• አየር መንገድ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፡-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገልግሎት ቅልጥፍና እና የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸምን አድንቋል። አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2018/19 አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ትናንት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ያስገነባቸውን የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ማስፋፊያ፣ የዕቃ ማስተላለፊያ፣ የአውሮፕላን መጠገኛ ጋራዥና የምግብ ማብሰያዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን ጭምር መኩሪያ ነው። በተለይ የአገልግሎቱ ቅልጥፍናና በማስፋፊያ ግንባታዎች ያሳየው አፈጻጸም ለሌሎች ተቋማት ትምህርት የሚሆን ነው።
አፈጉባዔው፤ እንደተናገሩት አየር መንገዱ ሌሎች የዓለም አየር መንገዶች በከሰሩበት ጊዜ ጭምር ትርፋማ ነው። ይህም ድርጅቱ በሚሰራቸው ስራዎች ውጤታማና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቁ ያስመሰግነዋል፡፡ ከምክር ቤቱ ለሚያስፈልገውን ዕገዛ ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን። የጀመራቸውን ውጤታማ ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ድሪቡ ጀማል በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ውጤታማ ድርጅት መሆኑን በተግባር አይተናል፡፡ አገልግሎቱ ቀልጣፋና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው። ይህም ለሌሎች ተቋማት በብዙ መልኩ አርአያ ያደርገዋል።
አየር መንገዱ እኤአ በ2018/19 አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ 12 ሚሊዮን ደንበኞችንና 431ሺህ859 ቶን ዕቃዎችን ማጓጓዙን ተናግረዋል፡፡ የአየር መንገዱ ስኬት የሰራተኛው ትጋት፣ የአስተዳደሩ ቁርጠኝነትና የመንግስት ድጋፍ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሁለት ሺህ 204 በረራዎችን የሚያደርግ ሲሆን 127 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ያነሱት አቶ ተወልደ በተለይ የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማሳደግ አምስት ኤርፖርቶችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አየር መንገዱ የ70 ዓመታት ዕድሜ ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ16ሺህ በላይ ሰራተኞችና 134 የተለያዩ አውሮፕላኖች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም