አዲስ አበባ አይደለም ለኖረባት አንድ ቀን በጉያዋ ለዋለባትና ላደረባት ሰው የደንብ አስከባሪዎችንና የነጋዴዎችን የሌባ እና ፖሊስ አባሮሽ ማስተዋል አይከብደውም። አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ከሸገር ጎዳናዎች አንዱ በሆነው መገናኛ አካባቢ የተገኘ ሰው ልጅነቱን የሚያስታውስበት የ‹‹አኩኩሉ›› ጨዋታ ሳይመለከት በፍጹም አይመለስም። በየዕለቱ ግርግር የማያጣው ይህ አካባቢ ከስራ ወደ ቤት ለመሄድ በሚቸኩሉ እና ታክሲ በሚጠብቁ ሰልፈኞች ከመጨናነቁ በተጨማሪ ሁልጊዜም በጎዳና ላይ ነጋዴዎች የተሞላ ነው። በተለይ የደንብ አስከባሪዎችና የጎዳና ላይ ንግዱን የሚያጧጡፉ ነጋዴዎች የሌባና ፖሊስ ትዕይንት እጅጉን አስደማሚ ነው። ሩጫና ግርግሩ ስንቱን “ባለሀብት” እንዳደረገ፤ ስንቱን ደግሞ ኪሱን እንዳራቆተ መገናኛና መሰሎቹ ምስክር ናቸው።
ቋሚ መሥሪያ ቦታ ሳይኖራቸው ሕዝብና ተሽከርካሪ በሚንቀሳቀስባቸው ጎዳናዎች የተለያዩ የግብይት እቃዎችን ይዘው ከአላፊና ከአግዳሚው ጋር መገበያየቱ እንግዳ ነገር አይደለም። የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የሞባይል ጌጣጌጦች፣ ሶፍት፣ ወረቀቶች፣ ማስቲካ፣ ከረሜላ፣ ሲጋራ፣ ወዘተ. የመገናኛና መሰል ጎዳናዎች የእለት ተዕለት ንግዶች ናቸው። በዚህም የተነሳ ለእግረኛ ተብሎ የተሰራውን መንገድ ለመርገጥ መብት ብሎ ነገር የለም። እንደውም አብዛኛው ሰው የመኪናውን መንገድ በእግሩ እንዲሄድበት ይገደዳል።
ትዕይንቶች
በነዚህ አካባዎች በተለይ መሸት ሲል የእግረኛው መንገድ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የደራ ገበያ ስፍራ ይሆናል። በነጋዴው እና በደንብ አስከባሪው መሃል ያለውን አስገራሚውን አባሮሽ ተሽከርካሪ ቦታ ላይ ቆሞ የተመለከተ እግረኛ ለነጋዴው በመቆርቆር ‹‹ደሃ ሰርቶ እንዲበላ የማይፈለግበት አገር ›› ብሎ ይተቻል። ትችቱን ሳይጨርስ በመኪና ይገጫል። የጎዳና ላይ ንግድ በመዲናዋ ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ መካከል በዋነኝነት የትራፊክ አደጋ ተጠቃሽ ነው። በአሁኑ ወቅት ለትራፊክ አደጋ መነሻ ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዱ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላትና ብሎም በቂ የሆነ የእግረኛ መንገድ አለመኖር ነው። ይሁንና አሁን ላይ እንደምንታዘበው ከሆነ የእግረኛ መንገድ ባላቸውም ሆነ በሌላቸው አውራ ጎዳናዎች ላይ የንግድ እንቅስቃሴ በመኖሩ የተነሳ እግረኞች በተሽከርካሪ መንገዶች ላይ እንዲጓዙ እየተዳረጉ ነው።
የእግረኛ መንገዶች አገልግሎታቸው ወይም የተገነቡበት ዋና ዓላማ ከትራንስፖርት ወርደው ወይም ለመሳፈር ለሚጓዙ እግረኞች ሳይሆን ለጎዳና ላይ ነጋዴዎች እንዲሁም በልመና ለሚተዳደሩ ታስበው የተገነቡ መምሰል ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ዓይን ውስጥ ከገቡት ጎዳናዎች መካከልም የመገናኛ፣ ሳሪስ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ …. አካባቢዎች ይጠቀሳሉ።
