እርስዎ በቤትዎ ገንፎ መብላት እያማሮዎት ዱቄት አልቆ ወይንም ደግሞ የሚሠራልዎት ሰው ባይኖር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ባይቻልም፤ ወደ አባጅፋር መንደር ጅማ ከተማ ሲያቀኑ ግን ፍላጎቶንም አምሮቶንም ሊወጡ የሚችሉበት ቤት እንዳለ ልንጠቁሞ እንወዳለን። የፍቅር ከተማ በሆነችው ጅማ ዘወር ዘወር ሲሉ ሥም አልባው ገንፎ ቤት እግር ሊጥልዎት ይችላል። እንደአጋጣሚ ከዚህ ሥፍራ ከደረሱ በሥም የበዙ፣ በአሰራርም ልዩ የሆኑ በመልክ ዓይነተ ብዙ የሆኑ ገንፎዎችን ሊያጣጥሙ ይችላሉ። ከዚህ ሥፍራ ‹‹አንድ ገንፎ በማር በቅቤ፣ አንድ ገንፎ በቅቤ፣ የቡላ ገንፎ፣ የበቆሎ ገንፎ…›› የሚሉ ጥድፊያ የበዛባቸውን ገንፎ! ገንፎ! አሁንም ገንፎ የሚል ትዕዛዝ ሲሰሙ አይገረሙ። ልክ አንድ ቅቅል በቅልጥም ብለው እንዳዘዙት ዓይነት ማለት ነው በጅማ። ይህ ቤት የገንፎ አምሮት ያላቸው ሰዎች ገንፏቸውን ስልቅጥ አድርገው አፋቸውንና አፋቸውን አብሰው ወደሚያስቡት አቅጣጫ የሚያቀኑበት ቦታ ነው።በዚህ ቤት ሲመጡ ሃሳብዎ አንድና አንድ ብቻ ነው።በቃ ገንፎ መብላት።ምን ልብላ፣ ምን ልጠጣ ብለው የምግብ ዝርዝር ‹‹ሜኑ›› እንደሚመጣሎት ዓይነት የምግብ ዝርዝር አይደለም።ቦታው ገንፎ መጋቢ እና ገንፎ ተመጋቢ ሰዎች በአንድ ሥፍራ የሚከትሙበት ነው።
ሰሚራ አህመድ ትባላለች። በተለምዶ የአካባቢው ሰዎች ሰሚራ ገንፎ፣ ሌሎች ደግሞ ቁርስ ቤት ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ምልክት ተጠቅመው ይገባቡበታል። ዞሮ ዞሮ ግን ገንፎ ቤቱ ማለታቸው ነው። ብቻ እንደምንም ብለው ከዚህ ስፍራ ይገናኛሉ። ሰሚራ የገንፎ ንግድን ብድግ ብላ አልጀመረችም። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል እንዲሉ አበው! እርሷም ሥራውን ከእናቷ ወርሳለች። እናቷ በርካታ ዓመታትን ገንፎ እያገነፉ የጅማ ነዋሪዎችን ሲመግቡ ኖረዋል፤ ትርፍ ሳይሆን የዕለት ጉርሳቸውን ብቻ አስበው።እግር ጥሏቸው ወደ አባጅፋር መንደር ጅማ ያመሩ ሰዎችም በሸጋ ቅቤ እና በማር ልውስውስ ያለውን ገንፎ አጣጥመው እያመሰገኑ ተመራርቀው ተሸኛኝተዋል።ሰሚራ አህመድ በጅማ ከተማ ገንፎ እያገነፋች፤ ሰዎችንም እያበላች ይኸው ዛሬ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ ብቅ ብላለች፤ በሚገባ ተዋወቋት።ጅማ ከተማ ኮሚሰሪያት ከሚባለው ሰፈር ከህብረት ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ ካለች አንዲት ደሳሳ መሳሳ ጎጆ በግምት ስፋቷ 30 ካሬ በምትሆን ቤት ውስጥ ያገኟታል።
የሦስት ብር ገንፎ
ገንፎ ቤቱ ሲጀመር ሰዎች ይበሉልናል ብለን ጀመርን፤ እውነትም ብዙ ደንበኞችም አፈራን ትላለች። ‹‹ሀ›› ብለን በሦስት ብር የጀመረነው ገንፎ አሁን ወደ 30 ብር ደርሷል። የበቆሎ፣ የቡላ እና መደበኛ የፉርኖ ዱቄት ገንፎ ይሰራል። በተለምዶ ገንፎ ማባያው ቅቤ ነው። ገቢያቸው አነስ ያሉ ሰዎች ደግሞ ዘይትን በቅቤ ምትክ ይጠቀሙታል። ከጅማው ገንፎ ቤት ግን ለየት ያለ ነገር ነው ያለው።ወለላ ማር እና ቅቤ ተደባልቆ ገንፎውን እያጠቀሱ መብላት ተለምዷል። ሰሚራም ገንፎ በቅቤ በማር፣ ገንፎ በማር፣ ገንፎ በቅቤ እያሏት ያዟታል። እርሷም ወደ ማዕድ ቤቱ ቱር! ብላ ገብታ ትኩስ ገንፎ ዛቅ አድርጋ፣ ከማር ከቅቤ ቆንጥራ ታቀርባለች።ጅማ በገንፎ ንግድ ብቻ ሳይሆን የገንፎ ማጥቀሻን ከቅቤ ወደ ማር አሸጋግራ አዲስ የመአጋገብ ባህል ይዛ ብቅ ያለች ይመስላል።
ድሃ ካልበላ ጉድ ፈላ!
