ባለፉት ሁለት ተከታታይ እትሞች ስለኢትዮጵያዊነት የተለያዩ ሐሳቦችን አንስተናል። በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ለጠቅላላ ግንዛቤ እንዲረዳ ስለ ማንነትና ኢትዮጵያዊነት አጠቃላይ ጉዳዮችን ለማንሳት ተሞክሮአል። በሁለተኛው ክፍል ኢትዮጵያዊነት መሆን የነበረበት መሆኑ ቀርቶ መሆን ያልነበረበት መሆን በመቻሉ ምክንያት ተዳክሞ መቆዩቱንና ይህ ለምን እንደሆነ ለማሳየት ጥረት ተደርጎአል። በዚህ ዝግጅት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት መሆን የሚኖርበትን መሆን እንዲችልና መሆን የማይገባውን በመሆኑ ምክንያት የተከሰቱትን ችግሮች ለማስወገድ ምን መደረግ እንዳለበት ለመጠቋቆም ይሞከራል።
የጥንካሬ፤ የሀብት፤ የውበት፤ የክብር፤ የኩራትና ብቃት ምንጭና መሠረት መሆን የነበረበት ኢትዮጵዊነት እኛው ኢትዮጵያውያን በፈፀምነው ስሕተት ምክንያት የችግርና የክፋት ማምረቻ ሆኖ ቆየ። አሁን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትዕግስቱን የጨረሰ ይመስላል። ማብቂያ የሌላቸውን ችግሮች መግፋት ሰልችቶታል። አብሮነት የሚጠቅም መሆኑ ቀርቶ የሚጎዳ ከሆነ ለምን የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው። ብሶቱ የፈጠራቸው የተለያዩ ችግሮች የሀገሪቱን ሕልውናና ልዕልና እየተፈታኑ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት የችግር ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ እንዲያበቃ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነትን ከብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት ጋር ማስታረቅ አለባት። ሌላውን በማሳነስ ለራሱ የተከበረ፤ ሌላውን ዝቅ በማድረግ ለራሱ ከፍ ያለ አለመኖሩን አረጋግጠናል። ሌላውን አለማክበር አለመከበርን እንጂ መከበርን የሚያስገኝ አለመሆኑን ተረድተናል።
እኛን ከምንም በላይ የሚያግባቡን፤ የሚያስተማምኑንና የሚያስተቃቅፉን አምስት ነገሮች አሉ። አንደኛው በኢትዮጵያዊነታችንና ግንኙነታችን ውስጥ ያለውን ክምር ውሸት መናድ የሚችል እውነት መሆኑን መረዳት ነው። ሁለተኛው ኢትዮጵያንና ሕዝብዋን ብቻ ማዕከል ያደረገ ሥርዓት መፍጠር ነው። ሦስተኛው የኢትዮጵያና የሕዝብዋ ፍላጎት የገዢነት አቅም ያለው መሆኑን መቀበል ነው። አራተኛው ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማግባባት የሚያስችል የሕግ በላይነትን ማክበርና ማስፈን ነው። አምስተኛ የዜግነት ማንነት የሆነው ኢትዮጵዊነት ከብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት ጋር መጣራዙ እንዲያበቃ የሁለቱንም እኩልነት ማረጋገጥና ይኸንኑ በሕጋዊ ማዕቀፍ ማስደገፍ ነው። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ለማሳያ ያህል ወስደን እንይ።
እውነት ያስማማል
ፖለቲካችንና ታሪካችን ውሸት ይበዛበታል። ኢትዮጵያዊነትም እንዲሁ ነው። አውነትና ውሸት ተቃራኒ ናቸው። በሰው ልጅ ሕይወትና ታሪክ ውስጥ አልሚና አጥፊ በመሆን ወሳኝ ቦታ አላቸው። እውነት ገንቢ ሲሆን ውሸት ግን አፍራሽ ነው ለሰው ልጅ። እውነት ያቀራርባል፤ ያፈላልጋል፤ ያስማማል። ይህ የሚሆነው ውስጣዊ ሕይወታችንን መቆጣጠር፤ መግዛት ወይም መምራት ሲችል ነው። ውሸት ግን ያራርቃል፤ ያጣላል። ይህን የማድረግ ጉልበት የሚያገኘው ደግሞ እውነትን በውስጣችን በማዳከም ነው። የራስንም ሆነ የሌላውን ሰው ሕይወት ይሰርቃል፤ ያበላሻል። እውነት በውስጣችን እንዲጎለብትና ውሸት ከውስጣችን እንዲወጣ መፍቀድ አለብን። እውነት ጉልበትና ሀብት፤ ፍቅርና ውበት ነው የሰው ልጆችን የሚያቀራርብና የሚያፈቃቅድ፤ የሚያፋቅርና የሚያወዳጅ ስለሆነ። ውሸት ግን የሚሰራው በተቃራኒው ነው።
