የልጅነት ጊዜ
አቶ ክፍሌ ስሜ ይባላሉ።የ78 ዓመት አዛውንት ናቸው።ተወልደው ያደጉት መርሃቤቴ ዓለም ከተማ ነው። በተወለዱበት አካባቢ በሚገኝ አንድ ደብር 14 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ የድቁና ትምህርት ተምረዋል።በኋላም አዲስ አበባ ኮልፌ አካበቢ በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።ትምህርታቸውን የተከታተሉትም በጄኔራል ታደሰ ብሩ ቤት በአሽከርነት እያገለገሉ ነበር።የያኔው ወጣት ክፍሌ በነበራቸው ቅልጥፍናና ትህትና በአሳዳሪዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበሩት ባለስልጣናት ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈዋል።ከመላላክ ጀምሮ ልብስ ማጠብ፥ አልጋ ማንጠፍና የባለስልጣናቱን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እስከማድረስ ድረስ በታማኝነትና በቅንነት አገልግለዋል።
ታማኙ አገልጋይ
ይህም መልካም ስብዕናቸውና ታታሪነታቸው ታዲያ በበርካታ ባለስልጣናት ቤት ውስጥ በአገልጋይነት እየተዘዋወሩ ለመስራት አስችሏቸዋል።በተለይም ራስ አበበ አረጋይ ቤት ለረጅም ዓመታት በአገልጋይነት የቆዩ ሲሆን የራስ አበበ ባለቤት ከልባቸው ይወዷቸው ስለነበር ቤተክርስቲያን እና አንዳንድ ግብዣዎች ላይም አብረዋቸው እንዲታደሙ ያደርጓቸው ነበር።የራስ አበበ አረጋይ ልጅ የሆኑትን ልጅ ወንድወሰን ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ድረስ ማድረስና መመለስም የአቶ ክፍሌ አንዱ የቀን ተቀን ተግባር ነበር።እንዲህ እንደዛሬ ቴክኖሎጂው ባልዘመነበት ጊዜ ሰዎች የሚጠያየቁት በመልዕክተኛ ስለነበርም አንዳንድ ጊዜ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር በመላክ ጭምር ልክ እንደእነሱ ሆነው ሰላምታ አቅርበው የሚመጡበት ጊዜም የበዛ ነበር።በዚህም ሳያበቃ አፈንጉስ ማቲዮስ የተባሉ የኤርትራ ገዥ ባለሟል የለኝም ብለው አቶ ክፍሌን በትውስት ለአንድ ዓመት የወሰዷቸው አጋጣሚም ነበር።
በራስ አበበ እና በሌሎችም ባለስልጣን ቤቶች አቶ ክፍሌ የነበራቸውን ቅልጥፍና ታታሪነትንና ትህትናን ያዩት ፊት አውራሪ ሃይለሚካኤል ፍልውሃ ድርጅት ውስጥ አስቀጠሯቸው።ሶደሬ በሚገኘው ፍልውሃ ድርጅትም በገንዘብ ያዥነት ቢቀጠሩ በነበራቸው የስራ ፍቅር የተነሳ ማዕድ ቤት ድረስ በመዝለቅ ሰራተኞችን በማገዝና ምግብ በማብሰል እንግዶቻቸውን ሳይሰለቹ ያስተናግዱ ነበር።በወቅቱ ጠብ እርግፍ ብለው ካስተናገዷቸውና ማዕድ ቤት ውስጥ ገብተው ምግባቸውን ካበሰሉላቸው ባለስልጣናት መካከልም አሃዱ ሳቡሬ፥ ታደሰ ሞገሴና አብዲሳ አለማየሁ ተጠቃሾች ናቸው።
የሶደሬው ገንዘብ ተቀባይ
ይህም የግለሰቡ ስራ ወዳድነትና ታታሪነት ታዲያ 30ብር የነበረውን ደመወዛቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ 75ብር ከፍ አስደረገላቸው።« በዚያን ጊዜ 20 ብር የሚከፈለው ሰው ቀለቡን ሸምቶ፥ እቁብ ጥሎ እንደልቡ ይኖር ነበር» የሚሉት አቶ ክፍሌ ዳሩ ግን በወቅቱ ለእሳቸው ይከፈል የነበረው ገንዘብ ለአንድ የመምህራን ኮሌጅ የሚከፈል ትልቁ ክፍያ እንደነበር አጫውተውናል።
ለፈረንሳይ ባለሟልነት ያሳጨው የማዕድ
ቤቱ ሙያ
በአቶ ክፍሌ መስተንግዶ እጅግ የተደመሙት ኮኔሪል ሃብተማርያም ስዩም ፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው ሲሾሙ ወደሚሄዱበት አገር ይዘዋቸው ይሄዳሉ።በፈረንሳይም የአምባሳደሩ ወጥ ቤት ኃላፊ ሆነው ይሾማሉ።ለጉብኝትም ሆነ ለእንግድነት የመጡትን ሚኒስትሮችን ሁሉ ጥዑምና ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸው ምግቦችን በማብሰል ያስደስቷቸው ነበር።የእሳቸውን ጥዑም ምግቦች ቀምሰው ከተማረኩና ካስተናገዷቸው መካከልም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፥ አምባሳደር ስዩም መስፍንና ገነት ዘውዴ ይገኙበታል።ይህም በሸጋ ባህሪ የታገዘው የምግብ ስራ ሙያቸው ታዲያ ከኮኔሪሉ ጀምሮ ስምንት አምባሳደሮችን በየተራ ለማገልገል አስችሏቸዋል።መንግስታትም ሆነ ባለስልጣኑ ቢቀያየሩም የቀደመው ለተረኛው የአቶ ክፍሌን የእጅ ሙያ እየነገረ ለዓመታት ፈረንሳይን እንዲከትሙ እድሉን ፈጠረላቸው፡፡
ዲያስፖራው ሼፍ
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለዓመታት ባለስልጣናቱን በፈረንሳይ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ኢትዮጵያ ሚሊኒየሟን ባበሰረችበት ዓመት ህዝባቸውን ለማገልገል ወስነው ያላቸውን ጥሪት ይዘው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ።ዳሩ ግን የሸጋዎቹ አገር አዲስ አበባ ያኔ ጥለዋት እንደሄዱበት ዘመን በ20 ብር ጮማ የሚቆረጥባት ፍሪዳ የሚጣልባት ሆና አላገኟትም።የኗሪዎቿ ቁጥርና የኑሮ ውድነቱ ሰማይ ደርሷል፥ ወጪ ወራጁ እንደእሳቸው በተረጋጋ የኢኮኖሚ ደረጃ ለኖረ ሰው ቶሎ የሚለመድ አልመስል አላቸው።ይሁንና በእሳቸው አቅም አነስተኛ ግሮሰሪ ለመክፈት ቢያቅዱም ያላቸው 80 ሺ ብር ስራ ሊያሰራቸው ቀርቶ ቤት ለመከራያት እንኳ የማይበቃ መሆኑን ይገነዛባሉ። የተወሰኑ መኝታ ክፍሎች ያሉትን ቤት ለማግኘት በአከራዮቹ የሚጠራው ዋጋ የትየለሌ ይሆንባቸውና ተስፋ ይቆርጣሉ።« በእኛ ዘመን ሚሊዮን የምናቀው የሰው ስም ነው እንጂ ብር አልነበረም›› በማለት የኑሮ ውድነቱ ጣራ መንካቱን ያወሳሉ፡፡
ተስፋን ያለመለመው የስልክ ጥሪ
የበርካታ ባለስልጣናትን ቀልብ ገዝተው ያገለገሉት ሼፉ ክፍሌ ባዩት ነገር እጅግ ተስፋ ቆርጠው ወደመጡበት አገር ለመመለስ ወሰኑ።ወደ ፓሪስ ለመብረር አምስት ቀን ሲቀራቸው ግን አንድ የስልክ ጥሪ ይደርሳቸዋል።ይህም ዝናቸውን ከፈረንሳይ ድረስ የሰማች አንዲት ባለሆቴል የአብረን እንስራ ጥሪ ነበር።ግለሰቧ ጅማ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆቴል ባለቤት መሆንዋን፤ ሆቴሉ በየቀኑ በርካታ ቱሪስቶች እንደሚያስተናግድ ይነገራቸዋል።ሼፉ ጥሪው ግራ ቢያጋባቸው ወደ ፈረንሳይ ለመመለስ አንገራገሩ።በዚህም ሳያበቁ የተባለውን ሆቴል በአካል ድረስ በመሄድ ለመጎብኘትና ለመወሰን ፈለጉ።እንዳተባለው የአባ ጅፏሯ ጅማም ሆነ ህዝቧቿ ካሰቧት በላይ እንግዳ ተቀባይ፥ የአየር ጸባይዋም ለኑሯ ተስማሚ ሆነው አገኙት።ከአዲስ አበባ ሁካታና ግርግርም ትገላግላቸው ዘንድ ወዷዷት፤ ከተሙባት፡፡
አሁን አዛውንቱ ሼፍ በጅማ ሴንትራል ሆቴል በዋና ሼፍነት በስምንት ሺ ብር ተቀጥረው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።ምንም እንኳ የእድሜያቸው ጣሪያ መንካት ለሰሚው በሚያስደነግጥም ከወጣቶቹ በላይ ማልደው በመነሳት እንግዶቻቸውን ጥዑም የሆኑ ምግቦችን አዘጋጅተው ይጠብቃሉ።በስራ አጋጣሚ እንግሊዝኛ፥ ፈረንሳይና ጣሊያን ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ።ይህም ታዲያ በተለይው ከቱሪስቶች ጋር በቀላሉ ለመግባባትና ወዳጅነት ለመመስረት አስችሏቸዋል።በመስተንግዷቸው የተማረኩ እንግዶች ከደመወዛቸው በላይ ጉርሻ ይሰጧቸዋል።
በፈረንሳይ ቆይታቸውም ከምግብ ስራ በተጨማሪ 250 ለሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ካምፕ የመግባት እድል ማመቻቸት ችለዋል። በስራቸው ምክንያት ትዳር ይዘው የአብራኮቻቸውን ክፋይ ማፍራት ባይችሉም ያሰደጓቸው ልጆች ዛሬም ድረስ ልክ እንደወላጅ አባት አለንልህ ይሏቸዋል። የተወለዱበትን ቀዬ ዛሬም ድረስ ሄደው የመጎብኘት እድሉን ባያገኙም፤ አብዛኞቹ ዘመዶቻቸው በህይወት ባይኖሩም፤ ያሳደጓቸው ልጆቻቸውና ያገለገሏቸው አምባሳደሮች ግን ጅማ ድረስ መጥተው ይጠይቋቸዋል። ይህም ቀሪ ዘመናቸው በሀሴት እንዲዘልቅ ምክንያት እንደሆናቸው ነው ያጫወቱን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር