ቀደም ባሉት ዓመታት በይፋ ሲተገበርና ባህል ሆኖ የኖረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋና ዋና ሹመኞች (በዋናነት ፕሬዚዳንቶች) ምደባቸው ፖለቲካዊ ሳይሆን በውድድር ስለመሆኑ ከተነገረንና ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጥቂት ጊዜያትን አስቆጥሯል፡፡ የመወዳደሪያ መስፈርቶቹም በምናምናቸውም ሆነ ጥርጣሬ ባሳደርንባቸው ሚዲያዎች በስፋት ሲተዋወቁና ዕጩዎችም “የልመረጥ ቅስቀሳ” ሲያደርጉ አንድ ሁለቴ ያስተዋልን ይመስለኛል፡፡ ተደጋግሞ ባናየውም፡፡ ሃሳባችሁን አትገድቡ ላለን የሀገራችን የወረት ዲሞክራሲ ምሥጋና ይግባውና “በኃላፊዎቹ ምደባ ላይ መቶ በመቶ የሚተገበረው በርግጡ የብቃት ወድድር ነውን? ወይንስ የፖለቲካው የእጅ ርዝመትም ከመዳበስ አልተቆጠበም?” እያለን እንጠይቃለን፡፡ የገና በዓል ሰሞን ስለሆነ በብዕሬ የአፍ ወለምታ “ምን ጥልቅ አደረገህ!” በማለት የበላይ አለቆች እንዳይቆጡ “በዲሞክራሲ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” የሚለውን ነባር ሀገርኛ ባህል ተገን በማድረግ ከጓዳ ሀሜት ነፃ መውጣት ይሻላል፡፡
አንዳንዶች በመስፈርቱ ንጽህናና በምድብተኞቹ ላይ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም እስከ ዛሬ ደፍረው ለአደባባይ ስላልገለጡት ከዚህ በላይ ብዕርን አስረዝሞ ሃሜቱን ማስጮኹ አግባብ አይመስለንም፡፡ ይልቅ የሚሻለውና አዋጭ ክርክሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመምራት የሥልጣን ወንበሩን የተፈናጠጡት ሹማምንት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ልጆቻችንን አደራ ለሰጠነው ለእኛ ለወላጆችና ለተራ ዜጎች ግምገማው ያለመድረሱ ነው፡፡ “በምን ሥልጣናችሁ ለመጠየቅ ከጀላችሁ?” የሚል ተቆጭ ከተነሳም “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እያልን በነባሩ አባባል መልስ እንሰጣለን፡፡
ከዛሬው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጤና ያጣ ውሎና እነርሱንና እግዚሃሩን አምነን ለትምህርት ወደየዩኒቨርሲቲው የምንልካቸውን ልጆቻችንን ምስክርነቶች ስንሰማ ግን አንዳንድ ሹማምንት ራሳቸው የአቅምና የማስተዳደር ብቃታቸው ፍተሻ ይደረግበት ብለን ብንጠይቅ የሚያቀያይም አይመስለንም፡፡
የነገይቱን ብቻ ሳይሆን የዛሬውንም ጭምር ሀገራችንን ይመራሉ ብለን በማመን ከልጅነት እስከ ወጣትነት ተስፋ እየመገብናቸው የጸሎትና የምርቃት ስንቅ አሲዘን የምንልካቸው ልጆቻችንን በድን መቀበል፣ ከፎቅ ላይ ተወረወሩን መስማት፣ በስለት ተወጉን ሰቀቀን ማሰላሰል እኛ ሀገር ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ሀገራት መካነ ዕውቀቶች የሞትና የእልቂት ማዕከል ሆኑ የሚል ዜናም ሆነ ወሬ እስከዛሬ አልሰማንም፡፡ እንደ ጸሐፊው የግል እምነት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ተገደለ፣ ተፈናቀለ፣ ታፈነ ወዘተ. ለሚለው ክፉ አዋጅ ሀገሪቱ ራሷ አመድና ትቢያ ነስንሳ ሱባዔ መግባት ነበረባት፡፡ ቤተ እምነቶችም በእግዚኦታ መቃተት ነበረባቸው፡፡
