አዲስ አበባ፡- ከብዙ አቅጣጫ ወደ ሶማሌ ክልል የሚገባው የአንበጣ መንጋ ከአውሮፕላን ርጭት አቅም በላይ በመሆኑ እስካሁን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ወቅቱ ለአንበጣ መራቢያ አመቺ መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ተጠቅሷል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በዚህ አመት ከሰኔ ጀምሮ በተደጋጋሚ የአንበጣ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ እነዚህን አንበጣ መንጋዎች ለመከላከል የምንከተለው ደግሞ በባህላዊ መንገድ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
በሶማሌ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልም አምስት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የተከራየን ቢሆንም በበአል ምክንያት ሁለቱ ወደ ስራ አልገቡም ያሉት አቶ ዘብዲዮስ፤ ሦስት አውሮፕላኖች በትክክል ስራቸውን እየሰሩ ቢሆንም በተፈለገው ልክ መቆጣጠር አልተቻለም ብለዋል፡፡
በተለይ ደግሞ በአንበጣ የተወረረው ቦታ ሰፊና ብዙ ቦታዎች ያካለለ መሆኑና ወደ ክልሉ የሚገባው መንጋው ከብዙ አቅጣጫዎች በመሆኑ በስራ ላይ ካሉ አውሮፕላኖች አቅም በላይ መሆኑን አቶ ዘብዲዮስ ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በሶማሌ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ለማዋል በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የአንበጣው መንጋ ከሞቃዲሾ፣ ከፑንት ላንድና ከሶማሌ ላንድ የመጣ ሲሆን ወቅቱ ደግሞ ለአንበጣ መራባት አጋዥ በመሆኑ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል፡፡
ችግሩ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን ለመከላከል በርካታ ፀረ አንበጣ አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጉና በባህላዊ መንገድ ለማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶች በሚፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዘብዲዮስ እንደተናገሩት፤ መንጋውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ህብረተሰቡ አባሮ ቁጭ ማለት ሳይሆን ያደረበትን ቦታ እየለዩ ለባለሙያ መረጃን በማቀበል በፀረ ተባይና በተለያዩ መንገዶች ቁጥሩን እንዲቀንስ ማድረግ ይገባል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ የአንበጣ መንጋን ማባረር ትክክለኛ መፍትሄ ካለመሆኑም በላይ ችግሩን ማባባስና ወደ ሌላ ቦታ እንዲስፋፋ ማመቻቸት በመሆኑ ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወረዳ፣ ከዞንና ከክልሉ መንግስት ጋር በቁርኝት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና የፌደራል መንግስትን ዘላቂ ጥረት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