በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕትመት የሚበቁ በርካታ የምርምር ሥራዎች አሉ። ነገር ግን በሥራ ላይ የሚውሉ የምርምር ሥራዎች አሉ ወይ? የሚለው ከመሪ እስከ ተመሪ ሲያነጋግር ይደመጣል። በየዓመቱ ከተለያዩ ተቋማት ተፈልፍለው በመደርደሪያ ላይ አቧራ ጠግበው የሚቀሩትንማ ተቋማት ራሳቸው ይቁጠሯቸው። ያወጡባቸውን ገንዘብ ማስላቱም የራሳቸው ሥራ ነው። የየትኛውም አገር እድገት በየዘርፉ በሚደረግ ጥናትና ምርምር ምርኩዝነት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ሲሆን መዳረሻ ውጤቱም ያማረ ይሆናል ሲሉም ምክረ ሐሳብ ይለግሳሉ።
በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ደግሞ ይነስም ይብዛ በየትኛውም ተቋም ለሚመዘገቡ ስኬቶችም ሆነ ውድቀቶች አስተዋጽኦ አላቸው ይላሉ። በዚህ መነሻነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋምን አስተዋጽኦ ለመቃኘት ሞክረናል።
ዶክተር በላይ ሐጎስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በትምህርት ረገድ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላለፉት 52 ዓመታት ተሰርተዋል።
ምን ያህል ምርምሮች ለሕትመት በቁ?
ኢትዮጵያ ውስጥ በእያንዳንዱ ተቋማት የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች አሉ የሚሉት ዶክተሩ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ክፍል በትምህርት ሳይንሳዊ መጽሔት ያሳተማቸው የምርምር ውጤቶች 40ኛ ቅጽ ላይ ደርሰዋል። በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም ሲሆን በእያንዳንዱ እትምም አምስት ጥናታዊ ጽሑፎች ይካተታሉ። በየዓመቱ በርካታ የምርምር ሥራዎች ይሰራሉ። ነገር ግን ሁሉም ይታተማሉ ማለት አይደለም። ያልታተሙትም ይወድቃሉ ማለት አይደለም። ለሕትመት የሚበቁት ምናልባትም ከሚሰሩት 20 በመቶ የሚበልጡ አይደሉም። ሂደቱ ራሱን በቻለ ኮሚቴ የሚከናወን ነው። መስፈርቱም ከአድሏዊ አሠራር የጸዳና መለያዎችን (ኮድ) የሚጠቀም ዓለም አቀፋዊ አሠራርን የተከተለ ነው። ስለዚህ ውድድሩ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በየዓመቱ ጥቂት የምርምር ወረቀቶች ለሕትመት የሚበቁበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በገለጻቸው፣ እነዚህ የምርምር ሥራዎች ቀላል አይደሉም። ባለፉት ጊዜያት ይታቀድ የነበረው ከአፍሪካ አስር ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ ለመሰለፍ ነበር። ይሄን ማሳካት ተችሏል። ለዚህ ስኬትም ለሕትመት የበቁ የምርምር ሥራዎች ብዛት የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረ አስረድተዋል።
የጥናትና ምርምር ሥራዎቹ በአብዛኛው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና፣በአጸደ ሕፃናትና ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲሁም በሥርዓተ ትምህርት(ካሪኩለም) ረገድ የሚያተኩሩ እንደነበሩ ዘርዝረዋል።
በተማሪዎችም (ለሁለተኛ ዲግሪ እና ለዶክትሬት ዲግሪ) መመረቂያነት በትምህርት ነክ ጉዳዮች በርካታ ጥናትና ምርምሮች ተሰርተዋል። ‹‹ኬኔዲ›› በተሰኘው የዩኒቨርሲቲው ቤተ መጽሐፍት ይገኛሉ፤ በዘመናዊ መንገድ በኤሌክትሮኒክስ ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
የምርምር ሥራዎቹ ምን ተጨባጭ ለውጥ አመጡ?
እንደ ዶክተር በላይ ገለጻ፣ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ያሉት 11 ተመራማሪዎች ብቻ ናቸው። በእነዚህ ተመራማሪዎች የተሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎቹ ያመጧቸው በርካታ ተጨባጭ ለውጦች አሉ። በየጊዜው በዘርፉ የሚታዩትን ውስንነቶች በመለየት ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች ተካሂደው በበቂ ደረጃም ባይሆን ለውጥ ማምጣት መቻሉን ያስረዳሉ።ለምሳሌ፡- የአገሪቱ የትምህርት ችግሮች ከሥርዓት የሚጀምሩ ናቸው። እነዚህ ችግሮች በጥናትና ምርምር ተለይተው እስከ ፖሊሲ የዘለቁ የመፍትሄ ርምጃዎች መወሰድ እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል። የ15 ዓመታት የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። በማዘጋጀት ሂደቱም አራት ተመራማሪዎች (ከአዘጋጆች 40 በመቶ እንደማለት ነው) ተሳትፎ ነበራቸው። የትምህርት ሥርዓቱ በአብዛኛው ትኩረቱ የትምህርት ዕድል በመፍጠር ላይ የሚያተኩር ነበር። በመማር ላይ፣ በትምህርት ላይ እና በእውቀት ላይ ያተኮረ አልነበረም ይላሉ።
እነዚህን ችግሮች በጥናትና ምርምር እያስደገፉ ከስር ከስር በመለየት በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጂት እየሰሩ ስለመሆኑ የሚገልጹት ዶክተሩ፣ ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የሥርዓተ ትምህርቱን ችግሮች በጥናትና ምርምር ለይቶ በመቅረፍ የተሳለጠ እንዲሆን የሚሰራው (RISE) የተሰኘ ፕሮጀክተር ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል። የምርምር ተቋሙ የሚደርስባቸውን ግኝቶች ለትምህርት ሚኒስቴር በማቅረብ መፍትሄ እያገኙ የሚሄዱበት አሠራር በመሆኑ ከዚህ በፊት ከነበረው ለየት ያለ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ መነሻም የችግሮች ዋናው ምክንያት የትምህርት ሥርዓቱ መበላሸት ነው የሚል ነው። ይሄ ሲስተካከል መማርና እውቀት ይስተካከላል የሚል እምነት ተይዞ እየተሰራ ነው፤ ሥርዓቱ ላይ ምን ቢስተካከል ነው መፍትሄ የምናመጣው በሚል ሰፊ ሥራ ይሰራል። ስለዚህ ትልቅ ለውጥ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
ሌላው የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በተመለከተ የተካሄደው ጥናትና ምርምር ይጠቀሳል። የዛሬ አስር ዓመት በጥናቱ መሠረት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተጠቃሚ ሕፃናት አራት በመቶ ነበሩ። በመሆኑም ሕፃናቱ ለመደበኛ ትምህርት ዝግጁ ሳይሆኑ አንደኛ ክፍል እንዲገቡ መደረጋቸው ስህተት መሆኑን አመላክቷል። በዚህ መነሻነት ዜሮ ክፍል ተጀመረ። አሁን ላይ 49 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽ ሆኗል። ጥናቱ ፖሊስ መቅረጽ ያስቻለም ነበር ብለዋል።
በትምህርት ሂደት ውስጥ ፈተና መፈተን ተጨማሪ ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች እንደሚሰጡም ተናግረዋል። ለምሳሌ፡-(GRE‚TOFL‚SAT‚SCA‚)የሚባሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች እንደሚፈትኑ አብራርተዋል። እነዚህ ፈተናዎች ደግሞ ውጭ አገር ሄደው ማጥናት ለሚፈልጉ ተማሪዎች ብዙ ዕድል ይፈጥራሉ።
በቅርቡም በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አቅም በምርምርና በሥልጠና ለመደገፍ (ሴንተር ፎር ሀየር ኢዱኬሽን ስቴዲስ) በሚል ተቋቁሞ ሥራ ሊጀምር መሆኑን ጠቁመዋል። ለሕትመት የበቁት የጥናትና ምርምር ውጤቶች በርካታ በመሆናቸው መንግሥት ሊጠቀምባቸው ከቻለ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። ለውጥም ያመጣሉ።
የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ ምን ይመስላል?
ዶክተር በላይ እንደገለጹት፣ የምርምር ሥራዎች የአያያዝ ሁኔታ ላለፉት ረዥም ዓመታት ምቹ አልነበረም። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በዘመናዊ መንገድ እንዲደራጁ ተደርጓል። ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በመደርደሪያ (ሸልፍ) ላይ የኖሩ የምርምር ሥራዎች ወደ ‹‹ኤሌክትሮኒክስ›› ተቀይረዋል። ሕትመት ከተጀመረበት ሰኔ 1967 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያሉ የምርምር ውጤቶች በ‹‹ሶፍት ኮፒ›› ተዘጋጅተዋል። ከ200 በላይ ይሆናሉ። ‹‹ኢንተር ኔት›› ባለባቸው ቦታዎች ሆነው በቀላሉ በእጅ ስልክ ጭምር ማግኘት የሚቻልባቸው መንገዶች መፈጠራቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ጆርናል ኦን ላየን (htt://ejol.aau.edu.et/) የመረጃ ቋት አማካኝነት የምርምር ሥራዎቹን ማግኘት እንደሚቻልም ነው የገለጹት። ዩኒቨርሲቲው አሠራሩን በማዘመን ተወዳዳሪ ለመሆን አልሞ እየሰራ ነው። ያም ሆኖ ግን ያሉት ተመራማሪዎች ውስን በመሆናቸው በቅጥር ለማሟላት ጥረት ቢደረግም በደመወዝ ስኬሉ ምክንያት መገኘት አለመቻሉን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን