አቶ ሰለሞን ክብሩ (ስማቸው የተቀየረ) ለልጆቻቸው የሚሰስቱት ነገር የላቸውም፤ አቅማቸው በፈቀደ መጠንም ሁሉን ነገር ያሟሉላቸዋል፡፡ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጧቸው፤ የሚንከባከቧቸውና የመኖራቸውም ምክንያቶች ናቸው። ይህንን ልፋታቸውን ደግሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ አረጋሽ ገብረሚካኤል (ስማቸው የተቀየረ) ይመሰክሩላቸዋል። አፍ አውጥተውም «ምንም ያጎደለብን ነገር የለም ከቤቱም አልጠፋም፤ ልጆቹንም ጥሩ ትምህርት ቤት ያስተምራል፤ ከራሱ ቀንሶ ለልጆቹ የሚያጎርስና ለቤተሰቡ ሁሉንም መስዋእትነት የሚከፍል አባት ነው» ይላሉ፡፡ ግና ወይዘሮ አረጋሽ ተስማምተን ለመኖር የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናልና ፍቺ ይሰጠን ሲሉ ለፍርድ ቤት አቤት ይላሉ።
ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት ደግሞ ትዳሩ ፈርሶ ቤተሰብ ተበትኖ ልጆች ለችግር እንዳይጋለጡ ጉዳያቸው በማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች መታየት ስላለበት በሕጉ በተቀመጠው የማሰላሰያ ጊዜ መሠረት ጉዳዩን እንዲያዩትና ምክረ ሀሳብ እንዲለግሱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መዝገቡን ይመራዋል። በጽሕፈት ቤቱ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ዮዲት ገብረመስቀል በበኩላቸው የደረሳቸውን ፋይል ተቀብለው ችግሩን ለመቅረፍ ደፋ ቀና ማለት ይጀምራሉ።
በቅድሚያም የሦስት ልጆች እናት የሆኑትን አቤት ባይ ወይዘሮ አረጋሽ ገብረሚካኤልን ምን ተፈጠረ? ባለቤትዎስ ይሄ ሁሉ ደግነት እያላቸው ትዳር የሚያናጋ ምን ርኩስ መንፈስ ገጠማችሁ? ሲሉ ጥያቄ ያነሱላቸዋል። ሚስትም ደግ ሥራው ብዙ ችግሩ አንድ ቢሆንም መፍትሄ ካልተበጀለት ግን በትዳሬ ለመቆየት እቸገራለሁ ሲሉ የገጠማቸውን ይናገራሉ። ባለሙያዋም እኛን አባት ጠርተው ያናግራሉ፡፡ እሳቸው እንደተረዱትም ከእድገታቸው ጋር በተያያዘ ለሴት ልጅ ያላቸው አመለካከት ክብር የተዛነፈ ሆኖ ያገኙታል።
ለእኚህ አባት ሴት ልጅ ከወለደች በኋላ ከቤት መውጣት የለባትም ፤ ሥራዋ ልጆች ማሳደግ ብቻ መሆን አለበት፤ ይሄ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ማመናጨቅ ተገቢ ያልሆኑ ቃላት መናገር ደግሞ የየዕለት ተግባራቸው አድርገውታል። እንዲህ ዓይነቱ የቤተሰብ ችግር ደግሞ ዛሬ ባሉት ባልና ሚስቶች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ለልጆች፤ ከእነሱም አልፎ ነገ ለሚመሰርቱትና ለሚፈጥሩት በቤተሰብም ሳንካ በመሆኑ ከጥንዶቹ ውጪ መላውን ቤተሰብ የሚመለከት ችግር ሆኖ ያገኙታል። እኒህን አባት ሰባት ጊዜ ቤተሰቡ ጋር አስራ አምስት ጊዜ ደግሞ ለብቻቸው በማግኘትና በማነጋገር ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ ቤተሰቡ ሳይፈርስ እንዲቀጥል ማድረግ ይችላሉ። ሂደቱ ግን እንዲህ እንደዋዛ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ አባት መጨረሻ ለማስተካከል መስማማታቸው ባይቀርም በመጀመሪያ አካባቢ ከቤተሰባቸው ያመጡት ሀሳብ ትክክል ነው ብለው ከማመናቸው ባሻገር የፍትህ አካላቱም ሊጋሯቸው እንደሚገባ ሲያሳስቡ ነበር።
