የትልቁ አንጀት መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀኝ የሆዳችን የታችኛው ክፍል ይገኛል፤ ቁመቱም እስከ 9 ሴንቲ ሜትር ሊደርስ ይችላል፤ ወፍራም ግድግዳም አለው፡፡ የትርፍ አንጀት ምንም አይነት ጥቅም እንደሌለው ለረዥም ጊዜ ሲታመንበት የኖረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2007 በተመራማሪዎች በተደረገ ጥናት ግን ጥቅም እንዳለው ተደርሶበታል፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ከሆነ ትርፍ አንጀት ጠቃሚ የሚባሉትን ባክቴሪያዎች የሚያስጠልል ሲሆን እንደ ደም ደም መቀላቀልና አጣዳፊ ተቅማጥ ባሉት የጤና መጓደል ሁኔታዎች ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ከሰውነታችን በሚወገዱ ጊዜ፣ ትርፍ አንጀት እነኝህን ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ካስጠለላቸው በማውጣት ለጠፉት የሚተካ መሆኑን መስክረዋል ወይም ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
የትርፍ አንጀት የሚገኝበት ቦታ በቀኝ የሆዳችን ክፍል ከታች ነው
ለትርፍ አንጀት በሽታ አብዛኛውን ጊዜ የቀዶ ጥገና ሕክምና የግድ ስለሚያስፈልግ ሕመምተኛን በአስቸኳይ ሕክምናውን ማግኘት ወደሚችልበት ሆስፒታል መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የትርፍ አንጀት በሽታ የሚከሰተው ከትልቁ አንጀት ጋር የተጣበቀው ጣት የመሰለው ተቀጥላ ወይም ትርፍ አንጀት ሲቆስል ነው፡፡ የሚገኘውም በታችኛው የሆድ ክፍል በቀኝ በኩል ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም ያበጠ የትርፍ አንጀት ሲፈነዳ የሆድ ብግነት (Peritonitus) ያስከትላል፡፡ የአንጀት አቃፊ በመግልና በበሽታ ተሃዋስያን ተበክሎ ሲቆስል የሚደርስ አደገኛ የሆድ ብግነት ሕመም (Peritonitus) ይባላል፡፡
የትርፍ አንጀት በሽታ ምክንያቶች
በባለሞያተኞች ጥናት መሰረት ለትርፍ አንጀት በሽታ ምክንያት ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ሁለት ምክንያቶች አሉ፡-
- በአንዳች በሽታ ልክፍት ምክንያት በሆድ ውስጥ የሚፈጠር ማመርቀዝ ( Infection)፡- በሆድ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚጋጥም ልክፍት ወደ ማመርቀዝ ደረጃ ሲደርስ፣ ያ ሁኔታ በመስፋፋት ወደ ትርፍ አንጀት በመዝለቅ የሚያጋጥም እና
- ቁራጭ ሰገራ በትርፍ አንጀት ውስጥ ተቀርቅሮ መቅረት (Obstruction)፡- ደረቅና ጠንካራ የሆነ ቁራጭ ሰገራ በትርፍ አንጀት ውስጥ በሚቀረቀርበት ወቅት በሰገራው ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች የትርፍ አንጀቱን በመመረዝ እንዲታመም ስለሚያደርጉ ነው የሚል ነው፡፡
የትርፍ አንጀት በሽታ ምልክቶች
- የማያቋርጥና እየጨመረ የሚሄድ የሆድ ሕመም
- ሕመሙ በመጀመሪያ እምብርት አካባቢ ይጀምርና ወዲያውኑ ወደ ታችኛው ቀኝ የሆድ ክፍል ይዞራል።
- መጠነኛ ትኩሳት፣ የሆድ ድርቀት፣ ተውከት ይኖራል፤ የምግብ ፍላጎትም ይቀንሳል፡፡
የትርፍ አንጀት በሽታን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ
- የሕመምተኛው ሆድ በስተግራ በኩል ከብሽሽቱ በላይ በዝግታ ጠንከር አድርጎ እስኪያመው ጫን ማለትና ከዚያም እጅን በፍጥነት ማንሳት፡፡
- እጅ በሚነሳበት ጊዜ እንደጦር የሚወጋ ሕመም ከተሰማው የትርፍ አንጀት ሕመም መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በስተግራ በኩል ምንም ዓይነት ሕመም ካልተሰማው በስተቀኝ በኩል በድጋሚ መሞከር ይገባል፡፡
የትርፍ አንጀት መሆኑ ጥርጣሬ ከገባን
- በአስቸኳይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያገኝ ወደሚችልበት ሆስፒታል መላክ
- የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር መሰጠት የለበትም፤ ሆዱንም ማጠብ አይገባም፤ በሽተኛው ከሰውነቱ ብዙ ፈሳሽ ወጥቶ ድካም ከተሰማው ጥቂት ውኃ ወይም ስኳርና ጨው የተቀላቀለበት ፈሳሽ ፉት እንዲል በማድረግ መርዳት ተገቢ ነው፡፡
- ግለሰቡ ከትከሻው በግማሽ ቀና ብሎ እንዲቀመጥ ማድረግ ለሕመምተኛው ምቾትን ሊሰጥ ይችላል፡፡
በምግብ እንሽርሽሪት መዋቅር ላይ ከሚያጋጥሙ በሽታዎች መካከል አብዛኞቹ በተዛባ አመጋገብና አኗኗር ዘይቤ አማካኝነት የሚከሰቱ ናቸው፤ አብዛኛው ሕዝብም በነዚህ በሽታዎች ይጠቃል፤ በተለይ የጨጓራ ሕመም የብዙ ሰዎች የጤና ችግር ሲሆን፣ የሆድ ድርቀትና ተቅማጥ የሚያስከትሉ የውስጥ ደዌ የጤና ችግሮችም በስፋት ይታያሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምግብ እንሽርሽሪት ስርዓት ላይ የሚያጋጥሙንን የጤና ችግሮች የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን በዚህ ዘዴ መቆጣጠር የማይቻሉትን ደግሞ ሕክምና በመከታተል ፈውስ ማግኘት የሚቻል ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012