ድሃ ካልበላ ምኑን ስራ ተባለ፤ ምኑንስ አተረፍን ስትል ድሆችን ያማከለ ስራ እንደሚሰሩ ትናገራለች-ሰሚራ።ብዙ ጊዜ ሰዎች እየበሉም ገንዘብ የለኝም ይላሉ።ያው ሰው ካልቸገረው እንዲህ አያደርግም።ታዲያ እነዚህን ሰዎች ማሸማቀቅ አግባብ አይደለም።ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች ማሳሰር ወይንም መጥላት ትርፉ ምንድን ነው? እነዚህን ሰዎች ማሳደድና ማዋረድ ከፈጣሪ ዘንድ ምን ያስገኛል? ዓለም ደጎችና ሀብታሞችን እቅፍ አድርጋ የያዘች መሆኑን ብገነዘብም፤ እኔ ግን ድሆችን አቅርቤ ችግራቸውን መጋራት እመርጣለሁ የምትለው ሰሚራ፤ ዛሬ በልተው ከሌላቸው ነገ እንደሚከፍሉ ስለማምን አልጫናቸውም ትላለች።ሰዎች ከአቅማቸው በላይ ካልሆነ እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ አይገቡም።ስለዚህ በሰው ልጅ ደካማ ጎን ማላገጥ ከፈጣሪ መጋጨት ነው ትላለች።
የሰው ችግርን ማቃለል ደግሞ ከፈጣሪ ዘንድም በረከት የሚገኝበት ሰብዓዊነትም የሚታይበት ነው።የሰው ልጅ ‹‹ዱኒያን›› ወይንም ምድራዊ ሕይወትን ብቻ እያሰበ የሚኖር ከሆነ የሰዎች ባህሪ ሳይሆን ለሆዱ የሚኖር እንስሳ ሆኗል ማለት ነው።ምንም እንኳን ገንፎውን የምነግደው ለማትረፍ ቢሆንም ሰዎች ሳይኖሩ ብር ብቻውን ዋጋ የለውም ትላለች።
700 ደንበኞች በቀን
በየቀኑ ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ ሰዎች ወደዚህ ገንፎ ቤት ብቅ ይላሉ።ይህ ቤት እንዲሁ የዋዛ አይደለም።እነዚህ ደንበኞችን ከማስናገድም በተጨማሪ ሌሎች ደንበኞች እንደሚመጡ ታሳቢ ሲያደርጉ ደስታው ወደር የለውም። በዚህ ስሟ በውል በማይታወቀው ገንፎ ቤት ሰሚራን ጨምሮ 15 ሰዎች ነው የሚተዳደሩበት። ማዕድ ቤት ውስጥ ያሉትን ሦስት ሠራተኞችንም ልክ እንደቤተሰቧ ትመለከታቸዋለች። ታዲያ በዚህ ቤት ውስጥ የሚስተናገዱ ደንበኞች በቀን ከ500 እስከ 700 ሰዎች እንደሚደርሱ ትናገራለች።
ደንበኞች ምን አሉ?
የገንፎ ቤቱ ደንበኞች ይህን ቤት ከቤታቻው ባልተናነሰ መልኩ በየቀኑ እየተመላለሱ ይጎበኙታል። አብዝተው ስለሚወዱትም ገንፎ ባይመገቡ እንኳን በዚህ አካባቢ ተቀጣጥረው የግል ጨዋታቸውን ተጫዋውተው፤ ሐሳብ ተለዋውጠው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ። እንግዳ ሲመጣባቸውም ገንፎ ልጋብዝህ ብለው ወደዚህ ስፍራ ይዘው ይመጣሉ።ወደ ካፌ ከማቅናት ይልቅ ይህን ገንፎ ቤት ይመርጣሉ።ብቻ ይህ ስፍራ ለበርካቶች የትዝታ መነሻ፣ የሕይወታቸው መሰረት ሆኖ ዛሬም አለ። ይህ ሥም አልባው ገንፎ ቤት ግን ለበርካታ ሰዎች ሥም መተዋወቂያ ሆኖ፣ ለበርካቶች ስም ከፍ ብሎ መጠራትም ወሳኝ ቦታ ሆኗል። ሥም የሌላቸው ሰዎች ይህ ገንፎ እየበሉ ክፉ ቀናቸውን አሳልፈው ስማቸው ገንኖ የሚጠራ ሆኗል።
የዛሬ 15 ዓመት በዚህ ቤት ገንፎ ማጣጣም የጀመረው አብዲ አባነጋ ‹‹እዚህ ቤት ስመጣ ፀጉሬ ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ነበር።አሁን ግን በግማሽ ነጭ ሆኗል። በዕድሜም ከልጅነት ወደ ጎልምሳናት ተሸጋግሬያለሁ። ነገር ግን ጣዕሙ እና አሠራሩ ያልተቀየረው የእነ ሰሚራ ገንፎ ጣዕምና አሰራር ነው›› ሲል አሰራራቸውና ሥራቸው ጣዕሙን ጠብቆ እንደቆየ ይነገራል።እርሱ ከዚህ ገንፎ ትልቅ ትዝታ አለው። ብዙ የችግር ጊዜውን በዚህ ቤት አሳልፏል።ትንሽ ሳንቲሞችን ይዞ ከዚህ ቤት ብቅ ይላል።በጠዋት በቅቤ የተለወሰ ገንፎ በልቶ ወደ ቀን ውሎው ያመራል።እርሱ ይህ ቤት በዚሁ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምኞቱ ነው።
‹‹ይህን ገንፎ በምላሴ አጣጥማለሁ፣ ስለቤቱ በአዕምሮዬ አስባለሁ፣ ስለሰዎቹ መልካምነት ደግሞ አሏህን አመሰግናለሁ›› የሚለው ደግሞ ወጣት ቶፊቅ አበዱልጀባር ሲሆን እርሱም ቤቱ በእጅጉ ተወዳጅ እንደሆነ ይናገራል።
የሰሚራ እቅዶች
ሰሚራ በዚህ ሥራ አልተሰላቸችም።በአሁኑ ወቅት የምትሰራበት ቤት በኪራይ ቢሆን በቀጣይ በራሷ ቤት የመስራት ውጥን አላት።በዚህ ገንፎ ሥራ በቃኝ ብሎ ሳይንስ የለም።ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች የገንፎ አምሮታቸውን እንዲወጡ አድርጋ መቀጠል ተፈልጋለች። የገንፎ ገበያ አድጎም የጅማ አንዱ መታወቂያዋ እንዲሆን ትፈልጋለች። የጣፈጠ ገንፎ፤ የጣፈጠ ሥራ፤ የጣፈጠ ህልም እንዳላቸው የምትናገረው ሰሚራ ገና ምን ሠርቼ ትላለች። ብዙ ጊዜ ከገንዘብ አሊያም ከትርፉ በላይ ድሆች ሲመገቡ ማየት የሚያስደስት በመሆኑ ኑሮ ውድነቱ ምንም ጣሪያ ቢነካም ዋጋ ከመጨመር ይልቅ ባለው ሁኔታ አቻችሎ ለመስራት ታስባለች። ደንበኞቹ እየበዙ በሄዱ ቁጥር የገንፎ ዓይነትም እያበዙ መሄድም የሰሚራ ውጥን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር