አንዲት የ12 ዓመት ልጅ ኩላሊት፣ እጢ፣ ኤች.አይ.ቪ፣ የሳንባ ምችን ጨምሮ ወደ አምስት በሽታ ነበረባት። ይህች ልጅ ደግሞ በበሽታ መሰቃየቷ ሳያንስ በመንገድ ላይ ወድቃ አንድ ወጣት ታገኛትና ወደቤቷ ይዛት ትሄዳለች። የዚህች ወጣት ጓደኞችም ይችን ታዳጊ ለመርዳትና ለማሳከም ይወስናሉ። እነዚህ ጓደኛሞች በቴአትርም፣ በቪዲዮና መሰል መስኮች የተመረቁ ስለነበር፤ ለዚህች ልጅ ማሳከሚያ ዶክመንተሪ ሰርተው ገቢ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። ሆኖም ዶክመንተሪው በተቀረጸ በሁለተኛው ቀን ልጅቷ አረፈች።
ሁኔታው አሳዛኝ ቢሆንም አንዴ ገቢ ማሰባሰቢያው ስለተዘጋጀና እናትዬዋም ችግር ላይ ስለነበሩ የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የስነጽሁፍ ምሽት እንዲካሄድ ተደረገ። ገቢ ማሰባሰቢያውም ሁሉንም እንዲያሳትፍ በማሰብ በ25 ብር መግቢያ ‹‹ዝክረ ቅድስት›› በሚል ተካሂዶ 20 ሺህ ብር ያክል ተሰበሰበ። በዚህም እናትዬዋና ከእርሷ ውጪ ያሏቸውን አራት ያክል ልጆች ይዘው ጎዳና ወጥተው ስለነበር እርሳቸውን ወደቤት በማስገባት ምን መስራት እንደሚችሉ በመጠየቅ ስራ እንዲጀምሩ ያደርጓቸዋል።
ከዚህ በኋላ እነዚህ ወጣቶች ቆም ብለው ማሰብ ይጀምራሉ። እንደቅድስት አይነት በርካታ ህክምና የሚፈልጉ ግን በችግር መታከም ያልቻሉ፤ እንደ ልጅ በሰፈራቸው ተጫውተውና ተምረው ማደግ የሚሹ ነገር ግን እጣ ፈንታቸው ከጎዳና የሆነ፤ ብዙ ህጻናት አሉ። ጧሪ ቀባሪ ያጡ፣ ራሳቸውን ማገዝና ከመንገድ የወደቁ አዛውንትና ወጣቶችም መኖራቸውን ተገነዘቡ። እናም በቅድስት ምክንያት እናቷን በዚህ መልኩ አግዘው ቤት ማስገባትና ሰርተው እንዲለወጡ ማድረግ ከቻሉ፤ እነዚህን ወገኖችም መደገፍና ከችግራቸው እንዲላቀቁ ማድረግ እንደማያቅታቸው በወጣት አእምሯቸው አመኑ። ተሰባስበውም በህይወት ዘመናቸው አንድ ቁምነገር ለመስራት ወስነው 13 ሆነው በወርሃ መስከረም ‹‹ቁምነገር የበጎ አድራጎት ማህበር››ን መሰረቱ።
ይሄን አጋጣሚ በማስታወስ ስለማህበሩ አመሰራረት፣ ዓላማና ጉዞ የሚናገረው ወጣት አቤል ጌታሁን፣ የቁምነገር በጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዚዳንት ነው። እርሱ እንደሚለው፤ ሰው የተወለደው በምክንያት እንደመሆኑ በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ቁም ነገር ሰርቶ ማለፍ አለበት። “ሰው ያለሰው መኖር ስለማይችልም፤ እኛ እንደወጣት ቢያንስ በዘመናችን አንድ ቁም ነገር ሰርተን እንለፍ የሚል ሀሳብ ይዘን ነው ወደስራ የገባነው” ይላል። ይሄን ዓላማ በመደገፍም በ13 ሰዎች የተጀመረው ጉዞ አሁን ላይ 150 አባላትን ማፍራት ችሏል። የማህበሩ አባላት ደግሞ አብዛኞቹ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎችም ናቸው። እናም ገቢውንም ድጋፉንም ለማሳደግ የገቢ ማሰባሰቢያ ትኬቶችን ከመሸጥ ጀምሮ የሊስትሮ ስራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ለዚህ ስራቸው ደግሞ የአባላት ቁጥር እየተበራከተ መምጣት የጠቀማቸው ሲሆን፤ ጊዜያቸውንም አቅማቸውንም በአግባቡ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል።
‹‹እኛ ለመብላት መስራት ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ የምንበላውም የምንሰራውም የምንኖረውም በትርፍ ጊዜያችን አይደለም፤›› አይደለም የሚለው ወጣት አቤል፤ ሌሎችን ለማኖርም ሆነ ለማብላት ስንል የምንሰራው ስራ በትርፍ ጊዜ እንደሚሰራ ሳይሆን ጊዜን ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አምነው ከትምህርታቸው የሚቀራቸውን ጊዜ በሙሉ እንደ መደበኛ ተግባራቸው ቆጥረው እንደሚያከናውኑ ይገልጻል። ምክንያቱም ለትምህርት፣ ለስራ፣ ለቤተሰብና ሌላም ጉዳዮቻቸው ጊዜ እንደሚሰጡ ሁሉ ለሚደግፏቸው ሰዎችም ጊዜ መስጠት እንዳለባቸው አምነው ሁሉም አባላት ያላቸውን ጊዜ ቁምነገር ላይ እያዋሉ ስለመሆኑም ይናገራል።
በእስካሁኑ ጉዟቸውም ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ ወገኖችን ወደቤት በማስገባት ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ችለዋል። እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ከፍለው የሚያስተምሯቸው ገንዘብ የሌላቸው ተማሪዎችም አሏቸው። ራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገርም ሆነ በራሳቸው አቅም ታግዘው የሚረዷቸው በፌስቱላ የተጠቁና የካንሰር ህመምተኞችም አሉ። በህመም፣ በእርጅናና በሌላም ምክንያት ወጥተው መስራት የማይችሉ ስድስት ቤተሰቦችንም በየወሩ የቤት ኪራይ በመክፈል፣ የምግብ ወጪ በመሸፈንና ሌላም ድጋፍ በማድረግ በቋሚነት ይደግፋሉ። የወደቁና የፈረሱ ቤቶችን የማደስና የመጠገን የበጎ ፈቃድ ተግባርም ያከናውናሉ። በተለያየ ምክንያት ከክልሎች እየተታለሉ የሚመጡ ሴት እህቶችን ወደቤተሰቦቻቸው የማድረስ ስራም ያከናውናሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ ከባለፈው ዓመት ገና ጀምሮ በክርስቲያንም በሙስሊምም በዓላት አቅም ለሌላቸው ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ቤተሰቦች ሙሉ የበዓል ወጪያቸውን የመሸፈን ተግባር እያከናወኑም ይገኛሉ። በዚህ ተግባራቸውም ለ20 እና 30 ዓመት ሌላው ቀርቶ ዶሮና እንቁላል በልተው የማያውቁ አረጋውያንና ቤተሰቦችን አግኝቶ የመደገፍ እድል የገጠማቸው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ትልቅ የመንፈስ እርካታንም ደስታንም የሚፈጥር ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ካለው ላይ ሳይሰስት የሚሰጥ ቸር ህዝብ ነው። በገንዘብ ማገዝ ቢያቅተው እንኳን አዳምጦ መረዳት የሚችል ነው። በዚህ መልኩ የማህበሩንና አባላቱን ሀሳብ ተገንዝበው የሚያግዙ በርካታ ቢሆኑም፤ በቋሚነት የሚረዳን ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም። ይሁን እንጂ ማህበሩን ለማገዝ የሚተጉ የመኖራቸውን ያክል በዛው ልክ የማህበሩን አባላት ከስድብ ጀምሮ እስከ ትንኮሳና ሴቶቹን ‹‹ካልሳምሺኝ አልተባበርሽም›› እስከሚል ግብረገብነት የጎደለው ስብዕና የሚገለጽባቸው ሰዎች አልታጡም። ይህ ግን ካለማወቅና ካለመገንዘብ የመነጨ ነው። እናም ለመልካም ስራ በሚደረግ ሂደት መሰል ችግር ማጋጠሙ የሚታወቅ እንደመሆኑ አባላቱ የበለጠ ለማስረዳትና ስራቸውን ለማከናወን እየተጉ ይገኛሉ።
የኮሌጅ ተማሪና የቁም ነገር የበጎ አድራጎት ማህበር አባል የሆነችው ወጣት መቅደስ አዲሱ እንደምትገልጸው ደግሞ፤ የዚህ ማህበር አባል በመሆኗና ሰዎችን መርዳት እንድትችል እድል በማግኘቷ እጅጉን ደስተኛ ናት። ምክንያቱም ማህበሩም የተቸገሩ ሰዎችን መደገፍ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ሲሆን፤ አባላቱም በዚህ መልኩ ሊስትሮ እየሰሩ ጫማ በመጥረግ የታመሙ ይጠይቃሉ፤ የተራቡን ያበላሉ፤ የታረዙንትም ያለብሳሉ፤ በችግር ውስጥ ያሉም ራሳቸውን እንዲችሉና ለቁም ነገር እንዲበቁ ያግዛሉ፤ በበዓል ወቅትም አቅም የሌላቸውን እየጎበኙ አለንላችሁ በማለት የበዓል መዋያ ይሰጣሉ፤ አብረውም ያከብራሉ። አጠቃላይ ሰዎች በችግራቸው ምክንያት ከሚሰማቸው ሀዘንና ቁዘማ ወጥተው ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆኑ ማገዝ ላይ አተኩረው ይሰራሉ።
እንደ ቁም ነገር ማህበር መልካም ዓላማን ሰንቀው እየሰሩ ሲሆን፤ ለዚህ ዓላማቸው መሳካትም ህጻናትና አዛውንቶችን ብሎም በተለያየ መልኩ ራሳቸውን ማገዝ ያልቻሉ ሰዎችን ከመደገፍ ባለፈ መሃል ላይ ያሉ ሰዎች (ወጣቶች) ላይ ትኩረት አድርገው ነው የሚሰሩት። አባላቱም እንደ ማህበሩ ስያሜ ሁሉ ቁም ነገር ለመስራት ተዘጋጅተው የተሰባሰቡ እንደመሆናቸው ሁሉም ያላቸውን ጊዜ በአግባቡ ለዚሁ ዓላማ እያዋሉት ይገኛሉ። እርሷም ለስራው ካላት ፍላጎት የተነሳ ከትምህርት ውጪ ያላትን ጊዜ እዚሁ ላይ ታሳልፋለች። አብዛኞቹም ተማሪ እንደመሆናቸው ከትምህርት ቤት እንደወጡ በዚሁ ስራ ላይ ይገኛሉ።
ስራው ለህሊና እረፍትና እርካታ ያለው ቢሆንም በርካታ ፈታኝ ነገሮች እንዳሉት የምትገልጸው ወጣት መቅደስ፤ ሀሳቡን ተረድተው ደስ ብሏቸው ጫማ የሚያስጠርጉና ከሚገባው በላይ የሚደግፏቸው ሰዎች እንደመኖራቸው ሁሉ በዛው ልክ ሀሳብና ዓላማው ያልገባቸው ሰዎች ደግሞ ከስድብ እስከ ትንኮሳ የሚያደርሱባቸው ስለመኖራቸውም ትናገራለች። ሆኖም ማህበሩ በተለያየ ምክንያት ከቤት ወጥተው በጎዳና የወደቁትንም ሆነ ቤታቸው ውስጥ ሆነው አስታዋሽ ያጡ እንዲሁም ራሳቸውን ማገዝ ያቃታቸውን ወገኖች የማገዝ ዓላማን ይዞ እየሰራ እንደመሆኑ ሊታገዝና አባላቱም ሊበረታቱ እንደሚገባቸው ትገልጻለች። እናም ከቤተሰብ ጀምሮ በፍቅር ማጣትም ሆነ በገንዘብ ማጣት ወደ ጎዳና የሚወጡ ህጻናትም ሆነ አዛውንቶችን እንዳይኖሩ መስራት፤ በችግር ምክንያት ለጎዳና እንዳይዳረጉ ማስቻል፤ ሁሉም በቤቱ ሆኖ የሚደገፍበትንና ራሱን ችሎ ሌሎችን የሚያግዝበትን እድልም መፍጠር የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ትናገራለች።
