ሲተርት በሚለው ማሰሪያ አንቀፅ መቋጨቱ ነው። እውነት ግን ተረትን ለአማራ ብቻ የሰጠው ማን ይሆን?…እውነት እንነጋገርና ተረትን የተረተው አማራ ብቻ ነው?… “ይህማ ምን ጥያቄ አለው አዎና” አላችሁ… ካላችሁ እሺ ተስማምቻለሁ። መስማማቴ እንዳለ ይሁንና ስለዚህ ስለተረት ነገር በሌላ ጊዜ እንድመለስበት ቀጠሮ ልያዝና ልቀጥል፤
ጉዳያችንስ ቢሆን ቀጠሮ እና የጊዜ አጠቃቀማችንም አይደል… አዎ አብዛኞቻችን ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ እጅግ የወረደ እና የሳሳ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ተግባራትን በተገቢው ጊዜ ባለመከወናችን ዋጋ እንከፍላለን። በአብዛኛው አገልግሎት ፈልገን በሄድንበት ሁሉ በጊዜው የሆነ ፈጣን ምላሽ አናገኝም። ይህ ደግሞ “ያለወቅቱ የዘነበ ዝናብ ለጥፋት እንደሆነ ሁሉ በጊዜውና በሰዓቱ ያልተሰጠ ምላሽም ረብ የለሽ ይሆናል።
እናላችሁ አሁን አሁን አየሩን የያዘው የለውጥ ሽታ ሽታ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ሁላችንም የበኩላችንን ለመወጣት የተለመደውን የአበሻ ቀጠሮ ትተን የፈረንጁን ብንይዝ ምን ይለናል… ምክንያቱም በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ የዘገየ ከመሆኑም በላይ እርካታን የማይፈጥር እና ባለጉዳዩን የሚያንገላታ ነው። እኔ የምላችሁ…“ደንበኛ ክቡር ነው” የሚለው አባባል ከአባባልነት አልፎ ተግባር ላይ የሚውለው መቼ እና የት ይሆን…
አሁን አሁንማ ከህዝብ ቁጥሩ በላይ በዝተው የተትረፈረፉ እጅግ በርካታ ጉዳዮች ያሉ ይመስል በየቀበሌው ተኮልኩለው ጠዋት ብርዱን ቀን ፀሐይና አቧራውን እየጠጡ ኃላፊን እና የኃላፊዎችን ውሳኔ የሚጠባበቁ ዜጎች አሉ። ታዲያ እነዚሁ ዜጎች ጉዳያቸውን ለማስፈፀም በሄዱበት ሁሉ ከጉዳዩ የገዘፈ ቀጠሮ ተሸክመው ይመለሳሉ።
ቀን ቆጥረው ቀጠሮ አክብረው ሳይታክቱ ወደ ጉዳያቸው ቢጓዙም አለቃ የለም። ፀሐፊዋ ስትጠየቅ መልስ አትሰጥም። ብትሰጥም ዘንቦ አባርቆ ካባራ በኋላ “ዛሬ አይገቡም ነገ ከነገ ወዲያ ተመለሱ” በማለት ተራዋን ሌላ ቀጠሮ ትሰጣለች። መድረስ አይቀርም የፀሐፊዋ ቀጠሮም ይደርስና ጉዳዬ ቢሳካ ብለው አሁንም ይጓዛሉ፤ ይመላለሳሉ ዳሩ ምን ዋጋ አለው፤ እንደተለመደው አለቃው የሉም ስብሰባ ናቸው ይባላል። አለፍ ካለም ኃላፊው ቦታውን ለቀዋል ይባሉና እርፍ። ይሄኔ ነገሩ ሁሉ ከዜሮ ይጀምርና ጉዳዮ እንደ አዲስ መታየት ይጀምራል።
ታዲያ እንደዚህ አይነቱ ውጣ ውረድ ህብረተሰቡን ከማማረር አልፎ ተስፋ እንዲቆርጥና መንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲሸረሽር ያደርገዋል። ከዚህም ባለፈ እዚህም እዚያም የሚነሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ወቅታዊና ፈጣን ምላሽ ካለመስጠት ጋር ተያይዞ የሚሰጠው የበዛ ቀጠሮ ነው። ይህ ደግሞ ህገወጥ የሆኑ ተግባራት ጭምር ህጋዊ የሆኑ ያስመስላል። ህጋዊ የሚመስሉ ህገ ወጥ ተግባራትን ስርዓት ለማስያዝ እና እርምጃ ለመውሰድም ዘግይተን እንነሳለን። በዚህም “ጅብ ካለፈ ውሻ ይጮሃል” ነውና ነገሩ ለብዙ ጉዳዮች ከዘገየነው በላይ በብዙ እጥፍ የሕይወት፣ የንብረትና የታሪክ ዋጋ ከፍለናል እየከፈልንም ነው።
እንግዲህ ሕይወት አጭር አንደመሆኗ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም፤ ብንችል ከዘመኑ መፍጠን አልያም ከጊዜ ጋር እግር በእግር ተከታትለን በመጓዝ ሁሉን በጊዜውና በሰዓቱ ልንከውን ይገባል። ካልሆነ ግን መሽቶ በነጋ ቁጥር የምናጠፋው ጊዜ እና የምንሰጠው የበዛ ቀጠሮ በኢኮኖሚያችንም ሆነ በማህበራዊ ሕይወታችን ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል።
ከዚህም በላይ በዓለማችን በየዕለቱ የምንመለከታቸውና የምንሰማቸው አዳዲስ ነገሮች አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ ከአቅማችን በላይ ይሆኑና ከጫወታ ውጭ ያደርጉናል። ይህ ደግሞ ድምፃዊቷ እንዳዜመችው “አልበዛም ወይ ድንዛዜው ቴክኖሎጂው በላይ በላይ…” ይሆንና ነገሩ በተሻለ ጊዜ የተሻለና የቀለጠፈ ስራ ካልሰራን እንዲሁም ከዘመነው ዘመን ጋር ካልተፎካከርን ነገሩ ሁሉ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆንና የምንመኘው ለውጥ እንደናፈቀን ይቀራል።
ታዲያ ለዚህ ሁሉ መፍትሔው ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ ከአገልጋይነት ስሜት በመነጨ መልካምነትና አንድነትን በማጣመር በተሰማራንበት ስራ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን መውተርተር የግድ ይለናል። በመጨረሻም ዘመን ተሻጋሪ በሆኑት ስራዎቹ የሚታወቀው አንጋፋው ድምፃዊ ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ስለቀጠሮ ባዜመው ዜማ ልሰናበት “አርቆ ማሰቢያ እያለን አዕምሮ እንደምን ተሳነን ለማክበር ቀጠሮ”
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
ፍሬህይወት አወቀ