ባለፉት ሥርዓቶች በተለይም ከ1983 ዓ.ም በፊት የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶች ሕይወታቸውን የሚያጡት በጦርነት ነበር። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ለሕይወታቸው ፈተና የሆኑባቸው ከሥነ ተዋልዶ ጤና እና ከሱስ ጋር የተያያዙ መዘዞች እንደሆኑ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። አሁን በኢትዮጵያ የወጣቶች ጤንነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምን ፈተናዎችስ አሉበት? የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ተሞክሯል።
ወጣት ማነው? አፍላ ወጣትስ?
በአለም የጤና ድርጅት ትርጓሜ መሰረት ወጣቶች(youth) ከ15 እስከ 24 ዕድሜ ያላቸው እንደሆኑ ያመለክታል። በ2004 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የወጣቶች ፖሊሲ ደግሞ እንደ አገር ወጣቶች በሚል ያካተታቸው ከ15 እስከ 29 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ነው።
ወጣቶች ምን አይነት የተዋልዶ ጤና መረጃ ይፈልጋሉ?
ወጣቶች ክህሎታቸውን በማዳበር የተዋልዶ ጤናቸውን በኃላፊነት እንዲጠብቁ ማብቃት አስፈላጊ ነው። በዋናነትም ከሱስ እና ከወሲብ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚገጥሟቸውን አደጋዎች በጥንቃቄና በአስተውሎት ማለፍ ለሕይወታቸው በዘላቂነት መሰረት መጣል ያስችላቸዋል ይላሉ። የዘርፉ አጥኝዎች።
ያልታቀደ እርግዝና፣የወሊድና የአባላዘር በሽታ ተጋላጭ መሆን የሚያመጣውን መዘዝ እና መከላከያ ዘዴዎችን ሳይሰለቹ በተደጋጋሚ እንዲያውቁ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ለአፍላዎች እና ለወጣቶች በአቻ ለአቻ ግንኙነት መንገዶችም ሆነ በተለያዩ ሥልቶች ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤናና የተለያዩ የጤና ችግሮች በግልጽ ማስተማር፤ ስለወሊድ ሁኔታና እውነታ በሴትና በወንድ ጾታዎች መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው። የሥርዓተ ጾታ ግንኙነት ከማህበራዊ ትርጓሜው የመነጨበትን ምክንያት ማሳወቅና ማስረዳት ከሚገጥሟቸው ስሜታዊ ድርጊቶች በመታደግ የተለየና አዲስ ነገር እንዳይመስላቸው ያደርጋሉ ነው የሚሉት የዘርፉ አጥኝዎች።
የጤና አገልግሎቱ ለወጣቱ ተደራሽ ነው ወይ?
አቶ እሚያምረው ሲሳይ በጤና ሚንስቴር የእናቶችና ሕጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ወጣቶችና የወጣቶች ጤና ጉዳዮች ቡድን መሪ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፣ በአገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሆስፒታሎች፣ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች አሉ። ነገር ግን ለወጣቶች ጤንነት አስበውና አቅደው በሰፊው እየሰሩና እያገለገሉ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። እ.ኤ.አ 2014 በተጠናው ጥናት መሰረት በአብዛኛው 60 በመቶዎቹ በተሟላም ባይሆን አገልግሎት ይሰጣሉ። በሰለጠነ ባለሙያ አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ ዝቅተኛ እንደሆኑ ያሳያል።
የጤና ስትራቴጂዎች የወጣቱን ስነተዋልዶ ጤና
ያካተቱ ነበሩ ?
ባለፉት ዓመታት በፖሊሲና በስትራቴጂ ረገድ ወጣቶች ብዙ ትኩረት የተሰጣቸው አልነበሩም። በዚህ የተነሳም የጤና፣ የትምህርትና የሌሎች የልማትና የእድገት ፍሬዎች ተቋዳሽ አልነበሩም። በየአካባቢው ለስራ አጥነትና ለሱስ የተዳረጉት በርካታ ወጣቶች ለዚህ አስረጂዎች ናቸው። ዛሬ ላይ ጫት የማያመነዥክ ወጣት ለውርርድ አይገኝም።
በጤናው ዘርፍ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን እንዲሁም 2004 ዓ.ም የተዘጋጀውን ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ተከትሎ የኢትዮጵያ የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ፖሊሲ በ1999 ዓ.ም ተዘጋጀ። መንግስትም ለወጣቶች እድገት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና የክህሎት መዳበር ለመጀመሪ ጊዜ በፖሊሲ በታገዘ አሰራር ትኩረት የሰጠበት ተደርጎ ይጠቀሳል፤ ይኸው ፖሊሲም እ.ኤ.አ ከ2007 እስከ 2015 ተግባራዊ ተደርጓል።
በዚህም የመንግስት፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማህበራት ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲተገብሩ አድርጓል። በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚስተዋሉ አመለካከቶችን ለመቅረፍ መሰረት የተጣለበት እንደሆነም ይነሳል። ሁለተኛው የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ደግሞ እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2016 ዓ.ም በመተግበር ላይ ይገኛል።
የሥነ ተዋልዶ ጤና ያለበት ደረጃ እንደ ማሳያ
አቶ እሚያምረው እንደገለጹት፣ አገራዊ የወጣቶችን የጤንነት ሁኔታ መከታተልና መጠበቅ የአገራዊ ደሕንነት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ይላሉ። ከ1998 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የሥነ ተዋልዶ ጤና ያለበትን ደረጃ የ2012 ዓ.ም የጤና ጥበቃ ሚንስቴርን መረጃ በማጣቀስ አብራርተዋል። በዚህ መረጃ መሰረትም ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ በወጣትነታቸው ለሞት ተጋላጭነታቸው መቀነስ የተስተዋለበት ነው። በተለይም እኤአ በ2005 እስከ በ2011 ድረስ ያለው ጥሩ መቀነስ ታይቷል። ነገር ግን እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ብዙ ለውጥ አለመኖሩን በመረጃዎች ያሳያሉ። በዚሁ ጊዜ በአፋላነትና በወጣትነት የሚገኙ ወንዶች የሞት ተጋላጭነታቸው ጨምሯል።
ከቤተሰብ ምጣኔ ጋር በተያያዘ፡- እኤአ በ2019 የተሰራው የኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ ጥናታዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከ20 እስከ 25 ዓመት ያሉት 50 በመቶ የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከ15 እስከ 24 ዓመት እድሜ ያላቸው ወጣቶች 35 በመቶ የቤተሰብ እቅድ ይጠቀማሉ።
ከኤች አይ ቪ ስርጭትና መከላከል አኳያ ደግሞ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣቶች ከ15 እስከ 24 እድሜ የሆናቸው 24 በመቶ ሴቶች እና 39 በመቶ ወንዶች ግንዛቤ እንዳላቸው ተመላክቷል። በከተሞች በተጠቀሰው እድሜ ያሉ 42 በመቶ ሴቶች እና 48 በመቶ ወንዶች ደግሞ ኤች አይ ቪን አስመልክቶ ግንዛቤው ያላቸው ሲሆን በገጠር 19 በመቶ ሴቶች እና 37 በመቶ ወንዶች ግንዛቤው እንዳላቸው አቶ እሚያምረው ገልጸዋል። እነዚህ በማሳያነት የቀረቡ እንጂ በሌሎች በርካታ የጤና ጉዳዮች የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ክፍተት የሚስተዋልበት እንደሆነ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን