ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ ትግበራ በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ይሁን እንጂ ዘርፉ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ይጠቀሳል፡፡
በአፋር ክልል በተገኘንበት ወቅትም ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን በክልሉ የተደራጁ ወጣቶች ነግረውናል።የቀን ስራ በመስራት ይተዳደር የነበረው የሰመራ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሙስጠፋ አብዱ በአሁኑ ወቅት ‹‹ሙስጠፋ፣ ፋጡማና መሀመድ የዳቦ መጋገርና ማከፋፈል ማህበርን›› 470 ሺ ብር ብድር በማግኘት በ10 አባላት አቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዳቦ ጋገራ ስራ የተሰማራ እምብዛም በለመኖሩ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችለናል የሚለው እሳቤ ዘርፉን ለመምረጥ እንዳነሳሳቸው ይናገራል፡፡
ሆኖም ዱቄት ከመንግሥት አካል በሚፈልጉት መጠን ባለማግኘታቸውም ከአትራፊዎች ለመግዛት ተገድደዋል። ይሄም ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የመስሪያ ቦታ አለመኖርም ሌላው በችግር የሚነሳ እንደሆነም ይጠቁማል፡፡
«አፋሮች ስራ አይሰሩም የሚለው አባባል እንዲጠፋ እንፈልጋለን» የሚለው ወጣት ሙስጠፋ፤ ይህንን ታሪክ ለማድረግ ሰርተን እና ተለውጠን እናሳየለን የሚል ራዕይ አንግቧል፡፡ ገንዘብ ላበደረን አካል ፈጥነን በመመለስ ስራችንን በማሳደግ አርአያ ሆነን መታየት እና ስኬታማ ሆነንም የተሻለ ኑሮ መኖር እንፈልጋለን ሲልም ይናገራል፡፡
ወጣቱ እንደሚለው የክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጀንሲ የገበያ ትስስር በመፍጠር የበለጠ ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ የሰመራ ዮኒቨርሲቲም የሚቀበለውን የዳቦ ብዛት ቢያሳድግልን ጥሩ ነው የሚል ሀሳብ አለው ፡፡
አሁን በየወሩ 20 ኩንታል ዱቄት እናገኛለን የሚለው ወጣት ሙስጠፋ፤ ይህ በቂ አይደለም፣ የሚመለከተው አካል የዱቄት ኮታን በማሳደግ በየወሩ ከ60 ኩንታል በላይ ቢያደርግ እና የመስሪያ ቦታም ቢሰጠን የተሻለ ውጤታማ እንሆናለን ብሏል፡፡ ይህ ካልሆነ ስኬታማ ለመሆን እንደሚቸገሩ ይጠቅሳል፡፡
የኤጀንሲው የአንድ ማዕከል አገልግሎትና አቅም ግንባታ ዳይሬክተሩ አቶ አብደላ ሁሴን፤ ኤጀንሲው በዋናነት ስራ አጥ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማደራጀት የስራ ዕድል የመፍጠር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ከተቋቋመበት ከ2004 ዓ.ም አንስቶ መዋቅሩን እስከ ወረዳ በማደራጀት እየሰራ መሆኑንና የሚደራጁ ወጣቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ከብድር አቅራቢ ተቋም ጋር የማገናኘት ስራ እንደሚተገበርም ይገልጻሉ፡፡
አቶ አብደላ እንደሚሉት፣የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከመምጣቱ በፊት የፋይናንስ አገልግሎት በክልሉ አልነበረም። ስራው ይሰራ የነበረው ከበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመተባበር ነበር፡፡ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ፋርም አፍሪካ፣ጂ አይ ዜድ እና የመሳሰሉ ተቋማት ጋር በመተባበር ወጣቶችን የማብቃት ስራ መሰራቱንና ከተቋማቱ ጋር በመቀናጀት በብሎኬት ማምረት፣በግንበኝነት፣በልብስ ስፌት፣በጽዳትና ውበት፣በችግኝ ማፍላት ዘርፍ በርካታ ወጣቶች ሰልጥነው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የንግድ እቅድ ተሰርቶ 11 ወረዳዎች ላይ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ ይህ ስራ ለወጣቶች፣ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና የተለያዮ ህብረተሰብ ክፍል የተካተቱበት ነው፡፡ይሁን እንጂ አሁንም የማይክሮ ፋይናንስ ባለመስፋፋቱ ከ32 ወረዳዎች እስካሁን እየተሰራ ያለው በ11 ወረዳዎች ላይ ብቻ ነው፡፡
በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ተመልምለውና ተደራጅተው የብድር አገልግሎት ስራ እንዲያገኙ የተደረጉ 76 ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ፤ ወንድ 715፣ ሴቶች 341 ናቸው። ለእነዚህም አንቀሳቃሾች 43 ሚሊዮን 600 ሺ ብር በገጠርና በከተማ መሰጠቱን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ወረዳዎች ላይ የአመራር ቁርጠኝነት፣ የማይክሮ ፋይናንስ አለመስፋፋት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ ስራ ትኩረት አለመስጠት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አለመስፋፋትና የአመለካከት ችግሮች ክፍተት ስራውን እየተፈታተነወ መሆኑንን ይጠቅሳሉ፡፡
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጀንሲ ለወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ እንደሚከታተል፣ እንደሚደግፍና በርካታ ወጣቶችን ከስራ አጥነት እንደሚያወጣ አያምኑም፡፡ ግንዛቤው አላቸው ለማለትም አዳጋች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ወጣቶችን አደራጅቶ ብድር ከመስጠት ባሻገር የገበያ ትስስር የመፍጠር ችግር አለ፡፡ በውሃ ማከፋፋል ስራ የተደራጁ ወጣቶችን በቀጥታ ከአምራች ተረክበው እንዲሸጡ ማድረግ፣ በተመሳሳይም በጨው ማከፋፈል ስራ ለተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር የመፍጠር ክፍተት መኖሩን ይናገራሉ፡፡
አቶ አብደላ እንደሚሉት ሶስት ቦታዎች ላይ የማምረቻና የገበያ ቦታ ተገንብተዋል፡፡ነገር ግን የመብራትና የውሃ አገልግሎት ባለመሟላቱ እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፡፡ ይህንን ለማስተካከል ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መሰረተ ልማቱን ለማሟላትም ተስፋ ሰጥተውናል፡፡ ቦታዎች በመያዛቸው ምክንያትም የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች በከተማው ለማግ ኘት አስቸጋሪ ሆኖብናል፡፡ ይህም ከከተማው ስለ ሚርቅ አምራቾች ምርቶቻቸውን ከማምረቻ ወደ መሸጫ ስፍራ ለማጓጓዝ አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ በተመሳሳይም የከተማ ነዋሪዎችም ወደ አምራቾቹ ተንቀሳቅሰው ለመግዛት እርቀት ገድቧቸዋል ይላሉ፡፡
ወጣቶች የስራ ባህል እንዲኖራቸው እና ስራን ሳይንቁ እንዲሰሩ የሚያስችላቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ወደ ተግባር ከመግባታቸው አስቀድሞም የንግድ እቅድ እና የሂሳብ አያያዝ ስልጠና እንዲያገኙ እንዲሁም የካይዘን ፍልስፍና ግንዛቤ እንዲጨብጡ ይደረጋል፡፡ ‹‹አፋሮች የስራ ባህል የላቸውም›› በሚል የሚነገር አስተያየት አሁንም አለ፡፡ ይህ የተሳሳተ ነው፡፡ በእርግጥ ድሮ ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን ግን የለም፡፡
የአፋር ክልል ወጣቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከጉልበት ስራ አንስቶ ተሰማርተው በክልሉ የተለያዮ አካባቢዎች እየተሳተፉ ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ይህንን አይነት ስራ ሲሰሩ አይታይም ነበር፡፡ በሰመራና ሎጊያ በኮብልስቶን ማንጠፍ፣ በችግኝ ማፍላት እና በተለያዮ ስራዎች ተሰማርተው የሚሰሩት የአፋር ልጆች መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
እንዲሁም በአገልግሎትና ንግድ ስራ ላይ ወጣቶች ተሰማርተዋል፡፡ የወንዶች እና የሴቶች የጸጉር ስራ፣ የእንስሳት ማደለብ፣ የአዮዲን ጨው ማከፋፈል፣ በባጃጅና በታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት በመደራጀት እየሰሩ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
ቀደም ሲል ስድስት ወረዳዎች ላይ ብቻ የነበረው የማይክሮ ፋይናንስ ተደራሽነት አሁን ወደ 11 ወረዳዎች እንዲያደርግ መደረጉ በጥንካሬ የሚጠቀስ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡ ያን ያህል ውጤታማ ሆነዋል ባይባልም መነሻ በመሆኑ ወጣቶች ተደራጅተው ስራ መጀመራቸው በጥንካሬ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ካደራጀናቸው መካከል ሎጊያ ዳቦ በመጋገር ስራ ተሰማርተው እየሰሩ ያሉ ወጣቶች ለሰመራ ዮኒቨርሲቲና ለአካባቢው ህብረተሰብ ዳቦ በማከፋፈል ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሰመራ እና ሎጊያ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች ከእነርሱ እንዲገዙ ትብብር ደብዳቤ በመጻፍ ጭምር የገበያ ትስስር እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ዱቄትም የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል፡፡
አቶ አብደላ እንደሚሉት በእሽግ ውሃ ማከፋፈል የተደራጁ ወጣቶች አሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከውሃ አከፋፋዮች እያገኙ አይደለም፡፡አሁንም ግን በቀጥታ ከውሃ አከፋፋዮች የሚያገኙበትን መንገድ የማመቻቸት ስራ እየሰራን ነው፡፡
ከወጣቶቹ የሚጠበቀውን ሲገልጹም፤ወጣቶች የጠባቂነት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ነገር ግን በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ዘርፍ ቀይረው መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚያገኙትን ስራ ከመስራት ባሻገር የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር መትጋት አለባቸው፡፡ አስተሳሰብና አመለካከታቸውን በመቀየር ስራ ፈጣሪ ሆነው ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለያዮ ስራዎች ለተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር ለመፍጠር በእኛ በኩል ያለው ክፍተትም መስተካከል ይገባዋል ይላሉ፡፡ በአፋር ክልል ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ሥራ የማስገባት ሂደቱ በበጎነት ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጂ ተደራጅተው ለሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ የተቀዛቀዘ እንደሆነ በተለያዮ አጋጣሚዎች የሚነሳ እና መስተካከል የሚገባውም ጉዳይ ነው፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራው ለኑሮ የሚሆን ገቢ የሚገኝበት እንደመሆኑ ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ ከአፋር ክልል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ይጠበቃል፡፡ ተስማሚ የሥራ ቦታ መርጦ ለሚደራጁ ወጣቶች ማመቻቸት፣ የአምራቾችን ክህሎት ማበልጸግ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም የገበያ ትስስር መፍጠርም ቀጣይ የቤት ስራው ሊያደርገው ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ዘላለም ግዛው
Your posts always leave me feeling motivated and empowered You have a gift for inspiring others and it’s evident in your writing