አዲስ አበባ:- በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል “አዲስ ጉዞ” የተሰኘ የሞባይል አፕሊኬሽን በመዲናዋ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
በከተማ መስተዳድሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግና የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉትን መሰረታዊ ችግሮች መፍታት ከማስቻሉ ባሻገር የማህበረሰቡን ህግ የማስከበር ሚና ከፍ የሚያደርግ “አዲስ ጉዞ” የተሰኘ የሞባይል አፕሊኬሽን በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በመዲናዋ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ አያሌ ችግሮች ቢኖሩም፤ በመሰረታዊነት ህብረተሰቡን እያማረሩት ከሚገኙት ችግሮች መካከል አገልግሎት ሰጪ ታክሲዎች ያለመስመራቸው መስራት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እና ተሽከርካሪው መጫን ከሚገባው የሰው ልክ በላይ መጫን ናቸው።
እነዚህ ችግሮች የቢሮው ተቆጣጣሪዎች ወይም ትራፊክ ፖሊሶች ብቻቸውን መፍታት አልቻሉም፤ በመሆኑም ቢሮው አሁን ላይ እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ‹‹አዲስ ጉዞ›› የተሰኝ የሞባይል አፕሊኬሽን አበልጽጎ በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ ነው።
ፕሮግራሙ በሙከራ ደረጃ መሬት ላይ ወርዶ ውጤታማ መሆኑን ዶክተር ሰለሞን ጠቁመው፤ በዚህም እያንዳንዱ ማህበረሰብ በሞባይሉ ወይም በእጅ ስልኩ ላይ እንደማንኛውም ፕሮግራም በመጫን የተሳፈረበትን ታክሲ ወይም አውቶብስ ታርጋ ፎቶ በማንሳት አገልግሎት ሰጪው መስመሩ ወደየት እንደሆነ፣ ታሪፉ ምን ያህል እንደሆነ እና ምን ያህል ሰው የመጫን አቅም እንዳለው እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በመሆኑም አሽከርካሪው እነዚህንና ሌሎች ጥፋቶችን ካጠፋ ተሳፋሪው ምንም ዓይነት ጭቅጭቅ ውስጥ ሳይገባ በቀላሉ የእጅ ስልኩን በመጠቀም የተሽከርካሪውን ታርጋ በፕሮግራሙ ፎቶ አንስቶ አሽከርካሪው ያጠፋውን ጥፋት ወደ ማዕከሉ ሪፖርት ማድረግ እንደሚችል ዶክተሩ ተናግረዋል።
ፕሮግራሙም ተሽከርካሪው ፎቶ የተነሳበትን ቦታ፣ ሰዓት እንዲሁም የጫነውን የሰው ብዛት እና በአሽከርካሪው ላይ የቀረበበትን ክስ ወዲያውኑ ማዕከል ላይ የሚያሳይ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመው፤ ተሳፋሪው በላከው መረጃ መሰረት ተሽከርካሪውን በመከታተልና የክሱን ትክክለኝነት በማረጋገጥ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኝ ወዲያውኑ በአካባቢው ላለ ተቆጣጣሪ በእጅ ስልኩ የቅጣት ሪፖርቱ ይደርሰዋል። በዚህ መሰረትም ተቆጣጣሪው አካል ቅጣቱን ይፈጽማል ብለዋል።
በደረሳቸው መረጃ መሰረት ተቆጣጣሪዎች ተገቢውን ቅጣት ካልፈጸሙ እራሳቸው ይቀጣሉ ያሉት ሃላፊው፣ ይህም ጥፋትን አይቶ እንዳላየ የማለፍን፣ ከአሽከርካሪው ጋር የሚደረጉ ድርድሮችንና እሰጣ ገባን ያስቀራል። በሌላ በኩልም ፕሮግራሙ ማዕከል ላይ በመሆን ሁሉም ተቆጣጣሪዎች በተመደቡበት ቦታ እየሰሩ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን ለመከታተል እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በፕሮግራሙን በእጅ ስልኩ ላይ በመጫን ችግሮች ሲያጋጥሙት ፎቶ አንስቶ ወደ ማዕከሉ መረጃ መላኩ ለተቆጣጣሪዎች አይንና ጆሮ እንደመሆን ይቆጠራል ያሉት ኃላፊው፤ በአመቱ መጨረሻ የላኩት የመረጃ ብዛት ታይቶ ግለሰቦቹ ለተወጡት ማህበራዊ ኃላፊነት ትልልቅ ሽልማቶች የሚበረከትበት አሰራር እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።
ኢቲቲኤ ታክሲ የሚባል አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ፕሮግራሙን ለቢሮው በነጻ ማበልጸጉን ዶክተሩ ተናግረው፤ ወደ ስራ ለማስገባት 700 የሚደርሱ የሞባይል ስልክ ቀፎዎችን ለተቆጣጣሪ ሰራተኞች ለመግዛት በሂደት ላይ ነው።ግዥው በቅርቡ ተፈጽሞ እንደተጠናቀቀ ፕሮግራሙ ተመርቆ ወደ ስራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012
ሶሎሞን በየነ