እስከ ዛሬ በተሾሙበት የዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ለተፈጠሩት መመሰቃቀሎችና ዘርዝረን በማንዘልቃቸው ጥፋቶች መንስዔነት በህሊና አስገዳጅነትም ሆነ የአካዳሚክሱ ሥነ ምግባር በሚመክረው መሠረት አንድም የዩኒቨርሲቲ ዋና የሥራ መሪ “እኔ በምመራው የትምህርት ተቋም ውስጥ በብቃቴም ሆነ በማነሴ ምክንያት ለተፈጠረው ቀውስና ጥፋት በሥልጣን ወንበሬ ላይ እንዳልቆይ ህሊናዬ ስለሚሞግተኝ ኃላፊነቴን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄያለሁ” ብሎ የወሰነ ኃላፊ እስከዛሬ አላየንም፣ አልሰማንም፣ አልነገሩንም፣ ወይንም ሊነግሩን አልፈቀዱም፣ አለያም ነግረውን ከልብ አላደመጥናቸው ይሆናል፡፡
በሌሎች ሀገራት ቢሆን ግን እንኳንስ እንደ ሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ክፉ ተደጋጋሚ አመጾችና ግድያዎች እየተፈጸሙ ቀርቶ ገና ለገና ይሆናል ተብሎ ለሚወራ ወሬ ሳይቀር የብዙ የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና የቦርድ አባላት ሳይውሉ ሳያድሩ ያጥፉም አያጥፉ ሕዝቡንና የሾማቸውን ክፍል ይቅርታ ጠይቀው ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ የሚያመነቱ አይደሉም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ራሱ ምስክር የሆነበትን አንድ አጋጣሚ ማስታወሱ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ያደረጋዋል፡፡
ጸሐፊው በሚገባ በሚያውቀው አንድ የውጭ ሀገር ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ ኢንተርናሽናል ጥቁር የአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎችን በተመለከተ “ከእኛ ጋር መማር ስለማይገባቸው በአስቸኳይ ግቢውን ለቀው ይውጡ!” የሚል የነጭ ቆዳ አፍቃሬ ተማሪዎች ማስፈራሪያ በስፋት በግቢው ውስጥ ተሰራጨ፡፡ አልፎም ተርፎ በየግድግዳዎቹ ላይ ሳይቀር አፀያፊ ስድቦች እየተለጠፉ ምስኪን ባዕዳን ተማሪዎችን ጭንቀት ላይ መጣል ጀመረ፡፡ ይህን መሰሉ ዛቻ ያሳሰባቸው የትምህርት ተቋሙ ኃላፊዎች ዛቻ የተሰነዘረባቸውን በተለይ የአፍሪካ ጥቁር ተማሪዎችን ከግቢው ውጭ ሆቴል ውስጥ እንዲያርፉ ካደረጉ በኋላ ነገሩ ሲረጋጋ ኃላፊዎቹ በይፋ ወጥተው በሚመሩት ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለተፈጸመው ስለዚያ የማይገባ ድርጊት ሀዘናቸውን ከገለጹ በኋላ ለወደፊቱም በአመራራቸው ላይ ተመሳሳይ ችግር ከመፈጠሩ አስቀድሞ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ፡፡ ትልቅ ማስተዋልና እርምጃ ነበር፡፡ ይህ ምሳሌ በነውጥና በአመጽ ወጀብ ለሚላጉት የሀገሬ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች ይመጥን አይመጥን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ “ችግሩ በእኛ ምክንያት አልመጣ ምን ስለሆንን ነው ሥልጣን የምንለቀው?” ብለው ቢሞግቱም መብታቸው ነው፡፡ “ሹመት ያዳብር!!”
“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣
ታላቅ ስጦታ ነው፡፡” ያለው ዜመኛ ምን አስቦ ይህንን እንዳንጎራጎረ ሳንጠይቀው ማለፉ ይቆጫል፡፡
ነጋ ጠባ እስኪሰለቸን ድረስ “ዩኒቨርሲቲውን ለመበጥበጥ ተልዕኮ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች አማካይነት” እየተባለ የሚሰጠው መግለጫ እስከ መቼ እየተዘመረለት እንደሚኖር ሊገባን አልቻለም፡፡ የጥፋቱን ተልዕኮ የተቀበሉት እነዚያ ግለሰቦችና ቡድኖች እነማን ናቸው? ተልዕኮውን የሰጠውስ አካል ማነው? የተልዕኮው ግብስ ምንድን ነበር? ይህ ጉዳይ በሚገባ ባለመገለጹ ብዙዎቻችን ቅሬታ አሳድሮብናል፡ ፡ ውሃ የማይቋጥረው ይህንን መሰሉ ምክንያት አንዳንዴ የማምለጫ መንገድ (Scape Mechanism) እንደሆንስ እያልን መንግሥታችንን ማማታችን አልቀረም፡፡ መግለጫው ትክክል ከሆነ ደግሞ እነዚያ ደርሰንባቸዋል የሚባሉት ሤረኞች ለምን በይፋ በሕዝብ ፊት እንደማይጋለጡ ግራ ያጋባል፡፡ በግሌ “ጓያ እንደሰበረው ሰው” የመንግሥት “ቆይ ብቻ!” ፉከራ የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡ ትርፉ “ደርሰንባቸዋል” የሚባሉት ሴረኞች “እነ እከሌና ያ ምንትስ የተባለው ቡድን ይሆንን!” እያልን ስንንሾካሾክ እርስ በእርስ እንድንጠራጠር ማድረጋቸው ነው፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎች ለሚሰሯቸው ዜናና ትንታኔዎች አንዳንዴ እውነትም ይሁን ውሸት አዘውትረው የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ አባባሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ “ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንዳንድ ግለሰቦች ወይንም ኃላፊዎች በሰጡን መረጃ መሠረት፤ የእከሌ አካባቢ አንዳንድ ነዋሪዎች እንደገለጹልን ወዘተ.” የሚሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ማስረጃዎችን መጥቀስ መብት ብቻ ሳይሆን “ውሸት” ሆኖ ቢገኝ ባለሙያዎቹን እንደሚያስጠይቅ ይጠፋቸዋል ብለን አንገምትም፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሹማምንትና ቃል አቀባዮች የምንሰማቸው መሰል ምክንያቶችም ከእነዚህ አባባሎች የሚሻሉ አይደሉም፡፡ “ሰላማችንን ለመበጥበጥ ተልዕኮ የተሰጣቸው!” ተብሎ መግለጫ ሲሰጥ ቢያንስ የተልዕኮ ሰጭው ማንነት በገደምዳሜም ቢሆን ተረጋግጦ የተገለጠ ስለሆነ “ያ ተልዕኮ ሰጭ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረብልን” በማለት ስለ ልጆቻችን ስንል ከዓይን አፋርነት ተላቀን መሞገት ይገባ ይመስለኛል፡፡
በዚህ ጸሐፊ እምነት አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በተከሰቱት ችግሮች ውስጥ እጃቸው አለበት ሲባል መስማት ለእነርሱ ከሞት የከፋ እፍረት ሲሆን በእኛ በወላጆች ዘንድ ደግሞ ምን ዓይነት መራራ ስሜት እንደሚያሳድር መገመቱ አይከብድም፡፡ የልጆቻችንን ስብዕና በእውቀት፣ በሥነምግባርና በኃላፊነት መንፈስ እንዲቀርጹልን አደራ የሰጠናቸው “መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች” በእንዲህ ዓይነቱ ቅሌትና ውርደት ውስጥ ከተገኙማ ፍርድ ሊሰጣቸው የሚገባው በፍርድ ቤቶች ውስጥ ባሉ ጠባብ ክፍሎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በግልጽና በአደባባይ መሆን ይገባዋል ማለቱ ድፍረት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በሺህዎች በሚቆጠሩ ልጆቻችን ላይ እነርሱ አስቀድመው ክፉ ፍርድ ስለፈረዱ፡፡
