ግጭት በተለያዩ መዝገበ ቃላትም ሆነ በዘርፉ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች እንደየነባራዊው ተጨባጭ ሁኔታ የሚገለጽ ቢሆንም፤ የሁሉም ማጠንጠኛ ማዕከል ሆኖ የሚስተዋለው ግን በተለያየ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌላም የፍላጎቶች አለመጣጣም ምክንያት ወይም የጥቅም ሽኩቻን ተከትሎ በግለሰቦች ወይም ቡድኖች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ወይም ጠብ መሆኑ ነው። ይህ አለመግባባት ወይም ጠብ ደግሞ በድርድር፣ በሽምግልና ወይም በዳኝነት መንገድ በባህላዊ አልያም በዘመናዊ የዳኝነትና የእርቅ ስርዓት የሚፈታ ሲሆን፤ ምንም እንኳን ግቡ እርቅ መፍጠርና ለግጭቱ እልባት መስጠት ቢሆንም ሂደቱ ከቦታ ቦታ እንደ ባህልና አካባቢያዊ ሁኔታው ይለያያል።
የዘርፉ ምሑራን እንደሚገልጹት፤ በግለሰቦችም ሆነ በቡድኖች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች መፈታት እንዳለባቸው፣ ሲፈቱም አዎንታዊ ጎን ኖሯቸው እንዲፈቱ ጥረት ሊደረግ ይገባል። በዚህ መልኩ አዎንታዎ መልክ ኖሯቸው ግጭቶችን ከመፍታትና ዘላቂ እርቅን ከመፍጠር አንፃር ደግሞ ባህላዊ የፍትህ ተቋማት ከመደበኛው የፍትህ ተቋም የተሻለ አቅምና እምነት አላቸው። ይሄም የባህል ተቋማት በህብረተሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ስለሚኖራቸውና በራሱ በማህበረሰቡ እሴት መሰረት የሚከናወኑ ስለሆኑ ቂምና በቀልተኝነትን በሚያሽር መልኩ ለማከናወን የሚያስችሉ በመሆናቸው ነው።
እኛም ለዛሬው ጉዳያችን አድርገን የያዝነው ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የአብሮነት እሴት ማበልጸጊያዎች መካከል የኩስሜ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን ሲሆን፤ በዚህም በብሔረሰቡ የሚስተዋሉ የግጭት አይነቶችና ምክንያቶች፣ የግጭት አፈታት ባህላዊ ሂደቱንና በሂደቱ ስለሚከወኑ ጉዳዮች ብሎም ስለ እርቁ ዘላቂነት ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂውማኒቲስ፣ የቋንቋዎች ጥናት፣ የጆርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ፣ ስነፅሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል የድህረ ምረቃ መርሐግብር ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍና ፎክሎር የኤምኤ ዲግሪ ማሟያነት በብሩክ ያሬድ በ2006 ዓ.ም የቀረበ ጥናትን ዋቢ በማድረግ ይዘን ቀርበናል።
በዚህ ጥናት እንደተመላከተው፣ የኩስሜ ብሄረሰብ የሚገኘው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሰገን ዞን በደራሼ ወረዳ በጋቶ ቀበሌ ሲሆን፤ ብሔረሰቡም ከስምንት ጎሳዎች (ሰውደታ፣ ከረካይታ፣ ኤሻላይታ፣ አርገማይታ፣ የኩማሊታ፣ ኤለይታ፣ ትግሳይታ እና ማሌታ) የተዋቀረ ስለመሆኑ ይነገራል። የብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደርም በበላይነት የሚመራው በንጉሥ ሲሆን፤ ከእርሱ ሥር አልጋሌ፣ አልማሌ፣ እግዴና ባደቱን የተሰኙ መንፈሳዊ መሪዎች ይገኛሉ። ንጉሱ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሥራዎችን በበላይነት የመምራት ሥልጣን አለው። ንጉሱ ከማስተዳደር ሥራው ባሻገር በየዕለቱ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ያከናውናል። ወንጀል ሲፈፀም መፍትሔ መስጠትም የንጉሡ ድርሻ ነው።
የኩስሜ ብሔረሰብ በዋናነት የሚተዳደረው በግብርና ቢሆንም እንስሳትም ያረባል። ባህላዊ መስኖ በመጠቀምም በዓመት ሁለቴ ያመርታል። አሁን ላይ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ጥቂት በዕደ ጥበብ ሙያ በመሰማራት ኑሯቸውን የሚደጉሙ የብሔረሰቡ አባላት ነበሩ። የኩስሜ ብሔረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ‹‹ኩስምኛ›› ይሰኛል። ከኩሻዊ የቋንቋ ቤተሰብ ሲሆን፤ የብሔረሰቡ አባላትም ከኩስምኛ ቋንቋ በተጨማሪ ኦሮምኛ ኮንሶኛና ደራሼኛ ይናገራሉ።
በጥቂቱም ቢሆን በዚህ መልኩ የሚገለጹት የኩስሜ ብሔረሰብ አባላት እንደማንኛውም ህዝብ ሰዋዊ ፍላጎትና ጥቅምን መሰረት ያደረጉ ከመልካም መስተጋብር ገጽታዎችም ሆነ ከቅራኔ ምክንያቶች ተለይተው አይገለጹም። በዚህም እንደማንኛውም ማህበረሰብ ለግጭትና ቅራኔ የሚዳርጓቸው ምክንያቶች አሏቸው። እነዚህን ቅራኔዎችና ግጭቶች የሚፈቱበት የራሳቸው የሆነ ባህላዊ እሴትም አዳብረው እየተገለገሉበት እና ግጭቶች ተባብሰው የከፋ ኪሳራ እንዳያደርሱ እርቅ የማውረድ ተግባርን እያከናወኑባቸው ይገኛል።
በኩስሜ ብሔረሰብ የግጭት መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በዋናነት ድንበር መግፋት፣ የቤተሰብ ጠብ፣ ግድያ፣ የብሔርና የቡድን ጠብን የመሳሰሉ የወንጀል ነክ ግጭቶች ተጠቃሽ ናቸው። በኩሰሜዎች የግጭት ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ማህበረሰቡ ተገቢ አይደለም የሚለውን ጉዳይ መፈፀምና የሰውን ነገር የራስ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ሌላው ምክንያት ነው። በኩሰሜ ብሔረሰብ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች መነሻቸው በአመዛኙ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሲሆን፤ በዚህም የእርሻ መሬት ድንበር መግፋት፣ ከግጦሽ ሳር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ የሀሳብ አለመግባባቶች እንዲሁም የቤተሰብ ጠብ፣ ወንጀልና የቡድን ጠብ በብሔረሰቡ ጎልተው ከሚታዩ ግጭቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ብሄረሰቡም እነዚህንም ሆነ ሌሎች ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል የራሱ ባህላዊው የእርቅ ስርአትና ሂደት አለው።
ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቱም ብሔረሰቡ በየትኛውም አጋጣሚ ግጭት ሲከሰት ውድመት ሳያስከትል እርቅ እንዲፈጸም የሚያደርግበት ነው። የባህላዊ እርቅ ስርዓቱን ለመፈጸም ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ሞራ(መሸንገያ) አንዱ ሲሆን፤ ይህ በየቀጠናው እና በየጎጡ የሚገኝ የፍርድ አደባባይ ነው። ይሄም ዙሪያውን በድንጋይ የተካበ ሲሆን መሃሉ ላይ እንደጥላ የሚያገለግል ዛፍ አለ። ሌላኛው አባ ዲባ(ዳኛ) ሲሆን፤ አጠቃላይ የህዝቡን ሰላም የሚጠብቅና ህዝቡን የሚያስተዳድር የሚያስታርቅ፣ በህብረተሰቡ የሚመረጥ የባህላዊ እርቅ ስርአቱ መሪ ነው። በኩስሜ ብሔረሰብ በየቀጠናው አንድ አንድ በሸንጎ የተመረጠ አባ ዲባ አለው። ይህ አባ ዲባ ወይንም አስታራቂ ሁሉንም ጉዳዮች የማየት መብት አለው። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በጥልቀት መታየት አለበት ብሎ ሲያሳብ ጉዳዩን ወደ በላይ ማለትም ወደ ዋናው አባ ዲባ ይልካል።
አባ ዲባዎች (ዋናው አባ ዲባና ንኡሳኑ) የእርከን ተዋረድ ያላቸው ሲሆን፤ በየቀጠናው አንድ አንድ ንኡስ አባ ዲባዎች ይኖራሉ። እንደቀጠናው ስፋትም የጎጥ ንኡስ አባ ዲባዎች ከቀጠናው አባ ዲባ ስር ይኖራሉ። የብሔረሰቡ አባላት በጋራ መክረው ውሳኔ የሚሰጡበት ዋናው የፍርድ አደባባይ ግን አንድ ብቻ ነው። መጠሪያ ስሙ ከሌሎቹ ሞራዎች በተለየ በሰው ስም ቆራኦኛ ተብሎ ይጠራል። ይህም የኦኛ እንጨት ማለት ነው።
ኩሰሜዎች አብዛኞቹን የግጭት ዓይነቶች የሚፈቱበት ወጥ የሆነ አካሄድ አላቸው። ዋና ዋና የሂደት ደረጃዎች ግን በስድስት ይከፈላሉ። አንደኛው እነዚህም ክስ (ሆለታ) ሲሆን፤ በኩሰሜ ብሔረሰብ አንድ ተበዳይ እገሌ በድሎኛል ስለዚህም ይታይልኝ ፍርድም ይሰጠኝ ብሎ ሲያስብ ጉዳዩን ወደ ሞራ ይዞ በቀጠናው ካለ ንኡስ አባ ዲባ ጋ የሚቀርብበት ነው። ሁለተኛው እርከን ማስረጃ ሲሆን፤ ይህ ግን ተከሳሽ በከሳሽ የቀረበበትን አቤቱታ አምኖ ከተቀበለ የሚዘለል ይሆናል። ሶስተኛው ደረጃ ሽማግሌ መጥራት ሲሆን፤ ይህ ደረጃ በሁለቱ ወገኖች መካከል ብዙ ክርክር ከተደረገ በኋላ ጉዳዩ ይበልጥ በሰከነ መልኩ እንዲታይና ሰዎቹ የሚግባቡበት መንገድ ካለ ይህንንም ለማየት ይረዳ ዘንድ በሞራው ከተሰበሰቡት ሁለቱም ወገኖች ያሸማግሉናል ብለው የሚያስቡትን ሽማግሌ የሚሰይሙበት ነው።
አራተኛው ደረጃ ደግሞ የተመረጠው ሽማግሌ የክሱን ትክክለኛነት አረጋግጦ ጥፋተኛውን ለይቶ ለዚህ ጥፋት ይህ ፍርድ ይገባል የሚለውን ውሳኔ ይዞ ወደ ሞራው ለአባ ዲባው የሚያቀርብበት የቅጣት አስተያየት ነው። አምስተኛው እርከን ደግሞ ብይት ሲሆን፤ ስድስተኛው ደግሞ ማዕቀብ/ዱፈና/ ደግ ብይን የተላለፈበት ሰው ብይኑን አልቀበልም ሲል ከህብረተሰቡ የሚገለልበት ሥርአት ነው። ይሄ ማዕቀብ የመጣል ስርአትም የኩሰሜ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓታቸው እስካሁን ዘልቆ እንዲቆይ ካደረጉ እሴቶች መካከል ጎልቶ የሚጠቀስ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ጥፋተኛ የተባለና በማዕቀብ መገለል የደረሰበት ሰው በማርካ /ይቅርታ/ ስርዓት ይቅርታ ጠይቆ ከህብረተሰቡ መቀላቀል ይችላል።
በብሔረሰቡ ዘንድ በተለይ ለግድያና ለብሔር ግጭት እርድ የእርቅ ሥነ ሥርዓት የመጨረሻው ስርዓት ሲሆን፤ ሌሎቹ ጉዳዮች ግን በካሳ ክፍያና በገንዘብ ቅጣት ይጠናቀቃሉ። ለምሳሌ፣ የግድያ ወንጀል ሲፈፀም ገዳይ ሮጦ ንጉስ ቤት ይገባል። ንጉሡ የገዳይንና የሟችን ወገን በማቀራረብ ያስታርቃል። በዚህ የዕርቅ ሂደት ከሌሎች ጋር በመሆን ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በገዳይ ወገን ላይ ጉማ (ካሣ) በመወሰን ፀበኞች ለበቀል እንዳይፈላለጉ ያደርጋል። በቤተሰብ ደረጃ የሚነሱ ግጭቶች ግን መንስዔና ውጤታቸው በጎረቤት ሽማግሌዎች ይታያሉ እንጂ ወደ ንጉሡ አይደርሱም።
ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚከሠቱ ግጭቶች በቅድሚያ ከየብሔረሰቦቹ በተውጣጡ ታዋቂ ሽማግሌዎች እንዲታዩ ይደረጋል። ይህ ሣይሳካ ሲቀር ግን የየብሔረሰቦቹ የጎሣ መሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን በጥልቀት መክረውበት አጥፊው ወገን ካሣ እንዲከፍል ያደርጋሉ። የህይወት መጥፋት ጉዳይ ከሆነ ገዳይና ሟች ለወደፊቱ በቂም በቀል እንዳይፈላለጉ ለማድረግ ፍየል በማረድ ደም የመርጨትና አጥንት የመከስከስ ባህላዊ ሥርዓት ይከናወናል። ባህላዊ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱም ወገኖች የጥፋት አላማን ከማሰብ የሚገድባቸው እና እንዳያፈነግጡ እርግማን ተከናውኖ የዕርቅ ሥርዓቱ ይጠናቀቃል።
የባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቱም በትክክል ፍርድ ይካሄድበታል ተብሎ ስለሚታመን ፍርዱን የማይቀበሉት ግለሰቦች ቢኖሩ እንኳን ከብሔረሰቡ ስለሚገለሉ ተቀባይነቱ የጎላ ነው። ከዚህ ባለፈም የባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቱ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ ሲሆን፤ ይሄም በተለይ የሐሰት አጣሪ በሚል በብሔረሰቡ የተቋቋመ ኮሚቴ መደበኛ ፍርድ ቤት በተሳሳተ መልኩ ውሳኔዎችን እንዳይወስን መረጃን በሚገባ በመሰብሰብ ድጋፍ ያደርጋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ እርቅ ጸንቶ እንዲቆይና ዘላቂ እንዲሆን የሚያደርጉ የባህሉ ትዕምርቶች አሉ። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከልም እርጥብ ቅጠል አንዱ ሲሆን፤ የተቀጣ ሰው እርጥብ ቅጠል ይዞ መቅረቡ ቅጣቱን አምኖ ምህረት ለመጠየቁ ማሳያ ነው። ሌላኛው እርድ ሲሆን፤ የእርድ ስነ ስርዓት የባህላዊ እርቅ የመጨረሻ ማሳረጊያ ነው። ብዙ ጊዜ የፍጹም እርቅ መፈጸምና የመንፃት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። እርድ ከተከናወነና በአንድ ላይ ከተበላ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ዳግም ለበቀል አይፈላለጉም።
እንደ አጠቃላይ የኩሰሜ ብሔረሰብ ባህላዊ የእርቅና የፍትህ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ ማህበረሰቡን የሚያሳትፍና በህብረተሰቡ ዘንድም ተዓማኒና ዘላቂ እርቅን ለመፈጸም የሚያስችል ነው። የባህላዊ የፍርድ ተቋማቱን የሚመራው የሞራው መሪ አባ ዲባም የሚመረጠው በህዝብ ይሁንታ ሲያገኝ ነው። ከተመረጠ በኋላም የፍትህ ስርዓቱን በዋናነት የመምራት ስልጣን በእጁ ቢሆንም ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በፍርድ አደባባይ የተሰበሰቡት ሰዎች የቅጣት አስተያየት እንዲሰጡ ማድረጉ የማህበረሰቡን ተሳትፎ የጎላ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ እንዲህ ያለ ተሳትፎ ማድረጉ ደግሞ አመኔታውን ያጠናከረ ሆኗል። በዚህም ወደ ዘመናዊ ፍርድ ቤት በመሄድ በሀሰት ፍርድ ለማግኘት እንደ ውሸታም ወደ ባህላዊው የፍትህ ተቋም መምጣትን እንደ ሀቀኛ እንዲቆጠር እያደረገውም ይገኛል።
ይህ አመለካከትና ተሳትፎ ደግሞ የብሔረሰቡ ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት ዋነኛ የጥንካሬ መገለጫዎች ከመሆኑም በላይ፤ ከዚያ በተጨማሪ ዘላቂ ሰላም በማውረድ እርቁን የማያዳግም በማድረግ ረገድ በብሔረሰቡ ዘንድ ከዘመናዊው ልቆ መገኘቱም የጥንካሬው አንድ መገለጫ ነው።
በጥቅሉ ሲታይ ባሃላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቱ ማህበረሰባዊ ተቀባይነቱ የጎላ እና የብሔረሰቡን አብሮ በሰላም የመኖር ህልውናን ማስጠበቅ የቻለ ስርዓት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ባህላዊ እሴት በሂደት ለውጦችን እያሰተናገደ መምጣቱ ስለማይቀር ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ ተደርጎለት ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 15/2012
ወንድወሰን ሽመልስ