ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ውበቷ በታሪክ ቅርስ በበርካታ ብሔር ብሄረሰቦች መገኛ በቱሪዝም አብቶቿ የምትታወቅ አገር እንደሆነች እሙን ነው። ከእነዚህ መካካል ባህል አንዱ እና ዋነኛው ነው። ባህል ሲባል በመሰረቱ እጅግ ክቡር ነው፤ የአንድ ህብረተሰብ ባህል በራሱ የህብረተሰቡ እንክብካቤ መጠበቅ መዳበር መሻሻልና የላቀ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት እሙን ነው። ባህልን የመንከባከብ ኃላፊነት የሚወድቀው ባለው ትውልድ ላይ ሲሆን እንክብካቤ የሚሹ መሆናቸውም እሙን ነው።
በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎች ታጅበው የሚደመጡት የሙዚቃ ዜማዎች እና እንቅስቃሴያቸው ቱባነታ ቸውን ሳይለቁ መቅረብ ቢኖርባቸውም በዚያው መጠን ባሉበት መዳከር እንደሌለባቸው አጠያያቂ አይሆንም።
እንደ ዋልያ እና እንደ ቀበሮ የመጥፋት አዝማምያ ላይ የነበረው ጥንታዊውና ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ በገና፤ በወጣቱ ፍቅርና ጽናት እያበበ መሆኑ እየተነገረለት ነው። በቤተ-መንግስት በመኳንቶች እና ሹማምንቶች ዘንድ እንደኖረ የሚነገርለት ጥንታዊውና ባህላዊ የዜማ መሳሪያ በገና፤ ተረስቶ ቆይቶ አሁን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ መነገሩንም በጀርመኑ ድምጽ “ዶቼ ዋሌ” አስነብቧል። በሀገራችን አሉ በሚባሉት በገና ደርዳሪዎች መካከል የበገና አባት እንደሆኑ በሚነገርላቸው በመጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ፤ ጽኑ የበገና ፍቅር ትውፊቱ ሳይዳፈን እስከዛሬ መቆየቱን ወጣቱ የበገና ደርዳሪ እንደመስከረም ዶቼ ቬሌ የብዙሃን መገናኛ ጠቅሷል።
የበገና ዜማ ልብን የሚነካ፤ ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት ራስንም ለማግኘት ጥቅም ላይ የሚውል ምስጋና ማቅረብያ የዜማ መሳሪያ ነው የሚሉንን ባለሞያዎች ይዘን ስለበገና ዜማ መሳሪያ ታሪክና ምንነት በጥቂቱ እንቃኝ! ስለ በገና ለማንሳት መንደርደሪያ የሆነን ወቅቱ ጥምቀት በመሆኑ ነው። እውቅ የሀገሪቱ ሹማምንቶች እና አገረ ገዥዎች ይጠቀሙበት ነበር። እጅግ የተከበረ፤ ትላልቅ ሰዎች ጋር የኖረም ነበር በገና ብለውናል፤ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ። በአጠቃላይ ከአምስት ሺ ስምንት መቶ ዓመት እድሜ በላይም ሆኖታል።
የሰውን ልጅ ስሜት የመግዛት ከፍተኛ ሃይል እንዳለው የሚነገርለት የበገና ድርድር በተለይ በጾም ወራት መደመጡ ለምን ይሆን? መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ ፤ በጾም ወራት እንዲሰማ የሆነው። በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አብይ ጾም ወቅት በራዲዮ ስለሚደመጥ ነበር እንጂ በገና ሁሌ የሚደመጥ ነው።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ስለ በገና በገዳማውያንም ዘንድ የተወደደና የተከበረ መሆኑ ነው የሚነገረው። ግን ኋላ ኋላ የመጥፋት አዝማምያ ገጥሞት በዓለሙ አጋ የበገና ፍቅር ጽኑነት፤ ዳግም ለትንሳኤ እንደበቃ ገልጿል። «በአገራችን አጼ ቴዎድሮስ በገና በመደርደራቸው ይታወቃሉ» በጾም ወቅትም ወደራስ የመመለሻም ጊዜ ስለሆነ ነው።
መምህር ሲሳይ በገና ይባላሉ፤ በገናን በመስራት በማስተማራቸው በገና የሚል መጠሪያን ማግኘታቸውን ይናገራሉ፤ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት መምህር ሲሳይ መጀመሪያ በገናን የሰሩት የዓለሙ አጋን ማስታወቂያ ተመልክተው መሆኑንም ነግረውናል። ዘመኑ የበገና ሆንዋል የሚለን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤ እንደገለጸልን፤ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት በገናን አፍቃሪ በመሆኑ በገና ድርደራን እየተማረ ነው። በገና በመጥፋት ላይ ነበር በገና ትንሳኤ እንዲኖረው ያደረጉት አለሙ አጋ ናቸው። ለበገና ያላቸው ፍቅር ጽኑ በመሆኑ ነው። አሁን አሁን ደግሞ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፤ ማህበረ ቅዱሳን፤ እንዲሁም አንዳንድ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች በ ገና ድርደራን በስፋት ያስተምራሉ።
በገና የዜማ መሳሪያ አመጣጥ መነሻው ከየት ይሆን? እንደ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ፤ ሁለት መነሻዎች አሉት የሚል አመለካከት አለ። «አንደኛው በገና ብለን የምንጠራው እኛ ራሳችን ኢትዮጵያውያኖች ስለሆንና፤ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ስለሆነች በገና የራሳችን ነው ወደ እስራኤል ከኢትዮጵያ ተወስዶ ነው የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በገናን ይበልጥ እንዲታወቅ ያደረገው ቅዱስ ያሬድ በመሆኑ፤ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ የንጉስ ሰለሞን አባት በመሆኑ እና በሰለሞን ስርወ መንግስት ጊዜ አብሮ ወደ ኢትዮጵያ መጣ የሚል እምነት አለ» ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤ መገኛው እስራኤል ነው ባይ ነው። «ከእስራኤል ነው በነዳዊት ነው እንደውም ዳዊት ነው ከፋፍሎ የበገና መዝሙር፤ የማስንቆ መዝሙር የጽናጽል የከበሮ እያለ መዘምራኑን ለአራት በአሰማራበት ጊዜ ነው ይበልጥ የታወቀው። በባቢሎን አካባቢም በገናን የሚመስሉ ምስሎች ተገኝተዋል። ከዝያ በኋላ የኦሪትን ቱፍት ስንወር አብረን ወርሰነው ኢትዮጵያዊ አድርገን ተጠቅመንበታል»
እንደበርካቶች እምነት በገና ደርዳሪ ወንዶች ብቻ ናቸው፤ ነገር ግን በገና ጾታ አይመርጥም የሚለን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመቀጠል፤ «በጥንት ግዜ ሁሉ ሴት በገና ደርዳሪዎች ነበሩ፤ አሁንም ቢሆን በገና ደርዳሪዎቹም ተማሪዎቹም በብዛት ሴቶች ናቸው። የጎንደርዋ እትዬ ምንትዋብም በብዛት የሚታወቁት በበገና ደርዳሪነታቸው ነው» ሌላዋ በገና ደርዳሪዎች ወንዶች ብቻ ናቸው የሚለውን እምነት አልስማማበትም የምትለን የበገና ድርደራ መምህርትዋ ወ/ት ገነት አለማየሁ፤ በምታስተምርበት የበገና ድርደራ ትምህርት ቤት የዘጠኝ ወር ኮርስ እንደሚሰጥ አጫውታናለች።
የበገና ግጥሞች ሀገራዊ፤ ሰምና ወርቅ፤ እንዲሁም ታሪካዊ በመሆናቸው፤ ሊጠበቁ ይገባል የሚሉን የበገና አባት መጋቤ ስብሃት አለሙ አጋ፤ በተለያዩ የአውሮፖ ሀገሮች ተዘዋውረዉው የበገና ድርደራቸውን አቅርበዋል። ወደጀርመንም ብዙ ግዜ ተመላልሰው በተለያዩ ከተሞች ዝግጅታቸውን አሳይተዋል። ከሁለት ወር በኋላም በኮለኝ ከተማ ከሌሎች ተማሪዎቻቸው ጋር በመምጣት ትልቅ ዝግጅትን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አጫውተውናል። የበገና ባህላዊ የዜማ መሳሪያችን ይላሉ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ፤ «በገና የመጸለያ ምስጋና የማቅረብያ እንደመሆኑ፤ በዚሁ መቀጠል አለበት እንጂ ከደንቡ ውጭ የመጠቀሙን ሁናቴ እንዲቆም በጥብቅ መከልከል አለብን።» ለዚህ ጽሁፍ ዶቼ ቬሌን ጨምሮ የተለያዩ በሙዚቃ መሳሪያው ላይ የተጻፉ መረጃዎች ተጠቅመናል፤ ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