በከተማችን የሚታየው የጎዳና ላይ ንግድ የከተማዋ ቁልፍ ችግር ሆኖ ከከተማዋ ጋር ተጣብቆ ጉዞውን በመደበኛነት ከቀጠለ ቆይቷል። ችግሩ እየሰፋ ቢሄድም ከከተማዋ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር ተዋህዶ መደበኛ የሥራና የኑሮ አካል ወደ መሆኑም ደረጃ ደርሷል። እንዲያውም አሁን አሁን ላይ ደግሞ ችግሩ ከጎዳና አልፎ ሌላ መዘዝ ሲያመጣ የምንታዘብበት አጋጣሚ በዝቷል።
‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› በሚል ማስፈራሪያ ባልታወቁ አካላት ንብረታቸው ተዘርፎባቸው ‹‹ወረዳ ውስጥ ታግዶ ነው›› የሚል ምላሽ የሚያገኙ ስንቶች አሉ መሰላችሁ። በግልጽ ብር አምጡ እየተባሉ መሆናቸውን በምሬት የሚገልጹ ነጋዴዎችም አልጠፉም። የመንገድ ላይ ቸርቻሪዎችን በአስፈላጊው የህግ አግባብ እንደመቅጣት አብረው በመመሳጠር ትስስር ፈጥረው የሚነግዱ ብዙ ደንብ አስከባሪዎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። (ታዲያ ለእነዚህ ደንብ አስከባሪዎች ሌላ ደንብ አስከባሪ አያስፈልጋቸውም ትላላችሁ፤)
የጎዳና ላይ ንግድን ‹‹የቀን ሌብነት ማስፋፊያ›› መሆናቸውን የተገነዘበ የመንግስት አካል ቢኖር በከተማችን የሚካሄዱትን ሥርዓት አልባ የጎዳና ላይ ንግዶች የሚከለክል ጠንካራ ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከነጋዴው እስከ ደንብ አስከባሪውም ጭምር የማያዳግም እርምጃ በወሰደ ነበር።
እስኪ ለአፍታ ዞር ዞር ብላችሁ ተመልከቱ መሐል አስፋልት ራሱን እንደሳተ ሰው ‹‹ፖሊስ መጣ…›› እያሉ ጨርቃ ጨርቅ እየጎተቱ ከወዲያ ወዲህ ከተማዋን የሚያውኩና የትራንስፖርት ሥርዓትን ጭምር በማዛባት ሌብነትን የሚያበራክቱ ትዕይንቶች በርካታ ናቸው።
ንግድ በመስቀለኛ መንገድ ላይ በማድረግ ለሂያጅ መጭው እንቅፋት መሆን በሁሉም አፍ ከመረገምና የራስን የኑሮ ዕድሜ ከማሳጠር ውጭ ምን ይፈይዳል። ነጋዴዎችስ ቢሆኑ የእግረኛውን መንገድ የግል ንብረታቸው አስመስለው ዘግተው የያዙት መንገድ የወላዶችም፣ የሐዘንተኞችም፣ የሕመምተኞችም በአጠቃላይ የሁላችንም መጠቀሚያ መሆኑን መገንዘብ እንዴት ተሳናቸው።
መንግስት ነጋዴዎች ከገዥ ጋር የሚገናኙበትን እንደ ‹‹ሰንደይ ማርኬት›› አይነት አማራጮችን ሰጥቷቸው ሳለ ጎዳናን ሙጥኝ ማለታቸው ለምን እንደሆነ አይገባኝም። ግብር መክፈል ተስኗቸው ይሆን ወይ የሚል ጥርጣሬ ግን አለኝ። ከዚህ ውጭ ሆኖ ‹‹አእምሮአችን ዳብሯል፤ ከመንገዳችንም አንወጣም›› ካሉ ደግሞ እነርሱን ብቻ የሚያገለግል መንገድና አደባባይ መሥራት ይኖርብናል። እንደውም ታዋቂ ሰዎች በየሰፈሩ በስማቸው መንገድ ሲሰየምላቸው በከተማችን ለጎዳና ላይ ነጋዴዎችና ለህገ ወጥ ህግ አስከባሪዎች ቢያንስ አንድ መንገድ ቢሠራላቸው ብርቅ ነው እንዴ? ይህ መንገድ እስኪሠራላቸው ግን በጎዳና ላይ ንግድ ጎርፍ እንዳትወሰድ ጥግህን መያዝ ነው።
ማንኛውም አካል የንግድ ቢሮ ሳያውቀው በራሱ ፈቃድ በተጨማሪም ተገቢ ያልሆነ እቃ ይዞ በጎዳና ላይ የተገኘ፤ ጎዳና የተሰራው ለሕዝብ መገልገያ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ዕቃ ይዞ ለተገኘ ሰው ሕገ ወጥ ነጋዴ የሚለው ስም እንደሚሰጠው ቢታወቅም፤ ስሙን ከማከናነብ ይልቅ ተግባሩን ግን ማስቆም አልተቻለም።
ደንብ አስከባሪ ነን ባዮች ደግሞ ለይምሰል እኮ ነው የሚያባርሩት። አንድ ሁለት ጊዜ ቦታውን እንደመቃኘት ይሉና መለስ ይላሉ። ያው የመንግስት ሥራ አይደል አልተቆጣጠራችሁም እንዳይባሉ ነው። ታዲያ ይህችን ትዕይንት ካሳዩ በኋላ ነጋዴውና ደንብ አስከባሪው የሽያጩን ትርፍ ሂሳብ የሚያወራርዱበት መስመር ደግሞ አለ። እኛ አገር እኮ ለሌብነት የሚዘረጋው ሲስተም ኅልቁ ወመሳፍርት ነው።
ከደንብ ማስከበር ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ እንዲህ ደንብ አስከባሪዎች ተብለው የሚመደቡ አካላት ህገ ወጥ ንግድ የሚካሄድባቸው መንገዶችን በየዕለቱ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው የሆነ ቀን ያውም በተወሰነ ስዓት ብቻ መጥተው ነጋዴዎችን ማባረር አንድ አንዴም ዕቃዎቻቸውን መውሰድ ብቻ ላይ መሰማራታቸው አንዳንዴም ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ እንደሚካሄድ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ከሚታዩባቸው ችግሮች ውስጥ ናቸው። (በነጋዴዎችና በደንብ አስከባሪዎች ቋንቋ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ማለት ከሸጥከው ላይ የድርሻዬን አስቀምጥልኝ እንደማለት ነው)
የደንብ አስከባሪው አልበቃ ብሎ በየጎዳናው ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በማባረር የነጋዴዎቹ እቃዎች በየቦታው ሲንጠባጠብ ለሌላ ዘራፊ የሚያጋልጡ፣ ትዕይንቱን በተመስጦ ውስጥ ሆኖ ሲመለከት የነበረ ግለሰብን ኪስ የሚያራቁቱ ህግ አስከባሪ ነን ባዮችስ መች ጠፉ። አንድ ህግ አስከብራለሁ ያለ ሰው ይህንን የአደባባይ ሌብነት ሲፈጽም ምን ያህል አገሪቷ ላይ በደል እያደረሰ እንደሆነ ለማሰብ አልበቃ ከሆነ ለአቅመ ህግ አስከባሪነት መድረሱን እጠራጠራለሁ። እነዚህ አካላት አንዳንዴ የደንብ ልብስ ሳይለብሱ መማታትና ዕቃ መድፋትም ዋና ሥራቸው ነው። ከዚህ የሚያተርፉት ደግሞ ነጋዴው በፍራቻ እቃውን ጥሎ ስለሚሄድ በስውር በማሸሽ እቃውን የግል ንብረታቸው ማድረግ አሊያም ከነጋዴዎቹ ያለ መንግስት እውቅና ብር ተቀብለው እቃውን ለመመለስ መደራደር ነው።
በሀገራችን ኢትዮዽያ ህገወጥ የጎዳና ላይ የንግድ ስራ ስር እየሰደደ መምጣቱ በሀገሪቷ ላይም ሆነ በህጋዊ መንገድ በሚሰሩት ነጋዴዎች ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ እሙን ነው። ህገ ወጥ ንግድ እና መዘዙ ለአንድ ሀገር እድገት አሉታዊ አስተዋፅዎ ከሚያደርጉ ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል። የንግድ ዘርፍ በሀገር እድገት ላይ የሚያመጣው ጥቅም ከፍተኛ ቢሆንም ይህንን የተዘረጋ የንግድ ዘርፍ የሚጣረስ በየጎዳናው የሚስተዋል ችግር አለ።
ጎዳናዎች በተለይም የእግረኛው መንገዶች በእነዚህ ህገ ወጥ ነጋዴዎችና ሸቀጦቻቸው ስለሚሞሉ እግረኞች ዋናውን (የተሽከርካሪ) መንገዶችን እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ። በዚህም የተነሳ የትራፊክ መጨናነቅ ብሎም የትራፊክ አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።ሌላኛው ችግር ይህ የጎዳና ላይ ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ተደርጎበት በቁጥጥር ስር እስካልዋለ ድረስ ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት አይነተኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ሌላ መዘዝ
