ሰውነት በተፈጥሮ የሚገጥሙትን ጉዳትና አደጋዎች የሚቋቋምበትና የሚፈታበት የራሱ የሆነ ስርዓት አለው። ደም በደህናው ጊዜ በደም ዝውውር ስርዓት ውስጥ እና በደም ቧንቧዎች ውስጥ እየተዘዋወረ ይኖራል። ነገር ግን የደም ቅዳ እና ደም መልስ (አርተሪ እና ቬይኖች) በሚጐዱበት ጊዜ ደም መፍሰስ ይጀምራል። ይህ ፍሰት ወደ ውጪ አለዚያ ውስጥ ወዳሉት ህብረ ህዋሳት(ቲሹዎች) ሊሆን ይችላል።
ይህን የደም መፍሰስ በማቆም ወደ ጤነኛ ስርዓት የሚመልስበት ሄሞስታሲስ የሚባል ስርዓት በሰውነታችን ተጠናክሮ ይገኛል። በዚህ ሂደትም የደም መፍሰስ በሚገጥም ወቅት የተጐዱት የደም ቧንቧዎች ራሳቸውን በማጥበብ ፍሰቱን ለመግታት ሲሞክሩ ፕላትሌትስ የተሰኙት የደም ክፍሎች ደግሞ እርስ በእርሳቸው በመጣበቅ የተጠላለፈ ክር መሳይ ድር ይፈጥሩና ቀዳዳውን ለመድፈን ይጥራሉ። ደም የማርጋት ሂደቱም በዚሁ ይጀመራል። ይህ የማርጋት ሂደት እንደተጀመረ ከ20 የሚያንሱ ቅመሞችና ንጥረ ነገሮች በቅደም ተከተል ይነቃቁና ደሙን ለማቆም ሂደቱ ይቀጥላል። በስተመጨረሻም ፋይብሪን የተባሉ ክሮች ተፈጥረው የተጐዳው አካባቢ ጋር በመጠቅጠቅ ጉዳቱ እንዲድን ያደርጋል። የደም መፍሰሱ እንደቆመና ጉዳቱ እንደዳነ ክሮቹ ይሟሙና አጠቃላይ የደም ስርዓቱ ወደ ቀድሞው ጤናማ ሁኔታው ይመለሳል።
ይህን ጤናማ የደም መፍሰስን የማቆምና የማርጋት ሂደት የሚያቀላጥፉ በርካታ ንጥረ ነገሮች ያገኛሉ። ከማዕድናት ደግሞ ካልሲየም ተጠቃሽ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ችግር ደም ሲፈሰን ቶሎ እንዳይቆም፣ ይህን ተከትሎም ለሚመጡ በርካታ የጤና ችግሮች ይዳርገናል። ሁኔታው በቁጥጥር ስር ካልዋለ እስከሞት ለሚደርስ አደጋ መጋለጥ ዕጣ ሊሆን ይችላል።
ደማችን መፍሰሱን ለምን አያቆምም?
የደም መፍሰስ ለመቆም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ የማርጊያ ቅመሞች አለመኖር ወይም መጠናቸው ማነስ ሊሆን ይችላል። ለዚህ የቅመሞቹ ማነስ ወይም አለመኖር ሁለት ዋነኛ መነሻዎች ይጠቀሳሉ። በዘር ከወላጆች ችግሩን ይዞ መወለድ የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደም የማርጋት ስርዓቱን የሚያደናቅፍ ከውልደት በኋላ የመጡ የጤና ችግሮች ናቸው። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በቀይ የደም ህዋሳት እና ቧንቧዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የጉበት ህመሞች፣ የኩላሊት ችግር፣ የቫይታሚን ኬ እጥረት፣ የመቅኒ ችግር እንዲሁም እንደ አስፕሪን ያሉ መድኃኒቶችን አዘውትሮ መጠቀም ቀድመው ይነሳሉ።
የደም መፍሰስ ያለመቆም ችግር ያለባቸው ሰዎች ችግር ከልጅነት ሊጀምራቸው አሊያም ካደጉ በኋላ በአጋላጭ ምክንያቶች ሊታይባቸው ይችላል። የደም አለመርጋት ችግር እንዳለ ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል በትንሹም በትልቁም መድማት፣ የአፍንጫ በተደጋጋሚ መድማት፣ የተለያዩ የቀዶ ጥገናዎች ከተደረጉ በኋላ የደም ፍሰት ቶሎ ያለመቆም፣ የድድ መድማት በብዙዎች ላይ ይታያሉ። እነዚህም ምልክቶች ተደጋግመው ከታዩ ሐኪም ጋር ቀርቦ ሁኔታው ከደም ያለመርጋት ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ይመከራል።
ሄሞፊሊያ በተለይ በወንዶች
የደም ያለመርጋት ችግር ወይም ሄሞፊሊያ በተለይ የበርካታ ወንዶች ችግር ነው። በአብዛኛው ጊዜም በዘር የሚወረስ ነው። ይህ ችግር በዘረ-መል ወንድ ልጅ ከእናቱ ሊወርሰው በሚችል ጤናማ ያልሆኑ ዘረ-መሎች እና የማርጊያ ቅመሞች ማነስ ምክንያት ይከሰታል። በዚህ ችግር የሚጠቃ ሰው አፍንጫው ቢደማ ቶሎ አይቆምም፣ በትንሽ በትልቁ ይደማል። ይህ ሁኔታ በሴቶች የመከሰት ዕድሉ አነስተኛ የሚባል ነው። የዚህን ዘረ-መል ዓይነት ሴቶች ቢሸከሙትም ህመም የመሆን አጋጣሚ ግን የለውም። እጅግ በጣም ጥቂት ሴቶች ላይ አልፎ አልፎ ምልክቶች ሊታዩ ቢችሉም ለክፉ የሚሰጣቸው አይደለም።
ሄሞፊሊያ የተሰኘው ይህ በዘር የሚተላለፍና ወንዶችን በተለይ የሚያጠቃ የደም አለመርጋት ችግር ፋክተር 8 በተሰኘ የደም ማርጊያ ቅመም ማነስ ምክንያት ይከሰታል። ችግሩ በምርመራ ከታወቀም ይህንኑ ያጠረ ቅመም በመስጠት ሊታከም ይችላል። የደም አለመርጋት መገለጫ ከሆኑት ሁለት ዋነኛ ሕመሞች ሁለተኛው ደግሞ ቮን ዊልብራንድ የተባለው የሕመም ዓይነት ነው። ይህ ችግር የሚፈጠረው ቮን ዊልብራንድ ፋክተር የተሰኘው ቅመም በማነሱ የደም መርጋቱን ለመፍጠር የሚረዱ የሚጠላለፉ ክሮችን መሥራት ባለመቻሉ ነው። የዚህ ቅመም ማነስ ሰዎች በሚደሙ ወቅት ደሙ ቶሎ እንዳይቆም ያደርጋል። ችግሩ በሴቶች ሲከሰት የወር አበባቸው ላይ ችግሩ ይፈጥራል። የወር አበባቸውም ቶሎ አይቆምም።
የደም መፍሰስ ጠንቆች
የደም መፍሰስ ችግሩ በደም ማጣት ብቻ አይወሰንም። መቆም ያልቻለው ደም ፍሰት በአጭር እና ረጅም ጊዜ የተለያዩ የጤና ችግሮችንም ያስከትላል። ደም ያለመቆሙን ተከትሎ የሚከሰት ሞትም ያጋጥማል። ከደም ያለመርጋት ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ ችግሮች ጥቂቶቹም የመገጣጠሚያዎች ጠባሳ እና የመገጣጠሚያ በሽታዎች፣ በዐይን ውስጥ ከሚከሰት የደም መፍሰስ የሚነሳ የዐይን ብርሃን ማጣት፣ የደም ማነስና የነርቭ ችግሮች ናቸው።
የጥንቃቄ ዕርምጃዎችና የሕክምና መፍትሔዎች
ደም ለመርጋት መቸገር እና የደም በብዛት መፍሰስ ችግሮችን ለማወቅ ቀደም ብለው የተጠቀሱ ምልክቶችን አስተውሎ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። የችግሩ ዓይነት እና ዝርዝር ሁኔታዎች በጥያቄዎችና የደም ምርመራዎች ከተለየ በኋላ እንደየግለሰቡ ሁኔታ ተመጣጣኝ የሆነ መፍትሔ በሐኪሞች ይሰጣል። ከእነዚህ መፍትሔዎች መካከል ደም ለማርጋት አስፈላጊ የሆኑት ቅመሞች ማነስ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ቅመሞቹን ወደ ደም እንዲደርስ ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው። ከበድ ያለ የደም መፍሰስ ጉዳት ካለም የቅመሞቹን መጠን ከመተካትና ማሳደግ በተጨማሪ ደም መተካትም አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በሕክምና ከሚሰጡ መድኃኒቶች በተጨማሪ የየራሳችን ለጤናማ የደም ግብአቶች ልንወስዳቸው የሚገቡ ማዕድናትን የያዙ ምግቦች መመገብም መልካም ነው። በተለይም እንደ ካልሲየም እና ፖታሲየም ዓይነት ማዕድናትን የሚይዙ አረንጓዴ አትክልቶችና የወተት ተዋፅኦዎች ጠቃሚ ግብአቶች ናቸው። ዋናው ነገር ችግሩን በጊዜ ተረድቶ የባለሞያ ዕርዳታ በመፈለጉ ላይ ይሆናል።
የደም መፍሰስ ለመቆም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ የማርጊያ ቅመሞች አለመኖር ወይም መጠናቸው ማነስ ሊሆን ይችላል
የደም ቅዳ እና ደም መልስ (አርተሪ እና ቬይኖች) በሚጐዱበት ጊዜ ደም መፍሰስ ይጀምራል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012