አዳማ፡- በጠመንጃ አፈሙዝ ሕዝብን በማስፈራራትና በማስገደድ ስልጣን ለመያዝ መሞከር የማይታሰብና ኢ-ሕገመንግሥታዊ ድርጊት መሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ የክልሉን መንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በየአካባቢው ያለውን የሕዝቡን ችግር መፍታት የሚቻለው በጠመንጃ ብቻ ነው›› ብሎ የሚያስብ ኃይል ካለ የክልሉ መንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራውን በተጠናከረ መንገድ እንደሚያከናውን ተናግረዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነና የማግባባትና የእርቅ ስራው እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አባ ገዳዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሐይማኖት መሪዎችንና የኦሮሞ ምሁራንን በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል። የፀጥታ መደፍረስ ችግሮችን የመፍታት ስራው ሕዝቡንና የፀጥታ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ክልሉን በገጠር በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ክላስተሮች ለይቶ ለመምራት የተሰራው ሥራ ክልሉን በተገቢው መንገድ ለመምራት ያስቻሉ እንደሆነ ተገምግሟል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ለቡና ልማትና ግብይት፣ ለገጠር የፋይናንስ ስርዓት ዝርጋታ፣ ለብድርና ቁጠባ አገልግሎት ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
የሰው ኃይልን አደራጅቶ ወደ ሥራ ከማስገባትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ በማጠናከርና በማደራጀት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ ጌታቸው ጠቁመው፤ ‹‹ለውጡ ሕዝቡን ያሳተፈ፣ ሕገ መንግሥታዊና ፓርቲው እየመራው የሚገኝ ሲሆን፤ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ውስንነቶችን ለማረም አቅጣጫ ተቀምጧል›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
ዘላለም ግዛው