አብዛኛው የመንገድ ላይ እቃዎች የውጪ ሀገር ምርቶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ የውጪ ሀገር ምርቶች እንዴትና ከየት መጡ ተብሎ ሲታሰብ አንደኛ የጥራት ደረጃ ያላሟሉ እቃዎች እንደመሆናቸው መጠን በህጋዊ መንገድ አለመግባታቸው የሚያጠያይቅ አይሆንም። በዚህ መልኩ የሚገቡ እቃዎች ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በዝቅተኛ ዋጋ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ስለሚደረጉ በቀላሉ በህገወጥ ነጋዴዎች እጅ ይገቡና በርካሽ እንዲሸጡ ይሆናል።
በእርግጥ በሱቅ ከሚሸጡት ተመሳሳይ እቃዎች እነዚህ የመንገድ ላይ እቃዎች በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡበት ሌላ ምክኒያትም አለ። እነዚህ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች የቤት ኪራይ፣ የገቢ ግብር እንዲሁም እቃዎቻቸው ሲያስገቡም ያለምንም የቀረጥ ግብር ስለሚገቡ ማለትም በህገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ መልኩ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያደርጓቸው በዝቅተኛ ቢሸጡም አዋጭነታቸው የሚያጠያይቅ አይሆንም።
ምን ይደረግ
ለነዚህ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችም ሊታሰብ ይገባል። በጎዳና ላይ እንዳይነግዱ መከላከሉ አንድ ነገር ሆኖ ነገር ግን ሲከለከሉም እስከ አማራጭ መሆን ይኖርበታል ። እነዚህ በጎዳና ላይ የሚነግዱ ሰዎች ስራ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ሊፈጠርላቸው ይገባል። ይህም በጎዳና ላይ ንግድ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ከሚል ዓላማ ብቻ ሳይሆን እነዚህም ዜጋዎች ናቸውና ስራ የመስራት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። ይህም እንዲደራጁ ዕድል መፍጠር ወይም ማደራጀት ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ። ይህ ህገ ወጥ የንግድ ስራ እየቀጠለ ከመጣ የሀገራች መፃኢ ዕድልን ሊያጠለሹ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል።
በእርግጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ብዙ መከራና ፈተናዎች ይገጥማቸዋል። ደንቦች ቅጽበታዊ በሆነ ግርግር መሀል ከመዘረፍ ጀምሮ ለመኪና አደጋ እስከ መጋለጥ ይደርሳሉ። ይህ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። ህጋዊ ፈቃድ ሳይገኙ እየሰሩ ካሉት የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ውስጥ ህጋዊ ሆነው እንዳይሰሩ አቅማቸው የማይፈቅድም አሉ። በህጋዊ መንገድ ለመስራት ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። የንግድ ቦታ ተከራይተው መስራት ይከብዳቸዋል። የሚሰሩበት ቦታ ተሰጥቷቸው በህጋዊ መንገድ መስራት እንዲችሉም ጆሮ ያለው መንግስት ይስማ።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
አዲሱ ገረመው