ለኢትዮጵያዊነት ጉልበት የሚሆነው እውነት ነው፤ ጉልበት የሚያሳጣው ደግሞ ውሸት ነው። የምናስበው፤ የምንናገረውና የምንሰራው ሁሉ እውነት መሆን አለበት። ሰው እውነተኛ መሆን የሚገባው በመጀመሪያ ደረጃ ለራሱ ነው። ምሉዕ ስብዕና ከሚያሰገኙ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው እውነት ነው። ውሸት መናገር ግን የሰውን ምሉዕ ስብዕና የሚፈታተን ነው። መዋሸት የተሳሳተ መረጃ መስጠት ነው። ሌሎች ከኛ የሚጠብቁትን መልካም ነገር (ትክክለኛ መረጃ) መስጠት አለመቻል ደግሞ ክብርን ይቀንሳል፤ አመኔታን ያሳጣል። ውሸት በመናገር የሚታወቅ፤ ስለአንድ ነገር የተለያዩ መረጃዎች ወይም ሐሳቦችን የሚሰጥ ሰው መታመን አይችልም። ስለዚህ ውሸት የራስን (የተናጋሪውን) ማንነት ይጎዳል።
እውነት ያፀዳል፤ ውሸት ግን ያቆሽሻል። በእርግጥ ውሸት የሌሎች እንከኖች መሸፈኛና ምልክትም ነው። ራሱን ከምንም አስበልጦ የሚወድ፤ የማይገባውን ነገር የሚፈልግ፤ በእውነት የሆነውን ነገር የሚደብቅ፤ ስግብግብነትና ፍርሃት ያለበት፤ የበላይነት ወይም የበታችነት ስሜት የተጫነውና የመሳሰሉት ችግሮች ያሉበት ሰው ነው ውሸትን የሚጠቀመው። ውሸት እምነትን መጣስ ነው። ሰው በማሕበራዊ ሕይወትና ቁርኝት ውስጥ የተሳካ ሕይወት መኖር የሚችለው ሌላውን በማመን፤ በሌላው በመታመን ወይም ለራስ በመታመንና እርስ በእርስ በመተማመን ነው። ውሸት ይህን እሴት ይጥሳል። ስለዚህ በተለያዩ መንገዶች ማንነታችንና ግንኙነቶቻችን ሲመርዝ የቆየውን ውሸት መታገል ይገባል። የእውነት በር እየሰፋ ሲመጣ የውሸት በር እየጠበበ ይሄዳል። ከኢትዮጵያዊነት የሚያስታርቀንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያርቅልን እውነት ብቻ ነው። በእውነት ከውሸት መፅዳት ከቻለ አትዮጵያውያንን ሁሉ ያስማማል።
የፈጸምነውን ስሕተት ማመን፤ መቀበልና ማረም
የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁን ያደረገው ረጅም የታሪክ ጉዞ ስሕተትና ውድቀት የበዛበት ነው። መሳሳት የሚያስከትለውን ውድቀት መቋቋምና ማረም፤ ማቆምና ማስወገድ የሚቻለው ከስሕተት በመማርና በመታረም ነው። የሰው ትልቁ ችግር መሳሳቱ አይደለም፤ ከስሕተት መማር አለመቻሉ እንጂ። እኛ ኢትዮጵያውያን የፈጸምነውን ስሕተት ለመቀበል፤ ለማመንና ለማረም መድፈር ይሳነናል። ስሕተትን አምኖ መቀበል ክብረ-ነክ መስሎ ይታየናል፤ መኖርና መስራት የማያስችለን ይመስለናል። እጅግ የሚጎዳን ስሕተት መፈጸማችን ሳይሆን ስህተት መፈጸምን አምኖ መቀበልና ማረም አለመቻላችን ነው። በዚህ ምክንያት ተመሳሳይ ስሕተቶች በተለያዩ ትውልዶች ተፈጽመዋል።
ብዙውን ጊዜ ሌሎች የሚፈፅሙብንን እንጂ በራሳችን ላይ ያደርስነውን ጉዳት በቀላሉ አንረዳም። በፈጸምናቸው ጥፋቶችና ስሕተቶች ልክ ራሳችንን ስናፈርስ ቆይተናል። ድምፅ-አልባ ጦርነት በራሳችን ላይ ከፍተን ራሳችንን፤ ሀገራችንና ትውልዶችን አሳንሰናል። በራሳችን ላይ ያደርስነው ጥቃት ጠላት ከሚያድርስብን የበለጠ እንጂ ያነሰ አይደለም። ግዙፉ ጉዳት በራሳችን ላይ የፈፀምነውን ጥፋት አለመረዳታችን ነው። ድርብና ድርብርብ ስሕተቶች መፈጸማችንን አምነን መቀበል ካልቻልን ከውድቀት የሚያድነን የለም።
እስካሁን የፈፀምናቸው ስሕተቶች ምን ያህል እንዳሳነሱን መረዳት አለብን። ብዙዎቻችን ድህነትና ኋላቀርነት ፈታናችን መሆናቸውን እንረዳለን። መንስኤዎቻቸውን ማወቅ ግን ቀላል አይደለም። ከእኛ ውጭ እንጂ በእኛ ውስጥ መሆናቸው አይታሰበንም። በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ መዳከም ዋናው ምክንያት ያለው በእኛ ውስጥ ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መልካምና መጥፎ የሆኑ ነገሮች ነበሩ፤ አሉ። በነበሩ የአገዛዝ ሥርዓቶች ባሕርያት ምክንያት መጥፎዎች የነበሯቸው ጉልበት መልካሞች ከነበሯቸው ጉልበት የበለጠ ነው። መጥፎነት በነበረው ጉልበት በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የነበረውን መልካምነት አቀጨጨው። ይህ አንደኛው ስሕተት ነው። በተግባር የሚኖረውን መጥፎነት በመልካም ቃላት ቀባብቶ ለመደበቅ መሞከር ሌላ ስሕተት ነው። በኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያውያንን ወደ ዳር መግፋት ሶስተኛ ስሕተት ነው። እነዚህን ስሕተቶች አለማረም ደግሞ የስሕተቶች ሁሉ ስሕተት ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ መሳሳታችን በቅንነት መቀበል አለብን። ስሕተቶቻችንን ለመቀበልና ለማረም ድፍረት ሊኖረን ይገባል። ምክንያታዊነት፤ ቅንነትና በጎ አሳቢነት በውስጣችን ካሉ ድፍረትን ማግኘት የሚከብድ አይደለም።
ለመሆኑ በእርስ በእርስ ባደርስነው በደል ማን ተጠቅሞ ማንስ ተጎዳ; ሌላውን በማሳነስ ለራሱ የተከበረ ወይም ሌላውን ዝቅ በማድረግ ለራሱ ከፍ ያለ ሰው አለ; መልሱ የለም ነው። ሌላውን አለማክበር አለመከበርን እንጂ መከበርን አያስገኝም። ስሜታዊ በሆነና ብስለት በጎደለው አስተሳሰብ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች በቅርበት የሚታያቸው ጥቅም እንጂ ጉዳት አይደለም። በሌላ ላይ በሚፈጽሙት ጥፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ራሳቸው የሚጎዱበት መሆናቸውን አይረዱም። ሌላውን በመጉዳት የሚገኝ ጥቅም ካለ በጣም ትንሽና ጊዜያዊ ነው። በዘላቂነት የሚያስከትለው ጉዳት ግን ከባድ፤ ዘላቂና ውስብስብ ሊሆን ይችላል። ካለማወቅ መሳሳት አለ። ሆን ብሎ መሳሳት አለ። ካለማወቅ የሚመጣው ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚፈፀመው ስሕተት እጅግ በድሎናል። በተለይ የኢትዮጵያ ሊህቃን ምን ጊዜም ቢሆን ከስሕተት መማር ተሳክቶላቸው አያውቅም። በአደባባይ ላይ ተቆልሎ የሚታይን ስሕተት ሰርተው ሲያበቁ ለውድቀትና ችግር ምክንያት የሚያደርጉት ሌላውን እንጂ ራሳቸውን አይደለም። መሻሻልና ዕድገት የሚኖረው ባለመሳሳት ሳይሆን ስሕተትን በማረም፤ ከስሕተት በመማር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሊህቃን ትላንት ለተፈፀመው በደል ሲባል ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚኖረው ሕይወትና ትውልድ ሲሉ ስሕተትን ለማረም ራሳቸውን መድፈርና ማደፋፈር አለባቸው።
ኢትዮጵዊነትና የብሔር-ብሔረሰብ ማንነት
እነዚህ ሁለት ማንነቶችን ማጣላትም ሆነ ማስማማት ይቻላል። ያለፉት ሥርዓቶች ለብዝሃነት እውቅና መስጠት ባለመፈለጋቸው በሀገራዊ ማንነት (ኢትዮጵዊነት) ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነትን ለማጥፋት ታግለዋል። ይህ ያልተቀደሰ ሙከራ ስለነበረ አልተሳካም። አሁን ያለው ብቸኛና እውነተኛ ምርጫ ዜጎች ሁለቱንም ማንነት በእኩልነት መያዝ እንዲችሉ ማድረግ ነው። ኢትዮጵያዊነት ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነትን ማቀፍ፤ ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነትም ኢትዮጵዊነትን ማቀፍ አለበት። የኛ የአስተሳበብ ድህነት አንዱን ከሌላው ያጣላው እንጂ ሁለቱም ያንድ ኢትዮጵያዊነት ሁለት የማይነጣጠሉ ገጽታዎች ናቸው።
በኢትዮያዊነት ዙሪያ የሚነሱ ችግሮች በአብዛኛው በሐሳብ ደረጃ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ርዕዮተዓለማዊ ጉዳዮች ናቸው። በመሬት ላይ በሚለኩበት ጊዜ በማንነት ላይ የተፈጠረው ልዩነት ያን ያህል የተጋነነ አይመስልም። ገዢዎች ኢትዮጵያዊነትን የመጨቆኛ ወይም የማግለያ መሳሪያ አድርገው ቢጠቀሙበትም ከፈለጉት ከፍታ አላደረሳቸውም። በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነታቸው የተገፉ ወገኖችም የነበራቸውንና ያላቸውን ማንነት የሚያሳጣ ሁኔታ አልተፈጠረም። በዜግነት ማንነታችንና በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነታችን መካከል ያለው ልዩነት ይህን ያህል ስላልሆነ በቀላሉ የሚታረቁ ናቸው። በአንዱ ሌላውን ማዳከም ከቀረ ሁለቱም ባንድ ላይ የሚታፈርና የሚከበር ማንነት ይፈጥራሉ። ስለዚህ በኢትዮጵያዊነትና በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት መካከል ያለው ልዩነት አትዮጵያንና ሕዝብዋን የሚያዳክሙ ሳይሆን የሚያጠናክሩ መሆን አለባቸው።
ሰላም፤ እርቅና ይቅርታ
እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርቀና ይቅርታን እንፈልጋለን። እርቅና ይቅርታን የምንፈልገው ሰላምን ለማውረድና ልማትን ለማፋጠን ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያሉትን እንከኖችን ለማፅዳት ብቻ ሳይሆን በማናቸው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊና ባሕላዊ ሕይወታችን ውስጥ ያሉ ህፀፆችን ለማረም እርቅና ይቅርታ እጅግ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ስም በኢትዮጵያውያን ግለሰቦች፤ ቤተሰቦች፤ ማሕበረሰቦችና ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳትና ውድቀት አድርሰዋል። ዜጎች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እሰከ መሸንሸን ደርሰው ነበር። ብዙዎች በራሳቸውና በሀገራቸው ጉዳይ ባይታወር ተደርገዋል። ዕድል በመነፈጋቸው ለሀገራቸው ማበርከት የሚገባቸውን ሳያበረክቱ ቀርተዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ የባከኑና የመከኑ ነገሮች አሉ።
ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮ ጵያዊነት ጋር ተጣልተዋል። ኢትዮጵያዊ ከራሱና ከባሕሉ ጋር ተጣልቶአል። ኢትዮጵያውያን ከበጎ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ጋር ተጣልተዋል። በተፈጠረው ግዙፍ ጥላቻ ምክንያት በርካቶች ውድ ልጆቻቸውን ወይም ወላጆቻቸውን፤ ባሎቻቸውን ወይም ሚስቶቻቸውን፤ እህቶቻቸውን ወይም ወንድሞቻቸውን፤ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን አጥተዋል። ኢትዮጵያም ውበትዋና ድምቀትዋ፤ ጉልበትዋ ሀብትዋ የሆኑ ዜጎችዋን አጥታለች። ይኸን ሁሉ ታሪካዊ ጥፋትና ክፋት ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማለፍና መኖር አይቻልም። የማይቻል መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ከእርቅና ይቅርታ መንገድ የተሻለ ሌላ መንገድ የለም።
የደረሱ በደሎች ግዝፈትና ጥልቀት ስለነበራቸው ዛሬም ቢሆን ቁስሎች አልጠገጉም። የደረሰውን በደል የሚያስረሳ ስራ አለመሰራቱ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ጥፋቶች እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ሥርዓት እስካሁን አልተፈጠረም። የበደልና የክፋት መረብ አሁንም አልተበጣጠሰም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮና ልብ ከሥጋትና ፍርሃት የፀዳ አይደለም። እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት የለም። በየቦታው የሚፈጠሩ ጥፋቶች ለዚህ ማስረጃ ነው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግና በአዲስ መልክ ለማነፅ በእርቅና በይቅርታ መጀመሩ አማራጭ የለውም።
ከሕዝቦቻችን ልምዶችና ባሕሎች ብዙ የምንማራቸው በጎ ነገሮች ቢኖሩም ገዢዎችና ሥርዓቶቻቸው በሚተበትቡት ተንኮል ችግሮቻችን የሚፈቱባቸው ቁልፎች አላደረግናቸውም። ዛሬ ግን በኢትዮጵያ የእርቅና የይቅርታ ጥያቄ የፖለቲካ ቡድኖች ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገብጋቢ ፍላጎት ሆኖአል። የሕዝብ ድምፅና ፍላጎት መደመጥ አለበት። የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ተደማጭነት ያላቸው ዜጎች ለእርቅና ይቅርታ የሚያደርጉትን ጥረት አክብሮ መቀበል የግድ ይላል። ወደ አስተማማኝ እድገት የሚወስደንን ጎዳና በእርቅና በይቅርታ ብናፀዳው ለአሸናፊነት አንበቃለን።
ኢትዮጵያዊነት እንዴት ይጠናከራል;
ስለኢትዮጵያዊነት ስናስብ ያለበት የኃላፊነት ድንበር፤ ስፋትና ጥልቀት ማየት ይጠበቅብናል። ኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ብቻ አይደለም። ማሰቢያ፤ መሆኛና ማድረጊያም ነው። ማሰብ፤ መሆንና ማድረግ ደግሞ መብትንም ሆነ ግዴታን የያዘ ነው። ለኢትዮጵያዊነት የሚቆረቆር ዜጋ ሁሉ ከክፋትና ከጥፋት ሊያፀዳ ይገባል። ምን ያህሉ ኢትዮጵያዊ ነው ስለሀገሩና ወገኑ የሚቆረቆረው; ኢትዮጵያዊነት በውስጡ ያሰረፀው የኃላፊነት ስሜት ምን ያህል ጥልቅ ነው; የጋራ ችግሮች በጋራ ጥረት ለመቋቋም ያለው ተነሳሽነት ምን ያህል ጠንካራ ነው; እነዚህ ኃለፊነቶች ምንድናቸው; እያንዳንዱ ዜጋስ ምን ያህል ያውቃቸዋል; እነዚህ ጥያቄዎች ማንሳት የተፈለገው መልስ ለመስጠት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ከቃል ባለፈ ብዙ ተግባራዊ ጉዳይ የያዘ መሆኑን ለመጠቆም ያህል ነው።
ኢትዮጵያዊነት በሀገር ፍቅር መገለጽ አለበት። ሀገሩን የማይወድ ዜጋ አለ ቢባል ራሱን የጠላ መሆን አለበት። ሀገርን መውደድ እናትን የመውደድ ያህል ነው። ሀገር ለዜጎቿ ሁሉ እናት ናት። እናት ደግሞ ትወደዳለች፤ ትከበራለች፤ የሚያስፈልጋት እንክብካቤ ሁሉ ይደርግላታል። ለእናት ያለን ፍቅር ከእርስዋ በምናገኘው ጥቅም አይለካም። ስትጠቅመን የምንወዳት፤ ሳትጠቅመን የምንጠላት እናት የለችም። ለሀገር ሊኖረን የሚገባው ፍቅር በዚሁ ልክ የሚታይ ነው። ሀገር በተለያዩ ምክንያቶች ለሁሉም ላትመች ትችላለች። ዜጎቿ የሚጎሳቆሉባት፤ በረሃብና በቸነፈር የሚሰቃዩባት፤ በሰላምና መረጋጋት እጦት ሁሌ የፍርሃትና ሥጋት ሕይወት የሚገፉባት ልትሆን ትችላለች። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ስላሉባት ብቻ አትጠላም። ኢትዮጵያ ዛሬ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች እየተፈታተኗት ነው። ስለደኸየች፤ ችግር በችግር ስለሆነች የሚገባትን ፍቅርና ክብር አንነፍጋትም። ለድህነትዋ ተጠያቂዎች እኛ ዜጎችዋ ነን። ኢትዮጵያዊነት በውስጣችን ማስረጽ የሚኖርበት ይህን እሴት ነው።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
ጠና ደዎ (ፒኤችዲ)፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