አገሪቷ ባለፉት ዓመታት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ስትመራ በነበረበት ወቅት ያጣቻቸውን እሴቶች በመመለስ ያገኘቻቸውን መልካም ጎኖች ለማስቀጠል መስራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።
አቶ ንጉሱ ሰሞኑን እንደገለጹት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ቅኝት ዜጎችን በመደብ የሚከፋፍል ከዛም አልፎ በኢትዮጵያ የተተገበረበት መንገድ ከመደብ አልፎ ህዝብን በመከፋፈል በርካታ ጥፋቶችን ያስከተለ መስመር ነው፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲ በባህሪው ወዳጅና ጠላት ብሎ በመከፋፈል የሚያምንና ከድርጅቱ ጎን ያልወገኑትን ለከፍተኛ ስቃይና መከራ ይዳርግ እንደነበረ አቶ ንጉሱ አስታውሰው መስመሩን ሲቃወሙ በነበሩት ዜጎች ላይም በስውር በርካታ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች እንዲደርስባቸው ከመደረጉም በተጨማሪ እስከዛሬም ድረስ የት እንደደረሱ የማይታወቁ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰለባዎች በርካታ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አማካኝነት ጨካኝና አረመኔያዊ ድርጊቶች በስፋት የሚሰሩበት ድርጅትና መንግስት በኢትዮጵያ ሰፍኖ መቆየቱን የፕሬስ ሴክሬተርያት ኃላፊው ገልጸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሌለበትና ጥቂቶች ሀብት የሚያከማቹበት፤ ሌሎች የበይ ተመልካች የሚሆኑበት ስርዓት እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋም እንደስርዓት በስፋት የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስርዓቱ ጸረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ የሌለውና በህዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የአብሮነት ዕሴት ለመሸርሸር ቀን ከሌሊት የሚሰራበት ከመሆኑም ባሻገር የህዝብን ጥቅም ለማስከበር የሚሟገቱ ወገኖችን ጠባብና ትምክህተኛ በሚል የሚፈረጁበት አፋኝ ስርዓት መሆኑን አቶ ንጉሱ አስረድተዋል፡፡ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የመነመነበትና ትዕዛዞች ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚወረወሩበት ሌሎች አካላት ተላላኪ እንዲሆኑ የሚያስገድድ አካሄድ ነው፡፡
ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድን ለመቀየርና ዴሞክራሲያዊ ባህሪን ለመላበስ ተፈጥሯዊ ማንነቱ ሳይፈቅድለት በ2010 ዓ.ም በህዝብ ጫና በአዲስ የለውጥ አመራር መተካቱን አቶ ንጉሱ በአዲሱ አመራርም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የደረሱ ጥፋቶችንና በደሎች ለማረም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኢህአዴግ በወጡት ሶስት ፓርቲዎችና አጋር ሲባሉ የቆዩት አምስት ድርጅቶች ተዋህደው የፈጠሩት የብልጽግና ፓርቲም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አማካኝነት በህዝቡ ላይ ሲፈጸሙ የቆዩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ለማረምና ሲሸረሸሩ የቆዩትን ዕሴቶች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ “የቆመባቸው ምሰሶዎች ፌዴራሊዝሙን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ናቸው” ያሉት አቶ ንጉሱ የብልጽግና ፓርቲ ግብም የኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ፣ ስነ አእምሮአዊና ስነ ልቦናዊ ሁኔታን ባካተተ መልኩ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና እሴቶች ተብለው የሚጠቀሱት ህብረ አገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ነጻነት መሆናቸውንም ጠቅሰው “ኢትዮጵያ አሃዳዊነትን ላይመለስ ሸኝታዋለች። ይህ ዓይነቱ ስርዓት ሊታሰብ አይችልም።”ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊነትን መገንባት የማይታሰብ መሆኑን ጠቁመው፤ አሀዳዊነት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚንድ መሆኑንም ጠቁመዋል።አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና እውነተኛውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመገንባት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከሰው ልጆች ባህርይ ተነስቶ ወደ አገራዊ ባህርይ ጎልብቶ የሚያድግ መሆኑንም ጠቁመዋል።ብልፅግና በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ቋንቋ ባህልና ማንነትን ተከትለው ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ባለመሰጠቱ ጥያቄ ሆኖ የተነሳና ያታገለ አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል።
ብልጽግና የዜጎችን ክብር የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን የግለሰብና የቡድን መብታቸው የሚከበርበት ግለሰባዊና ተቋማዊ ጭቆናዎች የሚወገዱበት ስርዓት እንደሚያሰፍንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር