የልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ህጻናትን በመድፈርና በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል።
ከሀምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጂግጂጋና በአካባቢው በተፈጸመ ወንጀል ህጻናትን በመድፈርና በግድያ ወንጀል በተጠረጠሩት ሁለት የሄጎ ቡድን አባላት ላይ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ አከናውኖ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ 10 ቀን ጊዜ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ወርሰሜ ሼክ አብዱር እና ጉሌ ዳበል ዳውድ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፥ በሄጎ ቡድን አባላት ስም በጂግጂጋ እና አካቢው ህጻናትን በመድፈርና በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተከናወነባቸው ይገኛል።
መርማሪ ፓሊስ በወቅቱ በተፈጸመው ወንጀል የተገደሉ ሰዎች አስከሬን፥ ከጳውሎስ ሆስፒታል ባለሙያ በመውሰድ ማስመርመሩንም ለችሎቱ አስረድቷል።
ከዚህ ባለፈም ከ100 በላይ የተለያዩ ተቋማት ላይ የደረሰ የጉዳት መጠንን የሚገልጽና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶችን መሰብሰቡንም ገልጿል።
ቀረኝ ያለውን የተለያዩ በዘረፋ ወንጀል ተሳትፈው የሸሹ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎች በተናጠልና በዝርዝር አደረሱ የተባለው ጉዳት አለመቅረቡንና ምርመራው ተመሳሳይ መሆኑን በመጥቀስ፥ ፍርድ ቤቱ ይህን ከግምት ውስጥ ሊያስገባ ይገባል በማለት ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል።
የመርማሪ ፖሊስን የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ እና የተጠርጣሪ ጠበቃዎችን ቃል ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ጊዜ ሰጥቶ ምርመራውን እንዲያከናውን 10 ተጨማሪ ቀናት መስጠቱን የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።