የአማራና የአፋር ክልል ህዝቦች መስተጋብር ዘመናትን ያስቆጠረና በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሮቹ ገለጹ።
የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ውይይት ትናንት በሰመራ መካሄድ ሲጀምር የአፋር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ‹‹የአፋርና የአማራ ሕዝቦች ሥነ ልቦናዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታና ማኅበራዊ መስተጋብር ከሉሲ ዘመን ይቀድማል›› በማለት መሰረቱ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አብሮ በሚኖር ማኅበረሰብ ቀርቶ በቤተሰብ ውስጥ እንኳን ግጭት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማንሳት አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች እንደነበሩም አስታውሰዋል። ‹‹ይሁንና ግጭቶቹን በማኅበራዊ መስተጋብሮቹ የመፍታት አቅም ያለው ሕዝብ ከታች አለ›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት መድረክ ዓላማም ይህንኑ ማጠናከርመሆኑም ገልጸዋል። የአፋር ክልል በ1980ዎቹ አካባቢ እንደ አዲስ ሲዋቀር በርካታ የማኅበራዊ ተቋማት ውስንነቶች እንደነበሩበት ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ዝቀተኛ አቅም እና ከፍተኛ ፍላጎት በነበረን በዚያ ወቅት የክልላችንን ማኅበራዊ ተቋማት እና ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመገንባት እገዛ ላደረገልን የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ያለን ክብር እና ፍቅር የተለየ ነው›› ሲሉም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው ‹‹ሁላችንም አፋሮች ነን። ሁላችንም አፋሮች ነን ስንል ምክንያታችን ብዙ ነው። አፋር እንኳን ህዝቡ ግመሎቹ እንኳን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማ በርቀት ይለያሉና›› ብለዋል። አክለውም የአማራ ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጋር ያለው መስተጋብር ዘመናትን የተሻገረው በጋራ የተመሠረተ ሥነ ልቦና ሰላለው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ተመስገን ጨምረውም “የሁለቱ ህዝቦች አገራዊ ሥነ ልቦና ከፍታ ባይኖረው ኖሮ የሁለቱን ክልል ሕዝቦች ለማለያየት በተሠራው ልክ አሁን አብሮ ለመቆም አይችሉም ነበር። መልከ ብዙ ችግሮቻችን እየፈታንና የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እየሞላን ከቀጠልን የማንወጣው ፈተና፣ የማናልፈው መሰናክልና የማይናድ የጥላቻ ግንብ አይኖርም›› ሲሉ የአማራ ሕዝብ ከአፋር ወንድም ሕዝብ ጋር በጋራ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ገልፀዋል። በሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን የሁለት ቀናት ቆይታም ይኖረዋል።
ምንጭ፤- የአማራ መገናኛ ብዙሃን
አዲስ ዘመን ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም