አዲስ አበባ፡- የፕሮጀክቶች መዘግየት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያሥችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጅቱ ተገለጸ።ባለፉት አምስት አመታት በመንግስት ከተከናወኑ 60 ትላልቅ ፕሮጀክቶች 70 ከመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው መንግስት ለተጨማሪ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ መዳረጉ ተጠቅሷል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን በፌዴራል መንግስት የኢንቨስትመንት አስተዳደር ላይ ማኬኒዜ የሚባል አማካሪ ድርጅት ያሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ከ20 እስከ 30 በመቶ ተጨማሪ በጀት ጠይቀዋል። ከ60 እስከ 160 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ በጀት የወጣባቸው እንዲሁም እስከ 400 በመቶ ድረስ ጭማሪ የታየባቸው ፕሮጀክቶች አሉ። ይህንን ብክነት ለማስቀረት የተጠናከረ የፌዴራል መንግስት የፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓት የህግ ሰነድ ተዘጋጅቶ ረቂቁ ለምክር ቤት ቀርቧል።
የፌዴራል መንግሥት የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ተዘርግቶ ቢተገበር ኖሮ ባለፉት አምስት አመታት በእዚህ ምክንያት የባከነውን አንድ ቢሊዮን ዶላር (የፌዴራል መንግስት የካፒታል ወጪ ውስጥ 15 በመቶ) የሚጠጋ ወጪ ማዳን ያስችል እንደነበር በተካሄዱ ጥናቶች መረጋገጡን የፌደራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓት የህግ ማዕቀፍ መነሻ ሀሳብ ይጠቁማል።
በመነሻ ሃሳቡ እንደተመለከተው፤ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ የተሰሩ ጥናቶች በስኳር፣ በባቡር፣ በማዳበሪያና በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የጊዜና የወጪ መናር በከፍተኛ ሁኔታ ታይቶባቸዋል። በተለይ ደግሞ የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች የጥራት ችግሮች አሉባቸው።
ችግሮቹን ለመቅረፍ ሲባልም ‹‹የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓት አዋጅ›› ተዘጋጅቶ ለምክር ቤት ቀርቧል። ከፕሮጀክቶች ዝግጅት እስከ ትግበራ ምዕራፎች ውስጥ የሚመለከታቸውን አስፈፃሚ አካላት ስልጣን በግልፅ በማመላከት ኃላፊነትን፣ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን ለማስፈን እንደሚያስችልም የተዘጋጀው ሰነድ ያመለክታል።
ረቂቅ አዋጁ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የሀገሪቱን ፕሮጀክቶች ውጤታማነት እንዲያጎለብት፣ ብክነትን እንዲያስወግድ ታስቦ መዘጋጀቱን ይጠቁማል። ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው አግባብ፣ ወጪ እና ጥራት እንዲተገበሩ ለማስቻል መሆኑም በሰነዱ ተመልክቷል።
በፕላንና ልማት ኮሚሽን የልማት ፕሮጀክቶች ዳይሬክተሩ አቶ በረከት ፍስሃጽዮን፤ አዲሱ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅ አጠቃላይ ፕሮጀክቶች ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ እንዲሁም ወደ አገልግሎት እስከሚገቡበት ጊዜ ድረስ የሚያልፉበትን ዑደት ባግባቡ መለየቱን ይናገራሉ። በዑደቶቹ ውስጥ መከተል ያለባቸውን አሰራር እና መርህ ማስቀመጡንም ይገልጻሉ። የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ስልጣንና ኃላፊነት ማስቀመጡንም ያብራራሉ።
በፕላንና ልማት ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት በመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲባል አዋጁን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ በመጠቆም፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የመንግስት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው አግባብ ወጪ እና ጥራት እየተከናወኑ እንዳልነበረም ይጠቁማሉ።
ችግሩን ለመፍታትና መንስኤዎቹን ለመፍታት ተከታታይ ጥናቶች መከናወናቸውን የጠቆሙት አቶ በረከት፤ ወጥ የሆነ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓት አለመዘርጋት ዋነኛው መሆኑን በጥናቶቹ ከተለዩት መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህንን ለመፍታት የመንግስት ፕሮጀክቶች የሚያልፉበትን ዑደት፣ መሰረታዊ መርሆዎች እና በዑደቶች ውስጥ የተለያዩ አስፈጻሚ አካላት ያላቸውን ስልጣን እና ኃላፊነት የሚያብራራ የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉም አዋጁ ሊዘጋጅ እንደቻለ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በአገር ውስጥ የሚተገበሩ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች አሰራር ተዘርግቶላቸው ነበር። ግን የፕሮጀክቱ መነሻና መድረሻ፣ እንዴት እንደሚተገበር በግልጽ የተቀመጠ አሰራር አልነበራቸውም።
በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው፤ ባለፉት 14 አመታት በፌዴራል መንግስት የተገነቡና እየተገነቡ ካሉ የመስኖ ዘርፍ ፕሮጀክቶች 15 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ ወጪ አስከትለዋል። በመንገድ ልማት ፕሮግራም ፕሮጀክቶች ውስጥም ከተገመተው በላይ መንግስት 32 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አውጥቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012
ዘላለም ግዛው