ዲላ፡- ዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ “ጥምር ተግባር ለሰላም̕̕ ̕ በሚል መሪቃል በደቡብ ክልል ጌደኦና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሰላም ግንባታ ፕሮጀክቱን አስጀመረ።
በትናንትናው እለት በዲላ ከተማ በይፋ የተጀመረው የሰላም ፕሮጀክት ቀደም ሲል በሁለቱም ክልል ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሲሆን፤ 18 ወራትን የሚዘልቅና ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ እንደሆነ ተነግሯል።
የዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ ይስሀቅ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ችግር የተፈጠረባቸውን ቦታዎች ለይቶ ሰላምን ማምጣት በሁለቱም ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን እርቅ ማጠናከር፣ አቅም እንዲኖረውና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ነው።
አቶ ኢዮብ ፕሮጀክቱ በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና የመንግሥት ተቋማት መያዙን ፣ በተለይ ወጣቶች በሰላም ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ ለ 675ቱ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና ከእነዚህ መካከል 135 የሚሆኑት የሰላም አምባሳደር በመሆን ተጨማሪ ስልጠና እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩልም የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰቡ መሪዎች የሁለቱም ክልል ህዝቦች በትብብርና በእርቅ የበለጠ እንዲሰሩ ጠቁመው ማህበረሰብ ተኮር እቅዶች በአገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት፣ በግብረሰናይና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የግጭት አፈታትን የማጎልበት ሥራ አንደሚሰራና በዚህም ውጤት እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።
ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን በአካባቢው ካሉ ሌሎች ፕሮጀክቶች ልምድ በመውሰድ እንደሚሰሩ አቶ ኢዮብ የተናገሩ ሲሆን ሁለቱም ህዝቦች የሚያመሳስላቸው የጋራ ታሪክ በመውረሳቸው ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
ይህ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ቀናት በጉጂ ዞን እንደሚጀመር በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህ መድረክ ላይ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ውይይት አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
ሃይማኖት ከበደ