የፈጠራና የምርምር ግኝቶችን በመጠቀም የሰውን ልጅ አኗኗር ሊያቀሉና ሊያቀላጥፉ በሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ማተኮር እጅግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም፤ ለአዳዲስ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ትኩረት በመስጠት የህብረተሰቡን ችግር ከስር ከመሠረቱ የሚቀርፉ ግኝቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ በሀገራችን የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ስርዓት ባለው መልኩ በማበረታታትና በመደገፍ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ሊበረታቱ ይገባል። በዚህ ፅሁፍ በ2011 ዓ.ም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምርና በፈጠራ ስራዎቻቸው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆኑት መካከል የፈጠራ ባለሙያና ተማሪ ኢፋባስ ቶለዋቅን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፤
በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት የማስተርስ ተማሪ የሆነው ኢፋባስ ቶለዋቅ ለገጠመው ችግር መፍትሔ ለማግኘት ከለጋነት እድሜው የጀመረው የፈጠራ ጥንስስ መነሻ ሆኖት የተለያዩ ፈጠራ ስራዎች መስራት አስችሎታል። ተወልዶ ካደገበት የገጠር መንደር ውሃ ለመቅዳት ወደ 40 ኪሎ ሜትር ከመጓዝ በላይ፤ ውሃ ከጉድጓድ ለማውጣት ባለው አዳጋች ስራ በመፈተኑ፤ ከወንድሞቹ ጋር በመሆን ውሃውን ከጓድጓድ የሚያወጡበትን መሳቢያ(ፑል) ሰራ። ለዚህ ስራው አጋዥ የሆኑት እናቱ በስራው እንዲገፈ ያበረታቱት ነበር። ኢፋባስም ከእናቱ ባገኘው የሞራል ድጋፍ በመነሳት በዙሪያው ላሉ ሌሎች ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ተለያዩ ፈጠራዎች መስራቱን ይናገራል።
የፈጠራ ስራዎች
የኢፋባስ ቶለዋቅ የፈጠራ ስራ የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ሊያቀልልና ሊያቀላጥፍ የሚችል፤ በቢስክሌት (ሳይክል) የሚሰራ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ነው። ይህ ማሽን 24 ሰዓት ይሰራል። ሩቅም ይሁን ቅርብ፤ ሰው ባለበት አካባቢ ሁሉ በማንቀሳቀስ ሊሰራ ይችላል። በተጨማሪም፤ የበረሃ አካባቢ አየር ማቀዝቀዣና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ እና ሌሎችንም በርካታ የፈጠራ ስራዎች ሰርቷል።
የፈጠራ ስራው ያስገኘው እውቅና እና ሽልማት
የፈጠራ ባለሙያው ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ አንደኛ በመውጣት በኮሌጁ እንዲሁም በ2011ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማትና የእውቅና ሰርተፈኬት አግኝቷል ።
የፈጠራ ስራው ውጤት ለየት የሚያደርገው
ኢፋባስ ስለ ልብስ ማጠቢያው መሳሪያ ሲገልጽ በአካባቢያችን ካሉ ያገለገሉ ቁሳቁሶች መስራት የሚቻል በመሆኑ፤ በገበያ ላይ ካለው ጋር በዋጋ ሲነጻጸር ተመጣጣኝ ነው። ለጤናም ከፍተኛ ጥቅም አለው። ምክንያቱም ልብሱን የሚያጥበው ሰው ቢስክሌቱን እየነዳ ልብሱን በሚያጥብበት ጊዜ ለራሱም እንቅስቃሴ ያደርጋል። በተለይ፤ በኮሌጅና በጤና ተቋም አካባቢ በየእለቱ ብዙ ልብስ ለሚያጥቡ እናቶች ድካም ይቀንሳል። በልብስ አጣቢነት ሙያ ለተሰማሩ ሰዎች ማሽኑን ወደሚፈልጉበት ቦታ ድረስ ማጓጓዝ ይችላሉ። ውሃና ሳሙና ከመቆጠብ አንጻርም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይናገራል ።
የፈጠራ ስራዎቹ ጠቀሜታ
ማሽኑ የተለያየ መጠን ያለው ሲሆን ልብስ በቀለም በመለየት በአንድ ጊዜ ከ10 እስከ 12 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ወይም ከ30-40 የሚደረሱ ልብሶች ያጥባል። ልብሶቹ በሚታጠቡበት ጊዜ እንዳይበጣጠሱ የሚጠበቅ መሳሪያ በውስጡ የተገጠመለት ሲሆን፤ ውስጣዊና ውጫዊ ሲሊንደሮች አሉት። ውስጣዊው ሲሊንደር ልብሱ የሚገባበት ሆኖ ሌሎች ቀዳዳዎች ያሉትና ከውጫዊው ሲሊንደር ውሃ በመውሰድ ልብሱን በማሸት ቆሻሻ እንዲለቅ ያደርጋል።
የልብሱ አስተጣጠብም ሶስት ሂደቶች ማለፍ ይጠበቅበታል። የመጀመሪያው፤ ውሃና ልብሱ ከተገናኛ በኋላ ቆሻሻ በሚወጣበት መስመር ላይ በማከማቸት፤ ሁለተኛው ፈሳሽ ሳሙና በማስገባት ለሶስት ወይም ለአራት ደቂቃ ሳይክሉን በመንዳት ማሸት ነው። የማሽኑ ፍጥነት ከፍተኛ ስለሆነ ብስክሌቱ ከአራት ደቂቃ በላይ ከተነዳ ልብሶቹ ሊቆራረጡ ይችላሉ። በተጨማሪም፤ የውሃ ብክነት እንዳይኖር ውሃውን ወደሌላ ማቆያ ቦታ መውስድ ያስፈልጋል። ሦስተኛው ደግሞ፤ ሳሙናውን በማለቅለቅ ማውጣት፤ ልብሱን ማጽዳትና በፍጥነት በመንዳት መጭመቅ ነው፤ ከዚያም ልብሱን አውጥቶ ማስጣት ይቻላል። የልብሱ መጠን ብዙ ከሆነ በቀጣይ ዙርም በመጀመሪያ በተጠራቀመው ውሃ ማሸት እንደሚቻል ኢፋባስ ያስረዳል።
ያጋጠሙ ፈተናዎች
የፈጠራ ስራዎች ተግባራዊ ሆነው ወደ ህብረተሰቡ እንዲደረሱ በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ማበረታቻ የማድረግ ሀላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል።
የኢፋባስ ህልም የፈጠራ ስራውን ለህብረተሰቡ በማድረስ ችግር ማቃለል የነበር ቢሆንም፤ ያጋጠመው የፋይናንስ ችግር፤ አበረታችና ደጋፊ አካል ማጣት ስራዎቹን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አላስቻለውም። በዚህ ረገድ ኢፋባስ የፈጠራ ስራዎቹን ለሌሎች ለማስተላለፍ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች ቢያንኳኳም ምላሽ አለማግኘቱን ይናገራል።
“ሀገራችንን በቴክኖሎጂ ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ከሚሰጠው ሽልማት በላይ ባለሙያው ለሀገር የሚጠቅሙ ስራዎችን እንዲሰራ መደገፍ ይገባል።” የሚለው ኢፋባስ፤ በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችን ለማበረታቻ የሚደረገው ጥረት ውስን በመሆኑ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ትኩረት መስጠት እንደልባቸው ይጠቁማል።
የዝግጅት ክፍሉም፤ እንደ ኢፋባስ ያሉ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል እንዲሰሩ ማበረታታት፤ የፈጠራ ስራዎች መሬት ላይ ወርደው ፍሬ እንዲያፈሩ ማገዝ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ተገቢ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም፤ የፈጠራ ባለሙያዎች ስራዎቻቸው ጥቅም ላይ ውለው፤ የህብረተሰቡን ኑሮ እንዲያቀልሉና እንዲያቀላጥፉ፤ እነርሱም በቀጣይ የተሻሉ ነገሮች እንዲፈጥሩ ማበረታታት ተገቢ መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
ወርቅነሽ ደምሰው