ገጣሚ እና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሀንስ (ገሞራው) የተፈጥሮ ሐብታችንን ተሸክሞ እየወሰደም ቢሆን ለዘመናት በግጥም፣ በቅኔ፣ በእንጉርጉሮ… ስንክበው የኖርነውን አባይን እንዲህ ሲል ይወርፈዋል።
«እናትክን!» በሉልኝ
ይፈሳል ይሉኛል፣ አባይ ዐይኑ ይፍሰስ
ያን ስንቱን ወገኔን የውሃ እጦት ሲያምስ
የድርቀት ጋንጩራ ሲበላ ስንቱን ነፍስ፣
ውሃ ውሃ እያለ ለጋው ሲቀነጠስ
ናይል አባያችን አለ ነበር ሲፈስ
ለፈፀመው ደባ ለሰራውም ግፉ
«እናትክን!» በሉልኝ በዚያ የምታልፉ…
የገራውን ሥነግጥም ማስቀደሜ ያው ስለአባይ ለማውራት ማቆብቆቤን ያሳብቃል። አዎ!.. የአባይ ወሬማ ማለቂያ የለውም። አሁንማ የወንዙ ምንጭ መሆናችን ጭምር እየተረሳ በሶስተኛ አገራት ፍላጎትና በአበዳሪዎቻችን ታዛቢነት በሚካሄድ ውይይት ከበድ ያለ ጫና ሥር ወድቀናል።
ሰሞኑን ሦስቱ የናይል ተፋሰስ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን) የሚኒስትሮች ስብሰባ በዋንሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ ሰንብቷል። በጋዜጠኞች የተለመደ አነጋገር ይህን ስብሰባ ለየት የሚያደርገው በተለይ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ የተንቦረቀቀ ልዩነት በፈጠሩ ማግስት መካሄዱ ነው። በሰሞኑ ድርድር አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ የስምምነት ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ቀጠሮ በመያዝ ተጠናቋል። ሶስቱ አገራት ከሁለት ሣምንት በኋላ እንደገና ወደዋሽንግተን በመመለስ በግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የተዘጋጀ የስምምነት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሣምንት በፊት ያለውጤት የተጠናቀቀው ስብሰባ የልዩነት ፍሬነገር የውሃ ሙሌት ዓመት ጉዳይ ላይ ስምምነት አለመደረሱ ነበር። ባሳለፍነው ሣምንት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ሲያካሂዱት የቆዩት አራተኛና የመጨረሻው የቴክኒክ ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረትም ስቦ መሰንበቱ የምናስታውሰው ነው።
ውይይቱ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ አዲስ ሃሳብ ይዛ በመቅረቧ መሆኑም ይታወቃል። ግብጽ ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመት እንዲሞላ የሚል አዲስ ሀሳብ አቅርባለች። ይኸ የግብጽ አዲስ ሃሳብ ሶስቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የህዳሴው ግድብ በ7 ዓመት ውስጥ እንዲሞላ የደረሱትን ስምምነት የሚጥስ ነው። የግብጽ አዲስ ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ የተደረገው ወዲያውኑ ነበር።
የግብጽ አዲሱ ሃሳብ ምን አንደምታ አለው የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል። 90 በመቶ የውሃ ፍላጎቷን ከናይል ወንዝ የምታሟላው ግብጽ የውሃ ሙሌቱ ከ12 እስከ 21 ዓመት ይሁን ስትል በአጭሩ የግድቡ ሥራ ይቁም ከማለት የሚተናነስ አይደለም። ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም የጂኦፖሊቲክስና የአፍሪካ ጥናት መምህር እንዲህ ይላሉ። የግብጽ አዲስ ሃሳብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚከተሉትን ሦስት መሠረታዊ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ያብራራሉ።
ምክንያት አንድ፡- መጠነ ሰፊ የኢትዮጵያ አንጡራ ኃብት የተከሰከሰበት ግድብ ሉዓላዊነታችንን በሚፈታተን መንገድ በሌሎች ኃይሎች ይሁንታ ስር መውደቅን ያመጣል፣
ምክንያት ሁለት፡- በግብፅ ዕቅድ መሰረት ሙሊቱ ከተካሄደ የሕዳሴው ግድብ ለረዥም ዓመታት ስራውን ከዓቅም በታች ስለሚያከናውን ተርባይኖቹ፣ ማሺነሪዎቹ፣ ብረታብረቶቹ ባጠቃላይ መሠረተ ልማቱ ባለመንቀሳቀስ ለሚመጣ ዝገት (corrosion) እንዲሁም በግልጋሎት ማነስ ለሚመጣ ብልሽት (wear out) ያጋልጣል፣
ምክንያት ሶስት፡-የውኃ አሞላሉ በከፍተኛ ሁኔታ መዘግየት፣ ግብፅ በድርቅ ወቅት ይህን ያህል ልቀቁ፣ ኢትዮጵያ ከግድቡ ቢያንስ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት ውኃ መልቀቅ አለባት ወዘተ ከምትላቸው አስገዳጅ ሃሳቦች ጋር ሲደመር የሕዳሴው ግድብ በ13 ተርባይኖች ታግዞ 6 ሺ 400 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫል ብሎ ለማሰብ ስለሚከብድ ነው።
አንዳንድ ምንጮች እንደሚያስረዱት የግብጽ ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ቢያገኝ ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ታጣለች። በጠቅላላው እስከ አስር ቢሊየን ዶላር ልታጣ ትችላለች።
ግብጾች በአሁን ሰዓት አዲስ ያመጡት ሃሳብ ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ አንጻር ብቻ የተቃኘ እንጂ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለድርድር በር የሚከፍት አለመሆኑን ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን አስተያየት የሰጡበት ነው። እንዲያውም ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በርካታ የውሃ ሐብት እያላት ለግብጽ ብቸኛ የሆነውን የአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመሥራት መነሳትዋ ጠብ አጫሪነትና የግብጽን ብሔራዊ ሕልውና መፈታተን ነው ከሚሉ የግብጽ ምሁራን ሀሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደጋገፍ ይመስላል። በቅርቡ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ “ግብፅ ከናይል ወንዝ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳልፋ አትሰጥም” ስለማለታቸው አህራም ዘግቧል።
እንደሚኒስትሩ ማብራሪም “[ኢትዮጵያ] 630 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የዝናብ ውሃ ታገኛለች፤ 10 ወንዞቿን ሳንጠቅስ ማለት ነው። ግብጽ ግን በውሃ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቃለች። . . . የናይል ውሃ ጉዳይ ለግብጽ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው።” በማለትም መናገራቸው ተዘግቧል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር የግብጽ ፓርላማ አባላት የሃገሪቷ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ያስከተለውን ቀውስ ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ እጅግ ደካማ ነው ሲሉ ስለመተቸታቸው አህራም ዘግቦ እንደነበር የሚታወስ ነው። ፓርላማው በወቀሳ ብቻ ሳይወሰን የህዳሴ ግድብ ግንባታን የሚከታተል ልዩ ጊዜያዊ ኮሚቴ እስከማቋቋም የደረሰ እርምጃ መውሰዱንና ኮሚቴው የግብጽን የናይል ውሃ የመጠቀም መብት ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንደሚያጠናም አህራም ማስነበቡም ስንስታውስ ግብጾች በዚህም፣ በዚያም ብለው የህዳሴ ግድብን ፕሮጀክት ለማስተጓጎል የቱን ያህል ርቀት እየተጓዙ እንደሆነ ጠቋሚ ነው።
የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር እና የግድቡ ቁልፍ ተደራዳሪ ዶ/ር ስለሺ በቀለ በቅርቡ ‹‹ለእኛ የሚገባን ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ፍላጎት እንዳላት ነው ›› በሚል ከሰሞኑ የሰጡት ማብራሪያ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያስረዳ ነው።
ሌላው ግብጻውያን በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ፈጥነው ለመጠቀም የቋመጡ መስለዋል። ፕሬዚዳንት አልሲሲ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በጉዳዩ በሽምግልና እንዲገቡ ከመጠየቅ አልፈው በጉዳዩ ምንም አግባብ የሌላቸው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምአፍ) እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (ወርልድ ባንክ) በታዛቢነት እንዲቀመጡ መደረጉ ኢትዮጵያ ላይ ስልታዊ ጫና ለማሳደር ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ሆኗል።
በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የውስጥ ቀውስ ለማባባስ አደናቃፊዎችን ስፖንሰር ማድረግ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚፈታ ብድርና ዕርዳታ እንድታገኝ በማድረግ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም እንድታለሳልስ ግብጽ የምታደርገው ግልጽ እና ስውር ጥረት ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል።
የህዳሴ ግድብ መገንባት በየዓመቱ ወደግብጽ የሚሄደውን የውሃ መጠን ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ቃል የገባች ቢሆንም ግብፅ ግን በየዓመቱ የምታገኘውን 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሊቀንሰው እንደሚችል ሥጋቷን ስትገልጽ ቆይታለች።
ከዚህ ቀደም በግድቡ የውሃ አሞላልና የመልቀቅ ሂደት ዙሪያ ሁኔታዎች እንዲያጠና የተቋቋመው የአገራቱ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ከመስከረም 19 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በካርቱም አምስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሂዶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።
የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካይሮ ስብሰባቸው ላይ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱንና አለቃቀቋን ዕቅድ ግብፅና ሱዳን የሚያቀርቡትን ሰነድ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ትንታኔና ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርብ ታዞ ነበር።
ይህ የተቋቋመው የሶስትዮሽ ኮሚቴም ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት (International Panel of Experts on GERDP-IPoE) የሚባል ሲሆን 10 አባላት ነበሩት። ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እያንዳንዳቸው ሁለት ባለሙያዎችን እንዲሁም 4 ዓለምአቀፍ ባለሙያዎች ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከእንግሊዝ ያካተተ ነበር። የዓለም አቀፍ ፓናል ኦፍ ኤክስፐርት በመጨረሻ ሪፖርቱ በዋናነት አንደኛ ግድቡ ለግርጌ ሀገራት ጉልህ ጉዳትን እንደማያመጣ ይልቁን የተሻለ ጥቅምን እንደሚያስገኝ፤ የግድቡ መጠን ከወንዙ ፍሰት ጋር የተመጣጠነ እንደሆነ ፣ የግድቡ ንድፍ/ ዲዛይን እና አሰራር/ግንባታ ዓለምአቀፋዊ ደረጃን /International Standard/ ያሟላል፣ እንዲሁም ግድቡ የሚገነባበት ቦታ ለግድቡ ደኅንነት አስተማማኝ እንደሆነ አሳውቋል።
አጥኚ ቡድኑ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሳይንሳዊ ቡድኑ ለአራት ቀናት ያህል በካይሮ ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያን የግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ እቅድ፤ ግብፅ እና ሱዳን ያቀረቡትን የሙሌትና እና የውሃ አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በማዳመጥ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመስማማት ቢደርስም አንዳንድ ሃሳቦች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ማናቸውም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ለሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ቀርበው ትንተና እንዲደረግባቸው የውይይት አካሄድ ቢከተሉም ግብፅ የሳይንስ ጥናት ቡድኑ ትንተናን አሻፈረኝ በማለት ያቀረብኳቸው ሃሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ካላገኙ ውይይቱ ሊቀጥል አይችልም በማለቷ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ሥራውን በተሟላ አኳኋን ማከናወን ሳይችል እንደቀረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው አትቷል።
ግብፅ አሻፈረኝ ማለቷ አዲስ አካሄድ ሳይሆንም ከዚህ ቀደምም በግድቡ ላይ ሦስቱ አገራት ሊያከናውኑት የነበረውን የውሃ፣ የአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖ ጥናት በግብጽ ወገን እንዲስተጓጎል በተደረገ ጊዜ የታየ የሳይንስ እና የምክክር የመፍትሔ አማራጭን የማፍረስ ዘዴ እንደሆነ ነው በማለት ኢትዮጵያ ትተቻለች።
ከግብፅ በኩል በነበረው እምቢተኝነትም የጥናት ቡድኑ በቀጣይ ስለሚሠራቸው ጉዳዮች መመሪያ ሳይተላለፍ እንደቀረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው አክሎ መግለጹም የሚታወስ ነው።
ሲጠቃለል
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጽያ ሕዝብ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱን ከፍጻሜ ማድረስ ወይንም ያለማድረስ ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅማችን ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።ግድቡ እስከዛሬም መራመድ የቻለውና ግብጽንም በአባይ ላይ እንኳንስ ግድብ መስራት ማሰብ አይፈቀድም ከሚል አቋሟ አለቅቆ ወደድርድር መድረክ እንድትመጣ የገፋት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጥንካሬ ነው።
የቅርብ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የግድቡ በአጠቃላይ የሲቪል ሥራው 84 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራው 28 ነጥብ 79 በመቶ፣ የብረታብረት ሥራው 2 ነጥብ 65 በመቶ የደረሰ ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሥራዎች በአማካይ 67 ነጥብ 97 በመቶ ደርሷል።
ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቱ ገጥመውት ከነበሩት ችግሮች መካከል በግንባታ ወቅት ጥልቅ ሸለቆ ማጋጠሙ፣ የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ የተጣበበ የኮንትራት ጊዜ መኖሩ እና ሜቴክ የተረከባቸው ሥራዎች መዘግየት ይጠቀሳል። ችግሩን ለመቅረፍም በተለይ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተረክቧቸው የነበሩ ውሎች ሙሉ በሙሉ የማቋረጥና በአዲስ የመተካት ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ለመረዳት ችለናል። ሜቴክ ኮንትራት ሰጥቶ ሲያሰራቸው የነበሩ ኮንትራክተሮችን ሙሉ የኮንትራት ማሻሻያ በማድረግ ወደሥራ እንዲገቡ፣ በአዳዲሶቹ ውል መሠረት ቅድመ ክፍያ በመክፈል በፍጥነት ወደሥራ የማስገባት እርምጃ መወሰዱን መሐንዲሶቹ አስረድተዋል።
የሃይድሮሊክ ስቲል እስትራክቸር ሥራዎች (HSS) አፈጻጸም በአጠቃላይ 2 ነጥብ 65 በመቶ መድረሱ ታውቋል። የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች (EM) ሥራ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዩኒቶች የሚሆኑ ትራንስፎርመሮች ተመርተው በተከላ ቦታው የደረሱ ሲሆን አጠቃላይ ሥራው 28 ነጥብ 79 ደርሷል።
መልሶ ማቋቋምና ማስፈር በተመለከተ ስድስት ወረዳዎችና 17 ማዕከላት ተለይተው የት/ቤቶች፣ የጤና ኬላዎች፣ የግብርና ማሰልጠኛዎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የፖሊስ ጣቢያዎችና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የተረዳን ሲሆን የእነዚህ ግንባታዎች አፈጻጸም 70 በመቶ ደርሷል። በተጨማሪም ከተለዩት 5 ሺ 390 አባወራዎችና እማወራዎች መካከል 4 ሺ 360 ያህሉ በአዲሱ ቦታቸው እንዲሰፍሩ መደረጉን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ መሀንዲሶች ገለጻ ለመረዳት ችለናል።
በሜቴክ አስቀድሞ በጀቱ መበላቱ ከሚነገርለት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራዎች አንዱ የደን ምንጣሮ ነበር። ይህ ሥራ በአጠቃላይ 123 ሺ 189 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን በኢትዮጵያ ጂኦስፓንሽያል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ግምት መሠረት እስካሁን መሰራት የቻለው 32 ሺ 734 ነጥብ 63 ሄክታር ወይንም ከአጠቃላይ ሥራው 26 ነጥብ 57 በመቶ ብቻ ነው።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ 12 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውም ተወጥተዋል።
የግድቡ ሥራ በአንድ በኩል እያፋጠኑ በሌላ በኩል ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ ድርድር ማድረግ ከመንግሥታችን ይጠበቃል። (ማጣቀሻዎች፡- የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ሪፖርተር፣ አዲስ ዘመን፣ ቢቢሲ…)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
ፍሬው አበበ