“ወጣት ማዕከላት” በወጣት ሊግ የሚሳተፉ እጩ ካድሬዎችና በሴቶች ሊግ የሚሳተፉ በዕድሜ የገፉ እናቶች የአራቱ እህት ድርጅቶች የምስረታ በዓል ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንና በቅርቡ በመጋቢት 24 ቀልቡ የተገፈፈው ግንቦት 20 ሲከበር የዳንስ ትርኢት የሚያሳዩባቸው የፖለቲካ ማዕከላት ሆነው ኖረዋል፡፡ አሁንም የተለየ ሚና ያላቸው አይመስሉም፡፡
እነዚህ “ወጣት ማዕከላት” ብዙ ታዝበዋል፡፡ አንደበት ኖሯቸው ቢናገሩ “ድሮ ድሮ እልልታ ውድ ነበር፡፡ ልጅ ሲወለድ ፣ የምስራች ሲሰማ ፣ ሠርግ ሲሰረግ፣ ታቦት ሲሸኝ ፣ ጀግና ከጦር ሜዳ ሲመለስ ፣ ብር አምባር ሲሰበርና አንዳች ታምር ሲፈጠር ነበር እልልልልልልልል የሚባለው፡፡ ዛሬ ግን ብዙዎች ደስታ አጠገብ ሳይደርሱ እልልታቸውን በ50 ብር አበል እየመነዘሩት ያደነቁሩናል፡፡ አምነውብት ከውስጣቸው በመነጨ ደስታ ተገፍተው ለሚያደርጉት አክብሮት አለን፡፡ ለአበሉ ሲሉ ለሚታበሉት በሊታዎች ግን ምክር አለን ፤ ሌላ ገቢ ማግኛ መንገድ ቢፈልጉ ይሻላቸዋል፡፡” የሚሉ ይመስለኛል፡፡
“ወጣት ማዕከላቱ” በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት “የ86 ዓመት ወጣት ነኝ፡፡ የወለቀ ጥርሴም እየበቀለ ነው” ሲል እንደተደመጠው አይነት “ወጣት” ተብዬዎች መዋያና ማደሪያ ከሆኑ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዕድሜያቸው ይታደስ ይመስል በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ለመታደም በብዛት ወደ “ወጣት ማዕከላቱ” የሚያመሩት ጎልማሶችና አረጋውያን ናቸው፡፡
ከሰሞኑ የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ስለነዚህ “ወጣት ማዕከላት” የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአገሪቱ ከሶስት ሺ በላይ የወጣት ማዕከላት አሉ፡፡ ነገር ግን የታለመላቸውን ወጣት ተኮር አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 1ሺ455 ብቻ ናቸው ሲል ተናዟል፡፡ ጨምሮም በወጣት ማዕከላቱ ወጣት ተኮር የሆኑ ፕሮግራሞች የሉም፤ የተሟላ የተዋልዶ ጤናና ኤች አይቪ ፕሮግራም አገልግሎቶች አይሰጡባቸውም፤ በሰው ኃይል ረገድም የእውቀትና ክህሎት ማነስ ችግሮች አሉባቸው እንዲሁም ማእከላቱ ለልጃገረዶችና አካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም ብሏል። በወጣት ማዕከላት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎችን በባለቤትነት አለመምራትና ቅንጅታዊ አሰራሮች አለመኖራቸው ተጨማሪ ችግሮች ናቸው ሲልም አክሏል።
የአዲስ አበባ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮም በአንድ ወቅት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተገነቡ ወጣት ማዕከላት መካከል ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡና ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡ ወጣት ማዕከላት ብሎ ነበር፡፡ የወጣት ማዕከላቱ የሚታይባቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ፣ የግብዓትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ከ265 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአምስት ዓመት በኋላም ተመሳሳይ ችግር ሲዘረዘር እየሰማን ነው፡፡
የቀድሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከዓመታት በፊት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት በ2002 ዓ.ም ለወጣቶች ማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥ የወጣው ደረጃ የወጣቱን አስተሳሰብና ፍላጎት የማይመጥን ነው፡፡ የተገነቡት ወጣት ማዕከላት በአገልግሎት ደረጃ አሰጣጣቸው ብቻ ሳይሆን በግንባታ ዲዛይናቸው ላይም ችግር አለባቸው ብሏል:: ወደፊት የሚገነቡት የወጣት ማዕከላት ዲዛይናቸው መሻሻል እንዳለበትም ጥናቱ አመላክቶ ነበር፡፡ ዳሩ የተቀየረ ነገር የለም፡፡
ባሳለፍነው ክረምት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዲስ አበባ የሚገኙ የሦስት ወረዳዎች የወጣት ማዕከላት ለወረዳ አስተዳደር ቢሮነት መዋላቸውን ዘግቦ ነበር። የካ ክፍለከተማ ወረዳ አራት ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የሚገኙ ወጣት ማዕከላት አሁንም ድረስ በወረዳ አስተዳደር ቢሮነት እያለገሉ ይገኛሉ።
“የወጣት ማዕከላት” ችግሮችን በመዘርዘር የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ሲሉ ቁጭታቸውን የሚገልጹ ዜጎች ተሳስተዋል፡፡ ማዕከላቱ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ አንድ የዘነጉት ነገር ማዕከላቱ ቀድሞውንም የተቋቋሙበት ዋነኛ ዓላማ ፖለቲካዊ መሆኑን ነው፡፡
በምርጫ 97 ዛሬ ግብዓተ መሬቱ የተፈጸመው ኢህአዴግ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች አለኝ ብሎ ከሚያስበው በታች ድጋፍ አገኘ፡፡ በከተሞች ደግሞ “በዝረራ” እንደተሸነፈ ተረዳ፡፡ ሆኖም በወቅቱ ተገዳዳሪ ሆኖ ቀርቦ ፍጻሜው ላይ የተልፈሰፈሰው ቅንጅት አመራሮች ለፓርላማው ወንበር ጀርባቸውን ሰጥተው ቃሊቲ ወረዱ፡፡ ገዢው ፓርቲም “ጥልቅ” ግምገማ አድርጎ ወጣቱ ላይ አለመስራቴ ዋነኛ ችግሬ ነው ፤ ከዚህ በኋላ ወጣቱን መያዝ አለብኝ አለ፡፡
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ወጣቱን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማጥመቅ የሚያስችሉ “የወጣት ማዕከላት” ግንባታ ተጧጧፈ፡፡ በየወረዳው ያሉ ካድሬዎች ጠመቃውን በቀላሉ መምራት እንዲችሉም “የወጣት ማዕከላቱ” ቀበሌዎች አጠገብ ተገነቡ፡፡ አንዳንዶቹም ከቀበሌዎች ጋር ግቢ ተጋሩ፡፡ ጎን ለጎን ወጣቱ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሁለተኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር በአንድ ለአምስት፣ በወጣትና በሴቶች ሊግ እንዲደራጅ ተደረገ፡፡ ከዚህ በኋላ ማዕከላቱ እረፍት እስኪናፍቃቸው ድረስ የአደረጃጀቶቹን ስብሰባዎች በማስተናገድ ቢዚ ሆኑ፡፡
ገዢው ፓርቲ በዚህ መልኩ ለዓመታት የሰራውን ስራ የሚፈተሽበት ምርጫ 2002 መጣ፡፡ የአደረጃጀቶቹ አባላት በየአካባቢያቸው ተቃዋሚዎችን በአይነ ቁራኛ በመከታተል ከስር ከስር ሪፖርት በማድረግና ቤት ለቤት በመዞር ኗሪው ፓርቲያቸውን እንዲመርጥ ከመቀስቀስ አልፈው የምርጫ ካርድ ቁጥሩን እየመዘገቡ ሪፖርት በማድረግ “በሚገባ” ስራቸውን ሰሩ፡፡ ገዢው ፓርቲም 99 ነጥብ ስድስት በመቶ የፓርላማውን ወንበር “በመቆጣጠር” አሸነፈ፡፡
“ስኬታማ” የሆነው “የወጣት ማዕከል” ፕሮጀክት የገዢው ፓርቲ አባላት ቁጥር በምርጫ 2007 ከ አምስት ሚሊየን እንዲልቅ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በውጤቱም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር 547ቱንም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በማግኘት “መቶ በመቶ” አሸነፈ፡፡
አሁን መነሳት ያለበት ጥያቄ ገዢው ፓርቲ ከገባበት ማጥ ለመውጣት ካቀዳቸው ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ የነበሩት “ወጣት ማዕከላት” በፖለቲካው መስክ አመርቂ ውጤት ስላስገኙ ቢያንስ ከዚህ በኋላ ለስማቸው የሚመጥን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ሆነው ይደራጁ የሚል ቢሆን ይሻላል፡፡ ሰሞኑን የታገቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ በማህበራዊ ድረ ገጾች ሰፊ ሽፋን አግኝቶ እንደነበረው ዘመቻ በመጀመር “ወጣት ማእከላቱን ወደ ስማቸው መልሱልን” አይነት ንቅናቄ ማካሄድ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
በኢትዮጵያ እድሜው ከ 30 ዓመት በታች የሆነው የማህበረሰብ ክፍል ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ እንደሆነ ይነገራል::
ይህን ያህል ቁጥር ላለው የአንድ አገር ህዝብ መንግስት ጤናው እንዲጠበቅ ፣ በትምህርት እንዲቀረጽና የስራ እድል እንዲያገኝ የማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ የወጣት ማዕከላት ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ከፖለቲካ ማዕከልነት ነጻ ወጥተው ምቹ፣ ግብዓት የተሟላላቸው፣ ወጣቶችን ስራ ፈጣሪ የሚያደርጉና በባለሙያ የተጠናከሩ ሲሆኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
የትናየት ፈሩ