አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የተጀመሩት የማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በስፋት ለመሳብ እንደሚያግዙ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።የኢትዮጵያና የብሪታንያ ግንኙነት ወደ ላቀ የትብብር ከፍታ ለማሸጋገር እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።
አቶ ደመቀ በለንደን በተካሄደው የ’ዩኬ – አፍሪካ’ ኢንቨስትመንት ጉባኤ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤፤ የማሻሻያ እርምጃዎቹ ከሃገሪቱ የለውጥ ጉዞ ባህሪ ጋር ተገናዝበው የሚወሰዱ በመሆናቸው፤ በኢን ቨስትመንት እና በንግድ ዙሪያ የጎደለውን ለመሙላት፥ የተሻለውን ለማጥበቅ እና ፈጣን ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዱ አብራርተዋል።
በተለይ በሃይል አቅርቦት እና በሎጂስቲክ ዘርፎች የተወሰዱት ማሻሻያዎች ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ትርጉም አዘል ድጋፍ እንደሚሰጡ በአብነት አንስተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፤ ሃገሪቱ የጀመረችው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማጎልበት ሰፊ ዕድል እና ተስፋ የሰነቁ ናቸው ብለዋል።
በማሻሻያው ላይ በዝርዝር የተመለሱ ጥያቄ ዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሳቢ ከመሆናቸው በላይ በተግባር ሂደት ውስጥ ችግር ፈቺ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የ’ዩኬ-አፍሪካ’ ኢንቨስትመንት ጉባኤ በኢ ትዮጵያ እና በእንግሊዝ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑን አክለዋል።
በመድረኩ ላይ በማዕድን እና ጂኦተርማል ሃይል አቅርቦት ዘርፍ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ይፋ መደረጋቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የፌስ ቡክ ገጽ ከአገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገ በው፤ ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለንደን እየተካሄደ ከሚገኘው የብሪታኒያ -አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር በተወያዩበት ወቅት የኢትዮጵያና የብሪታንያ ግንኙነት ወደ ላቀ የትብብር ከፍታ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ተስማምተዋል።
በተመሳሳይ በቤኪንግሃም ቤተመንግስት በተደረገው የእራት ግብዣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከልዑል ዊልያም ጋር ተገናኝተዋል፤ ልዑል ዊልያም ኢትዮጵያውያን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው በገለፁላቸው መሰረት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበውላቸዋል።
በሌላ በኩልም ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ ጋር በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ሰፋ ያለ ወይይትን ማድረጋቸውን፤ በውይይቱ የሁለቱ ሃገራት የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።
የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ በበኩላቸው፥ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የለውጥ ማሻሻያ ተግባር ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዲያጆ ማኔጅመንት ግሩፕ ጋር በኩባንያው እንቅስቃሴ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ኩባንያ በሃገሪቱ ከፍተኛ የግብር ከፋይ መሆኑን በማንሳት በቀጣይ ለኩባንያው ውጤታማ እንቅስቃሴ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012
እፀገነት አክሊሉ