አራት ኪሎ
ቅዳሜ ከሠዓት አራት ኪሎ የሰው እግር በዝቶባታል:: የዓመት በዓሉ ዝግጅት ጥድፊያ የፈጠረ ይመስላል:: ፀሐይ አቅሟን አሰባስባ አናት የሚበሳ ሙቁቷን ትለቃለች:: በዚህ መሃል አላፊ አግዳሚው ሁሉ ሸማች ይመስል ወደ ሱቆች ያማትራል:: አንዳንዱ ደግሞ ዋጋ የመጠየቅ አባዜ የሆነበት ይመስል እያገላበጠ ያገኘውን ዕቃ ሁሉ ይጠይቃል:: በተለይ በዓሉን አስታከው ከመንገድ ዳር የወጡ የገና ዛፎች፣ ጌጣጌጦች፣ በዓል በዓል የሚሸቱ ቁሳቁሶች የመንገደኛውን ቀልብ ያዝ ያደረጉ ይመስላል::
በዚህ ትዕይንት ውስጥ እየንቀሳቀስኩ ሣለሁ ከአራት ኪሎ ሐውልት ከፍ ብሎ ካለው የብረት መሸጋገሪያ ድልድይ ላይ ደረስኩ:: እንቅስቃሴው ቀጥሏል:: ሰዎች ይሄዳሉ፤ ይመጣሉ:: በዚህ ድልድይ ላይ ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 15 የሚሆኑ ህፃናት ‹‹ዲጅታል ሚዛን›› አስቀምጠው ተመዘን! ተመዘን! ተመዘኚ! እያሉ ሰዎችን ይጎተጉታሉ:: ሰዎችም የመሠላቸው አድርገው ያልፋሉ:: ከእነዚህ ልጆች መሃል በዕድሜ ከፍ ካለው ልጅ ጋር ጨዋታ ጀመርን::
ከቤት የወጣሁ ዕለት
ቢኒያም መኮንን ይባላል:: ወላይትኛ እና አማርኛ አቀላጥፎ የሚናገር ሲሆን ከሰዎች ጋር በፍጥነት ይግባባል:: ከጓደኞቹ ጋር ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ህይወት አስቸጋሪ ሆነችበት:: የእናት ፍቅር፣ የቤተሰብ ናፍቆት ብቻ ሁሉም ነገር ግራ አጋባው:: ተመልሶ አይሄድ ነገር ብዙ ሥራ ሊሠራ፤ ብር አጠራቅሞ ህይወቱን ለመለወጥ ቆርጦ ከሀገሩ ወጥቷል:: በዚህ ላይ ወደ ሐዋሳ ለመመለስ ሲያስብ ጓደኞቹ ለምን ብለው በተደጋጋሚ በጥያቄ ናላውን ያዞሩታል:: እርሱም ሁኔታዎችን እየተላመደ ሲመጣ ወደ ሐዋሳ መመለስ የሚለውን እርግፍ አድርጎ ተወው:: ግን ደግሞ ብር መያዝ የሚለው ሃሳብ ከልቡ አልጠፋም:: ወደ አዲስ አበባ ሳይመጣ ያጠራቀማት ትንሽ ብር ላይ የተወሰነ ገንዘብ ጨምሮ ሰዎች የሚመዘኑበት ‹‹ዲጅታል ሚዛን›› በ500 ብር ገዛ:: ከዚያን ከመንገድ ዳር ሆኖ አሁን የሚተዳደርበትን ሥራ ጀመረ:: በእርግጥ ከዚህ ሥራ ውጭ ሌላ ሥራ ለመስራት ሞክሮ ነበር አልተሳካም እንጂ::
የባከኑ ነፍሶች
በርካታ ህፃናት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበት መንገድ እጅግ አሳዛኝ እና የበርካቶች ነፍስ ከመንገድ ዳር እንድትቀር ዋንኛ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል:: በሐዋሳ እና አካባቢዋ ሆን ብለው ህፃናትን ከቤተሰባቸው እንዲኮበልሉ የሚያደርጉ ሰዎች መኖራቸውና በዚህም ብዙ ህፃናት ህይወታቸው በሰዎች እጅ እንዲወድቁ የሕይወት መስመራቸውም እንዲበላሽ እያደረጉ ነው:: በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ብር እንደ አሸን ታገኛላችሁ የሚለው የብልጣብልጥነት አካሄድና ህፃናትን የማሞኘት ስልት በደንብ ይጠቀሙበታል:: ህፃናት ደግሞ ነገሮችን በሚገባ ማጤን እንደማይችሉ፤ ቢችሉ እንኳን በትንሽ ብር እንደሚታለሉና በተደጋጋሚ ስለሚጎተጎቱ ትምህርታቸውን እያቋረጡ የተስፋ ምድር ትሆናችኋለች ወደምትባለው አዲስ አበባ ይመጣሉ::
ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ልጆቻችሁን እናስተምርላችኋለን›› እያሉ ህፃናትን ከወላጆቻቸው ነጥለው ይወስዳሉ:: ግን እነዚህ ሰዎች የሚገቡትን ቃል አያከብሩም:: እንኳንስ ማስተማር ቀርቶ ጥሩ ልብስ ሳይገዙላቸው፤ ወደ ትምህርት ቤትም ሳይልኳቸው ጉልበታቸውን ብቻ ይጠቀማሉ:: በቢኒያም ምልከታ እነዚህ ሰዎች ልጆቹን በቅርብ ርቀት እየተከታተሉዋቸው ብር የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ ያደርጓቸዋል:: ለአብነት ሚዛን በ500 ብር ይገዙና ይሰጧቸዋል:: ታዲያ እነዚህ ህፃናት ሙሉ ቀን ሲሠሩ ውለው ማታ ላይ ብሩን ለአሰሪዎቻቸው ይሰጣሉ:: አንዳንዶቹን በሱቃቸውና በምግብ ቤታቸው አካባቢ ተላላኪ እያደረጓቸው የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ::
200 ብር ለቤት ኪራይ
ቢኒያም በቀን እስከ 50 ብር ያገኛል:: በየቀኑ ድግሞ 25 ብር በእቁብ መልክ ያጠራቅማል:: ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን 50 ብር ዕለታዊ እቁብ ገብቷል:: እቁቡ ሲወጣ በጋራ 8000 ብር የሚደርሳቸው ሲሆን፤ ያኔ የተሻለ ሥራ ለማከናወን አስቧል:: አሁን ግን በዚሁ ስራ ህይወቱን እየመራ ነው:: ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በየወሩ እያንዳንዳቸው 200 ብር ቤት ተከራይተዋል:: ታዲያ ቢኒያም 200 ብር መክፈል ስላለበት ይህችን ብር ለማግኘት ሁሌም ሩጫ ላይ ነው:: ከትምህርት መልስም በፍጥነት ወደ ስራው ይሮጣል::
ቢኒያም በርካታ ጓደኞቹ ትምህርት ምን ይሰራል፤ አርፈህ ብር አታጠራቅም እያሉ ይጨቀጭቁታል:: እርሱ ግን ከትምህርት መለየት አይፈልግም፡ ወደፊትም ዶክተር ሆኖ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው ይፈልጋል::
300 ብር የጠፋብኝ ቀን!
ከዕለታት በአንዱ ቀን ለሳምንታት ሠርቼ ከኪሴ ውስጥ የነበረ 300 ብር ጠፋብኝ የሚለው ቢኒያም፤ በዚያን ቀን እጅግ ብስጭት ብዬ ነበር ይላል:: ብሯን ከዕለት ጉሩሱ ቆጥቦ ያስቀመጣት እንጂ የቅንጦት አልነበረችም:: ይህን ብር በመጣሉ ይዘን እንጂ በአጭር ጊዜ እንደሚገኘው በማሰብ ተጽናና፤ ጓደኞቹም አይዞህ አሉት:: ለጊዜው እርሱም ነገሩን ረሳው:: ግን ዛሬም ድረስ ሳስታውሳት ትቆጨኛለች ይላል:: ከዚያን ቀን ጀምሮ በኪሱ ውስጥ ብር ከማስቀመጥ ይልቅ ዕለታዊ ዕቁብ መጣል ካልሆነ ደግሞ ዘመድ ዘንድ ማስቀመጥን ቀዳሚ አማራጭ አድርጎ ወሰነ:: ለራሱ ብቻ ሳይሆን ጓደኛውንም አማክሮ በጋራ 50 ብር ዕለታዊ እቁብ ጀመሩ::
የትምህርት ቤት ምገባ- ባለውለታ
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የምገባ መርሐ ግብር ቢኒያምን ብዙ ነገር አቃልሎለታል:: ቁርስ አልበላሁም፤ አላዘጋጀሁም ብሎ እንደድሮ ከትምህርት ቤት አይቀርም:: እርሱ የሚማርበት ‹‹በዓታ ትምህርት ቤት›› በጀመረው የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ስለሆነ ቁርሱን እዚያው ይበላል:: ምሳውም እዚያው ስለሚዘጋጅለት የምሳ እና የቁርስ ጣጣውን ጥንቅቅ የሚያደርገው እዚያው በዓታ ትምህርት ቤት ነው:: ግን እራቱን ለመሸፈን ሲል ማሰብ ግድ ይለዋል:: ከትምህርት ቤት እንደወጣ ወለም ዘለም የለም:: ቀጥታ ወደ ቤቱ ይሄድና ልብሱን ቀይሮ ሚዛኑን አንጠልጥሎ አምስት ኪሎ አሊያም ደግሞ ስድስት ኪሎ ሆኖ ክብደታቸውን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ይጠባበቃል:: ያገኛትን ያክል ይሰራና ወደ ሠፈሩ ያቀናል:: ማታ የቤት ሥራውን ይሰራና ስለሚቀጥለው ቀን ያስባል:: ከምን በላይ ግን የትምህርት ቤት ምገባ- መጀመሩ ባለውለታው እንደሆነ ይነገራል::
እሁድ ልዩ ቀን
እሁድ ለቢኒያም ብዙ ነገር ናት:: ፕሮቴስታንት እምነት ወደሚሄዱበት ቤተ እምነት ይሄዳል:: በዚህም ደስታውንም ችግሩንም ለፈጣሪ ይናገራል:: የነገ ህልሙ እንዲሳካ ከፈጣሪ ይማፀናል:: የተሻለ ሥራ ቢኖረው ይመኛል፤ ይህን ምኞቱን ደግሞ የሚናገረው ብቸኛ አምላኬ ረዳቴ፤ መካታዬ ለሚለው አምላኩ ነው::
እሁድ ወደ ቤተ እምነት ለፀሎት የሚሄድባት ቀን ብቻ አይደለችም:: እንደምንም ሠዓቱን እያብቃቃ የኳስ አምሮቱን ለመወጣት ወደ ጃን ሜዳ ይሄዳል:: ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር እየተሯሯጠ በዚያን ሰፊ ሜዳ የልቡን መሻትና በውስጡ የሚንቀለቀል ፍላጎቱን ለማርገብ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ራሱን ያዝናናል::
እሁድ ለቢኒያም ከእሁድም በላይ ናት:: ወደ ቤተ እምነት ሄዶ ከፈጣሪው የሚገናኝበት፤ የኳስ አምሮቱን የሚወጣበት ነው:: በዚያው ቀን ደግሞ ሳምንቱን ሙሉ በአቧራ ያደፈ ልብሱን የሚያጥብበት ቀን ነው:: በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ እሁድ በጣም ታጥርበታለች:: ግን እንደምንም ብሎ ነገሮችን በአግባቡ ሊከውን ይሞክራል:: ምናልባት ከዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ የምትተርፈው ጊዜ ካለችው ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር ይጫወታል:: ማታ ላይ ደግሞ በሰፈሩ በቅርብ ርቀት ላይ ሚዛን ይዞ ወጣ ይልና የተወሰነች ሳንቲም ‹‹ለመሸቀል›› ደፋ ቀና ይላል:: ማታ ቤት ሥራውን አጠናቆ ለሠኞ ማለዳ የትምህርት ቤት ዝግጅት ያደርጋል:: በዚህ የሕይወት ዑደት ውስጥ ሁለት ዓመታትን አሳልፏል::
‹‹ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ››
‹‹አሁን እየሠራሁ ባለሁት ነገር ደስተኛ ነኝ:: ቢያንስ እናቴ አደራ ያለችኝን ትምህርት እየተማርኩ ነው:: ወደፊት ደግሞ የተሻለ ቦታ እንደምደርስ እርግጠኛ ነኝ:: እናቴም ሆኑ ዘመዶቹ በትምህርት እንድገፋበት ይመክሩኛል:: እኔም ትምህርቴን በጣም እወዳለሁ:: በመሆኑም የጀመርኩትን ሥራ እያጠናከርኩ በትምህርቴም በሚገባ መግፋት እፈልጋለሁ:: ትምህርቴንም ሳጠናቅቅ ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ›› ይላል:: ለዚህም ደግሞ የሣይንስ ትምህርቶች ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ያጠናል::
ምናልባት በዚህ ሐሳቡ ነገሮች የማይሳኩ ከሆነ ብዙ አማራጮችን አስቀምጧል:: ዶክተር ሆኖ ታማሚዎችን የማገዝና ጤናቸውን የመታደግ ህልሙ የማይሳካ ከሆነ በእግር ኳስ ጨዋታ አንቱ የተባለ ሰው መሆን ይፈልጋል:: ለዚህም ከአሁኑ ስፖርት ትምህርትንም ሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን በፍቅር ይሠራል፤ ይማራል:: በሚዛኗ ደግሞ የዕለት ጉርሱን ይሰፍራል::
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ክፍለዮሐንስ አንበርብር