በእንቅስቃሴ ወቅት የመፋጨት ድምፅ ሊኖር ይችላል
በዕለት ተለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ በድንገትና ባላሰብነው ሁኔታ ከመለስተኛ አደጋዎች እስከ ከባድ የአጥንት ስብራት ሊደርስብን ይችላል። የአጥንት መሰበር በፍጥነት ህክምና አግኝቶ እንክብካቤ ካልተደረገለት ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ ሊያመራ የሚችል ነው። በመሆኑም ስለአጥንት መሰበር የተወሰነ እንመልከት።
የአጥንት መሰበር በሁለት መንገድ ሊገጥመን ይችላል። አንደኛ፣ የቆዳ እና ሥጋ አካል ክፍላችንን ዘልቆ በመግባት የሚደርስ የአጥንት መሰበር ወይም የሚታይ ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ የተጎዳ ስጋችን እና አጥንታችን ከፍተኛ የጉዳት መጠን ይኖረዋል። በዚህ ጉዳት አጥንታችን፣ ስጋችንን ቀዶ ፈጦ ሊወጣ ይችላል። በእንዲህ ሁኔታ የሚፈጠር ቁስለት ኢንፌክሽን ሊፈጥር ስለሚችል የመዳን ሂደትን ሊያረዝም እና ሊያወሳስብ ይችላል። ለዚህ ችግር መጀመሪያ መደረግ ያለበት የተሰበረውን አጥንት ወደ ቦታው በመመለስ እንደ ሸምበቆ ወይም እንጨት ያሉ ቁሶችን ተጠቅሞ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ ማሰር ነው። ቁስለቱን እንደ ማንኛውም ቁስል በማፅዳት እና በንፁህ ጨርቅ በመጠቅለል ወደ ሕክምና እስከምንደርስ ድረስ መከታተል ነው። በዚህ መልኩ ዕርዳታ ያገኘ ተጎጂ እራሱን ከእንቅስቃሴ በመግታት ማገገም መቻል አለበት፤ አለበለዚያ ሁኔታው ሊባባስ ይችላል። ሁለተኛው ደግሞ የሰውነታችንን የሥጋ ክፍል ዘልቆ ሳይገባ ወይም ቁስለት ሳይፈጥር የሚገጥመን የማይታይ የአጥንት መሰበር ወይም መሰንጠቅ ነው። ሁኔታውን ለመረዳት ስዕሎቹን ተመልከቱ፤ በጉዳት ወቅት የሚከተሉት ምልክቶች የአጥንት መሰበርን ወይም መሰንጠቅን ሊጠቁመን ይችላሉ። አደጋው ባጋጠመን አካል ወይም ቦታ ላይ፡-
• ከፍተኛ ህመም
• በቆዳችን ላይ የሚፈጠር የቀለም ለውጥ
• እብጠት
• የቅርፅ ለውጥ
• ሰውነት አልታዘዝ ማለት
ስብራቶች በሚታከሙበት ወይም ወደቀድሞ ይዞታ ቸው ለመመለስ በሚሞከርበት ጊዜ የሕመም ስቃያቸው ከባድ ስለሚሆን፣ ተጎጂው ራሱን ስቶ የሚገኝ ከሆነ ሳይነቃ በፍጥነት ተስተካክለው መልክ ቢይዙ የሚመረጥ ነው። ስብራትን ለመደገፍ የምንጠቀማቸው የተለያዩ ቁሶች ሰውነት እያበጠ ሲመጣ ህመም ሊፈጥሩ ስለሚችሉ፣ ለስላሳ የሆኑ ነገሮች በገላና በመደገፊያዎቹ መካከል ብንጎዘጉዝ ሕመሙን ይቀንሰዋል። እንዲሁም የውጥረት መጠኑን ክትትል በማድ ረግ የደም ዝውውርን እንዳይገታ ማላላት ያስፈልጋል። ስብራት ተስተካክሎ አንዴ ከታሰረም በኋላ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ በደንብ መታሰር አለበት፤ ነገር ግን ምንጊዜም የደም ዝውውር ላይ ዕክል እንዳይፈጥር በመከታተል የማላላት እርምት መውሰድ መዘንጋት የለብንም።
የስብራት አደጋ ዋናው ችግሩ የሚያስከትለው ህመምና ስቃይ ከፍተኛ መሆኑ ነው። በተለይ ጉዳቱ በገጠመን ቦታ እና አካባቢው ላይ የሚገኙት የነርቭ ጫፎች፣ ትንሽ እንኳን ሲነኩ ከፍተኛ ህመም ይኖራቸዋል። በእንዲህ አይነት ችግሮች ውስጥ ያለ ሰው እንቅስቃሴን በፍፁም ማስወገድ አለበት። ሌላው የዚህ አደጋ ትልቁ ችግር፣ የሰውነት ውስጥ ለውስጥ ደም መፍሰስ ሊያስከትል መቻሉ ነው። ይህ ሁኔታ ከባድ በመሆኑ እራስን ሊያስትና የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል።
ስብራቶች እንዳይነቃነቁ አድርጎ ማሰር
ድንገተኛ ስብራት የገጠመው በእግር ላይ ከሆነ፣ ሙሉ የእግር መዋቅር ምንም እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተደርጎ በተለያዩ ቁሶች መታሰር አለበት። ምንም ዓይነት ቁስ በእጃችን ባይገኝ እንኳን ስብራት ካልገጠመው ጤነኛ እግር ጋር ድጋፍ እንዲሆነው ተደርጎ ተጣምሮ መታሰር አለበት። ስብራቱ ከገጠመው አካል በላይ እና በታች እንዲሁም መጋጠሚያ ጋር ንቅናቄን እንዳይፈጥር አድርገን ማሰር አለብን።
የአከርካሪ አጥንት ስብራት
አንድ ተጎጂ ወገቤን፣ አንገቴን፣ እግሬንና እጄን ማንቀሳቀስ አልቻልኩም እያለ የሚጮኸ ከሆነ እንዲሁም እግሮቹም ሆኑ እጆቹ ሲነኩ ስሜት አልባ ከሆኑበት፣ ምናልባትም የገጠመው የአከርካሪ አጥንት ስብራት ሊሆን ይችላል። አካሉን ስንነካው ምንም ካልተሰማው እና ምንም ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ እንዲሁም ጣቶቹን እንዲያንቀሳቅ ስንጠይቀው የማይችል ከሆነ ሁኔታው ከባድ ስለሆነ ምንም እንዳይንቀሳቀስ አድርገን የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት እስከሚችል ድረስ እንዲያርፍ ማድረግ አለብን። ጉዳተኛውን ወደ ተሻለ ቦታ መውሰድ ወይም የሕክምና ዕርዳታ ሊያገኝ ወደሚችልበት ቦታ ማጓጓዝ ካስፈለገ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤ እንዲህ ዓይነት ጉዳት የገጠመውን ሰው ስናጓጉዘው ምንም ሊያንቀሳቅሰው በማይችል አልጋ ወይም ቃሬዛ ላይ ጭነነው መሆን አለበት፤ ስንጭነውም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊለየን አይገባም።
አንድ ተጎጂ ወገቤን፣ አንገቴን፣ እግሬንና እጄን ማንቀሳቀስ አልቻልኩም እያለ የሚጮኸ ከሆነ እንዲሁም እግሮቹም ሆኑ እጆቹ ሲነኩ ስሜት አልባ ከሆኑበት፣ ምናልባትም የገጠመው የአከርካሪ አጥንት ስብራት ሊሆን ይችላል
አስታውሱ! በአጥንት መሰበር ምክንያት ቦታውን የለቀቀው አጥንታችን በትክክለኛው እና በቀድሞው ቦታ መግጠም ካልቻለ የእግር ማጠር፣ መርዘም እና መጣመም ሊከተል ይችላል፣ ሁኔታውን በየጊዜው በመከታተል የማስተካከያ ዕርምጃ ማድረግ ተገቢ ነው።
የአጥንት መሰበር በሁለት መንገድ ሊገጥመን ይችላል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012