የሕብረተሰቡ ችግር የወለዳቸው የፈጠራ ሥራዎች

በሀገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎችን ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ባለተሰጥኦዎች እንዲበረታቱ የሚያነሳሱ ሥራዎች በየጊዜው እየተሰሩ ይገኛሉ። የፈጠራ ስራዎቹ በተለያዩ አውደ ርዕዮች እንዲታዩና እንዲወዳደሩ የማድረጉ ሂደት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንትም ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ዘጠነኛው ዙር ሀገራዊ የሳይንስና ምህንድስና ቀን አስመልክቶ አውደርዕይ ተካሂዷል። አውደርዕዩን የትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ነው።

በአውደ ርዕዩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ስቲም ማዕከላት እና ከየክልሉ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች እና መምህራን የሰሯቸውን የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ይዘው ቀርበዋል።

94 ተማሪዎች ከስቲም ማዕከላት በኢንጂነሪንግ እና በሮቦቲክስ ዘርፍ የሰሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች ያቀረቡ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ 50 ተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ተሳታፊ ሆነዋል። በአውደርዕዩ የቀረቡት ሥራዎች በስምንት ዘርፎች ለውድድር የሚቀርቡ ሲሆን፣ ከስምንቱ ዘርፎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የሚወጡ ተወዳዳሪዎች ሽልማቶች እንደሚበረከትላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

አውደ ርዕዩ የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የቀረቡበት ነው። እነዚህ አገር ተረካቢ ተማሪዎች እንዲሁም መምህራን የፈጠራ ሥራዎች የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ከመሆናቸው ባሻገር እንደ አገር የተያዘውን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው። በተለይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አገሪቱ ያላትን ተስፋ የሚያሳዩ መሆናቸው ተመላክቷል።

በአውደ ርዕዩ የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው ከቀረቡት ስቲም ማዕከላት መካከል አንዱ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ነው። ከማዕከሉ የመጣው የአስረኛ ክፍል ተማሪው ዑመር አሊ የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን ይዞ ቀርቧል።

ተማሪ ዑመር ቀደምሲልም የፈጠራ ሥራዎችን ይሰራ እንደነበር ይናገራል። በተለያዩ ጊዜያት የሰራቸውን የፈጠራ ሥራዎች በማሻሻል የተሻለ የፈጠራ ሥራ ይዞ እየወጣ መሆኑን ጠቅሶ፣ አሁንም ደግሞ የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን መስራት መቻሉን ይገልጻል። ይህን ማሽን ለመስራት የተነሳሳበት ዋንኛ ምክንያት በሚኖርበት አካባቢ በቅርበት የተመለከተው የእንሰሳት መኖ እጥረት ነው። በዚህ የተነሳ በእንሰሳት እርባታ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሲቸገሩ መመልከቱን ይገልጻል።

እሱ በሚኖርበት አካባቢ እንሰሳት የሚያረቡ ሰዎች ለአንድ ጊዜ ፍጆታ የሚውል አንድ ኩንታል መኖ በ900 ብር ሲገዙ አስተውሏል። ዋጋው ከፍተኛ ስለመሆኑ በመግለጽ እጅጉ ሲቸገሩ ይመለከታል። ለእዚህ ችግር መፍትሔ ለማምጣት በማሰብ የመኖ ማቀናበሪያ ማሽን መስራት መቻሉን ገልጸል።

በአገሪቱ የእንሰሳት እርባታ የተመጣጣነ የእንሰሳት መኖ አቅርቦት አለመኖሩ እንሰሳትን ለማርባትና የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንዳላስቻለ የሚያመላክቱ ጥናቶች እንዳሉም ጠቅሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን ማመንጨት እንደሚያስፈልግ ያመላክታል። እሱም መፍትሔ ያለውን ሀሳብ አፍልቆ የእንሰሳት መኖ በቀላሉ ለማዘጋጀት የሚያስችል የፈጠራ ሥራ መስራቱን ይገልጻል።

የእንሰሳት መኖ ማቀናበሪያ ማሽኑን ለእንሰሳት መኖ አገልግሎት የሚውሉ መኖዎች ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም ገልጾ፣ ረጃጅም ሳሮችንና የተለያዩ የሰብል አይነት አገዳዎችን በመጠቀም የእንሰሳት መኖ ማዘጋጀት እንደሚያስችል ተናግሯል።

ተማሪ ዑመር እንደሚለው፤ ማሽኑ በአካባቢው ከሚገኙ እንደ ብረትና ብረት ነክ ነገሮች፣ ላሜራና ፌሮ የመሳሰሉት የተሰራ ሲሆን፣ ለመስራት ሁለት ወራት ገደማ ፈጅቷል። በኤሌክትሪክ፣ በሶላር እና በነዳጅ በሁሉም አማራጮች ሰዎች በሚፈልጉት መልኩ ሊሰራ ይችላል። በአንድ ሰዓት ውስጥ አምስት ኩንታል መኖ ፈጭቶ ያዘጋጃል።

ዲዛይናቸው ይለይ እንጂ እንደዚህ አይነት በሀገር ውስጥ የተሰሩ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች እንዳሉም ጠቅሶ፣ የሚሰጡት አገልግሎት እሱ ከሰራው ማሽን ያነሰ፣ ዋጋቸው ግን የኅብረተሰቡን አቅም ያላገናዘበ መሆኑን ያብራራል። በገበያ ላይ እስከ 125ሺ ብር ድረስ እየተሸጡ መሆናቸውንም ይገልጻል።

የእሱ ማሽን ግን ከእነዚህ ማሽኖች ከፍ ባለ መልኩ በጥራት የተሻለ ተደርጎ መሰራቱን ጠቅሶ፣ ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት መሆኑንም አመልክቷል። ድጋፍ የሚያደርጉለት አካላት ካገኘ በቀላሉ በሚፈልገው መጠንና ልክ ሰርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብም እንደሚችል አመላክቷል።

ይህን ፈጠራውን ሲሰራ የመምህሮቹና የወላጆቹ ድጋፍና እገዛ እንዳደረጉለት የሚናገረው ተማሪ ዑመር፤ እንደሱ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሰሩም መክሯል።

ሌለኛዋ በአውደ ርዕዩ የፈጠራ ሥራዋን ይዛ የቀረበችው ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ሲናና ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው መምህርት ሰሚራ አብዱልማሊክ ናት። መምህርት ሰሚራ፤ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ሰርታለች። ማሽኑን በሀገር ውስጥ መስራት መቻሉ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ገዝቶ እንዲጠቀምበት ይረዳዋል ትላለች።

በአገራችን አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀመው የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ከውጭ ሀገር የሚመጣና ዋጋውም በዚያ ልክ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሳ፣ እንዲህ አይነቱን ማሽን በማንኛውም ሰው ቤት በቀላሉ ማግኘት እንደሚከብድ መምህርቷ ተናግራለች። ይህን ማሽን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል ሁሉም ሰው ገዝቶ ሊጠቀምበት ይችላል ብላ እንደምታሰብ ትገልጻለች።

‹‹ሽንኩርት ያለ ማሽን በእጅ መክተፍ የሚያጋጥመውን ችግር በእጅጉ አውቃለሁ። ይህንን ችግር ለመፍታት የተሻለ ነው ያልኩትን አማራጭ ስፈልግ ያገኘሁት መፍትሔ በሀገር ውስጥ ማሽን መተካት ቢቻል የሚል ሆኖ ይህንን መፍትሔ ማፍለቅ ቻልኩ›› ስትል ታብራራለች። ‹‹መምህርት በመሆኔ የፈጠራ ሥራዎች በመስራት ለተማሪዎች አርአያ ለመሆን በማሰብ ይህንን የፈጠራ ሥራ መስራት ችያለሁ›› ትላለች።

የመምህርት ሰሚራ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ፈጠራ ስራዎች ሁለት አይነት ናቸው። አንደኛው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በባትሪ ድንጋይ የሚሰራ ነው። በተለይ በባትሪ ድንጋይ የሚሰራው የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ኤሌክትሪከ በሌለባቸው ቦታዎች እና ኤሌክትሪክ በሚጠፋበት ጊዜ ጥቅም ላይ በማዋል ፈጣን መፍትሄ የሚያስገኝ መሆኑን አመልክታለች።

‹‹ብዙ ጊዜ ሽንኩርት ቤት ውስጥ ስንፈጭም ሆነ ገንዘብ ከፍለን ውጪ ስናስፈጭ አጋጣሚ ሆኖ መብራት ከጠፋ መብራት እስኪመጣ መጠበቅ አሊያም በእጅ ወደ መክተፍ የምንገባባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው›› ስትል ጠቅሳ፣ ይህ ማሽን ተክተን ብንጠቀም ጊዜአችንን በአግባቡ መጠቀም ያስችለናል›› ትላለች።

እነዚህ የሽንኩርት መፍጫ ማሽኖች በአካባቢዋ ከሚገኙ የወዳደቁ ቁሳቁሶች መስራቷን ትገልጻለች። የፕላስቲክ ሳህኖች፣ ዲናሞ፣ ቻርጀር፣ ትልቅ የባትሪ ድንጋይ እና ትናንሽ ቢላዎች ተጠቅማ መስራቷን ትገልጻለች። ‹‹ሁለቱንም ማሽኖች ተፈትሸዋል። እኔም ተጠቅሜባቸዋለሁ አይቼቸዋለሁ፤ በፍጥነትም ሆነ በምን መልኩ ከውጭ ከሚገባ የተሻሉ እና በየትኛውም አካባቢ ያለ ሰው ሊጠቀምበት ይችላል ›› ስትል ትገልጻለች።

መምህርቷ እንደምትለው፤ ሽንኩርት መፍጫ ማሽኑ በአንድ ጊዜ አንድ ኪሎ ሽንኩርት መፍጨት ይችላል። ከዚህ በላይ እንዲፈጭ አድርጎ መስራትም ይቻላል። ከውጭ ከሚመጣው በኤሌክትሪክ ከሚሰራውም ሆነ በእጅ ከሚሰራው ማሽን ጋር የተወሰነ ልዩነት አለው።

በሀገር ውስጥ የተሰራ ማሽን ልዩ የሚያደርገው በባትሪ ድንጋይ መስራት መቻሉ አንዱ ሲሆን፤ ዋጋውም የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበና ተመጣጣኝ ነው። ኅብረተሰቡ የሽንኩርት ማሽኑን በቀላሉ ገዝቶ ሊጠቀምበት ይችላል፤ ሁሉም ሰው ሊኖረው የሚችል አይነት ነው።

ከውጭ የሚገባው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው ሽንኩርት መፍጪያ ማሽን ዋጋ በአሁኑ ወቅት ከ3500 ብር በላይ እንደሚገመት ጠቅሳ፣ የእሷ የፈጠራ ውጤት የሆነው ማሽን ግን 500 ብር ዋጋ የተተመነለት መሆኑን አመላክታለች።

እነዚህን የሽንኩርት መፍጫ ማሽኖች አሁን ባሉበት ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል የምትለው መምህርቷ፤ ማሽኖቹ ሽንኩርቱን የሚፈጩበት ቢላዋ የተበየደ ነው፤ እነዚህ ቢላዎች ሽንኩርቱን ከፈጩ በኋላ እንዳይዝጉ በፕላስቲክ እንዲሆን የሚያደርጉ ሥራዎች ያስፈልጉታል። መሻሻል ያለባቸውን እያሻሻሉ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።

ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሰሩ ስታበረታታ መቆየቷን የምትናገረው ሰሚራ፤ እሷም የፈጠራ ሥራዎቿን እያሳደገች መምጣቷን ትገልጻለች። በተለይ መምህራን በአካባቢያቸው ላይ የሚያጋጥማቸው ችግር ነው ብለው በቸልታ ከሚያልፉ ለችግሩ መፍትሔ ያሉትን በማሰብ ማፍለቅ እንዳለባቸው ትገልጻለች። ‹‹ በቀላሉ ለችግሮቻችን በራሳችን መንገድ መፍትሔ መስጠት መልመድ አለበን። ለራሳችን ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ያለብን እኛው ነን›› ስትልም አስገንዝባለች።

ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የመጣው የ11ኛ ክፍል ተማሪው ይበልጣል ኮራ ሌላኛው የአውደርዕዩ ተሳታፊ ነው። ተማሪ ይበልጣል አውቶማቲካል የመስኖ ሲስተም መስራት ችሏል። ተማሪ ይበልጣል እንደሚለው፤ ሲስተሙ ያለሰው እርዳታ በራሱ ይሰራል። ማሳው በሚደርቅበትና ውሃ በሚያስፈልገው ወቅት ራሱ ሴንስ እያደረገ ውሃ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ ማሳው በቂ ውሃ ሲያገኝ ደግሞ ውሃ እንደበቃውና እንደማያስፈልገው አውቆ በመዝጋት በራሱ የሚቆጣጠር ሲሰተም የተገጠመለት ነው።

ይህ የመስኖ ሲስተም ሰውን ተክቶ የመስኖ ሥራ ይሰራል። ከዚህ ተጨማሪም ወፎችም ሆኑ ሌሎች እንሰሳት ዘሩን ወይም ሰብሉን እንዳይበሉ ያደርጋል። በተገጠመለት ሴንሰር አማካኝነት ደውል በመደወል ከአካባቢው እንዲሄዱ ያባርራል። ሲስተሙ በማሳ ላይ የሚዘረጋ እንደመሆኑ በአካባቢ ላይ ውሃ እንዲኖር ከተደረገ በኋላ ያንን ውሃ ማሳው በሚፈልግበት ጊዜ ያጠጣል፤ የመስኖ ሥራውን ለማቀላጠፍ ያስችላል።

ሲስተሙ በኤሌክትሪክ ኃይልና በሶላር ኢነርጂ የሚሰራ ሲሆን ኤሌክትሪክ በሚጠፋበት ወቅት አውቶማቲክ እንደመሆኑ ወደ ሶላር ኢነርጂ ቀይሮ ይጠቀማል። በሶላር ኢነርጂ ብቻ መጠቀም ሲፈለግ ደግሞ ኤሌክትሪኩን በመተው ለመጠቀም እንዲቻል ሆኖ የተሰራ ነው።

ይህን የፈጠራ ቴክኖሎጂም በአካባቢው ላይ ከሚያገኛቸው የወዳደቁ ቁሳቁስ እንደሰራው ነው ተማሪ ይበልጣል የሚናገረው። ይህ ሲስተም በግብርና ዘርፍ በተለይ አርሶ አደሩን ከብዙ ድካምና ልፋት የሚታደግና የጎላ ፋይዳ ያለው ነው ይላል።

አርሶ አደሩ የመስኖ ማሳውን ውሃ ሲያጠጣ ለማሳው የሚያስፈልገውን ያህል ውሃ ሳይመጠን ቀርቶ ውሃ ማሳው ላይ እየበዛ ሲቸገር ማየቱ እንዲሁም አብዛኛውን የመስኖ ውሃ ለመሳብ ጥቅም ላይ የሚውለው ጀነሬተር መሆኑንም መመልከቱ ይህን የፈጠራ ሥራ ሰርቶ የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት እንዳነሳሳው ይገልጻል።

ወደፊትም በፈጠራ ሥራው ላይ ማሻሻያ ማድረግ ባስፈለገ ጊዜ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሰራ የሚናገረው ተማሪ ይበልጣል፤ አርባ ምንጭ የስቲም ማዕከል ያገኘው ስልጠናና ድጋፍ ይህንን የፈጠራ ሥራ እውን እንዲሆን እንዳስቻለው አስታውቋል።

የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ተማሪዎች በውስጣቸው ያለውን ሀሳብ እንዲያወጡ የሚያነሳሳቸውና የሚያበረታቸው ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል ሊኖር እንደሚገባ ጠቅሶ፤ እንደዚህ አይነት የፈጠራ ሥራዎች የሚያቀርቡበትና የሚወዳደሩበት እድሎች መመቻቸታቸው ጥሩ እድል እንደሚፈጥር ተናግሯል።

 አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You