በመድኃኒቶች አማካኝነት በሰውነት ላይ የሚፈጠር አለርጂክ ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን በአንዳንድ ሰዎች ላይ እስከሞት የሚያበቃ የአለርጂክ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ መድኃኒቶች በፈሳሽ መልክ፣ በሚዋጡ እንክብሎች ወይም በመርፌ መልክ ሊወሰዱ ይችላሉ፤ በተለያየ መልክ የምንወስዳቸው እነኝህ መድኃኒቶች በሰውነታችን ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት አልፎ ተርፎም ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ለተለያዩ በሽታዎች የሚወሰዱት የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በአንዳንድ ሰዎች ላይ አለርጂ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሰው ለቶንሲል የምንወስደው የፔኒሲሊን መድኃኒት ነው፤ ይህ መድኃኒት በሰዎች ላይ የሚፈጥረው አለርጂ እስከሞት ሊያበቃ ይችላል፡፡
ቢያንስ ከምናውቃቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ለፔኒስሊን አለርጂክ የሆነ ሰው ልናውቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም በዓለማችን ላይ 10 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ለዚህ ወሳኝ ለተባለ የአንቲባዮቲክ መድኃኒት አለርጂክ ናቸው
በሰውነት ላይ የአለርጂክ ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉ የመድኃኒት ዓይነቶች
• ፔንስሊን እና ተመሳሳይ የሆኑ የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣
• ሰልፋ ድረግስ( sulfa drugs) የተባሉ የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣
• አስፕሪን፣ ኢፖፕሮፊንና ሌሎች ለሕመም ማስታገሻ የሚወሰዱ መድኃኒቶች (nonsteroidal anti-inflammatory drugs (NSAIDs))፣
• የኬሞቴራፒ ሕክምና መድኃኒቶች የሚጠቀሱ ናቸው::
በመጀመሪያ መድኃኒቶችን ስንወስድ የአለርጂክ ሁኔታዎች ላያጋጥመን ይችላል፤ ምክንያቱም ሰውነታችን ለማንኛውም እንግዳ ሆኖ ወደ ሰውነት ለሚገባ ነገር፣ ፀረ እንግዳ( antibodies) አካል ምላሽ እያዘጋጀ ሊሆን ስለሚችል ነው፤ ነገር ግን በሌላ ጊዜያት ከዚህ በፊት የወሰድነውን መድኃኒት ስንወስድ ሰውነታችን ነገሩን የእንግዳ ነገር ወረራ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል፤ በመሆኑም የሰውነታችን ድኀነት ስርዓት(Immune system) ምላሽ ይሰጣል፤ በሂደቱም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመልቀቅ እንግዳ ነገሩን ይዋጋል፤ በዚህን ጊዜ የተለያዩ የጤና መታወክ የሚመስሉ ምልክቶች በሰውነታችን ላይ መታየት ይጀምራሉ፡፡ ከነዚህ ምልክቶች ውስጥ፡-
• በቆዳ ላይ ከፍተኛ የማሳከክ ሁኔታ፣
• በቆዳ ላይ ሽፍታ መውጣት፣
• ለመተንፈስ መቸገር ወይም የትንፋሽ ማጠርና
• የሰውነት ማበጥ ሊታይ ይችላል፡፡
የመድኃኒት አለርጂክ እንዳጋጠመን እንዴት እናውቃለን?
