አብዛኛውን ጊዜ የሚጥል በሽታ ጤናማ የሚመስሉ ሰዎች በድንገት ሕሊናን የመሳትና የመንፈራገጥ ችግር ሲታይባቸው ይታወቃል፡፡ ሕመሙ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ ያለበት ሰው ከመጠቃቱ በፊት በቅድሚያ አንዳንድ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል፤ መጥፎ ጣዕም፣ ጠረንና ኃይለኛ የሆድ ሕመም የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነኝህ ምልክቶች ሲያጋጥሙ ሕመምተኛው በድንጋጤ ስለሚዋጥ በመሮጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ዐይናቸው ተገልብጦ ነጩ ብቻ ተሰጎ ሊታይ ይችላል፡፡ የሚጥል በሽታ መጠነኛ ከሆነ ሕመምተኛው ለቅፅበት ያለበት ይጠፋውና ወዲያውኑ ሕሊናውን ሊያውቅ ይችላል። ከዛም ግለሰቡ ልክ ከእንቅልፉ እንደባነነ ዓይነት ጠባዮችን ያሳያል። የሚጥል በሽታ የማይተላለፍ ቢሆንም በዘር የመተላለፍ ሁኔታ ግን አለው፤ ተመሳሳይ የቤተሰብ አባላትን ሊይዝ ይችላል።
የሚጥል በሽታ በወሊድ ወቅት በሕፃናት ላይ በሚደርስ የአእምሮ ጉዳት፣ በከፍተኛ ትኩሳት፣ የኮሶ ትል በጭንቅላት ውስጥ መኖር፣ በማጅራት ገትር እና በመሳሰሉት ጠንቆች ሊባባስ ይችላል፡፡ ይህ በሽታ እስከ ሕልፈተ ሕይወት አብሮ ሊቆይ የሚችል የጤና ችግር እንጂ የሚድን አይደለም፡፡ ነገር ግን ሕፃናት እያደጉ ሲሄዱ በሽታው አቅም እያጣ ይመጣል፡፡ የሚጥል በሽታን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ መድኃኒቶች ያሉ ሲሆን ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ይቀንሳሉ፡፡
የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው ሲወድቅ ምን እናድርግ?
አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ የሚቆየው ከ60-90 ሰከንድ ነው፤ ነገር ግን ከ3 ደቂቃ በላይ ከቆየ ባፋጣኝ ወደ ሕክምና መኬድ አለበት፡፡ እንዲሁም በልምድ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ክብሪት ስናጨስ ይነሳል፣ ይተወዋል የሚሉት በዚህ አጭር ሰዓት ውስጥ ራሱ ነቅቶ ስለሚነሳ፣ የተነሳው ባጨሱት ክብሪት እንደሆነ ስለሚመስላቸው ነው እንጂ ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
• ራሱን ስቶ ሲወድቅ መንፈራገጥና መንዘፍዘፍ ስለሚኖር ከአካባቢው ሊጎዱት የሚችሉ ስለት ነገሮችን ከርሱ ማራቅ፤
• በመንፈራገጥ ወቅት ጭንቅላቱ ሊጎዳ የሚችልበት ሁኔታ ካለ ጉዳት እንዳይደርስበት መደገፍ፤
• በመውደቅ ወቅት መጎዳትና ደም መፍሰስ ካለ፣ የደም መፍሰስ ማቆም እርዳታ መስጠት፤
• ጥርሱ ከገጠመ በኃይል ለማላቀቅ አለመሞከር፤
• እንደ እሳትና ኤሌክትሪክ አካባቢ ከወደቀ ጉዳት እንዳይደርስበት መከላከል፤
• በሽተኛው በሕመሙ ከተጠቃ በኋላ ራሱን ሲያውቅ ሊደብተውና እንቅልፍ እንቅልፍ ሊለው ይችላል፤ ስለዚህ ተኝቶ እንዲቆይና እንዲያርፍ ማድረግ፤
• ጥቃቱ ለረዥም ጊዜ የሚቆይበት ከሆነ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ አለብን፡፡
የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው ሁኔታው ሲያጋጥመው መርዳት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012