ከ66 ኪሎ ቮልት በታች በመሆናቸው እኛን አይመለከትም -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል
አዲስ አበባ፡- ለአስራ አራት አመታት ባለቤት አልባ ሆነው የቆዩት ትራስፎርመሮች የአደጋ ስጋት እንደደቀነበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእድገት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስታወቀ፡፡ የማስተዳደር ስልጣን የተሰጠኝ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ ሀይል ያላቸውን ትራንስፎርመሮች በመሆኑ ባለቤት አይደለሁም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ፡፡
የእድገት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ፍፁም መልኬ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በትምህርት ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ አስር ትራስፎርመሮች በአምስት ኮንቲነሮች ውስጥ ታሽገው ተቀምጠዋል፡፡
ትራንስፎርመሮቹ ያለ ስራ ከተቀመጡ ከአስራ አራት አመት በላይ ሆኖአቸዋል ያሉት ርዕሰ መምህሩ ከትምህርት ቤቱ ጠባብነት ጋር ተደምሮ ተጨማሪ ችግር ፈጥሮብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የትራንስፎርመሮቹ አቀማመጥ ያልተስተካከለና ተደራርቦ የተቀመጠ በመሆኑ በሰው ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚሉት አቶ ፍጹም፤ ትራንስፎርመሮቹ እንዲነሱልን በተደጋጋሚ ከወረዳ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ድረስ ብናመለክትም ኃላፊነት ወስዶ ለማንሳት የሞከረ አካል የለም ብለዋል፡፡ርዕሰ መምህሩ አክለውም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተወሰነ ጊዜ በፌዴራል ፖሊሶች መጠበቅ ቢጀመርም ባላወቁት ምክንያት ጠባቂዎች እንዲነሱ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ፍፁም ገለፃ፤ ትራንስፎርመሮቹ ግድብ የማንቀሳቀስ አቅም እንዳላቸው በተለያየ ጊዜ የመጡ ባለሙያዎች እንዳስረዱአቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተዳድረው ከ66ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ ትራንስፎርመሮችን ሲሆን የእነዚህ ትራንስፎርመሮች አቅም ከ66 ኪሎ ቮልት በታች በመሆኑ እኛን አይመለከተንም ብለዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ ውስጥ ታሽገው የሚገኙት ትራንስፎርመሮች የግልገል ጊቤ ሁለት ፕሮጀክት የሚሰራ የግለሰብ ንብረት መሆናቸውንና እነሱ የመረከብም ሆነ የመውሰድ ኃላፊነት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡ የትራንስፎርመሩን ባለቤት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ በቀጣይ የምናገኛቸው ከሆነ የምናስተናግድ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