ልጆቹ በአደባባይ ሲሞቱ በግላጭ እዬዬ እያልንና ፀጉር እየነጨን ማንባታችን ዋጋ ሳይሰጠው የአጥፊዎቹን ግብርና ስም “ሰብዓዊ ክብራቸውን ለመጠበቅ” ሲባል በግላጭ ለመግለጽ መሽኮርመሙ ለጊዜው ምክንያቱ አልገባንም፡፡ ለሙግታችን ተገቢ መልስ የሌለው የሥራ መሪም ሆነ የትኛውም አካል ቢሆን የሚናገረው ጠፍቶት ሲርበተበት አዝነን ከማለፍ ባለፈም ሥራውን እንዲለቅና ወደ ቀድሞ የማስተማርም ሆነ የአስተዳደር ስራው እንዲመለስ መምከር ብልህነት ነው፡፡
የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ማደጉ እንደ ጀብድ እየተቆጠረ መንግሥታችን ሲፎክር አብረው የሚያዳምቁ ምሁራን “ከቁጥሩ በፊት ጥራት ይቅደም” ብለው አጥብቀው መሞገት ያለመቻላቸው ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙት ለትምህርት መስፋፋት ታስቦ ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታነት እንዲውሉ ታቅዶ እስኪመስል ድረስ “ሃይ ባይ!” የጠፋበት ውሳኔ እንደሆነ ስንጠረጥር ኖረናል፡፡ ብዙዎች ባይሆኑም አንዳንድ ለህሊናቸው ያደሩ ምሁራን በዚህ ጉዳይ “የመንግሥት ያለህ!” እያሉ ሃሳባቸውን መግለጻቸውን ግን በፍጹም አንክድም፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት (ዛሬም ችግሩ ተባብሷል) የከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን ዋና ችግሮች እንደሆኑ በማመን እያጯጯኹን የከረምነው በዋነኛነት ሁለት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ በየትምህርት ተቋማቱ የምንልካቸው ልጆቻችን ለሱሰኝነት መጋለጣቸውና የዩኒቨርሲቲዎቻችን ዙሪያ ገብ አካባቢዎች ለዚሁ ጥፋት የመመቻቸታቸው አሳሳቢነት ነበር፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በፀሐይና በግላጭ “የመመረቂያ ጽሑፎች እንሰራለን” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየዩኒቨርሲቲው ደጃፍ ላይ እየተለጠፉ ልጆቹን የዕውቀት መካን የማድረጋቸው አደጋ ነበር፡፡
አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችማ በንቀትና በትዕቢት ተሞልተው በግላጭ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ስለሚገዙት የመመረቂያ ወረቀቶች ጉዳይ መግለጫ ሲሰጡ “ምን አዲስ ነገር አለ፤ እንዲህ ዓይነቱ ችግር በሰለጠኑት ሀገራትም ጭምር በስፋት የሚስተዋል ነው” በማለት ሲሳለቁ ተደምጠዋል፡፡ “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ ይህንን መሰሉን አሳፋሪ መግለጫ የሰጡ ሹም ከዩኒቨርሲቲ ኃላፊነታቸው ሲነሱ በአምባሳደርነት ተሹመው ሀገር እንዲወክሉ ታላቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ተመልክተናል፡፡
ለሁለቱም ሀገራዊ ችግሮች መንግስታችን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ወይንም “ይውጣላችሁ ምን እንዳታመጡ ነው!” በሚል ማንአለብኝነት ሊሆን ይቻላል ተገቢውን እርምጃ ወስዶ ችግሮቹን ከሥራቸው ከማድረቅ ይልቅ “እዚህ አካባቢ ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ” የሚለውን ዜና ብቻ እንድናደምጥ ተፈርዶብናል፡፡ ጸሐፊው በአግባቡና በሥርዓቱ በተገቢው ጥናት ላይ ተመስርቶ ለሚደረግ የዩኒቨርሲቲ መስፋፋት ተቃውሞ እንደሌለው አስረግጦ መግለጽ ይወዳል፡፡
አንጋፋና ስመ ጥር ታሪክ ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ጎን (ያውም አጥሩን ተጎራብቶ) የቢራ ፋብሪካ ሲከፈትና በተቋሙ ዙሪያ የመጠጥ ቤቶች ሲስፋፉ የአካባቢው አስተዳደርም ሆነ ፌዴራል መንግሥቱ እንዳላየና እንዳልሰማ በመሆን ጆሯቸውን ደፍነው በምንቸገረኝነት በማለፍ ሀገራዊ ዕዳችንን ሸክም ሲያከብዱብን ሃይ የሚል ደፋር አልተገኘም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የተስፋፉት የሱስ አሲያዥ ዕፆች መናኸሪያዎችም ልጆቻችንን እየበከሉ ተገዢ ሲያደርጓቸው ነገሮች እየታለፉ ያለው በቸልታ ነው፡፡
አልፎም ተርፎ “እከሌ የተባለው ዕፅ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው” እየተባለ በውጭ ዶላር አመንጭነት ሲሞካሽ የምንሰማው በዚሁ ለጉድ በጎለተው ጆሯችን አማካይነት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እርሙን ያወጣው ከጥቂት ዓመታት በፊት አንጋፋውና የተከበረው ዕድሜ ጠገቡ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት አብዛኛውን ዜጎች፣ በተለይም ዩኒቨርሲቲ የምንልካቸውን ልጆቻችንን የሱስ ተገዢ አድርጎ ለሚያናውዛቸው “ዝነኛው” ሱስ አስያዥ ዕፅ አራት የመታሰቢያ ቴምብሮች አሳትሞ በመላው ዓለም ሲበትን አይተናል ሰምተናል፡፡ ስለሆነም ዕፁ ከኢኮኖሚ፣ ከሃይማኖት፣ ከባህልና ከፖለቲካ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ከቶውንም የሚላላ ስለማይመስል ከትውልድ ወደ ትውልድ እሽሩሩ እየተባለ መቀጠሉ አይቀሬ እንደሆነ ከገባን ሰነባብቷል፡፡
ትናንት ከትናንት ወዲያ ዩኒቨርሲቲ የምንልካቸውን ልጆች ያሰጋሉ እንላቸው የነበሩ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ የዛሬው ችግር ደግሞ ከመተለቅም አልፎ ገዝፎና ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ በልጆቻችን ሕይወት ላይ ሲመጣ ስናይ ከመንግሥትም ጋር ሆነ ከፈጣሪ ጋር ብንሟገት አይደንቅም፡፡ ይህንን ሁሉ ሸክም የተሸከሙት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ዛሬ ዛሬ ዕውቀትን ከመመገብ ይልቅ የችግር መፈልፈያ መሆናቸውን ማየትና መስማት ስሜትን ያንኮታኩታል፤ ተስፋን ያመክናል፡፡ ለዚህም ነው ርዕሴን “መማር ያሳፍራል!?” በማለት የሰየምኩት፡፡
ይህንን መሰሉን ሀገራዊ ደዌ በጥናትና በምርምር ችግሩን አንጥሮ ከነመፍትሔው የሚያቀርቡ ምሁራን ማጣታችን በራሱ አሳሳቢ ነው፡፡ ካሉም ድምጻቸው አልተሰማም ብለን ማለፍ እንችላለን፡፡ የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለው ዝምታን መርጠው ከሆነም በውጭ ተመራማሪዎችና መፍትሔ ጠቋሚዎች ተቀድመው እንደለመዱት “እከሌ የተባለው የውጭ ምሁር በጻፈው የምርምር ጽሑፍ ላይ እንዳረጋገጠው” እያሉ በማጣቀስ የራሳቸውን ጉዳይ ከባዕዳን ጽሑፎች ላይ እንደ ባዕድ ተመራማሪ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ሲያቀርቡ እየታዘብን አንገታችንን መድፋታችን የሚቀር አይመስልም፡፡ ሰላም አውሎ ሰላም ያሰማን!!!
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com