በትምህርት ቤት በተለይም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ይጓጓሉ።አሁን አሁን ግን በዩኒቨርስቲዎች በሚያስተውሏቸው ግጭቶች ምክንያት ፍላጎታቸው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩ አይቀርም። ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር ላይ በሚገኙ እህትና ወንድሞቻቸው የተነሳ ወላጆቻቸው በየእለቱ ሰቀቀን ላይ መሆናቸው አስረጂ ነው።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየአካባቢው የሚገኙ በመሆናቸው በየእለቱ የሚፈጠረውን የሰላም እጦት፣ ግርግርና የተማሪዎችን ሞት ለመስማትም ሆነ ለማየት ቅርብ መሆናቸው ደግሞ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ይነሳል። እነዚያ የሚናፈቁ እና ተዓምር መስሪያ ተደርገው የሚታሰቡ ተወዳጅ የእውቀት ገበያዎች በአሁኑ ጊዜ ስማቸው ከስሟል፤ ዝናቸው ጎድፏል።
“ከመምህራን እስከ አስተዳደር ሰራተኞች የኮታ ውጤቶች ናቸው። ከእውቀት መፍለቂያነት ወደ ጠብ መፍለቂያነት ተቀይረዋል” የሚለው በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ አቤል መልካሙ ነው። በግጭቶች ምክንያት ትምህርቱን አቋርጦት ከመጣ ወራት ተቆጥረዋል። የገጠመውን ፈተና ሲያስብ እንባ ይቀድመዋል። ይሁን እንጂ ትምህርት መጀመሩን ቢሰማም ‹‹እባብን ያዬ …›› ሆነና ነገሩ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለም። ቤተሰቦቹም ወደ ዩኒቨርስቲው ተመልሶ ትምህርቱን እንዲቀጥል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ተናግሯል።
ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን ስራዎች ተሰርተው ነበር?
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ለሕዝብ እንደራሴዎች እንዳብራሩት፣ ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑ መጠነ ሰፊ የቅንጂት ስራዎች ብዙ የግጭት መፍጠሪያ ሴራዎች ማክሸፍ ተችሏል። ኃላፊነት የማይሰማቸው የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫዎቻቸውን በለጋ ወጣቶች ሕይወት ላይ ማድረጋቸው የሚያሳፍር ተግባር ነው።
ሚኒስትሯ እንዳሉት፣ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት እንዲቀረፉ እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አስቀድሞ ታስቦበት ስራዎች ተሰርተዋል። በተለይ ለግጭት አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየት ከተሰሩት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አዳዲስ መመሪያዎች ማውጣት፣ ነባሮቹንም መከለስ፣ የተማሪዎችን ምደባ የበለጠ ሕብረ ብሔራዊ እንዲሆን ማድረግ፣ የሰው ሃይልና ግብዓት ማሟላት፣ፈጣን ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን ለይቶ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ፣ተማሪዎች የግልና የጋራ ኃላፊነት የሚወስዱባቸው ውሎች ማስፈረም፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከአቀባበል ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ እንዲሰጡ መደረጉ ተጠቃሽ እንደሆነ ተናግረዋል። 30 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአካል በመገኘት ጥረታቸውን ማገዝ ተችሎ ነበርም ነው ያሉት።
አሁን ከሚገኙበት የባሰ ምን ይፈጠር ነበር?
ከፍተኛ በጀት መድበው እና የሰው ሀይል አሰልጥነው የብጥብጥና የጥፋት ሴራ ላይ የተሰማሩ የተደራጁ አካት አሉ። በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አነጣጥረው ሰፊ ስራ ሰርተዋል፣አሁንም እየሰሩ ነው። ነገር ግን ከእቅዳቸው አኳያ አልተሳካላቸውም ማለት ይቻላል። መንግስትም ተግባሩን ለማክሰም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ችሏል። በዚህ የተነሳም የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት መከላከል መቻሉን ፕሮፌሰር ሂሩት አስረድተዋል።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተደርገውም ከሕዳር ወር ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰላም መታወክና በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች አጋጥመዋል። በዚህ ሳቢያም የወጣቶች ሕይወት አልፏል።አካል ጎድሏል። ንብረትም ወድሟል። በወላጆችና በተማሪዎች ላይ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ጫናም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
ከገንዘብ እስከ ብረት መሳሪያ በማስታጠቅ ችግሮቹን ከሚፈጥሩት እኩዮች ባለፈ የተዛቡ የሚዲያ ዘገባዎች(መደበኛ ሚዲዎችን ጨምሮ)ችግሮቹን የሚያባብሱ ቤንዚኖች ነበሩ። የሐይማኖትና የብሔር መልክ የማስያዝ ሁኔታዎችም ተስተውለዋል።
ዩኒቨርስቲዎችም አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ ርምጃዎችን በወቅቱ አለመውሰድ፣ የአመራር ውህደት ክፍተት(አልፎ አልፎ)፣መሰረተ ልማቶች አለመሟላት (መብራት፣አጥር…ወዘተ)፣ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙበት ክልላዊ እና አካባቢያዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በዋናነት የሚጠቀሱ አባባሽ ጉዳዮች መሆናቸውን ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል።
ርምጃዎቹ መፍትሄ ይወልዱ ይሆን?
በዩኒቨርስቲዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና ብጥብጦች ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከግቢ ወጥተው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተገድደው እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተደረጉ ጥረቶች አሁን ላይ ወደ ትምህርት ገበታዎቻቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
ችግሮቹን በመፍጠርና በመሳተፍ በተጠረጠሩ አካላት ላይም ርምጃዎች ተወስደዋል። ለአብነትም የቦርድ አመራሮችን በዘንድሮው ዓመት በተለየ መንገድ እንዲዋቀሩ ተደርገዋል። ለዩኒቨርስቲው ቅርብ የሆነ ከተማ ከንቲባ ወይም የዞን አስተዳዳሪ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆኗል። ይሄ የሚፈጠሩ ችግሮችን በቅርበት በመከታተልና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ያስችላል፤ ተማሪዎቹንም ይታደጋል የሚል እሳቤ አለው።
በተገቢው ያላገዙ አምስት የቦርድ ሰብሳቢዎች እንዲነሱ ተደርጓል። ሶስት ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነት ተነስተዋል። ሶስት ዋና ፕሬዚዳንቶች እና አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተቀጥረዋል። 921 ተማሪዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል።(417 ተማሪዎች ከአንድ ዓመት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ዓለም እስከ ማሰናበት፣ 504 ከቀላል እስከ ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ)፣ 30 መምህራን (ሶስት የደመወዝ ቅጣት፣አራት ከኃላፊነት ማንሳት፣23 ከቀላል እስከ ከባድ ማስጠንቀቂያ) ርምጃ ተወስዶባቸዋል።
እንዲሁም 256 የአስተዳደር ሰራተኞች (10 ከስራ ማሰናበት፣ 244 ከቀላል እስከ ከባድ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ሁለት ከኃላፊነት ማንሳት) ርምጃ ተወስዷል። የ140 ተማሪዎች እና 14 መምህራን ጉዳይ እየተጣራ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ አክለዋል።
በመንበራቸው ያልተገኙት ምሁራን
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በአርቲ ቡርቲ ተጠምደው ከምሁርነት መንበራቸው የወረዱ ይመስላል። ለውጥ የናጠውን ማህበረሰብ መርቶ አቅጣጫ ከማሳየት ይልቅ አብረው መንገድ ስተዋል። ዶክተር አለማየሁ አረዳ ‹‹ምሁር›› በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት በማናቸውም ማበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ምሁራን ለለውጥ እና ለእድገት ተፈላጊ የሆነው የእውቀት ባለቤቶች ናቸው። በለውጥ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎም ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም ማህበራዊ ለውጥ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ይከናወን ዘንድም ምሁራን አስፈላጊ መሆናቸው ተመላክቷል።
ሲጠቃለል
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፈ ብዙ ለውጥና ችግር ፈች የምርምር ውጤቶች የሚመነጭባቸው ተቋማት ናቸው። በመሆኑም ይህ ዓለማቸውን ያሳኩ ዘንድ ጠንካራ የአሰራር ስርዓትና መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። ተቋማቱን የፖለቲካ ፍላጎት ማራመጃ የማድረግ ዝንባሌዎች የማይታረሙና በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ ትውልዱን ይዘው ከመክሰም አይድኑም።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጦስ በማህበረሰቡ እና በመማር ላይ ባሉት ለጋ ወጣቶች ዘንድ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚጠገን ባለመሆኑ ትኩረት ይሻል። በትምህርት ዘርፉ የተካሄዱ ስርነቀል የለውጥ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርገው የትምህርት ስርዓቱን እና የትውልዱን ሥብራት ሊጠግኑት ይገባል፤መምህራኑ ከምሁርነት መንበራቸው፤ ተቋማትም ከክብራቸው ይመለሱ እንላለን።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን