የህክምና ባለሙያዎችን ሆ! ብለው እንዲነሱ ያደረገ፣ የፈጣሪ ሰላምታ እንኳ በቅጡ እንዳይሰጥ ያደረገም ነው፤ ስለዚህም በሰላምታ አለመለዋወጥ ምክንያት ወዳጆትን መቀየም ክልክል ነው። ስለዚህም አማራጫችን ሰላምታችንን በሩቅ ማድረግ ይሆናል። ይህም የሚሆነው ታክሲና አውቶቢስ ላይ ካልተገናኘን፤ ሀዘን ቤትና ሰርግ ላይ ሳንሰባሰብ ነው።
አልፎ አልፎ ሻይ ቡና እንባባል ሲባልም እንደተለመደው አፍና አፍንጫችንን በእራፊ ጨርቅ (ማስክ) ማፈን ይጠበቅብናል። ምክንያቱም ከወደቻይና የመጣው ቫይረስ እኛም ጋር ላለመግባቱ ማረጋገጫ የለንም። ቢያንስ መድሀኒት ተገኘለት ብንባል እንኳ ትንሽ ፈታ እንል ይሆናል። ግን ክስተቱ ቅጽበታዊ ከመሆኑም በላይ መመከት የሚችሉት አይነት አይደለም።
ሀኪሞች በጥምረት ሆነው ቢነሱም መከላከያውን እንኳን አላወቁትም። በቫይረሱ የተጠረጠረውን ሰው ነጥሎ በማስቀመጥ ምርመራ ብቻ ነው የሚያደርጉት። በዚህም አገራት ዜጋዬን ላድን የሚል ርብርብ ላይ ናቸው። በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ብዙ ሰው ለህልፈት ሲዳረግ ማየት የየዕለት ዜና ሆኗል።
የኮሮና ቫይረስ በዚያው በቻይና ብቻ የተወሰነ አይደለም። ስለዚህም አለም ዜጋዬን ነክቷል አልነካም እያለ እየታመሰ ነው የሚገኘው። በዚህም አደገኛ ቫይረሱ እንዳይሰፋ የተገኘባቸውን ሰዎች በማቆያ በማድረግ ሌሎች እንዳይዙ የተለያዩ ክልከላዎችን እያደረጉ መሆኑን በዜናዎች በየቀኑ እየሰማን ነው።
ከሁሉ ግን ያስገረመኝ ከወደ ኢንዶኖዥያ የተሰማው ወሬ ነው። ለዜጎቿ ልዩ ጥበቃ እያደረጉ መሆኑን በሚገባ ያሳያል።ምኑ ካላችሁ ደግሞ ከአየር መንገድ ውስጥ የሚወጣ ማንኛውም ሰው እንደሰሞኑ ወረርሽኝ አንበጣ ጸረ ቫይረስ ይረጫል። በተለይ ከአውሮፕላን ላይ የሚወርዱ ሰዎች ምናቸውም አይቀርም ሲርከፈከፍባቸው። እናም በዚህ ሁኔታ ይህ ቫይረስ አገራቸው እንዳይገባ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ይገኛሉ።
ነገሩን አነሳሁ እንጂ የኮሎና ቫይረስ ጉዳይ አይደለም እንደአንበጣ መረጨት ከዚያ በላይ ካለም ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አገር ውስጥ ከገባ በተለይም እንደኛ በማደግ ላይ ላሉ፤ ባህልና ልምዳቸው ላስተሳሰራቸው ህዝቦች በለጸግን ለሚሉትም አስጊና ኢኮኖሚን የሚያደቅ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ቻይና ብዙ ነገሮቿ እየተወደዱላት አይደለም። ብዙ ወጪም እያወጣች ትገኛለች። ለአብነት በሰሞኑ ዜና እንኳን በሁለት ቀን የገነባችው ሆስፒታል በርካታ ገንዘብ አስወጥቷታል።
ቻይና አደጉት ከሚባሉት ተርታ በመሆኗ በሁለት ቀን ጤነኛውን ከበሽተኛው ለመለየት ከ1000 በላይ ታካሚዎችን ሊያሰተናግድ የሚችል ሆስፒታል ገንብታ እየሰራች ነው። ይህ ነገር ለዓመታት አንድ ፕሮጀክት ታቅፈን ለምንቆይ ለእኛ ቢሆን ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም መገመት ያዳግተዋል ብዬ አላምንም። እናም ይህ እኛ ጋር እንዳይከሰትና እንዳይገባ ለማድረግ አንድ ነገር ብቻ ማድረግ ይኖርብናል። ይኸውም ቀድመን መከላከል የምንችልበትን አማራጭ ሁሉ መጠቀም ነው።
እንደሚታወቀው በሽታው እያየለ መጥቶ ብዙዎችን ለህልፈት እየዳረገ ነው። ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንድምታውንም መልኩን እንዲቀይር እያደረገው ነው። በዚህም ከአውስትራሊያ መንግስት ጀምሮ ሌሎች አገራትም ከቻይና ግዛት የመጡ ዜጎችን በደሴት እንዲቀመጡ እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶች ደግሞ በረራቸውን ጭምር አቁመዋል።
የእኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ይህንን አላደርግም። ሆኖም አለማቀፍ የበረራ ጥንቃቄዎችን ማድረጉ እንደማይቀር ይናገራል። አለማቀፍ የጤና ድርጅት የሚያወጣው መመሪያንና መስፈርቶችን በማሟላት በረራዬን አድርጋለሁም ብሏል። ይህ ግን ለእኛ ይቻል ይሆን? እኔ ግን አይመስለኝም። የእኛ አገር የአኗኗር ዘይቤ ይህ ነገር ከተከሰተ መመለሻ የሚያጥረን ይመስለኛል። ምክንያቱም አብሮ መብላት፣ መጠጣት እንዲሁም መንቀሳቀስ የሚወድ ነው።
በሽታን ለመቋቋምም የሚያስችለው ሁኔታ አናሳ ነው። ስለዚህም ምን ይደረግ ከተባለ መልሱን ለእናንተው ልተወው። ግን አንድ ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ። በሽታው የሚተላለፈው በንፋስና በንክኪ በመሆኑ በጥርጣሬ እያዩ መቆየት እንደማያዋጣ መረዳት ያስፈልጋል። ባለፈው በተደረገው ምርመራ እዚህ ነጻ ናቸው ተብሎ ደማቸው ለምርመራ የት እንደሄደ ይታወቃል። ስለዚህም በየጊዜው ሌላ አገር እየላክን ለምናስመረምረው ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሚባለውን እርምጃ መጓዝ ካልቻልን ያሰጋል።
ኮሮና ቫይረስ በመድሀኒት የሚቋቋሙበት፤ መከላከያ ምን እንደሆነ የማይታወቅበት፤ አሁን በሚታየው ብቻ ምልክቱ የተገለጸበት ነው። በዚህም ሰውና ሰው ሲነካካና በትንፋሽ ብዙዎች ዘንድ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህም ሀብታም፣ ደሃ፣ ልጅ አዋቂ ሳይል ያገኘውን ይይዛል ይገድላልም። ‹‹ ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል›› ሳይል ሁሉንም በአንድነት ነው የሚጠራርገው። ስለዚህ ለአገራችን ቢመጣ ማንም አይመክተው።
ግን አንድ እምነት አለኝ። ኢትዮጵያን ከእንዲህ አይነት አሰቃቂ አደጋ የሚጠብቃት አምላክ አላት። እናም አይመጣም፤ አልፈራም። ይህ ሲባል ግን አንጠንቀቅ ማለቴ እንዳልሆነ ታሳቢ ይደረግልኝ። በኢትዮጵያ ህብረተስብ ጤና ሣይንስ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች አማካኝነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዜጎችን የሚደረገው ምርመራ ሊጠናከር ይገባዋል።
በአየር መንገድ የሚወሰዱና መሰል የመግቢያ በሮች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችም ጠንካራ መሆን አለባቸው። በመጀመሪያ አራት ተጠርጣሪዎች ተገኙ፤ ከዚያ ምንም እንደሌለባቸው ታወቀ። አሁንም ዳግም ሶስት የቻይና ዜጎች እና ከእነሱ ጋር የሚሰራ ኢትዮጵያዊ በአክሱም ለብቻ ሆነው ክትትል እየተደረገባቸው ነው። ስለዚህ ይህ ስጋት እውን እንዳይሆን ይታሰብበት።
ዛሬ ህብረተሰቡ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው። እንደውም አንዳንዶች በከተማዋ ውስጥ አፍነው ይንቀሳቀሳሉ። ግን ይህ ብቻ በቂ መከላከያ እንዳልሆነ ማንም መገንዘብ አለበት። ስንቱን በርቀት ሰላም እንላለን፤ አፍኖ ሰላም ማለትም በባህላችን ስድብ ነው። ስለዚህ እንከላከልለት ወይስ ስድቡን እናቁምለት። መፍትሄ የሌለው ጭንቀት ውስጥ ይከተናልና የመንግስት አካላት ኮሮናን ወደ ኩሬ ከቶ ማንም እንዳይጠጋው ያድርጉልን።
አዲስ ዘመን የካቲት 1 / 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው