የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የምርምርና የፈጠራ ክህሎት ያለው፤ ብቃቱ የተረጋገጠ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ለኢንዱስትሪው በማሸጋገር የሚያደርገው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን በማስፋፋት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ይገኛል። በግብርና፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪና በተለያዩ ዘርፎች የኅብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ጠቃሚ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ ተከታታይነት ያለው ሥራ ለመስራት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታችና ይበል የሚያሰኙ ናቸው።
በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎችም ለሀገራቸው የድርሻቸውን ለመወጣት፤ ያላቸውን ችሎታና እውቀት ለማካፈል በመትጋት ላይ ናቸው። ለአብዛኛዎቹ የምርምርና የፈጠራ ባለሙያ መነሻ መሠረት የሆኑት ደግሞ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው እሙን ነው።
በዛሬ የሳይንስ አምዳችን በ2011ዓ.ም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምርና በፈጠራ ሥራዎቻቸው ተሸላሚ ከሆኑት የፈጠራ ባለሙያዎች ውስጥ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚውን የተማሪ ሰለሞን ባህሩን የፈጠራ ሥራ ምንነትና የፈጠራ ልምዱ ይመለከታል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሰለሞን ባህሩ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ነው። የፈጠራ ፍላጎት ያደረበት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ አንድ ጓደኛው ዘንድ በመሄድ ያይ የነበረው የፈጠራ ሥራ ስቦት ነው። ጓደኛው ይህንን ውስጣዊ ፍላጎት በመረዳት አበረታቶት እሱም የፈጠራ ሥራውን መሞካከር ጀመረ።
ሰሎሞን በፈጠራ ሥራዎቹ የአካባቢው ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ሞክሯል። ወደ አካባቢው ችግሮች ዓይኖቹን አዙሮ ለምን በቆሎ በእጅ ይፈለፈላል? የሚል ጥያቄ በአእምሮው እየተመላለስ ያስጨንቀዋል። በቆሎ
በእጅ ከመፈልፈል በማሽን መፈልፈል እንደሚቻል ውስጡን በማሳመኑ ይህን እውን ለማድረግ ቆርጦ በመነሳት ያሰበውን ለማሳካት ሙከራ ጀመረ። በዚህ የቆሎ መፈልፈያ ማሽን መስራት ቻለ።
የፈጠራ ሥራ ያለ እገዛና አይዞህ ባይነት ከባድ ነው። ሰሎሞንም በፈጠራ ሥራዎቹ እገዛና ድጋፍ የሚያደርጉለት አብረውት ሆነው አይዞህ በርታ በማለት ከጎኑ ሳይርቁ የሚያግዙት ጓደኞቹ እንደሆኑ ይናገራል።
የፈጠራ ባለሙያው ሌሎች ፈጠራዎች
የፈጠራ ሥራዎቹ በግብርና ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ ዘመናዊ የጤፍ፣ የስንዴና የገብስ በመስመር መዝሪያ፣ የበቆሎ መዝሪያ፣ መኮትኮቻ፣ በቆሎ መፈልፈያ፣ ጤፍ ማበጠሪያ ባለሙያው ሰሎሞን ከፈጠራቸው መካከል ናቸው።
ሰሎሞን ስለፈጠራው አዲስነት እንዲሁም ከሌላ ፈጠራ የሚለይበትን ባህርይ ሲገልጽ የፈጠራ ሥራው ከዚህ በፊት አገሪቱ ውስጥ ያልተሞከረ አዲስ ፈጠራ ሲሆን ጤፍ መዝሪያው በመስመር እንደሚዘራና ከዚህ በፊት ከነበሩት ተመሳሳይ ማሽኖች የሚለይ መሆኑን ያስረዳል። ማሽኑም በአንድ ጊዜ ሜትር ከሃምሳ ስፋት መስመር በማውጣት እየመጠነ በሃያ ሳንቲሜትር ይዘራል።
ማሽኑ ጤፍና ማዳበሪያ ለየብቻ ከዘራ በኋላ አፈር ያለብሳል። ማሽኑ በራሱ የሚሰራው ስለሆነ ማንኛውም ሰው ሳይቸገር ሊጠቀመው ይችላል። በተጨማሪም በአንድ በሬ ወይም በሁለት በሬ ያለበለዚያ በአህያም በመጠቀም መዝራት ይቻላል። ማሽኑ ትራክተር ላይ ከኋላው ተገጥሞ እየተጎተት በቀላሉ መዝራት እንዲቻል ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ይገልጻል።
የፈጠራ ሥራው ያስገኘው እውቅና ሽልማት
በ2011 ዓመት ምህረት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው አገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት የእውቅና ሰርተፊኬትና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እጅ ተቀብሏል። በተጨማሪ በወረዳ በዞንና በክልል ደረጃ በፈጠራ ሥራው እውቅናና ማበረታቻ ሽልማቶችን አግኝቷል።
የፈጠራ ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
በአገሪቱ ውስጥ የሚሰሩ ብዙ የፈጠራ ሥራዎች የሚያጋጥማቸውን ዕጣ ፈንታ የገጠመው የሰሎሞን የፈጠራ ሥራ የእውቅና ሽልማት ከተሰጠው ወዲህ በነበረበት ቆሟል። ፈጠራ ምን ላይ ደረስ? ብሎ የሚደግፍና የሚከታተል አካል ባለማግኘቱ፤ በራሱ አቅም ለማስቀጠል ባለመቻሉ ተሰፋ ቆርጦ እንደተወው ይናገራል። በተጨማሪ ሌሎች የፈጠራ ሥራ ያላቸው ጓደኞቹም ተሰፋቸው ተሟጥጦ ወደ ሌላ ሙያ መግባታቸውንም ይናገራል።
ነገር ግን የሰሎሞን የፈጠራ ሥራ ሀሳብን በመወሰድ በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶችና አርሶ አደሮች ባለ አራት ጎማ የነበረው የበቆሎ መፈልፈያ በጋራዥ አስበይደው በብዛት የሚጠቀሙበት መሆኑንም ሰሎሞን ይጠቁሟል።
የፈጠራ ሥራው ተግዳሮቶች
ከአካባቢው ችግሮች በመነሳት መፍትሔ ለመስጠት የፈጠራ ሥራዎችን የሰራው ተማሪ ሰሎሞን የፈጠራ ሥራዎቹን ያከናወናቸው በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ነው። ፈተና የጀመረው ገና አንደኛ ደረጃ በመማር ላይ ሳለ ከትምህርት ቤት መምህራኖቹ ነበር። የፈጠራ ሥራውን ሳይረዱ በማንቋሸሽ ካርቶን ይዘህ ትመጣለህ? በማለት እንዳጣጣሉበት ይገልጻል።
ሰሎሞን ብዙ ችግሮች ካሳለፈ በኋላ ትምህርት ቤቶቹ እየደገፉና እያበረታቱት የፈጠራ ሥራውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉለት ዛሬ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣውረዶችን ማለፍ ግድ ሆኖበት እንደነበር ይጠቁሟል።
የሰሎሞን ህልም የፈጠራ ሥራውን ወደ መኪና በመቀየር የተሻለ ውጤት ማምጣት የነበረ ቢሆንም ያጋጠመው የፋይናንስ ችግር ዕቅዱ ሊዘልቅለት እንዳይችል አድርጓል። ብዙ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች አቅሙ እያላቸው ብዙ መስራት ሲችሉ በኢኮኖሚ ማነስ ምክንያት ሥራቸውን ሲያቋርጡ ዝም ብሎ ማየት አይገባም፤ መደገፍና መረዳት አለባቸው በማለት ምክረ ሀሳቡን ይሰጣል።
አገሪቱ ቴክኖሎጂ ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ለፈጠራ ባለሙያዎች ከሚሰጠው ሽልማት በላቀ ባለሙያው ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን እንዲሰራ መደገፍ ይገባል የሚለው ተማሪ ሰሎሞን፤ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጀምሮ ለምርምርና ለፈጠራ ሥራ ምቹ የሆነ ቦታና ሁኔታ አለመኖሩ፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ለማበረታት የሚደረገው ጥረት ውስን መሆኑ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ይጠቁማል።
እንደ ሰሎሞን ዓይነት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ለሳይንስና ቴክሎጂው መሠረቶች በመሆናቸው ከአካባ ቢያቸው በመነሳት የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ሳይሰለቹ እንዲሰሩ ማበረታታት፤ የፈጠራ ውጤታቸው ፍሬ እንዲያፈራና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ትኩረት ስጥቶ ማበረታት ይገባል። ፈጠራው ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ፤ በግብርና ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2012
በወርቅነሽ ደምሰው