የመድኃኒቶች አለርጂ በየትኛውም የሰውነታችን ክፍል ላይ ሊያጋጥም ይችላል፤ አብዛኛውን ጊዜ አደገኛ የሚባል የአለርጂ ሁኔታ በሰውነት ላይ የሚፈጥረው ፔኒስሊን የተባለው የአንቲባዮቲ መድኃኒት ነው፤ ለፔኒስሊን መድኃኒት ሰውነታችን የአለርጂክ ምላሽ ሰጠ ማለት ለሌሎቹም የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ለምሳሌ አሞክሳስሊን፣ ተመሳሳይ ምላሽ ይሰጣል ማለት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን የመሆን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳም በአንድ ወቅት ሰውነታችን ለፔኒስሊን አለርጂክ ከነበረ፣ ወደፊት በሌላ ጊዜ መድኃኒቱን ስንወስድ የግድ አለርጂው ላያጋጥመን ይችላል፡፡ እንደ ባክትሪም( Bactrim) እና ሴፕትራ( Septra) ያሉ ሰልፋ( sulfa drugs) ያላቸው መድኃኒቶች አልፎ አልፎ የአለርጂክ ሁኔታ በሰውነት ላይ ሊፈጥሩ ይችላሉ። በአጠቃላይ በወሰድነው መድኃኒት አማካኝነት አለርጂ እንዳጋጠመን በምርመራ ልናውቅ እንችላለን፡- ይኸውም
• የቆዳ ላይ ምርመራ በማድረግ(ለፔኒስሊን መድኃኒት ብቻ)
• ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት የመድኃኒት አወሳሰድ በሆስፒታሎች በማድረግ ልናውቅ እንችላለን፡፡
ለመድኃኒት አለርጂ መወሰድ ያለበት ፈጣን ሕክምና
• አለርጂ የሚፈጥሩብንን መድኃኒቶች መለየትና መጠቀም ማቆም፣
• አንዳንድ የአለርጂክ ምልክቶችን ለማስቆም የፀረ ሂስታሚን( antihistamines) መድኃኒቶችን መውሰድ፣
• የአለርጂክ ሁኔታዎች ተፈጥረውብን እየባሱ ከሄዱ በፍጥነት ወደ ሕክምና ማዕከል በማምራት የወሰድነውን የመድኃኒት ዓይነት ነግረን ሕክምና ማግኘት ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች ናቸው፡፡
ከዚህ በላይ እንደጠቀስነው ምርመራዎችን በማድረግ የአለርጂ ሁኔታ እንደገጠመን ልናውቅ እንችላለን ብለናል፤ ይህ ይባል እንጂ በወሰድነው መድኃኒት ምክንያት የሚፈጠሩ የአለርጂክ ሁኔታዎች መለየት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሁኔታው የበሽታ ምልክት ሊመስል ይችላል፤ በአንፒስሊን አማካኝነት የሚፈጠርን አለርጂ፣ በቆዳ ላይ ምርመራዎች በማድረግ በአስተማማኝ ሁኔታ መለየት ይቻላል፤ በሌላ መድኃኒቶች የሚፈጠሩ አለርጂዎች ማለትም ትንፋሽ ማጠር፣ ሽፍታና ሰውነት ማሳከክ ከበሽታ ሁኔታ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ስላላቸው መለየት ሊያስቸግር ይችላል፡፡
የአለርጂ ሁኔታ ሲያጋጥም ሐኪሞች ከታማሚው ማወቅ የሚፈልጓቸው ወሳኝ መረጃዎች ያሉ ሲሆን እነርሱም፡-
• ምን ዓይነት መድኃኒት እንደወሰድን፣
• መቼ መውሰድ እንደጀመርንና መቼ መውሰድ እንዳቆምን፣
• መድኃኒቱን ከወሰድን በኋላ በምን ያክል ጊዜ ውስጥ አለርጂው እንደጀመረንና ምን እንደሚሰማን፣
• ምልክቶቹ ምን ያክል አብረውን እንደቆዩና ሁኔታውን ለማቆም የወሰድነው ሌላ ነገር መኖርና አለመኖሩን፣
• የታዘዘም ይሁን በራሳችን ፍቃድ የወሰድናቸው ሌሎች መድኃኒቶች መኖርና አለመኖራቸውን፣
• የባሕል ወይም የቪታሚንና የሚኒራል ሰፕልመንት መድኃኒቶች መውሰድና አለመውሰዳችንን፣ ከወሰድን ደግሞ ምን እንደሆኑ ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡
• ከአለርጂክ ምልክቶች በመነሳት ሐኪሞች የቆዳ ወይም የደም ምርመራ እንድናደርግ ሊያዙን ይችላሉ፡፡
የመድኃኒቶች አለርጂ ካጋጠመን መውሰድ ያለብን ከፍተኛ ጥንቃቄ
• ለሐኪሞች የምንነግራቸው የአለርጂ ምልክቶች በትክክል መግለፅ መቻላችንን፣
• ሐኪሞችን፣ መውሰድ የሌሉብን ሌሎች ተያያዥ መድኃኒቶች ምን ምን እንደሆኑ መጠየቅ፣
• አለርጂ የማይፈጥሩብንን ሌሎች ተለዋጭ መድኃኒቶች ካሉ በምትኩ እንዲሰጡን መጠየቅ፣
• ለምን ለምን መድኃኒቶች አለርጂክ እንደሆንን በእጅ ላይ የሚታሰሩ ወይም በአንገት የሚጠለቁ ምልክቶችን ማድረግ፤ ይህ ሁኔታ ራስን የመሳት ሁኔታ እንኳን ቢያጋጥመን ለሐኪሞች ሊያሳውቅ ይችላል፡፡
አናፊላክሲስ( Anaphylaxis)
አናፍላክሲስ የሚባለው አደገኛ የሆነ ህይወትን በፍጥነት ሊያሳጣ የሚችል የአለርጂ ሁኔታ ነው፤ ምክንያቱም በሰውነታችን ላይ ሁለት ወይም ከዛ በላይ በሆኑ አካላት ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰውነት ማበጥ ሁኔታ እና ለመተንፈስ መቸገር በወሰድነው መድኃኒት ምክንያት በአንድ ላይ ሲያጋጥሙ፣ ጉዳተኛውን በአጭር ጊዜ ለህልፈት ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲሰማን ወይም ሲያጋጥም በፍጥነት ወደ ሕክምና ሳናቅማማ ማምራት አለብን፡፡ ገጠመኙ በቅርብ በምናውቀው ቤተሰብ ላይ ካጋጠመና ተጎጂው ራሱን ከሳተ፣ የወሰደውን መድኃኒትና መቼ እንደወሰደ ጽፈን ለሐኪሞች መስጠት ወይም መንገር አለብን፡፡ ያጋጠመን አለርጂ ለአደጋ የሚያጋልጥ ካልሆነ ሐኪም የፀረ ሂስታሚን መድኃኒት ሊያዝ ይችላል፡፡
በሕክምና ተቋም ቁጥጥር የሚደረግበት የመድኃኒት አወሳሰድ
አንዳንዴ የአንቲባዮቲክ ሕክምና የግድ ሲያስፈልገን፣ ግን ደግሞ ለመድኃኒቶቹ አለርጂክ ከሆንን፣ በሆስፒታሎች ተኝተን ቁጥጥር የሚደረግበት የመድኃኒት አወሳሰድ ሊያስፈልገን ይችላል፡፡ ይኸውም መድኃኒቱን ከዝቅተኛ መጠን በመጀመርና ቀስ እያሉ መጠኑን በመጨመር የአለርጂክ ሁኔታ የሚፈጠርበት መጠን ላይ እስኪደርስ መድኃኒቱን መውሰድ ነው፤ ይህ ዘዴ የአለርጂክ ሁኔታ በድንገት ቢያጋጥም እንኳን ሐኪሞች በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል፡፡
የፔኒስሊን አለርጂ
ቢያንስ ከምናውቃቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ለፔኒስሊን አለርጂክ የሆነ ሰው ልናውቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም በዓለማችን ላይ 10 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ለዚህ ወሳኝ ለተባለ የአንቲባዮቲክ መድኃኒት አለርጂክ ናቸው፤ በመሆኑም በሆስፒታሎች ከሚያጋጥሙ የአለርጂክ ሁኔታዎች አብዛኞቹ በፔኒስሊን ምክንያት ያጋጠሙ ናቸው፡፡
ፒኒስሊን በ1928 እ.ኤ.አ በአሌክሳንደር ፍሌሚንግ የተገኘ መድኃኒት ሲሆን ዛሬ ላይ ይህ መድኃኒት ለብዙ የጤና መታወኮች ሊታዘዝ ይችላል፤ በተለይ ለቶንሲል በሽታ በስፋት የሚወሰድ መድኃኒት ነው፡፡ ይህ መድኃኒት አመርቂ የሚባል ውጤት ያለው ቢሆንም ብዙዎች የአለርጂክ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል በሚል ስጋት ለመውሰድ አይመርጡትም፡፡ የፔኒስሊን አለርጂን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ይህ መድኃኒት በጣም ፍቱን በመሆኑ ነው፡፡