ባለሙያዋ እንደሚናገሩት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ምክንያቶች በወቅቱ በተገቢው መንገድ ባለመታከማቸው ለትዳር መፍረስና ለቤተሰብ መበተን ዋነኛ ምክንያቶች ሲሆኑ በስፋት ይስተዋላል። የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራም በእንደዚህ ዓይነት መታረምና መስተካከል በሚችሉ ምክንያቶች ትዳር እንዳይፈርስና ቤተሰብ እንዳይበተን ማማከርና ድጋፍ ማድረግ ነው። ቤተሰብ ተበትኖ በተለያየ ሁኔታ የሚያድጉ ልጆች እናትና አባታቸው ስለሌሉ ሳይሆን ትዳሩ ስለፈረሰ ብቻ አነሰም በዛ የሚገጥማቸው ችግር በመኖሩም እነሱን የመታደግ ሥራ ይሰራል ይላሉ።
ወይዘሮ ዮዲት እንደሚያብራሩት በርካታ ጥንዶች ትዳራችን በቃን የቤተሰባችን ጉዞ በዚህ ይገታ ብለው ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በአብዛኛው ከቤተሰብ እስከ ጓደኛ፤ ከሰፈር ሽማግሌ እስከ የሃይማኖት አባት፤ የሽምግልናውን መንገድ ሞክረውት ነው። ነገር ግን በእነዚህ ሂደቶች የሰለጠነ ባለሙያ ባለመኖሩ የማስማማት ሥራው የሚሰራው ችግሩን ከመሠረቱ መቅረፍን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን ነገሮችን በማለባበስ አንተም ተው አንቺም ተይ በሚል በማቻቻል አካሄድ በመሆኑ ብዙ ጊዜ በዘላቂነት ውጤታማ የመሆኑ ነገር እምብዛም ነው። በአንድ በኩል በአንዱ ወገን በተለይ በሴቶች ላይ ጫና ስለሚበዛባቸውና ያለፍላጎታቸው ውሳኔውን ስለሚቀበሉ ውለው ሳያድሩ ተመልሰው ወደሽምግልና ወይንም ሌላ አማራጭ ለመሄድ ይገደዳሉ። በሌላ በኩል ውሳኔውን ተቀብለው ቢቀመጡ እንኳ አለመግባባቱ ስለሚቀጥል ለጥንዶቹ ብቻ ሳይሆን መላው ቤተሰብ የሚኖረው ሕይወት ጤነኛ አይሆንም። ስለዚህም በባለሙያ ምክር ማግኘቱ ለሁሉም የሚበጅ ይሆናል።
በተለመደው የጽሕፈት ቤቱ አሠራር የማማከር ሥራው የመጀመሪያ ተግባር በትዳር እንዲቀጥሉ ለማስቻል መጣር ሲሆን፤ ለዚህም አቤት ባዮች ሲቀርቡ ሥራው ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ በመንገር ሁለቱን ጥንዶች በግልና በተናጠል እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ቢያንስ ከስምንት እስከ አስር ጊዜ የማማከር ሥራ ይሰራል። በዚህ ሂደትም ከባልና ሚስቱ ንግግር ባለፈ ሕፃናቱ እድገታቸው ከዕድሜያቸው ጋር መመጣጠኑን ከንጽህና ጀምሮ የተያዙበት ሁኔታ በመገምገም ችግሩን ለመፍታት ይሰራል። ለዚህ ደግሞ አመልካችና ተጠሪ የተዘጋጀላቸውን መጠይቅ እንዲሞሉ ይደረጋል። ለቀጣይም ቀጠሮ ይሰጣቸውና ሕፃናቱን ይዘው መጥተው ሰፋ ያለ ውይይት ይደረጋል። አንዳንድ ጊዜ በዚህ መልኩ መረጃው ተሰብስቦም ውሳኔ ለመስጠት በቂ የመሆኑ ነገር አጠራጣሪ ሆኖ ሲገኝ ወደ ቤት፤ ጎረቤት፤ ትምህርት ቤትና አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎች ድረስ በመሄድ ተጨማሪ መረጃ የመሰብሰብ ሥራ ይከናወናል።
ይሄ አልሳካ ብሎ መለያየቱና የቤተሰቡ መፍረስ የግድ ሲሆን ደግሞ ቤተሰቡን ያጡት ልጆች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የቤተሰብ እንክብካቤና ፍቅር እንዲያገኙ ለማስቻል የጥንዶቹ ቀረቤታ እንደ እህትና ወንድም እንዲቀጥል ሌላ ሥራ ይሰራል። ልጆች በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን እንዲያድጉ የሚመከረው በወላጅ እናትና አባት ስር ቤተሰብ ውስጥ ሆነው ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረው እናትና አባት ሲለያዩና የመሰረቱት ቤተሰብ ሲፈርስ የሕፃናቱ መብት፤ ጥቅምና ደህንነት ተጠብቆ ከማን ጋር ቢያድጉ የተሻለ ይሆናል የሚለው በስምምነት እንዲለይ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ ያሳዳጊነት መብት ያላገኘው አካልስ እንዴት ለልጆቹ የአባትነት አልያም የእናትነት ፍቅሩን ለመስጠት መቼ መጎብኘት አለበት የሚለውን ሁሉ መለየት ስለሚኖርበት ለዚህ የሚጠቅሙ መረጃዎች ይሰበሰቡና ለውሳኔ እንዲረዱ ለዳኞች ይቀርባሉ።
በዚህ ሂደትም የቀለብ አቆራረጥ የልጆች መጎብኛና መሰል ጉዳዮች ከሕግ አስገዳጅነት ይልቅ በስምምነት እንዲከወኑ ይመረጣል። ይህም የሚደረግበት ምክንያት ቀለብ መስፈሩም ሆነ ልጆችን የመጎብኛው ጊዜ በስምምነት ሳይሆን በፍርድ ቤት ቀጥተኛ ውሳኔ ብቻ ከሆነ እልህ የመገባባት ነገር ስለሚፈጠር ነው። እልህ ከተጋቡ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠሩ በወቅቱ ልጅን አላሳይህም፤ አላሳይሽም የማለት፤ በገንዘብም በኩል ጥሩ ገቢ እያለ ቀለብ ላለመስፈር ሥራ ፈትቼያለሁና አልችልም ወይንም ሌላ ምክንያት ማቅረብ የተለመደ ስለሆነ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ደግሞ ልጆች በቤተሰብ መበተን የደረሰባቸው ችግር ሳያንስ ለተለያዩ ቁሳዊ ችግሮችና የእናትና አባታቸውንም ፍቅር ለማጣትና ተገቢ ያልሆነ ባህሪ ለመያዝ ይዳረጋሉ።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዴ የጥንዶቹ ስምምነት የልጆችን አስተዳደግና ጥቅም የሚነካ አልያም ለጉዳት የሚዳርግ መሆኑ ከውስጥ አዋቂ መረጃ ሲገኝም፤ ለምሳሌ አንድ እናት ወይም አባት በሱስ ተጠቂ መሆናቸውን እያወቁና በሕፃኑ ፊት እየተጠቀሙም እንደሆነ እያወቁ ከተስማሙ ሕፃኑ የሚጎዳ በመሆኑና ስምምነቱም ለሕፃናቱ ችግር ያለበት በመሆኑ፤ ሱሰኛ በመሆናቸው ሳይሆን በዚህ የተነሳ ችግሩ ወደ ቤተሰብ በመሄድ በሕፃናቱ ላይ የሚፈጥረውን ችግር በማየት ስምምነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠትና ተጨማሪ ጥናት በባለሙያ እንዲያሰራ የሚረዱ ግብአቶች ይቀርባሉ።
በአሁኑ ወቅት በቤተሰብ ጉዳይ ተካሰው መጥተው ተስማምቶ የመቀጠሉ ነገር ዝቅተኛ ቢሆንም በልጅ አስተዳደግና በቀለብ ሰፈራው በኩል ግን በብዛት ሲስማሙ ይታያል። ይህም ልጆችንም ለመጎብኘት ሲገናኙ የልጆቹን ስብእና የጠበቀ እንዲሆን ይረዳል። ይሄ ደግሞ ልጆች በቀደመ ቤተሰባቸው ውስጥ ያገኙ የነበረውን ያህል ጥቅምና ፍቅር የማያገኙ ቢሆንም ባለመስማማት ካለው መለያየት በተሻለ የቁሳዊም ሆነ የህሊና እርካታና ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
ለትዳር መፍረስና ለቤተሰብ መበተን እንደ ምክንያት ከሚቀርቡት ጉዳዮች መካከልም ሱሰኝነት ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፤ ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ለቤተሰብ ጣልቃ ገብነት መጋለጥ ዋናዎቹ ናቸው። በመሆኑም በትዳር የተጣመሩ ጥንዶች የቤተሰባቸውን ህልውና አደጋ ላይ ላለመጣል እነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠትና ካለ ይሉኝታ መወያየት ይጠበቅባቸዋል። ነገሩ ከዚህ ካለፈ ደግሞ ቤተሰብን ያህል አንድ የማህበረሰብ አካል የሚመለከት ትልቅ ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት በተቻለ መጠን ባለሙያ ጋር ቀርበው ማመከር እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባሉ።
«ቤተሰብ ዋናው የማህበረሰብ መሠረት ነው። በመሆኑም ከችግሩ አንጻር ለባለ ትዳሮች እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በቂ አይደለም» የሚሉት ደግሞ በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ልዑለስላሴ ሊበን ናቸው። እንደ ዳኛ ልዑለስላሴ ማብራሪያ ባለትዳሮች ሲጣሉ ወደ ፍቺ ከመሄዳቸው በፊት ቀጥታ ፍቺ ስለማይፈጸም ማንኛውም ችሎት የግዴታ የማሰላሰያ ጊዜ ይሰጣል። ነገር ግን ያንን የማሰላሰያ ጊዜ ለሽምግልናና ለድርድር የመጠቀሙ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። በ1952 በወጣው ሕግ መሠረት በቂ ምክንያት ከሌለ ፍቺ መፈጸም ክልክል ነበር በአዲሱ ሕግ ግን አብሮ ለመኖር አለመፈለግ ብቻውን ለፍቺ በቂ ነው። ለምን የሚለውን ምክንያታቸውን እንዲያወጡ የሚገደዱበት አካሄድ የለም። በዚህ መካከል ጥንዶቹ በትንንሽ ጉዳዮች ትዳራቸውን እንዲፈቱ ክፍተት ይሰጣል። ትዳር ሲፈርስና ቤተሰብ ሲበተን በርካታ ችግሮችን የሚያስከትል ሲሆን በተለይ ልጆች ላይ የሚደርሰው ደግሞ ከፍተኛ ነው።
ለሕፃናት ምቹ የማደጊያ ስፍራ ቤተሰብ ቢሆንም ብዙ ሕፃናት ለችግር የሚጋለጡት ቤተሰብ ስለሌላቸው ብቻ ግን አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቤተሰብ ከአቅም ማጣት ትኩረት አይሰጥም በየቤቱ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለችግር ያጋልጧቸዋል። በቤተሰቡ ውስጥ ሱሰኛ ሰው ኖሮ ለቤት ውስጥ ጥቃት የተጋለጠና ጥቃት ሲፈጸም የሚያይ ልጅ በጤነኛ ቤተሰብ ከሚያደገው ጋር ተመሳሳይ ሰላም አይኖረውም። ስለዚህ ቤተሰብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ልጆችን ሊጠብቅ የሚችልም መሆን አለበት።
እስካሁንም በማዕከሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከዚህ ማዕከል የድጋፍና የምክር የማስማማት አገልግሎት እያገኙ ሲሆን የሕግ ባለሙያዎቹ የሙያተኛ ክፍያ የማይከፈላቸው በጎ ፈቃደኞች ናቸው። የሚይዟቸው አንዳንዶቹ ጉዳዮች ግን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ብሮችን ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። ቁጥሩ በየወቅቱ ከፍ ዝቅ የሚል ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ሃያ የሚደርሱ የማዕከሉ ሠራተኞች ሲኖሩ፤ ሰላሳ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ፤ እንዲሁም አራት የሥነልቦና፤ ምክርና የማስታረቅ ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉት።
ሕፃናት በአንዳንድ ጥፋቶች ተይዘው የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥባቸው በተቻለ መጠን እንደ ቤተሰብ ባለ ቦታ ቢቆዩ ይመረጣል። በኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለው የሕፃናት ማቆያ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ሲሆን እሱም አንድና ከ175 በላይ ታራሚዎችን መያዝ የማይችል ነው። በከተማ ውስጥ ደግሞ በየቀኑ በርካታ ወንጀሎች የሚሰሩ በመሆኑ በብዙ ቦታ ልጆች ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙና መታሰር አለባቸው ተብሎ ሲወሰን የሚላኩት ወደ አዋቂዎች ማረሚያ ቤት ነው። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬክሽን፤ በአፍሪካ የሕፃናት ቻርተር፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የወንጀል ሕግ ጭምር የተከለከለ ነው።
አንድ የልጅ ጥፋተኛ በፍርድ ቤት ከተወሰነበት በኋላ ወደ ማረሚያ ቤት ሳይሆን ከትምህርት ቤት ሲወጣ በሰፈሩ አካባቢ ሽማግሌዎችና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ባሉበት ምክር እያገኘ እንዲቀመጥ ይጠበቃል። በዚያም የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የሙዚቃ መሣሪያ ሥልጠና የመሳሰሉት ነገሮች ተሟልተው የበለጠ ከማህበረሰቡ ሳይራራቅ ተስተካክሎ ቤተሰቡን እንዲቀላቀል ይረዳዋል። ነገር ግን በማህበረሰቡ ውስጥ ያልነበሩት የእርምት አገልግሎት ማዕከላት የዛሬ አስር ዓመት እንዲዘጉ ተደርገዋል። ከዚህ ቀደም «የጎዳና ሕፃናት ወዳጆች ማህበር» የሚባል በአዲስ አበባ አምስት ቦታዎች ላይ የእርምት ማዕከሎች ነበሩት። በወቅቱ የወጣው ሕግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከሕግ አካላት ጋር እንዳይሰሩ ስለሚከለክል ተቋርጧል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን በመንግሥትም ሆነ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማምጣት በከተማዋ ባሉት አስር ክፍለ ከተሞች አንዳንድ ይህ እንኳ ባይሳካ ለሁለት ክፍለ ከተማ አንድ ማረሚያ ቤት መዘጋጀት ይጠበቃል።
የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት መጀመሪያ የተቋቋመው ከሃያ ዓመት በፊት በወንጀል ነክ ነገሮች ውስጥ ገብተው የተገኙ ልጆችን ጉዳይ ለማየት ነበር። በወቅቱ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች በወንጀል እየተከሰሱ በፖሊስ ፍርድ ቤት ይቀርቡ ነበር። እነዚህ ልጆች ደግሞ ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጡ ከመሆናቸው ባሻገር ከሌላው በተለየ ቤተሰባቸው የፈረሰ በመሆኑ የሚቆጣጠራቸውም ሆነ የሚረዳቸው ባለመኖሩ ነበር። በወቅቱ የነበሩት የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች ናቸው ይህንን ፕሮጀከት ያስጀመሩት። ከጊዜ በኋላ ግን ነገሩ ሲታይ የሕፃናት ጉዳይ ከወንጀል ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን ሰፊ ችግሮች ያሉበት በመሆኑና በፍርድ ቤት ውስጥም ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ የጥቃት ሰለባ ሆኖ መምጣት መጨመሩ፤ ሌሎች የፍትሀ ብሔር የቤተሰብ ጉዳዮች ውስጥም ልጆች ገብተው ስለሚገኙ ሰፋ ባለ መልኩ የሕፃናት ፕሮጀክት ቢሮ ተብሎ መንቀሳቀሱን ቀጠለ። በአሁኑ ወቅትም ከጎዳናም አልፎ ቤተሰብ ውስጥም ሆነው የተለያዩ ጥቃት የሚደርስባቸውን ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን ጉዳይ ከቤተሰብ ጋር በማያያዝ እየሰራ ይገኛል።
ጽሕፈት ቤቱ በአዲስ አበባ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በልደታ፤ በየካና በንፋስ ስልክ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችና በድሬዳዋ ቢሮዎች አሉት። በተጨማሪ በትብብር ከኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማህበርና ሌሎች ጋር እየሰራ ይገኛል። በቅርቡም በአማራ፤ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ከዚህ ትምህርት ወስደው ይህንኑ አሠራር እንዲተገብሩ እየተሰራ ሲሆን፤ ባጠቃለይም ከሕፃናት ፍትህ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የወንጀል ብቻ ሳይሆን ከአሰሪና ሠራተኛ ሕግና በአስተዳደራዊ ጉዳዮችንም አካቶ እየሰራ ይገኛል። ለቀጣይም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አማራጭ የሙግት መፍቻ መድረክ በሚል ራሱን የቻለ ክፍል ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