የልጅነት ዕድሜውን የገፋው ቤተሰቦቹን በመታዘዝና በጉልበቱ በማገዝ ነው። ዕጣ ፈንታው ሆኖ በትምህርቱ ከአምስተኛ ክፍል በላይ አልተሻገረም። አበራ የቤቱን ችግርና የወላጆቹን እጅ ማጠር ጠንቅቆ ያውቀዋል። ወላጆቹ እሱን ጨምሮ እህትና ወንድሞቹን ለማሳደግ ራሳቸውን ሲጎዱ ኖረዋል።
ሞልቶ የማይሞላው ጓዳቸው ሁሌም ከችግር ጋር እንደቀጠለ ነው። በኑሮው በወጉ ተደስቶ የማያውቀው ቤተሰብ ዛሬን ጠግቦ ቢያድር ነገን በባዶ ተስፋው ማለምን ለምዷል። በቂ ጥሪትና እርሾ የለውምና የሩቅ ሃሳብና ዕቅድ ኖሮት አያውቅም ።
አበራ ዘወትር ስለወላጆቹ መብሰልሰል እንደሌለበት ካሰበበት ቆይቷል። ከዚህ በኋላ የራሱን ድርሻ ለመወጣት የበኩሉን ማድረግ ይኖርበታል። ከነሱ ጉያ ሳይርቅ የአቅሙን ለማበርከት የመጀመሪያ ምርጫው ደግሞ በእረኝነት መቀጠር ብቻ ነው።
ከስራው የሚገኘው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያም ሆኖ ከምንም እንደሚሻል አስቦ ከጀመረው ሰንበት ብሏል። አሁን የመንደሩን ከብቶች ከሜዳ አውሎ ሲመሻሽ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ጊዜው ደርሶ የድካሙን ሲቀበልም ያገኘውን ቆጥሮ ለቤቱ ጎዶሎ ያውላል።
እንዲህ እያለ ወራት አልፎ አመትን ተሻገረ። በዕድሜው መብሰል ሲጀምር ግን አእምሮው በርቀት አሻግሮ ማሰብን ያዘ። በእረኝነት ከሚገኝ ገቢ ብቻ ወላጆቹን ከመርዳት ራቅ ብሎ ቢሄድ የተሻለ እንደሚሆን አመነበት። ይህ ዕምነቱ ከምንም የተሻለ መሆኑን ለማወቅ ብዙ መልፋት አላሻውም።
ከዚህ ቀድሞ ከእነሱ ቀዬ ወጥተው ርቀው የተሻገሩ የአገሩ ልጆች ይዘው የተመለሱትን ሲሳይ ጠንቅቆ ያውቃል። በቂ ገንዘብ ቋጥረው ራሳቸውን ቀይረዋል። ጥሩ ስራም ይዘው ለሌሎች ተርፈዋል።
ወደመንደራቸው በመጡ ጊዜ አበራ ብዘዎቹን በጉጉት እያየ እነሱን ለመሆን ሲመኝ ቆይቷል። ያኔ በልጅነት እይታው ለእሱ ሁኔታቸው ሁሉ ድንቅ የሚባል ነበር። ልብስና ጸጉራቸው፣ ንቃትና ንግግራቸው ሁሉ ዛሬም ድረስ ትውስ ይለዋል።
ዘወትር እነሱን ባሰበ ቁጥር አንድ ቀን ባለፉበት መንገድ እንደሚከተላቸው እርግጠኛ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ቀን ደግሞ አሁን ስለመሆኑ ልቦናው ነግሮታል። አበራ ዛሬ እንደሌሎቹ በዕድሜ ልቆ በአካል በርትቷል። ከቀዬው ርቆ ያሻውን ሰርቶ ቢመለስ ደግሞ ከወላጆቹ ምርቃትን ያገኛል።
ከቀዬ መራቅ
አበራ ቀዬ መንደሩን ለቆ ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ዘለቀ። በስፍራው ሲደርስ ሲጠብቀው የቆየው የአጎቱ ልጅ ተቀበለው። ጥቂት ቀናትን በእንግድነት አሳልፎ ከተማውን ለመልመድ ላይ ታቹን ሲቃኝ ቆየ። ከብዘዎች ተግባብቶም መግቢያ መውጫውን አወቀ። ስራ ጀምሮም ገንዘብ መቁጠር ጀመረ።
ጥቂት ቀናት አለፍ ብሎ በእንግድነት የተቀበለው የአጎቱ ልጅ ከአንድ ዘመድ ቤት አደረሰው። ሰውዬው የጋራ ዘመዳቸው ነው። ከአንድ ጓደኛው ጋር የቤት ኪራይ ተጋርተው ይኖራሉ። ከአብሮ ኗሪ ጓደኛው ጋር ዓመታትን ሲዘልቁ መተዳደሪያቸው የቀን ስራ ሆኖ ቆይቷል።
ሁለቱም ሲደክሙ ውለው ማታ ሲገናኙ ወጪያቸውን እኩል ይጋራሉ። ያገኙትን በአንድ አቅርበው ‹‹ቸር አሳድረን›› ብለው ይጎርሳሉ። ይህን የሚያውቀው የአበራ ዘመድ ሁሉን አስረድቶ ከእነሱ ጋር እንዲኖር በነገረው ጊዜ እንጀራ ፈላጊው እንግዳ ደስተኛ ሆነ። ባልንጀራሞቹም አብሯቸው ቢኖር እንደሚፈቅዱ በሙሉ ልባቸው ገለጹ።
ሁለቱም አበራ አብሯቸው ለመኖር በተቀላቀላቸው ጊዜ አልተከፉም። እነሱን መስሎ መቀጠል ከቻለ ፍቅር እንደሚያሳድራቸው አሳምነው በደስታ ተቀበሉት። ከሁለት ወደሶስት ጨምረው ኑሮን ሲቀጥሉም ይከፍሉት የነበረው ኪራይ ቀነሰላቸው። ወጪያቸውም ከቀድሞው በተሻለ አንሶ ገንዘብ መቆጠብ ጀመሩ ።
ጓደኛሞቹ ቀሪውን ፍጆታ በስምምነት እየተጋሩ ቤት ጓዳቸውን አሟሉ። ሁሌም ሳሎናቸው በሳቅና ጨዋታ ደምቆ ያመሻል። የቀን ውሏቸውን እያወጉም ስለነገው ተስፋቸው ያወራሉ። አለፍ ብለውም የወደፊቱን እያቀዱ በሃሳብ ይሻገራሉ።
ሶስቱም በፍቅርና በሰላም ህይወታቸውን መምራት ቀጥለዋል። እንደትናንቱ ዛሬን በሰላም ሸኝተውም የነገውን ቀን በስራ ድካም ለማሳለፍ መዘጋጀቱን ለምደዋል። አንድ ቀን ከሶስቱ አንደኛው ያሰበውን ዕቅድ ለባልንጀሮቹ ተናገረ። በቅርቡ ሊያገባ እንደሆነና ለአዲሱ ትዳርም የብቻውን ጎጆ መቀለስ ግድ እንዳለው አሳወቃቸው።
ሁለቱ የባልንጀራቸውን ሃሳብ ባወቁ ጊዜ ደስታቸውን በፍቅር ገለጹለት። ሃሳቡን ደግፈውም ለትዳሩ ስኬት መልካሙን ሁሉ ተመኙለት። ከቀናት በኋላ ጎጆ ወጪው ጓደኞቹን ተሰናብቶ በሌላ ቤት ከባለቤቱ ጋር ተጣመረ።
ሁለቱ…
አበራ የቅርብ ዘመዱን ወደ ትዳር ከሸኘ በኋላ ኑሮውን ከቀሪው ጓደኛው ጋር ቀጠለ። ተከታዩን ህይወት በጥምረት የጀመሩት ባልንጀሮች እንደቀድሞው ሆነው ጎጇቸውን ሊያቀኑ ደፋ ቀናቸውን ያዙ። በ‹‹አንተ ትብስ እኔ ›› መተሳሳብም ቀናትን አሳለፉ። ጊዜው ሳብ ሲል ግን በጥንቃቄ የሚጋሩት የቤት ወጪ ይከብዳቸው ያዘ።
በእነሱ ትከሻ ብቻ አልገፋ ያለው የኑሮ ውድነት እያደር ማሻቀቡ ራስ ምታት ሆነባቸው። የአበራ የኑሮ አጋር ታደሰ ከቀድሞ ባልንጀራው ጋር በተለየ መከባበር ጊዜያትን አሳልፏል። የዛኔ አንዳቸው ሲቸገሩ ከአንዳቸው ተበድረው ጎጇቸውን ሞልተዋል። ደስታን በእኩል ተጋርተው ኀዘን መከራውን ተካፍለዋል።
ዛሬም ቢሆን በዚች ጠባብ ጎጀ ህይወት እንደነገሩ ቀጥሏል።አንዳንዴ ታደሰ ገንዘብ ከእጁ ባጣ ጊዜ ከአበራ እየተበደረ ጉዳዩን ይሞላል።አበራ ደግሞ አሁን በስራው የበረታበት ጊዜ ሆኗል። በላቡ ወዝ ያገኘውን እየቋጠረ ገጠር ላሉ ዘመዶቹ ይልካል። በአውደ ዓመትና በእረፍት ጊዜውም አምቦን ተሻግሮ ከቤተሰቦቹ ይከርማል።
አንድ ቀን አበራ ሁሌም እንደሚያደርገው ከእሱ የሚጠበቀውን የቤት ኪራይ ለመክፈል ገንዘቡን ቀድሞ በመቁጠር አዘጋጀ። ጥቂት አለፍ ካለ ሰላም የማይሰጧቸውን አከራይ ባህሪይ ያውቃል። ይህ ሲገባው ባልንጀራው አስኪመጣ ጠብቆ የድርሻውን ብር እንዲያዋጣ ጠየቀው።
ደባሉ ባልንጀራው ጥያቄውን በወጉ ካደመጠ በኋላ መልሶ ለእርሱ የ ‹‹ክፈልልኝ›› ጥያቄን አቀረበ። ለዚህኛው ወር የሚበቃ ገንዘብ ስለሌለው የእርሱን ድርሻ ጨምሮ እንዲሰጥለት ለመነው። አበራ ቅር እያለውም ቢሆን ‹‹እሺ›› ሲል ተስማማ። ጊዜው ደርሶ ብድሩን ሲመልስለትም ሊያደርገው ያሰበውን ከወዲሁ እያቀደ ሲብሰለሰል ቆየ።
ሚያዚያ 30 ቀን 2001 ዓም
የወሩ የቤት ኪራይ ክፍያ እየተቃረበ ነው። ያለፈውን ወር ሙሉ ኪራይ የሸፈነው አበራም ጓደኛው ቀኑን አስቦ የአሁኑን እንደሚከፍል ገምቶ የሚለውን ለመስማት ይጠብቃል። የሁለት መቶ ብሩን ብድር ጨምሮ የወሩን ኪራይ ማዋጣት የሚጠበቅበት ታደሰ በሃሳብ ከተዋጠ ቆይቷል። አሁንም በቂ የሚባል ገንዘብ ኪሱ የለም።
አራት መቶ ብር ከእሱ እንደሚጠበቅ በገባው ጊዜ ያለአንዳች ንግግር ዝምታን መርጧል። ዕለቱን ደሞዝ ስለመቀበሉ የሚያውቀው አበራ ደግሞ ጓደኛውን ከመንገድ ጠብቆ የኪራዩን ብር እንዲሞላና የተበደረውንም እንዲመልስ ጠየቀው።
ታደሰ የአበራን ቃል በሰማ ጊዜ ፈጥኖ ምላሽ ሰጠ። አንዳችም ገንዘብ እንደሌለውና አሁንም ኪራዩን አሟልቶ እንዲሰጥለት፣ እሱም ሁሉንም ገንዘብ በሚቀጥለው ወር እንደሚከፍለው አሳወቀው።
አበራ ታደሰ የተናገረውን በሰማ ጊዜ ውስጡ በንዴት ተናጠ። እልህና ብስጭት እያንጨረጨረው አፍጥጦ ተመለከተው። ስሜቱን መቆጣጠር ቢያቅተውም ደጋግሞ ስለገንዘቡ ጠየቀው። ታደሰ ከቀድሞ የተለየ ምላሽ አልሰጠውም።
በሁኔታው ብስጭት ያደረበት አበራ ትዕግስቱ ተሟጦ በእልህ ተንተከተከ። ደጋግሞ እጁን በእጁ እያፋተገ ገንዘቡን እንዲመልስ አፋጠጠው። አሁንም የተለየ ምላሽ አልተገኘም። አፍታ ቆይቶ ጥያቄና መልሱ ወደጭቅጭቅ ተለውጦ መካረር ላይ ደረሰ። ስምምነት ጠፍቶ ሀይለቃሉ ሲበረታ ሁለቱም ከነበሩበት ተለያይተው ለየቅል አመሩ።
ከሰአታት በኋላ አበራ ወደቤት ሲመለስ ታደሰ እንደቀደመው አወቀ። ወዲያው ለራት የሚሆን ወጥ ለመስራት መንጎዳጎድ ሲጀምር ጓደኛው ደረቅ እንጀራ ለማምጣት ወደመንደር ወጣ። ወጡ ደርሶ ራታቸውን ሲበሉ እንደቀድሞው በአንድ ገበታ ነበር።
ምሽቱን እንደተኮራረፉ ሆድና ጀርባ ሆነው ቆዩ። ታደሰ ያልተለመደው ቆይታ የተመቸው አይመስልም። በጊዜ ወደ መደመኝታ አምርቶ ጋደም ማለትን መረጠ። ጥቂት ቆይቶ መላ አካሉ ለዕንቅልፍ ተረታ። ይህን ያስተዋለው አበራ ደግሞ በኩርፊያ ያመሸው ህሊናው መንቃት ጀመረ።
አበራ የቀን ንዴቱ አልበረደለትም። ለዚህ ምላሽ ያሰበውን ለመፈጸም ደግሞ ከዚህ ሰአት የተሻለ ጊዜ እንደማይኖር አምኖበታል። ቀና ብሎ ወደ ታደሰ አስተዋለ። በከባድ ዕንቅልፍ እንደተዋጠ ተኝቷል። ትንፋሹን ውጦ ወደመኝታው አመራ። ዕንቅልፍ አልወሰደውም።
ከለሊቱ 9፡00 ሰአት
አሁን አበራ ያለ ዕንቅልፍ ሲቁነጠነጥ ከቆየበት መኝታው ተነስቶ ዳግም ባልንጀራውን መቃኘት ጀምሯል። አሁንም በጥልቅ ዕንቅልፍ ውስጥ ያለው ታደሰ አልተንቀሳሰም። ይህን ሲያውቅ ኮቴውን አጥፍቶ የታደሰን ልብሶች እየመረጠ በሻንጣ መክተት ጀመረ። ከጎኑ የሻጠውን ቢጫ ቢላዋ እየነካካም ያወለቀውን የቀን ልብሱን መፈተሸ ያዘ። አፍታ ሳይቆይ እጆቹ ከኪስ ቦርሳው አደረሱት።
ፊቱ በፈገግታ እንደተሞላ ቀና ሲል ታደሰ እየተገላበጠ መሆኑን አይቶ ተደናገጠ። የጨፈገገ ፊቱን በወጉ ሳይፈታ ከጓደኛው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ። በሆነው ንዴት የገባው አበራ በሁኔታው ላለመደንገጥ እየሞከረ በሩን ከፍቶ ወደ ውጭ አመራ።
ታደሰ በአበራ እጆች የገቡትን ንብረቶቹን እንዳየ በውስጥ ሱሪው ላይ ዥንጉርጉር አልጋልብሱን ደርቦ በፍጥነት ተከተለው። የውጭ በሩ ለመክፈት የሚታገለውን አበራን እምብዛም ሳይርቅ ደረሰበት።
ሁለቱ ዳግመኛ ሲፋጠጡ ታደሰ ንብረቶቹን ለማስለቀቅ መታገል ጀመረ። ንዴትና ድንጋጤ ያደረበት አበራ በቀላሉ ሻንጣውን ለመልቀቅ አልፈለገም። ወደኋላ እየገፈተረው እንዳይቀርበው ለማራቅ ሞከረ። የታደሰን ጉልበት እንዳሰበው መቋቋም አልተቻለውም።
የውጭ በሩን ከፍቶ ለመውጣት መታገል የቀጠለው አበራ ከታደሰ ከባድ ትግል ገጠመው። ከዚህ በኋላ መታገስ እንደሌለበት ውስጡ ሹክ ይለው ጀመር። ጊዜ አልፈጀም። በጉኑ የሻጠውን ስል ቢላዋ አንስቶ ከታደሰ ግራ ጡት ላይ መሰገው።
ታደሰ የደረሰበትን ጥቃት መቋቋም ተስኖት ወደኋላው ተዘረጋ። ባለበት ሆኖም ጭንቅ በተሞላበት ድምጽ የድረሱልኝ ድምጽ አሰማ። ጩኸቱን ሰምተው ከወደቀበት የደረሱት ግቢው ነዋሪዎች አበራ በአጥሩ ዘሎ ሲያመልጥ ተመለከቱ።
የፖሊስ ምርመራ
ስለድርጊቱ መረጃ የደረሰው ፖሊስ ከስፍራው ሲደርስ የታደሰ ህይወት አልፎ ነበር። መረጃዎችን አሰባስቦና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ የሟችን አስከሬን አነሳ። በቂ የቴክኒክ ምርመራዎችን ከማስረጃዎች አዋህዶም የጥንቃቄ ርምጃውን ቀጠለ። የድርጊቱ ፈጻሚ ማንነት ቢጠረጠርም በወቅቱ ለመያዝ ባለመቻሉ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ እንቅስቃሴው ተጀመረ።
አበራ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ማለዳውን ወደ አውቶቡስ ተራ አምርቶ ወደ አምቦ ከተማ አቀና። ለአንድ ቀን አልጋ ይዞ በማደርም በደላላ አገናኝነት ወደ ፊንጫ ለስራ ተጓዘ። ይህን ከማድረጉ በፊት የሟች ጓደኛውን ልብሶች በሶስት መቶ ሃምሳ ብር ሸጣቸው። ለስራ ባመራበት ስፍራ ግን እምብዛም አልቆየም። በጥርጣሬ ሲቃኙት ከነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ በመውደቁ ለህግ ተላልፎ ተሰጠ። በወቅቱ የሟች መታወቂያና ፎቶግራፉ በኪሱ ነበር።
የአዲስ አበባ ፖለሱ መርማሪ ረዳት ሳጂን ሲሳይ በላይ በየጊዜው በመዝገብ ቁጥር 1093 /09 ላይ የሚያሰፍረው ሪፖርት በተጠርጣሪው መያዝ መጠናቀቁን እንዳወቀ ጉዳዩን ወደ ዓቃቤ ህግ አሳልፎታል። ዓቃቤ ህግም አስፈላጊ መረጃዎችን አጠናክሮ ለመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለፍርድ ቤት እንዲደርስ አድርጓል።
ውሳኔ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሹ ላይ የቀረቡ የሰው፣ የህክምናና የሰነድ ማስረጃዎችን አጣርቶ ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል። መጋቢት 18 ቀን 2001 ዓም በዋለው ችሎትም በአበራ ዋቅጋሪ ላይ የአስራ አምስት ዓመታት ጽኑ አስራትን በመበየን ዶሴውን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
መልካምስራ አፈወርቅ