የእነዚህን በጎ ፈቃደኝነት ሀሳብ ደግፈው ጫማቸውን ሲያስጠርጉ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል አቶ ይስሐቅ እንድርያስ እንደሚሉት፤ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች አግኝተው አዋሩኝ፤ ጫማ አስጠርጌም በምከፍለው ሂሳብ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እርዳታ እንደሚያደርጉ ነገሩኝ። ይህ ደግሞ ቀና ተግባር ስለሆነ እኔም ሀሳባቸውን ለመደገፍ ጫማዬን አስጠረግሁ። ምክንያቱም ወጣቶቹ ቤተሰብ የሌላቸውን፣ ደጋፊ ያጡ፣ የታመሙ፣ በጎዳና ላይ ያሉ ልጆችንና ሌሎችንም ችግረኛ ቤተሰቦች እንደሚረዱ፤ ለዚህም በተለያየ ቦታ መሰል የበጎ ፈቃድ ስራ እየሰሩ ገቢ እንደሚያሰባስቡ ስለነገሩኝ ነው አጋዥ ለመሆን ነው እሺ ያልኩት።
ምክንያቱም አሁን ላይ በአገራችን እያጣን ያለነው ነገር ሰብዓዊነት ነው። ሆኖም ከህግም ሆነ ሌሎች ነገሮች በፊት ቀድሞ ሊመጣ የሚገባው ነገር ሰብዓዊነት ነው። እናም ለሰብዓዊነት የሚደረጉ ነገሮች ለአገርም ሰላም መሰረት ናቸው፤ ለፖለቲካውም ሆነ ለኢኮኖሚው መረጋጋት የሰው ልጅ የሰብዓዊነት ስሜት ወሳኝ ነው። ሰዎች ሰብዓዊነት በተሰማቸው ቁጥር እርስ በእርሳቸው ይደጋገፋሉ፤ ማህበራዊ ትስስራቸው ይጠነክራል። ይህ በመተሳሰብና በመደጋገፍ የሚመራ ማህበራዊነት ደግሞ የኢኮኖሚውንም ሆነ የፖለቲካ ትርምሱን ያረጋጋዋል። እናም በዚህ መልኩ የሰብዓዊነት አቀንቃኝ ወጣቶች መፈጠር በኢትዮጵያ ወደፊት የተሻለ ነገር እንደሚመጣ እንድንጠብቅ ያደርገናል።
ይህ ተግባር ደግሞ ወጣቶች አሁንም ቁም ነገር መስራትም ማድረግም እንደሚችሉ ያሳየኝ፤ ከምንም በፊት ሰብዓዊነትን አስቀድሞ መስራት እንደሚገባ ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ነው። በመሆኑም የእነዚህን ወጣቶች መደገፍ፤ የመልካምነት ጉዟቸውንም ማቅናት እንጂ ባልተገባ መንገድ ከቀናው መንገዳቸው ማውጣት አይገባም። ለምሳሌ፣ ትጉህ የሚባለው የጉንዳን ሰልፈኛ ከፊት ያለው በሚመራው መንገድ ነው የሚፈልግበት ቦታ ሊደርስም ላይደርስም የሚችለው። በእኛ ሁኔታ ደግሞ አሁን ወጣቱን ከፊት ሆኖ የሚያስተባብር አካል፣ ወጣቱ የተደላደለውን ጎዳና ሳይሆን እንደ ዝንጀሮ ዳገትና ቋጥኝ የበዛበት ተራራማ መንገድ ላይ እንዲጓዝ እያደረጉት ነው ያሉት። በመሆኑም በአመራርነትም ሆነ በሌላው መስክ ከፊት ሆኖ ወጣቱን የሚያሰማራ አካል ቆም ብሎ እነዚህን ወጣቶች በምን መልኩ የነገ አገር ተረካቢነታቸውን እውን ላድርግ፤ እንዴት ቀናና መልካሙን ጎዳና ላቅና፤ በዚህ ጎዳና እንዲመላለሱስ እንዴት ላለማምድ ብሎ ማሰብ ይርበታል። ይህ ሲሆን ነው ወጣቶች ሰብዓዊነትን ተላብሰው የተሻለች አገርን መገንባት፤ የህዝብ አጋርና አለኝታም መሆን የሚችሉት።
ወይዘሮ ሰላማዊት መልካ የተባሉ ጫማ አስጠራጊ እንደሚሉት ደግሞ፤ ወጣቶቹ ለአረጋውያንና ሌሎች አቅም ለሌላቸው መርጃ ገንዘብ ማሰባሰቢያ እየሰሩ መሆኑንና ጫማ አስጠርጌ የምሰጣቸው ገንብም ለዚህ ተግባር እንደሚያውሉት ባስረዱኝ መሰረት በደስታ ጫማቸውን እያስጠረጉ ነው። የእነዚህ ወጣቶች ተግባር ደግሞ ደስታንም ተስፋንም የሚሰጥ እንደመሆኑ፤ ሁሉም መሰል ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች ለመደገፍ የሚያስችል የመልካምነት ተግባር ሊያከናውን እንደሚገባም ትምህርት የሚሰጥ ነው። አሁን የእነዚህን ወጣቶች ሀሳብና ተግባር ከመመልከቴ በፊትም ሁል ጊዜ የማስበውና በየመድረኩም የምናገረው ነው። ምክንያቱም ህጻናት ሰብሳቢ በማጣታቸው በየመንገዱ ሲያድሩ፣ ቤንዚንና ማስቲሽ ሲስቡ ማየቱ እጅጉን ያሳዝናል። ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጎዳና የወጡ ወገኖችን ሰብሳቢ መሆን ያለበት መንግስት ቢሆንም፤ የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ቢሮ ባለበት ስፍራ ይሄን ነገር መመልከቱ ደግሞ ጉዳዩ በህዝቡ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ምን ያክል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳያል።
እናም በመንግስትም በህብረተሰቡም ቀናነት እንዚህን ወደኖች እየሰበሰቡ በማገዝ ራሳቸውን እንዲደግፉ ማስቻል ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ ቀላል ተግባር ቢሆንም ስራው ግን በቅድሚያ ሰው ሆኖ ሰው ለመርዳት መዘጋጀትን፤ ይሄን ለማስረግም በጎ አስተሳሰብን መያዝ ይጠይቃል። ይሄን ማድረግ ከተቻለ ህጻናት በጎዳና አይወድቁም፤ ንጹህ አስተሳሰባቸውም አይበረዝም። በቀና አሳቢዎች ቀናነትን ስለሚማሩ፤ ሰርተው መብላትን ስለሚለምዱም ለራሳቸውም ለአገርም አለኝታነታቸውን ያሳያሉ። አዛውንቶችም እርግማንን ሳይሆን ምርቃንን ትተው ያልፋሉ። በመሆኑም ሁሉም በዚህ መልኩ ሰው ሆኖ ሰብሰብ በማለት መርዳት፤ የተሰባሰቡትንም መደገፍ ያስፈልጋል።
‹‹ቁም ነገር ችግር ፈቺ ነገር ይዞ መጥቷል ብለን እናምናለን›› የሚለው ወጣት አቤል፤ ሰዎችን መደገፍ ማለት ከወደቁ በኋላ በማንሳት ሳይሆን ጎዳና ሳይወጡ በቤታቸው እያሉ በመደገፍ ከቤት እንዳይወጡ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ይገልጻል። እንደ ቁም ነገር የበጎ አድራጎት ማህበርም በቀጣይም ይሄን ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ በቋሚነት መስራት እንደሚፈልግ በመጠቆምም፤ ዛሬ ላይ በርካቶች ለጎዳና የመዳረጋቸው፣ የአዕምሮ ህሙማን የመብዛታቸው፣ ራሳቸውን ማገዝ የማይችሉ በርካታ ወገኖች የመበራከታቸው ምክንያት ምንድንነው የሚለውን በማሰብ አንድ ስራ መስራት እንደሚገባ በማመን ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው ለመስራት መወሰናቸውን ይናገራል።
እንደ ወጣት አቤል ገለጻ፤ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ችግር ተፍጥሮ ቤተሰቡም ችግር ላይ ሲወድቅና ጎዳና ሲወጣ፣ እድል የቀናቸው አረጋውያን ወደ አረጋውያን መርጃ፣ ህጻናትም ወደ ህጻናት ማሳደጊያ ሲገቡ፤ ወጣቱ ግን መንገድ ላይ ይቀራል። ከዚህ ባለፈም እርሱ ሰርቶ ማገዝ ሲችል ቤተሰቡን ለጎዳና ዳርጎ በመበተኑ ስነልቡናው ስለሚጎዳ ለተለያዩ ሱሶች ይዳረጋል። አዕምሮው ይነካናም ወደ አዕምሮ ህመምተኛነት ሊቀየር ይችላል። በመሆኑም አንድ ቤተሰብ ከመፍረሱ በፊት ባለበት እንዲቆይ ለማስቻል መሃል ላይ ያለውን ወጣት መደገፍና ሰርቶ ራሱንም ቤተሰቡንም እንዲደግፍ ማድረግ ይገባል። በእስካሁን ጉዟቸውም በዚህ መልኩ ሰባት ያክል ቤተሰቦችን ከጎዳና መታደግ የሚያስችል ስራ ያከናወኑ ሲሆን፤ በቅርቡም በተመሳሳይ አስር ቤተሰቦችን ይዘው ከጎዳና ለመታደግ እየሰሩ ይገኛል።
ለዚህ ደግሞ ወጣቶችን በማሰልጠን የሙያ ባለቤት የማድረግና በሙያቸው እንዲሰሩ የማስቻል አቅጣጫን እየተከተሉ ሲሆን፤ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የልብስ መስፊያ ሲንጀር፣ የጸጉር ማሽኖችና ሌሎችንም በሙያቸው ሰርተው የሚለወጡባቸውን ነገሮች ገዝቶ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ነው። በዚህ መልኩ መስራት ከቻሉና ወጣቱ ከራሱ አልፎ አያቶችና ልጆች ወደጎዳና እንዳይወጡ ማገዝ ከቻለ ነገ ከነገ ወዲያ ጎዳና ላይ የሚወጣ ህጻንና አዛውንት፤ ቤተሰቦቹ በመበተናቸው ምክንያት አእምሮው ተጎድቶ የሚታይ ወጣት የማይኖርበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። አሁን ይሄን ማየት ያልተቻለው ደግሞ ህጻናቱንም ሆነ አረጋውያኑን ከቤታቸው ሳይወጡ ሳይሆን ከጎዳና ከወደቁ በኋላ መሰብሰብ ላይ ትኩረት በመደረጉ ነው። እናም ቤተሰቦቹን ከጎዳና የመታደግ ቀርቶ አገርን ይለውጣል ተብሎ የሚታመንበትን ወጣት ደግፎ ማብቃት ላይ የመስራት ዓላማን ይዘው ነው እንደ ማህበራቸው እየሰሩ ያሉት።
‹‹አንተ ራስህን ሲያምህ ከተሰማህ በህይወት አለህ ማለት ነው፤ ሌሎች ሲታመሙ ግን አንተን ከተሰማህ በትክክል ሰው ነህ ማለት ነው›› የሚል አባባል እንዳላቸው የሚናገረው ወጣት አቤል፤ ‹‹እኛ እንደ ማህበር አባላት የሌሎች ህመም ስለሚሰማን ሰዎችን ለመደገፍ የተቻለንን እየሞከርን ነው›› ብሏል። ይሁን እንጂ ላሰቡት መሳካት የሚደግፋቸው አካል ሊኖር፤ ቢያንስ ወጣቶችን ለማሰልጠንና ለማብቃት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚያግዟቸው በቂ የማህበሩ አባላት ባለሙያዎች ስላሉ ለስልጠና የሚሆን ቦታና ማሽን ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል ቢኖር መልካም ነው። ምክንያቱም ሰው በወቅታዊ ድጋፍ ከተረጂነት ሊላቀቅ ስለማይችል በሙያም በቁሳቁስም ድጋፍ አግኝቶ ራሱን እንዲያቋቁም የሚያደርግ ስራ መከናወን ይኖርበታል።
በዚህ መልኩ ሁሉም ከተባበረ በአዕምሮም፣ በስነልቡናም፣ በአመለካከትም የተሟላ ስብዕናን አስይዞ ቤተሰቡን ከመበተን የሚያድን፤ አገርንም ወደ ብልጽግና የሚያስጉዝ ወጣትን ማፍራት፤ በጎዳና የሚያድሩ ህጻናትና አዛውንቶችን የማይታይባት አገርም መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ወንድወሰን ሽመልስ