እንደ ግለሰብ ሁሉ ቡድንም፣ ማሕበረሰብም፣ ኅብረተሰብም ሆነ ሀገር በአንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች በመፋዘዝ ውስጥ የሚዘፈቁባቸው አጋጣሚዎችና ምክንያቶች በርካታ ሲሆኑ የድብርቶቹ ዓይነትም ዥንጉርጉር ናቸው። በውጤቱም የተነቃቃ መንፈስ በቅዝቃዜ በረዶ ይርዳል፣ የነቃ ህሊናም ያሸልባል። የመፋዘዙ አጋጣሚዎች የመብዛታቸውና የመዥጎርጎራቸውን ያህል በጉዳዩ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች አናሳነትና የተጠኑትም ቢሆኑ በአግባቡ ተግባር ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ ብዙ ጉዳዮች ጉድና እንቆቅልሽ እንደሆኑ ዘመናት ተቆጥረዋል።
በየትኛውም መልኩ ቢሆን ግን ድብርት መንፈስንና ቅስምን እንክትክት አድርጎ መስበሩ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። የሀገርን መፋዘዝ በተመለከተ ለጊዜው አንዳንድ የጋራ ጉዳዮችን ብቻ መዘን ጥቂት የንባብ ቁዘማ እናድርግ። በኅትመት ጥራዝ ውስጥ ከታጨቁ የምርምር ወጤቶችና ፖለቲከኞች ወይንም የማሕበረሰብ ተመራማሪዎች ከሚሰጡት ትንተና ይልቅ ለጸሐፊው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው “ሀገር (መሬት) ሲያረጅ መጭ ያበቅላል” የሚለው ሀገራዊ አባባል ነው።
ሀገር (መሬት) እንደ ሰው ሊያረጅ የሚችለው በምን ምክንያት ነው? እንደምንስ ድብርትና መፋዘዝ ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል? መጭ ያበቅላል መባሉስ በምን ምክንያት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ብዙ ነገሮችን ይቆሰቁሳሉ። ብዙ ጥናቶችንም ይጠይቃሉ።
“መጭ” ከአካባቢ አካባቢ ትርጉሙ ካልተለያየ በስተቀር ኑግ መሰል የአረም ዓይነት ነው። በርቀት ሲመለከቱት ለምለም ሣር ይመስላል። የተመቸውን የመጭ ዛላ ቀርበው ሲያዩትም ከጤፍ አዝመራ ጋርም ይቀራረባል። ጦም ባደረ መሬት፣ ሞፈር ባኮረፈበት ማሳ፣ የአካባቢው ነዋሪ በስደት በለቀቀው “ነጻና እርቃናም መሬት” ላይ የሚበቅለው መጭ በተፈጥሮ ሕግ ታዞ መብቀሉ ግድ ቢሆንም ዛላውና ፍሬው ለምንም አይረባም። አይዘመር፣ አይወቃ፣ በጎተራ አይከተት፣ አይሰለቅ፣ አይጋገር እንደው ከንቱ ነገር ነው። እርግጥ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ለምጣድ ማሰሻነት ሲውል ይስተዋላል። ምድር ሲያረጅ የሚያበቅለው ይህንን ነው። የአባባሉን ሰምና ወርቅ ዝቅ ብለን በቅደም ተከተል እንነካካለን።
ከገራገሩና ከመልካሙ ሃሳብ እንጀምር። የሀገር መንፈስ የሚነቃቃባቸው በርካታ ምክንያቶችን መደርደር ቢቻልም የጋዜጣው የወርድ ስፋት ስለሚገድበን አንዳንዶችን ብቻ እንጠቃቅስ። ትልቁ የሀገር እስትንፋስና የመረጋጋት ምልክቱ የሰላም እሴት መረጋጋጥ ነው። ሰላም ያለው ሀገር፣ በተረጋጋ ሕዝብ የተባረከ ምድር ተፈጥሮና ሳር ቅጠሉ ይዘምርለታል። ዓየሩና ዕፅዋቱ በሃሴት መዓዛ ይታጠናል። የቤትና የዱር እንስሳት በየመስካቸው፣ በየጋጣቸውና በየግዛታቸው በሃሴት ይፍነከነካሉ። እንደ አፈጣጠራቸውም ያንቧሉ (እንቧ እያሉ ድምጻቸውን ያሰማሉ)።
ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነው የሚለው ፍልስፍና እንደተጠበቀ ሆኖ በዚያ የሰላም ምድር የሚኖረው ብዙው ባለሀገር አንደበቱ የሚያፈልቀው ዝማሬን ነው። ቁዘማን ስሜቱ ይጠየፈዋል። ህልሙና ቅዠቱ ከእለት ጉርሱ፤ ከዓመት ልብሱ ስጋት ነፃ የሆነ ነው። ለራሴ ምን እበላለሁ፣ ለልጆቼስ ምን አጎርሳለሁ ብሎ በመጨነቅ ፈጣሪውን በእለት እንጀራ ተማፅኖ ፋታ አይነሳውም። ዓመት በዓሉ ይደምቃል፤ ዐውዳመቱም ይናፈቃል። ሕጻናቱ በደጃፋቸው ሲቦርቁ፣ ወጣቶች በሠፈር ሲንጎማለሉ፣ አረጋውያን የዕድሜያቸውን ጀንበር በእረፍት ሲሞቁ፣ ጎበዛዝት ለሥራ ሲተጉ፣ ነጋዴውና አርሶ አደሩ በስኬት ሲፍነከነኩ፣ የእናቶች እልልታ ጎልቶ ሲደመጥ ያኔ ሀገርም አብራ ትስቃለች። ወንዞችና ተራሮች በቋንቋቸው ያሸበሽባሉ፤ ፀሐይና ጨረቃ ይፈነድቃሉ። ይህንን መሰል ሕዝብ ያለው ሀገር የሚያስበው ለራሱና ለሕዝቡ ነፍስ ብቻ ሳይሆን እጆቹን አስረዝሞ የሚታደገው መከራና አሳር ያደቀቃቸውን የዓለም ዜጎች ጭምር ነው።
ሀገሬ አድምጭን፤ መሪዎቻችንም አድምጡን፤
ሀገሬ ተፋዛለች። ተስፋችን ጠውልጓል። ልጆቻችን በምሬት፣ አዛውንቶቻችን በፀፀት እየተከዙ ነው። እናቶች በስቅቅ አጥንታቸው እየተፋቀ ነው። ምሬታችን አየሩን ሞልቶታል። ስለ ዛሬ እንጂ ነገን ተስፋ አድርጎ መኖርም ብርቅ ሆኖብናል። ሀገሬ መጭ ማብቀል ከጀመረች ሰንብታለች። መፋዘዛችን እስከ አድማስ ጥግ ደርሷል። ይህንን መሰል ሀገራዊ ዛሬነታችንን የምሄሰው በቀቢፀ ተስፋ ውስጥ ተዘፍቄ አንባቢውም በተስፋ እጦት እንዲሸበር ከመፈለግ ምኞት አይደለም።
ቀቢፀ ተስፋነትን የምጠየፈው አጥብቄ ነው። ሟርተኛነትም አሟራቹን ራሱን እንደሚገድል የገባኝ በዕድሜዬ ማለዳ ላይ ነው። የሀገሬ ወቅታዊ ጉዳይ ግን ከማሳሰብ ደረጃ አልፎ ወደማቃዠት ስላሸጋገረን እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ለማደር መጨከኑ ግድ ይመስለኛል። ስለዚህም የሚመሰገን ሀገራዊ ስራ ሲሰራ ማድነቅ፤ የጎደለው እንዲሞላ መምከር፣ የተበላሸው እንዲቃና መሄስን ብዕሬ እንዲለማመድ ያደረግሁት በዓመታት ውስጥ ፈተናን ተቋቁሞ እንዲያልፍ አለማምጄው ነው።
ሁሉም ኖሮን ሁሉንም ያጣን ሕዝቦች ሳንሆን የቀረን አይመስለኝም። ክፋትና እብሪት አየራችንን ከበከለው ሰነባብቷል። የፖለቲካው ትርምስ ሀገራዊ ሰላማችንን አናግቶብን ጥላ ወጊ ሆኖብናል። ከወዲያም ሆነ ከወዲህኛው ወገን የፖለቲካ ማሊያ ለብሰናል ብለው በዲሞክራሲ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ገመዱን የሚጓተቱት አብዛኞቹ ቡድኖች ለበጎነት እያዘጋጁንና እያስተማሩን ሳይሆን ብሽሽቅና ስድብ እየጋቱን መሆኑን ተረድተውት ይሆን።ቋንቋቸው ስሜት ይፍቃል። መወራጨታቸው ያሳቅቃል። ዛቻቸው ያስደነብራል። ፉከራቸው ያስበረግጋል። ስብዕናቸው ያሳፍራል። ድርጊታቸው ያበግናል። ተክለ ፖለቲከኛነታቸው እንደ ወፍ ማስፈራሪያ (ጉራጌዎች አውከሬ ብለው እንደሚጠሩት) ማስካቸውን ለብሰው ሲታዩ ያስደነብራሉ። ስለዚህ ደንግጠን ፈዘናል። ሀገርም አዚም ወድቆባት ተክዛለች።
ነጋዴውንም ቀርበን እህ ብለን ብናዳምጠው የምሬት ሳግ እየተናነቀው ብሶቱን ሊዘረግፍልን ይችላል። እኛም ዜጎች ስለነጋዴው ተናገሩ ብንባል ብዙ የምንለው አለ። በንግድ ስራ ላይ ማጭበርበርና ማምታታት እንደ ባህል የተቆጠረበት ዘመን እንደ ዘንድሮ ታይቶ አይታወቅም እያልን ነጋዴውን በጅምላ ስናማ አይሰቀጥጠንም፤ እውነት ነዋ። በመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ ንጽህና ሲጠፋ፣ ህሊናን አፍቅሮተ ነዋይ ገሎ ሲቀብረው እያስተዋልን እንዴት ዝም እንድንል ይጠበቃል። ጠንከር አድርገን ከመሠረታዊ ጉዳይ እንነሳ እንኳ ቢባል እንዳቅሙ ሆቴል ለመብላት ደስተኛ የሚሆን ሰው ማግኘት ያዳግታል። የምግቡ ጥራት ብቻ ሳይሆን መጠኑም መዓት የገባ እያስመሰለባቸው ስለመሆኑ ለሆቴል ቀላቢዎቻችን ብንናገር በምን ሞራል ውሸት ልንባል እንችላለን። ቀድሞውንስ ቢሆን ብዙው ሰው ሆቴል የሚበላበት ገቢ አለው ብሎ ማመን እንደምን ይቻላል።
ግብር መክፈል ውዴታን የሚጠይቅ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ያለበትም ስርዓት ጭምር ነው። ነጋዴው ካተረፈው ላይ ቆንጥሮ በታማኝነት የግብር ግዴታውን ተወጥቶ መብቱን ማስከብር እንደሚገባ አጥብቄ አምናለሁ። ችግሩ ግብር መክፈልና ያለመክፈል ብቻ አይደለም። ሸቀጥ የሚሸመትበት የውጭ ምንዛሪ ከመንግሥት ካዝና መሟጠጡ ከተነገረ ውሎ አድሯል። ለአንዳንዶች ግን ከተለየ ምንጭና ሰንዱቅ የሚዘገን የውጭ ምንዛሪ እንዳለ መንገዱና አሰራሩ የገባቸው ጩልሌዎች ከባንክ ቤት ሲወጡ በሚያሳዩት ፈገግታ እንደምን ረጥበው እንደወጡ በቀላሉ መለየት አያዳግትም።
ተርታው ነግዶ አደር ወገን ራሱንና ቤተሰቡን ማኖር የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ አማራጭ ብሎ የወሰነው የንግድ ሱቁን ከርችሞ ወይንም ቁልፍ ሸጦ ዞር ማለት ብቻ ነው። እየተንፈራገጠ ያለውን ነጋዴ በእንብርክክ እያስኬደው ያለው ዋና ጉዳይ ያልሰራበትን ግብር እንዲከፍል መጠየቁ ብቻ ሳይሆን ተያያዥ የመስተንግዶና የአገልግሎት አሰጣጦችም በራሳቸው አግላይ፣ ደንታ ቢስነትና መንፈስን አዋኪ ናቸው።
በግብር ሰብሳቢው ተቋምና በነጋዴው መካከል መተማመንና መተዛዘን መቼ እንደሚለመድ ግራ ያጋባል። ችግሩና የሚያሳስበን ጉዳይ መንግሥትና ነጋዴው እስከ መቼ በሌባና ፖሊስ የልጆች ጨዋታ አባራሪና ተባባሪ ሆነው እንደሚዘልቁት ነው። ርህራሄ የታከለበት የዜጎችን ብሶት የማድመጥ ባህርይ በሀገሪቱ ሹማምንት ነፍስ ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ፈጣሪን መማጠን የዜጎች ውዴታ ሳይሆን ወቅቱ ራሱ ከማስገደድ ደረጃ ላይ አድርሶናል። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሀገሬ ፈዛ ቅንድቧን ጥላለች። ሕዝቡም የዕለት ጉርሱንና የገመና መሸፈኛ አልባሳቱን ማሟላት፣ የሌሊት መጠለያውን ማግኘት ተራራ የመግፋት ያህል ስለተገዳደረው ግራ ተጋብቶ በግርታ ስሜት ውስጥ ለመውደቅ ተገዷል። ብዙኃኑ የከተማ ነዋሪ ሕዝብ በዕለት ኑሮ ጣጣ ብቻ ሳይሆን ነጋ ጠባ ውሽንፍሩ እየበረታ ባለው የፖለቲካ ትርምስምስ ሳቢያ ድንግዝግዝ ባለ የተስፋ እጦት ሀሞቱ መፍሰሱን ከታዘብን ሰነባብቷል።
የዕለት ጉርስ አቅራቢ የሀገራችን አርሶ አደሮችም ቢሆኑ ሙሉ ጉልበታቸውንና መንፈሳቸውን ሰብስበው ተስፋ ያደረጉት በበሬዎቻቸው ጫንቃና በማሳቸው ላይ ብቻ እንዳልሆነ ተረድተናል። የፖለቲካው ነፋስ እያናወዛቸውና በመሃላቸው ሾልከው የገቡት አመጽ ቆስቋሾች እየጎተጎቷቸው ብዙዎቹ በውስጣዊ መረጋጋትና ጤና ማጣት የተነሳ የበሬዎቻቸውን ቀንበር ለመፍታትና፤ ኩርማን መሬታቸውን ለ“መጭ” አረም አሳልፎ እስከ መስጠት በመድረስ በግራ መጋባት ውስጥ የተከበቡ ይመስላሉ።
በብዙ ሀገራት ተሰምቶ የማያውቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንና የተማሪዎቻችን ወቅታዊ ህመም ከክፉ ወረርሽኝ በላቀ ሁኔታ ግራ ከማጋባት አልፎ ሀገርን ጤና ነስቶ ሕዝብንም አንገት አስደፍቷል። ልጅን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ልኮ ማስተማርና ማስመረቅ የወላጆች ኩራት መሆኑ ቀርቶ የስቅቅ ሰበብና መንስዔ ሆኖብናል። ልጆቻችን፣ ሀገሪቱና ወላጆች እኩል ታመን እያቃሰትን እንዳለን አለነው። ኢ ሰብዓዊ የሆነ የጠለፋ ድራማ የተከወነባቸው ሴትና ወንድ ልጆቻችን ደብዛቸውና ዱካቸው ጠፍቶብን የህልማችንም የእውናችንም ቅዠት ከሆኑ ወራት ተቆጥረዋል። ሀገር አቀርቅራና ቅዝዝ ብላ እያነባች ነው።
