ርዕስ፡- ህልም ብርሀን እድሜ
ደራሲ፡- ያዴል (ቤዛ) ትእዛዙ
ዘውግ፡- የግጥም መድብል
ዋጋ፡- 100 ብር
የህትመት ዘመን፡- 2012 ዓ.ም.
አሳታሚ፡- ያዴል (ቤዛ) ትዕዛዙ
የገፅ ብዛት፡- 115
በህልም ብርሀን እድሜ የግጥም መድብል ላይ የተሰጡ ምሑራዊ ሂሶችን ስለመቃኘት፤ ምሁራዊ ሂሱ የተሰጠው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና ስነ ፅሁፍ መምህር በሆኑት አቶ ዘመዱ ደምስሰው ሲሆን መምህሩም አጠር አጠር ያሉ ማሳያዎችን በማሳየት ፟የህልም ብርሀን እድሜ፟ የግጥም መድብል ላይ የተካተቱ ዋና ዋና ሀሳቦች ለማየት የሞከሩበትን መንገድ ቃል በቃል የእሳቸውን ንግግር በመውሰድ አካፈልኳችሁ። መልካም ንባብ!
የሀያሲው ቃል የሚጀምረው ወንድ ልጅ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያምጠው በኪነጥበብ ነው ከሚል ገዢ ሀሳብ ነው። የኪነጥበብን ምጥ እና ድካም ከሴት ልጅ የ9 ወር እርግዝና እና ምጥ ጋር በማወዳደር ደራሲውም የኪነጥበብን እርግዝና አምጦ መውለድ መቻልን ትልቅ እውቅና በመስጠት በሀገራችን በብዛት የተለመደውን ለወላዶች የሚሰጠውን “እንኳን ማርያም ማረችህ” አባባል የመጀመሪያ ልጁ እንደተገላገለ በመግለጽ የህልም ብርሀን ዕድሜ የግጥም መድብል ምርቃት በተመለከተ መልካም ምኞታቸውን በማስቀደም ተጀመረ።
ሀያሲው ያነሱት ሀሳብ ግጥም የሰውን ልጅ ክስተት፣ አጋጣሚ፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ ማህበረሰብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ በአጠቃላይ በሰው ልጅ የህይወት ዙርያ ገቢራዊዊ ኩነቶች የሚታዩበት መነፅር ነው። ግጥም ሀሳብን ይገልፃል ሰውም በሀሳቡ ይረቃል፤ ግጥም እምነት ለማሳየት ለማስቀመጥ ይረዳል። ግጥም ማህበራዊ ሂስ ሆኖ ያገለግላል ሽሙጥን፣ ምፀትን፣ የአዝማሪ ግጥምን እንደምሳሌ መጠቀም ይቻላል። ግጥም በባህሪው ሙዚቃዊ የሆነና ሲሰማ ደስታን የሚሰጥ፤ ፍሰት፣ ምት፣ ዜማ ያለው ደረቅ ከሆነ ዝርው ንግግር የሚለይ ይህም ሰዎች በቃል የመያዝ አቅማቸው የሚያጎለብት ባህሪው ያለው ነው።
ግጥም ሁለት መሰረታዊ ጥንቃቄዎች ያስፈልጉታል። የመጀመሪያው የቃላት ምርጫን ይፈልጋል ቃላትን ሲጠቀም ለትርጉም አፅእኖት መስጠት (meaning effects) ይጠቀማል። በሁለተኝነት ደግሞ በቤት መምቻ (Sound effects) የሚጠቀም ሲሆን ሁለቱ በጋራ በመሆን ገጣሚው ማስተላለፍ የፈለገውን ሀሳብ ግቡን እንዲመታለት ካደረጉለት ያ! ግጥም ይባላል። ግጥም ቤት ስለመታ እንዲሁም ትርጉም ስለሰጠ ብቻ ግጥም አይሆንም።
ለምሳሌ፡- ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች እናት
እስኪ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት
ብሎ አንድ ገጣሚ ቢገጥም የምት ችግር የለበትም። ከቃል የጎደለ የትርጉም አፅእኖት አለው። ስንኞች ምጣኔ ና ሙዚቃዊ ቃና ስላላቸው እንዲሁም ቤት መምታት ስለቻሉ ብቻ ግጥም መሆን አይችሉም። የተነሱበትን መሰረታዊ ሀሳብ ትርጉም መሳት የለባቸውም በትክክል ቦታ ይዘው መገኘት አለባቸው እንጂ።
ሀያሲው የግጥም ቃላት ለትርጉም ለሙዚቃዊ ቃና ለምት ጥንቃቄ እንደሚሹና የሀሳብና ቃላት አጠቃቀሙም የማይጎረብጥ መሆን እንዳለበት በማስመር እንዲሁም ግጥም የሁሉንም የህይወት አቅጣጫ ማሳየት ያለበት መሆኑን በመናገርና ስለግጥም መሰረታዊ ሀሳብ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ህልም ብርሀን እድሜ ምንምን ነገሮችን ይዟል?
የሽፋን ስእሉን በማንሳት ህልም- ብርሀንና እድሜ እንዴት አብሮ ሊሄድ እንደሚችል ታዳሚው በልምድ ተሞክሮው እንዲያስተያይ በመጋበዝ መድብሉን የሚመለከተውን የንግግራቸውን አቦል ለታዳሚው ያስቀመሱት ሀያሲው መፅሐፉ ህልም ብርሀንና እድሜ እንዴት እንደሚተሳሰሩ ለማሳየት የተሞከረበትን መንገድ በማድነቅ በስእሉ ላይ ያሉትን የእድሜ ገመዶችን እንደሚያሳይ በመናገር ህልምን ብርሀንንና እድሜን ለየብቻ ለማየት ሞክረዋል።
ህልም ምንድነው?
በስነ ልቦናው ዘርፍ ላይ ታላላቅ ጥናቶችን ያደረጉ ታላላቅ ተመራማሪዎች ህልምን ፟ሰው በእውን አለም አልሳካለት ያለውን ሲተኛ በምናቡ የሚከሰት ምስለ እውነታ ድምፅና ድርጊት ለመፈፀም የሚያደርገው ትንቅንቅ ነው፟ ይላሉ። በስነ ፅሁፍ የሚገለፁ ሀሳቦች ላይ ደግሞ ህልም ህልም ቢሆንም ግልባጩ ፟ሰው በእውኑ አለም ሊሰራው ሞክሮ ያልተሳካለትን ነገር ለመድረስ ሲል በሚፈጥራቸው ገፀባህሪያት፣ የግጥም ሀሳቦች፣ ድራማና ሌሎች ዘውጎች በራሱ ላይ እንደደረሰበት አድርጎ ለማሳየት የሚያደርገው ሙከራ ነው።፟ ብለው ይከራከራሉ።
ህልም ከቅዠት የሚለይ፣ ተተኝቶ የሚታለም፣ በእውን እያዩ ነገዬ እዚህ ጋር ይደርሳል ብለው እያሰቡ የሚያደርጉትና የሚያቅዱት እቅድ ነው። ህልም ራእይ ይለያል። ህልም በዘፈቀደ የሚሆን ሲሆን ርእይ ሲሆን ግን እቅድ አውጥተን ከዚህ ጊዜ በኋላ እዚህ ላይ እደርሳለሁ ብለው የሚያስቀምጡት ነው። ህልም ከራእይም ይለያል ራእይ ብዙ ጊዜ መለኮታዊ የሆኑ ነገሮች በሰው አእምሮ ሲመጡና የመገለጥ ነገር ሲኖር ነገ ከነገበስቲያ ይሄ ሊከሰት ይችላል ብሎ መናገር ማለት ነው።
በህልም ብርሀን እድሜ የግጥም መድብል ስለ ህልም ምን ተባለ?
በመፅሐፉ በህልም ስር ያሉት 26 ግጥሞች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ 21ንዱ በቃል በሀረግና በአርፍተ ነገር ርእስ የተሰጣቸው ሲሆን አምስቱ ብቻ የግእዝ ቁጥር (፩፣ ፪፣ ፫፣፬፣፭) እነዚህም በገፅ 5፣ 14፣18፣26፣30 ላይ ተቀምጠዋል። ረጃጅሞቹን ለማየት ብዙ ሰዓት ስለሚፈጅ የተመረጡ ያሏቸውን አጫጭር ግጥሞች ለመዳሰስ ሞክረዋል። በህልም ስር የቀረቡት ግጥሞች ገጣሚው ይሁነኝ ብሎ በመረጣቸው ምኞት፣ ሀሳብ፣ የእይታ አድማስ ረቂቅ የህይወት ፍልስፍና ላይ አተኩሯል ብለው ቀጣይ ወደሆነው ብርሀንን ምንነት አብራርተዋል።
ብርሀንስ የቃሉ ተፈጥሮ ምንድነው?
ብርሀን በባለሙያዎች ብያኔ መሰረት በአይን የሚታይና የሚደረግ የተፈጥሮ ሞገድ ነው። ምሁራኑ የብርሀን ሞገድ ከኤሌክትሪክና ከመግነጢስ የተሰራ ስለሆነ ሞገዱ የኤሌክትሮኒክስ መግነጢስ ነው ብለው ያስቀምጡታል። የብርሀን ጠባዮች ተብለው በመምህሩ የቀረቡት የመጀመርያው በፊዚክስ አስተምህሮ መሰረት ብርሀን በአለም ላይ ካሉ ነገሮች በሙሉ እጅግ በጣም ፈጣኑ ነገር ነው። ሁለተኛው የብርሀን ፀባይ መንገዱ ቀጥተኛ ነው። አንዳንዴ በውስን ምክንያቶች አቅጣጫውን ካልሳተ በስተቀር።
የብርሀን ተምሳሌታዊ ምልከታዎች ብዙ ናቸው ያሉት ሀያሲው ብርሀን መገለጥን እንዲሁም እውቀትን ይወክላል። ሁለተኛ የብርሀን ተምሳሌት መለኮታዊ ድህነት ወይም ደግሞ መዳንን ይወክላል። ያዴል ትዕዛዙ (ገጣሚው) የትኛውን የብርሀን አንድምታ ነው የተጠቀመው ብለው ምላሹን ለአንባቢ በመተው ምልከታቸውን ቀጣይ የመፅሐፉ ክፍል ወደሆነው ወደ እድሜ አሸጋግረዋል።
ግጥም መድብሉ ብርሀንን እንዴት ገለፀው?
አብዛኛው ሰው ብርሀንን ያደንቃል ይወዳል። የገጣሚው ፍልስፍና ግን ብርሀንን ለማድነቅ የተጓዘበት መንገድ ጭለማን መሰረት አድርጎ ነው። ገጣሚው ብርሀንን የሚያይበት መነፅር ከጨለማ ትልልቅ መነፅሮችን በመዋስ ነው። የብርሀን መሰረቱ የጨለማው መኖር ነው ይላል ደራሲው። በመፅሐፉ ውስጥ ከጨለማ ውስጥ በመሆን ብርሀን፣ ውበት፣ ጥበብ፣ ፀጥታን መስማት፣ የምስጦችን ጉርምርምታና ሀሜት እስከመስማት ድረስ የሄደ መሰጠት የቻለች ነፍስ አለች። መፅሐፉ የብርሀንን ግልባጭ ማየት የሚቻለው ከጨለማ ውስጥ መሆኑን ያሰመረ ነው።
በሌላ በኩል መፅሐፉ ውስጥ ጨለማ ሲኖር ጥሩ ነው የሚል መከራከሪያ ሀሳብ ያላቸው ግጥሞች አሉ። ለምሳሌ ብርሀን ሀጥያትን፣ ሙስናን፣ ክፉ ሀሳብን፣ ወንጀልን፣ ምቀኝነትን፣ ሌብነትን እና በርካታ ነገሮችን ያጋልጣል፤ ስለዚህ ይሄ ሁሉ የክፋት አሰራር መደበቅን ይሻል የሚል ነፍስያ ያላቸው ገፀባህርያት ይታያሉ።
እድሜስ ምን ይሆን?
እድሜ በሀያሲው እይታ የአንድን ነገር በጊዜ ማእቀፍ ውስጥ መነሻ ዘመኑ ወይ በቃል አልያም በመዛግብት ተመዝግቦ መቆጠር ከተጀመረበት እለት እስከ መደምደምያው አልያም እስከ የትየሌሌው ድረስ ነው። አንዳንዴ እድሜ ከዚህ እስከ እዚህ ተብሎ ይበየናል አንዳንዴ ደግሞ ተቆጥሮ እና ተሰፍሮ የማያልቅ ነው። ተቆጥረው የተበየኑትም ይሁኑ መቆጠር ያልቻሉ የእድሜ ቀመሮች በያዴል (ደራሲው) የሶስተኛው ክፍል ግጥሞች ውስጥ ምን ምን ነገሮችን በማስቀመጥ ነው አንዳንዶቹን እድሜያቸውን የገደበው አንዳንዶቹን ደግሞ እድሜያቸውን የትዬለሌ እንዲሆን ያደረገው? ብላችሁ ለማንበብ ሞክሩ።
መፅሐፉ እድሜንስ ማነህ አለው?
እድሜ በመፅሐፉ መመልከቻና መታዘብያ ሆኖ ቀርቧል። ጥሩ ነው ብዙ ነገር ያስተምራል ታዛቢና የተለየ እይታ ያለው ሰው ያደርጋል፡: ግጥም መድብሉ ውስጥ እድሜ የትልልቅ ትዝብቶች መነሻ ሆኗል።
መፅሐፉ ምን ልዩነት ፈጠረ?
ሀያሲው ገጣሚውን ልዩነት አመጣ ብለው ያሞካሹት በዋናነት የቋንቋ አጠቃቀሙን ሲሆን ረቀቅ ያሉ ሃሳቦችን በማምጣት መስራቱን ሲሆን፤ ከፍተኛ ክስተት ታሪክና መሰል ነገሮች ላይ ሳይሆን ሀሳብና ፍልስፍና ላይ ትኩረትን የሚያደርጉ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸራቸው የሆነ የካህሊል ጂብራን፣ ፓፓ ሩሚእና ፓፓ ጣሂርን የመሳሰሉ የፋርስ ጸሐፍት ተፅእኖ ስር ያለ ይመስላል የአንድ ገጣሚ ትልቁ መለያም መሆን ያለበት መፈላሰፍ መቻል ነው።
በሀያሲው የደራሲው ብልጠት ተብሎ የታየለት አብዛኛዎቹን ማስተላለፍ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ መጠቀሙን ነው ለነገሮች ተጨማሪ መነፅር እንደሚኖር ማሳያም ነው። ለጀማሪ ጸሐፍትም እንደ መማርያ መቅረብ ያለበት ነው ብለዋል።
መፅሐፉ ምን ጎደለው?
መፅሐፉ ከተወደሰበት ሀሳብ ጋር ባይወዳደርም የስርአተ ነጥብ አጠቃቀም የመጽሐፉ የመጀመሪያ እክል ሲሆን፣ የመፅሐፉ ማውጫ በጥቅሉ ነው የወጣለት ይህም ሌላኛው እክል ነው፤ ሃያሲው በስተመጨረሻም ገጣሚው ከዚህ በተሻሉ ሌሎች ስራዎች ማየት እንደሚሹ በመጠቆም ሂሳቸውን አጠናቀዋል። እኔም ይህንን መጽሐፍ እንዲያነቡ ጋበዝኩኝ። መልካም ዕለተ ሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲት 1 / 2012 ዓ.ም
ዳግማዊት ግርማ