የሀገሪቱ ቢሮክራሲና አጠቃላይ ሲስተም ተንገራግጯል። ለእኛ ለተራ ዜጎች የፖለቲከኞች መላቢስ ዲስኩር ቁርስ፣ ምሳና እራታችን ወደ መሆን የተለወጠ ሲሆን ለፖለቲከኞቹና ለቢሮክራሲው ዘዋሪ ሹማምንት ደግሞ በእለት ተእለት እፎይ የማይባልበት የስብሰባ አዙሪት ቀለባቸውና እስትንፋሳቸው ሆኗል። ምድሪቱ አፍ አውጥታ ብትናገር አቤት የችግራችን አበዛዙ።
«ኧረ ጎበዝ ሀገር ተፋዛለች!” ብለን የምንጮኸው መፍትሔውን እንድንጠቋቆምና መላ እንድንዋዋስ እንጂ “አሉ ተባባሉ” ለመባባል አይደለም። ሀገር ፈዛለች። ሕዝብ ቆዝሟል። ኢኮኖሚው ተሽመድምዷል። ማኅበራዊ ትስስሩ ላልቷል። ሃይማኖታዊው ጉልበት ዝሏል። ሕግን ለማስከበር መንበር የተጎናጸፈውና ሰይፍ የታጠቀው መንግሥታችንም “ፋታ! ፋታ! ፋታ!” እያለ መማጠኑን ያበዛው ስለመሰለን ብንነግረውም፤ ብናማውም ወይ አልገባውም ወይ “ይጯጯሁ ምን እንዳያመጡ” ብሎናል አለያም እኛን ጯሂዎቹን ያልገባን ነገር አለ።
የሀገራችንን አየር የበከለው ፍዘትና ሕዝባችንን የተጫጫነው አዚም ስለሚገፈፍበት ጉዳይ ልብ ተቀልብ ሆነን መመካከር ያለብን ጊዜ አሁን ይመስለናል። ለብዙ ሀገራዊ ችግር መንስኤ የሆኑት ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ቆም ብለው የሚውገረገረውን አቋማቸውን ሊፈትሹ ይገባል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችም ከቻሉ በጥበብ ቢመሩ ካልሆነላቸውም ወደሚሆንላቸው መስክ ቢሰማሩ አይከፋም። ነጋዴውና “የባለሀብትነትን ክብር ለራሱ የሸለመው” የቱጃር ስብስብም ከኪስ ብልፅግና በፊት የወጣበትን ሕዝብ እያሰበ ሀብቱን እንዲያባዛ እንጂ “ግርግር ለሌባ ይመቻል” መርህን ባይከተል ይመረጣል። የሃይማኖት አበውና ቤተሰቦች ለቅዱሳት መጻሕፍታቸው ትእዛዛት ቢገዙ እንጂ ለአዋኪ ፖለቲከኞችና ቡድኖች ፊት ከመስጠት ቢታቀቡ የችግራችን ግዝፈት ሊቀንስ ይችላል። ጎበዝ! የተሰበረው የሀገር ቅስምና ግራ የተጋባው ሕዝብ ተረጋግቶ ይህንን ፈታኝ ጊዜ እንዲያልፍ ሁላችንም በእጃችን ላይ ያለውን መልካምና በጎ ዘር በምድሪቱና በተገኘንበት ቦታ፣ በተሰማራንበት የስራ መስክና ውሎ ሁሉ በመዝራት የእኛንም የቀጣዩንም ትውልድ እጣ ፈንታ እናሳምር። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com